በአገልግሎታችሁ ላይ ጠንቃቆች ሁኑ
1. በአገልግሎት ላይ ሳለን ጠንቃቆች መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 “በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች” ተደርገው የተገለጹት የአምላክ አገልጋዮች የስብከቱን ሥራ የሚያከናውኑት “በጠማማና በወልጋዳ ትውልድ መካከል” ነው። (ማቴ. 10:16፤ ፊልጵ. 2:15) ስለ እርስ በርስ ጦርነትና የሕዝብ ዓመፅ እንዲሁም ሰዎችን አግቶ የጭካኔ ድርጊት ስለ መፈጸም የሚገልጹ አስፈሪ ዜናዎች የተለመዱ ሆነዋል፤ ይህም ክፉ ሰዎች “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” እንደመጡ በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። (2 ጢሞ. 3:13) በአገልግሎት ላይ ሳለን “ጠንቃቆች” እንድንሆን የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?—ማቴ. 10:16
2. ክልሉን ለቅቀን በመውጣት ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ማገልገል የጥበብ እርምጃ የሚሆነው መቼ ነው?
2 አስተዋይ ሁኑ፦ ምሳሌ 22:3 ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ስናይ “መጠጊያ” መፈለጋችን ጠቃሚ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። አገልግሎት ላይ ስትሆኑ ሁኔታዎችን በንቃት ተከታተሉ! በአንድ የተረጋጋ አካባቢ ያለው ሁኔታ በድንገት ሊለወጥ ይችላል። ፖሊሶች በአካባቢው ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ወይም ሰዎች መንገድ ላይ ሲሰባሰቡ ታስተውሉ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አገልግሎት ላይ እያላችሁ አንድ ሰው አደገኛ ሁኔታዎች እንዳሉ በደግነት ሊያስጠነቅቃችሁ ይችላል። ምን ሊከሰት እንደሚችል ለማወቅ በቦታው ከመቆየት ይልቅ አካባቢውን ወዲያውኑ ለቆ መውጣትና ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ማገልገል የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 17:14፤ ዮሐ. 8:59፤ 1 ተሰ. 4:11
3. መክብብ 4:9 ላይ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት በአገልግሎት ላይ ስንሆን የሚሠራው እንዴት ነው?
3 ከሌሎች ጋር አገልግሉ፦ መክብብ 4:9 “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” በማለት ይናገራል። ብቻህን የማገልገል ልማድ ካለህ እንዲህ በማድረግህ እስካሁን ምንም ችግር አላገጠመህ ይሆናል፤ ይሁንና አሁንም ሁኔታው እንደዚያ ነው? በአንዳንድ አካባቢዎች ምንም ችግር አይኖር ይሆናል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች፣ አንዲት እህት ወይም አንድ ወጣት በተለይ ከመሸ በኋላ ብቻቸውን ከቤት ወደ ቤት ማገልገላቸው ጥበብ አይደለም። ከአደገኛ ሁኔታዎች ለመራቅ የተቻለንን ሁሉ ጥረት የምናደርግ ቢሆንም ንቁ የሆነ የአገልግሎት ጓደኛ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ከተሞክሮ ማየት ይቻላል። (መክ. 4:10, 12) በቡድን ሆናችሁ ስታገለግሉ የሌሎቹን የቡድናችሁን አባላት ደኅንነት በንቃት ተከታተሉ። የአገልግሎት ክልሉን ለቅቃችሁ ስትሄዱ በክልሉ ውስጥ ለሚያገለግሉት ሌሎች አስፋፊዎች ማሳወቃችሁን አትርሱ።
4. የሁሉም የጉባኤው አባላት ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘ነፍሳችንን ተግተው የሚጠብቁ’ እንደመሆናቸው መጠን በአካባቢው ያለውን ሁኔታ መሠረት በማድረግ ጠቃሚ መመሪያዎችን የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። (ዕብ. 13:17) እኛም ልካችንን የምናውቅና ከእነሱ ጋር ሙሉ በሙሉ የምንተባበር ከሆነ ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሚክ. 6:8 NW፤ 1 ቆሮ. 10:12) ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ በክልላቸው ውስጥ ውጤታማ ምሥክርነት ለመስጠት በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንመኛለን።