ወደኋላ አትበሉ
1. በትምህርት ቤት ለመመሥከር ምን ይጠይቃል? ለምንስ?
1 ልጆች እንዳያሾፉባችሁ በመፍራት በትምህርት ቤት ከመመሥከር ወደኋላ ያላችሁበት ጊዜ አለ? በተለይ ደግሞ ዓይን አፋር የሆነ ሰው በትምህርት ቤት ለመመሥከር ድፍረት እንደሚጠይቅበት እሙን ነው። በዚህ ረገድ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?
2. በትምህርት ቤት በመመሥከር ረገድ አስተዋዮች መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?
2 አስተዋዮች ሁኑ፦ ትምህርት ቤታችሁ የእናንተ የአገልግሎት ክልል እንደሆነ ቢሰማችሁም ከቤት ወደ ቤት እንደምታደርጉት ከእያንዳንዱ ሰው ጋር መንፈሳዊ ውይይት መጀመር አለባችሁ ማለት አይደለም። መቼ መናገር እንዳለባችሁ ስትወስኑ የማመዛዘን ችሎታችሁን መጠቀም ይኖርባችኋል። (መክ. 3:1, 7) በክፍል ወስጥ የሚነሱ ትምህርታዊ ውይይቶች ወይም የሚሰጣችሁ የቤት ሥራ እምነታችሁን ለመግለጽ አጋጣሚ ይፈጥርላችሁ ይሆናል። አሊያም ደግሞ አብሯችሁ የሚማር ልጅ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች የማትካፈሉት ለምን እንደሆነ ሊጠይቃችሁ ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ለአስተማሪዎቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ የሚነግሯቸው ከመሆኑም ሌላ ስለ እምነታችን የሚያብራሩ ጽሑፎች ይሰጧቸዋል። ሌሎች ደግሞ አብረዋቸው የሚማሩ ልጆችን ፍላጎት ለማነሳሳት ሲሉ ጽሑፎቻችንን ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጣሉ።
3. በትምህርት ቤት ለመመሥከር ዝግጁ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?
3 ዝግጁዎች ሁኑ፦ ዝግጅት በራስ የመተማመን ስሜታችሁን ያዳብረዋል። (1 ጴጥ. 3:15) በመሆኑም ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በመገመት ምን ዓይነት መልስ መስጠት እንደምትችሉ አስቡ። (ምሳሌ 15:28) የሚቻል ከሆነ መጽሐፍ ቅዱሳችሁንና እንደ ማመራመር፣ የወጣቶች ጥያቄ እንዲሁም ከፍጥረት ጋር የተያያዙ ጽሑፎችን ትምህርት ቤታችሁ አስቀምጡ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ የምትፈልጉትን መረጃ በቀላሉ ማግኘት ትችላላችሁ። በተጨማሪም በቤተሰብ አምልኮ ወቅት የልምምድ ፕሮግራም እንዲያካትቱ ወላጆቻችሁን ጠይቁ።
4. በትምህርት ቤት መመሥከራችሁን መቀጠል ያለባችሁ ለምንድን ነው?
4 አዎንታዊ አመለካከት አዳብሩ፦ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባነሳችሁ ቁጥር አብረዋችሁ የሚማሩ ልጆች ያሾፉብኛል ብላችሁ አታስቡ። አንዳንዶች ድፍረታችሁን ሊያደንቁ አልፎ ተርፎም ሊያዳምጧችሁ ይችላሉ። ይሁንና ማንም ሰው ጥሩ ምላሽ ባይሰጣችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ጥረት በማድረጋችሁ ይሖዋ እንደሚደሰት አትዘንጉ። (ዕብ. 13:15, 16) ‘በፍጹም ድፍረት መናገራችሁን መቀጠል’ እንድትችሉ አዘውትራችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። (ሥራ 4:29፤ 2 ጢሞ. 1:7, 8) ሰሚ ጆሮ ስታገኙ ምን ሊሰማችሁ እንደሚችል እስቲ አስቡ! ምናልባትም ውሎ አድሮ ግለሰቡ የይሖዋ አገልጋይ ሊሆን ይችላል።