ለአምልኮ የምንጠቀምባቸው አዳዲስ መዝሙሮች!
ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ ጥቅምት 4 ቀን 2014 ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የመዝሙር መጽሐፋችንን ለማሻሻል እቅድ መያዙ በማስታወቂያ ተነግሮ ነበር። ይህ በጣም አስደሳች ዜና ነበር! የመንግሥቱ መዝሙሮች በአምልኳችን ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳላቸው በስብሰባው ላይ ለተገኙት ሁሉ ተገልጾላቸው ነበር።—መዝ. 96:2
2 ‘መዝሙር መጽሐፉን ማሻሻል ያስፈለገው ለምንድን ነው?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያለን መረዳት አሁንም እየጠራ ነው፤ ይህ ደግሞ በመዝሙሮቹ ግጥም ላይ ለውጥ ያመጣል። (ምሳሌ 4:18) ሌላው ምክንያት ደግሞ በበርካታ ቋንቋዎች፣ መዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ አገላለጾች የተወሰዱት ከቀድሞው አዲስ ዓለም ትርጉም መሆኑ ነው። እነዚህ ግጥሞች ከተሻሻለው ትርጉም አንጻር መታረም ይኖርባቸዋል። ግጥሙን ማሻሻል በራሱ ብዙ ሥራ ስለሚጠይቅ በዚህ አጋጣሚ ጥቂት አዳዲስ መዝሙሮችን በመጽሐፉ ውስጥ ለመጨመር ተወስኗል።
3 አዳዲሶቹን መዝሙሮች መጠቀም ለመጀመር አዲሱ የመዝሙር መጽሐፍ እስኪታተም መጠበቅ አለብን? እንደዚያ ማድረግ አያስፈልገንም። በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ በርካታ አዳዲስ መዝሙሮች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ እንደሚወጡ ስንገልጽላችሁ ደስ ይለናል። አዲስ መዝሙር ሲወጣ በአገልግሎት ስብሰባ መደምደሚያ ላይ እንዲዘመር ዝግጅት የሚደረግ ሲሆን ፕሮግራሙ ላይ “አዲስ መዝሙር” የሚል መግለጫ ይኖራል።
4 አዳዲሶቹን መዝሙሮች መለማመድ የሚቻለው እንዴት ነው? አዲስ መዝሙር መለማመድ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ያም ሆኖ እንደ መዝሙራዊው በጉባኤ መካከል መዘመር እንጂ “ዝም” ማለት አንፈልግም። (መዝ. 30:12) አንድን አዲስ መዝሙር ለመለማመድ የሚከተሉትን ቀላል ዘዴዎች ተከተሉ፦
በድረ ገጻችን ላይ የሚወጣውን የመዝሙሩን የፒያኖ ቅጂ በተደጋጋሚ አዳምጡ። ሙዚቃውን ብዙ ጊዜ በሰማችሁት መጠን ዜማውን ማስታወስ ቀላል ይሆንላችኋል።
ግጥሙን አጥኑት፤ እንዲሁም በቃላችሁ ለመያዝ ሞክሩ።
መዝሙሩን በመክፈት ግጥሙን ከዜማው እኩል ለማለት ሞክሩ። መዝሙሩን በደንብ እስክትችሉት ድረስ ደጋግማችሁ እንዲህ አድርጉ።
ቤተሰባችሁ አዳዲሶቹን መዝሙሮቹን ጥሩ አድርጎ መዘመር እስኪችል ድረስ በቤተሰብ አምልኮ ላይ በተደጋጋሚ ተለማመዷቸው።
5 በመጪዎቹ ወራት በአገልግሎት ስብሰባ መደምደሚያ ላይ አዲስ መዝሙር የሚዘመር ከሆነ ተሰብሳቢዎቹ መጀመሪያ ፒያኖውን ብቻውን እንዲያዳምጡት ይደረጋል። ከዚያ ለሁለተኛ ጊዜ ሲከፈት ወትሮ እንደሚደረገው ፒያኖውን ተከትለው ይዘምራሉ።
6 በስብሰባዎቻችን ላይ መዘመር፣ ድምፃችንን አስተባብረን ይሖዋን የማወደስ አጋጣሚ ስለሚከፍትልን ደስታ ያስገኝልናል። በመሆኑም ለመዘመር ስንዘጋጅ ሳያስፈልግ ከቦታችን ተነስተን የመሄድ ልማድ እንዳይኖረን መጠንቀቅ ይገባናል።
7 ቅዱስ ለሆኑት መዝሙሮቻችን አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሩ በፊት ሙዚቃ ይኖራል። ቅንዓት ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ከአራቱም የምድር ማዕዘናት ለአምልኮ የምንጠቀምባቸውን ግሩም መዝሙሮች ለማዘጋጀት በራሳቸው ወጪ ወደ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በዓመት ሁለት ጊዜ ይመጣሉ። በመሆኑም ሊቀ መንበሩ ወንበራችንን በመያዝ የተዘጋጀውን በኦርኬስትራ የተቀነባበረ መዝሙር እንድናዳምጥ ሲጋብዘን መመሪያውን መከተል ይኖብናል። እንዲህ ማድረጋችን ቀጥሎ ለሚቀርበው ትምህርት ልባችንን እንድናዘጋጅ ይረዳናል።—ዕዝራ 7:10 NW
8 ዛሬ ስብሰባችንን የምንደመድመው “በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣ!” የሚል ርዕስ ባለው አዲስ መዝሙር ነው። በቅርቡ በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የወጣው ይህ መዝሙር የተቀነባበረው የመንግሥቱን መወለድ 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ነው።
9 አዲሶቹ መዝሙሮች ከይሖዋ ያገኘናቸው ‘ጥሩ ነገሮች’ እንደሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 12:35ሀ) እንግዲያው አዳዲሶቹን መዝሙሮች ለመማርና ለአምላካችን ውዳሴና ክብር በሚያመጣ መንገድ ከልባችን ለመዘመር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!—መዝ. 147:1