ለጥናት የሚረዱ ሐሳቦች
‘መንፈሳዊ መዝሙሮችን’ በቃልህ ያዝ
“የከንቱነት ስሜት ሲሰማኝ ይሖዋ JW ብሮድካስቲንግ ላይ ባሉት መዝሙሮች አማካኝነት ያበረታታኛል።”—ሎሬን፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ክርስቲያኖች ከጥንት ጀምሮ ‘መንፈሳዊ ዝማሬዎችን’ ለአምልኮ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። (ቆላ. 3:16) እነዚህን መዝሙሮች በቃልህ ከያዝክ የመዝሙር መጽሐፍ ወይም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በእጅህ ባይኖርም እንኳ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። የሚከተሉት ሐሳቦች መዝሙሮችን በቃልህ ለመያዝ ይረዱሃል።
ግጥሙን በጥንቃቄ በማንበብ ትርጉሙን ለመረዳት ሞክር። የአንድ ነገር ትርጉም በደንብ ከገባህ ማስታወስ ቀላል ይሆንልሃል። ኦሪጅናል መዝሙሮችንና ለልጆች የተዘጋጁ መዝሙሮችን ጨምሮ የሁሉም መዝሙሮቻችን ግጥም jw.org ላይ ይገኛል። “ላይብረሪ” በሚለው ክፍል ሥር “መዝሙሮች” የሚለውን ተመልከት።
ግጥሙን በእጅህ ጻፍ። እንዲህ ማድረግህ ስንኞቹ በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጹ ሊያደርግ ይችላል።—ዘዳ. 17:18
ጮክ ብለህ ተለማመድ። መዝሙሩን በተደጋጋሚ አንብበው ወይም ዘምረው።
የማስታወስ ችሎታህን ፈትን። ግጥሙን ሳታይ ስንኞቹን ለማስታወስ ሞክር፤ ከዚያም ምን ያህል ማስታወስ እንደቻልክ ገምግም።