በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ የሚገኙትን አትርሷቸው
1. በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ ላሉ ሰዎች ምሥራቹን ማካፈል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
1 ብዙዎች በዕድሜ መግፋት ሳቢያ ከሚመጡ ችግሮች ጋር እየተጋፈጡ ነው። (መክ. 12:1-7) በዕድሜ የገፉ አንዳንድ ሰዎች የሚኖሩት በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት በመሆኑ ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት ልናገኛቸው አንችልም። በአንዳንድ አገሮች አረጋውያን በዕድሜ ሲገፉ ከልጆቻቸው ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲኖሩ ማድረግ የተለመደ ነው፤ ይሁን እንጂ በእነዚህ አገሮችም እንኳ በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ ሰዎች አሉ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያን እንደ ልባቸው መንቀሳቀስ ባይችሉም ወይም የመርሳት ችግር ቢኖባቸውም እንኳ ስለ ይሖዋ መማርና ማወቅ እንዲሁም እሱን መውደድ ይችላሉ። ታዲያ ‘አስደሳች ተስፋ’ የያዘውን ምሥራች ልናካፍላቸው የምንችለው እንዴት ነው?—ቲቶ 2:13
2. የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማትን የያዘ ዝርዝር ማዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው?
2 የመጀመሪያው እርምጃ፦ በአካባቢያችሁ የሚገኙ የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማትን የያዘ ዝርዝር ለማዘጋጀት የስልክ ማውጫ መጠቀም ይቻላል። እነዚህ ተቋማት የተለያየ መጠሪያ ሊኖራቸው ስለሚችል የተለያዩ ስያሜዎችን ተጠቅማችሁ መፈለግ ትችላላችሁ። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ፣ ብቃት ያላቸው አስፋፊዎች ተቋማቱን እንዲጎበኙ ዝግጅት ያደርጋል። አስቀድመን እቅድ የምናወጣ እንዲሁም በይሖዋ የምንታመን ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንችል ይሆናል።—ምሳሌ 21:5፤ 1 ዮሐ. 5:14, 15
3, 4. (ሀ) የቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ማንን ማነጋገር ይኖርብናል? (ለ) የጥናቱን ፕሮግራም በተመለከተ ምን ማብራሪያ መስጠት ትችላላችሁ?
3 መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ጥያቄ የምናቀርብበት መንገድ እንደ ተቋሙ ዓይነት ሊለያይ ይችላል። በርካታ ነዋሪዎችና ሠራተኞች ወዳሉባቸው ትላልቅ ተቋማት ስትሄዱ ወደ እንግዳ መቀበያ ክፍል ሄዳችሁ ኃላፊውን ለማነጋገር መጠየቃችሁ የተሻለ ነው። ጥቂት አረጋውያንና እነሱን የሚንከባከቡ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ባሉባቸው አነስተኛ የመኖሪያ ተቋማት ውስጥ ደግሞ የቤቱን ባለቤት በቀጥታ ለማነጋገር ቀጠሮ መያዙ የተሻለ ነው።
4 ወደ ሁለቱም ዓይነት ተቋማት በምትሄዱበት ወቅት የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ እንደሆናችሁ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና በዚያ ላይ መወያየት የሚወዱ ሰዎችን ለማነጋገር እንደመጣችሁ ግለጹ። በሳምንት ለ30 ደቂቃ ያህል በሚካሄድ የቡድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ነዋሪዎች ካሉ ጠይቁ። ውይይቱን ለማካሄድ የተለያዩ ጽሑፎችን መጠቀም ትችላላችሁ፤ ይሁንና ብዙ አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እና እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባሉት መጻሕፍት ተወዳጅ እንደሆኑ ገልጸዋል። እነዚህን ጽሑፎች ለኃላፊው ልታሳዩት ትችላላችሁ። የቡድን ውይይቱ የሚካሄድበትን ቀን፣ ሰዓት ወይም ቦታ ከኃላፊው ጋር በመነጋገር ልትወስኑ ትችላላችሁ፤ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች በተቋሙ ውስጥ ይለጠፋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችሁን ከመግለጽ ወደኋላ ማለት የለባችሁም። በተጨማሪም እዚያ የምትሄዱት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማከናወን ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመስጠት እንደሆነ ለኃላፊው ግለጹለት።
5. ጥናቱ አስደሳችና ጠቃሚ እንዲሆን ከተፈለገ የትኞቹን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?
5 ጥናቱን መምራት፦ ጥናቱን የምትመሩበት መንገድ በተቋሙ ውስጥ ያለውን ሁኔታና መንፈስ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፤ በመሆኑም አስተዋዮችና ዘዴያችሁን እንደ ሁኔታው ለመቀየር ዝግጁ መሆን አለባችሁ። ጥናቱን የሚመራው ሰው የሚጠናውን ጽሑፍ በርከት አድርጎ ማምጣት እንዲሁም ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ጽሑፎቹን መሰብሰብ ይኖርበታል። ለአንዳንዶቹ፣ በትላልቅ ፊደላት የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማምጣት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ አንቀጽ ከተነበበና ጥያቄ ከተጠየቀ በኋላ በተለመደው መንገድ ሐሳብ መስጠት ይችላሉ። ፈቃደኛ የሆኑና ችሎታው ያላቸው ሰዎች አንቀጾቹንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንዲያነብቡ መጠየቅ ይቻል ይሆናል። ጥናቱን በምትመሩበት ወቅት ዘና ያለ መንፈስ እንዲሰፍን ማድረግ እንዲሁም አዎንታዊ መሆንና ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት ይኖርባችኋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኃላፊውን በማስፈቀድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት የሚገነቡ ወይም የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጠቀሜታ የሚያጎሉ የድርጅቱን ቪዲዮዎች ማሳየት ትችላላችሁ። ጥናቱን አጭር ጸሎት በማቅረብ መጀመርና መዝጋት ይቻል ይሆናል። እንዲያውም አንዳንድ አስፋፊዎች የመንግሥቱ መዝሙሮች እንዲዘመሩ አድርገዋል።
6. የተቃውሞ ሐሳብ በሚሰነዘርበት ወቅት ምላሽ መስጠት የምትችሉት እንዴት ነው?
6 ጥናቱን በምትመሩበት ወቅት ከመካከላቸው አንዱ የሚነበበውን ወይም የሚብራራውን ሐሳብ ቢቃወምስ? መልስ ስትሰጡ አስተዋዮች ሁኑ። (ቆላ. 4:6) ምናልባት ላነሳው የተቃውሞ ሐሳብ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመጠቀም አጭር መልስ መስጠት ትችሉ ይሆናል። እንዲህ ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ከተሰማችሁ ግን ቅሬታውን እንደተቀበላችሁ ልትገልጹለትና ከጥናቱ በኋላ ብቻውን ልታወያዩት እንደምትችሉ ልትነግሩት ትችላላችሁ።
7. አንድ ሰው ጥያቄ ካለው ወይም ከፍተኛ የማወቅ ፍላጎት እንዳለው ካስተዋላችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
7 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጥያቄ የሚጠይቅ ወይም የበለጠ ለማወቅ ፍላጎት እንዳለው የሚገልጽ ሰው ይኖራል። አንዲት እህት ይህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማት እንዲህ ትላለች፦ “በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ይህ የእርስዎ የግል ጥያቄ ስለሆነ ጥናቱን ከጨረስን በኋላ ብንነጋገርበት አይሻልም? ያኔ ለብቻችን ሆነን እንወያይበታለን።” ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ካሉ በሌላ ጊዜ በግለሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ዝግጅት ማድረግ ይቻል ይሆናል።
8. በቡድንና በግለሰብ ደረጃ የሚመሩ ጥናቶች ሪፖርት የሚደረጉት እንዴት ነው?
8 በተቋሙ ውስጥ የሚካሄደውን ጥናት የሚመሩት ሰዎች ባይቀያየሩ ብዙውን ጊዜ የተሻለ ነው። በዚህ ሥራ የሚካፈሉ አስፋፊዎች በሙሉ ሰዓቱን ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። ጥናቱ አንዴ ቋሚ ከሆነ በኋላ ጥናቱን የሚመራው አስፋፊ የቡድን ጥናቱን በመራ ቁጥር አንድ ተመላልሶ መጠየቅ ሊይዝ በየወሩ ደግሞ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብሎ ሊመዘግብ ይችላል። ትምህርቱን መረዳት የሚችሉ አረጋውያንን በግለሰብ ደረጃ በምናስጠናበት ወቅት ግን ጥናቱን በተለመደው መንገድ ሪፖርት ማድረግ ይቻላል።
9, 10. በዚህ ሥራ የሚካፈሉ አስፋፊዎች ምን ዓይነት ባሕርያት ሊኖሯቸው ይገባል? አብራራ።
9 ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ፦ የቡድን ጥናቱ የሚመራበት ቋሚ ቀንና ሰዓት ቢኖረው ጠቃሚ ነው። በቡድን ጥናቱ የሚካፈሉት አረጋውያንም ሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች ጥናቱ በቋሚነት እንደሚደረግ እንዲሁም በሰዓቱ ተጀምሮ እንደሚያልቅ ይጠብቃሉ። (ማቴ. 5:37) በመሆኑም ቃላችሁን የምታከብሩ፣ ትጉዎችና ሥርዓታማ መሆን ይኖርባችኋል። የቡድን ጥናቱን ለመምራት ብቃት ያላቸው ሁለት አስፋፊዎች አብረው እንዲሄዱ ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ በተሞክሮ ታይቷል። (መክ. 4:9, 10) በትላልቅ ተቋማት ውስጥ ግን ተጨማሪ አስፋፊዎች ያስፈልጉ ይሆናል።
10 በተጨማሪም ወዳጃዊ ስሜት ማሳየትና በግለሰብ ደረጃ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው። (ፊልጵ. 2:4) በመጀመሪያው ቀን በጥናቱ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ ለመተዋወቅ ጥረት አድርጉ። ስማቸውን ማስታወሻ ላይ ያዙ፤ እንዲሁም በሚቀጥለው ጥናት ላይ እስክትገናኙ ድረስ ስማቸውን ለማጥናት ሞክሩ። ይሁንና አንዳንድ አረጋውያን በደንብ የማያውቁት ሰው በስማቸው ብቻ ሲጠራቸው ቅር ይሰኛሉ። ታጋሽና ርኅሩኅ ከሆናችሁ በጥናቱ ላይ የሚገኙ ሁሉ ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግላቸውና ከፍ ተደርገው እንደሚታዩ ይሰማቸዋል።
11. የቡድን ጥናቱን የሚመሩት አስፋፊዎች በተቋሙ ላሉት ሠራተኞች እንዲሁም ለአረጋውያኑ ቤተሰብ አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
11 በተቋሙ ላሉት ሠራተኞች እንዲሁም ለአረጋውያኑ ቤተሰብ አክብሮትና ደግነት ማሳየታችሁ አስፈላጊ ነው። ጥናቱ አንዴ በቋሚነት መካሄድ ከጀመረ በኋላ ኃላፊውን ሳታማክሩ ጥናቱ የሚመራበትን ቀንና ሰዓት እንዲሁም ውይይቱ የሚካሄድበትን መንገድ አለመለወጣችሁ ጥበብ ነው። ጥናቱ ከሚካሄድበት መንገድ ጋር በተያያዘ አስተያየት እንዲሰጣችሁ አልፎ አልፎ ኃላፊውን ጠይቁት። የአረጋውያኑ ቤተሰብ ጥናቱ በሚካሄድበት ቀን ሊጠይቋቸው ከመጡ ከእነሱ ጋር ለመተዋወቅ ጥረት አድርጉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምታደርጉበትን ዓላማ ግለጹላቸው። በተቋሙ ውስጥ ላለው የቤተሰባቸው አባል ከልባችሁ እንደምታስቡ አረጋግጡላቸው። በጥናቱ ላይ ተገኝተው እንዲያዳምጡ ጋብዟቸው።
12, 13. በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ መመሥከር ግሩም ውጤት እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ተናገር።
12 ምን ውጤቶች ተገኝተዋል? ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ጉባኤዎች በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ አበረታች ውጤቶች እንደተገኙ ሪፖርት አድርገዋል። በአንድ ተቋም ውስጥ በመጀመሪያው ዕለት በተደረገ ውይይት ላይ 20 አረጋውያን ተገኝተዋል። ይህም ስድስት አረጋውያን በግለሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ በር ከፍቷል። ከእነዚህ መካከል አንደኛው ከጊዜ በኋላ ተጠምቀዋል። በሌላ ተቋም በጥናቱ ላይ የተገኙ አንዲት የ85 ዓመት አረጋዊት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የተነሳሱ ሲሆን ለመጠመቅ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በአንድ ተቋም ውስጥ ደግሞ የአሠራር ለውጥ በተደረገበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱት የቡድን ጥናት እንዲሰረዝ ተወስኖ ነበር፤ ይሁን እንጂ አረጋውያኑ ለተቋሙ ኃላፊ ተቃውሟቸውን አሰሙ! በኋላም ጥናቱ በድጋሚ የተጀመረ ሲሆን ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ሰዎች በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመሩ።
13 በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ ላሉ ሰዎች የምናሳየው ፍቅር የሚነካው የአረጋውያኑን ልብ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ጊዜ የተቋሙ ሠራተኞች በጥናቱ ላይ ሊገኙ አልፎ ተርፎም ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ላሉት አረጋውያን በግለሰብ ደረጃ ትኩረት መስጠታችን ለአካባቢው ሰዎችም ግሩም ምሥክርነት ይሰጣል። (1 ጴጥ. 2:12) አንድ ኃላፊ የጥናቱ ዓላማ ከተነገረው በኋላ “ታዲያ እስካሁን ያልመጣችሁት ለምንድን ነው? ለመሆኑ መቼ ነው የምትጀምሩት?” ብሏል። ሌላ ኃላፊ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በዚህ አካባቢ በሚገኙ የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት በሙሉ ይህ ጥናት ቢካሄድ በጣም እደግፋለሁ። ይህ ሥራ የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ በነፃ ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት አንዱ ነው።” በሃዋይ የሚገኝ የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም የይሖዋ ምሥክሮች በተቋሙ ላሉ ሁሉ “ውድ ሀብት” እንደሆኑ በመግለጽ ላከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የምሥክር ወረቀት ሰጥቷቸዋል።
14. በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ ያሉትን ለመርዳት መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ አረጋውያን እሱን እንዲያወድሱት ጋብዟቸዋል። (መዝ. 148:12, 13) ይህ ግብዣ በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ የሚኖሩትንም ያጠቃልላል። ታዲያ ምሥራቹን ልትነግሯቸው የሚገቡ በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚገኙበት የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም በክልላችሁ ውስጥ አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችና የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት ኃላፊዎች በሚያደርጉልን እገዛ ተጠቅመን በእነዚህ ቦታዎች ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንችላለን። በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ የይሖዋን ምሳሌ እንከተላለን።—መዝ. 71:9, 18