“ከአምላክ ቃል ጋር ተዋወቅ” —ውይይት ለመጀመር ተጠቀሙበት
1. ለአገልግሎት የሚረዳ ምን አዲስ መሣሪያ አግኝተናል?
1 አዲስ ዓለም ትርጉም መግቢያው ላይ “ከአምላክ ቃል ጋር ተዋወቅ” የሚል ክፍል አለው። ለአገልግሎት መግቢያ በምንዘጋጅበት ወቅት ይህን አዲስ መሣሪያ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ክፍል ልክ እንደ ማመራመር መጽሐፍ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ሥር ጥቅሶችን የያዘ በመሆኑ ውይይት ለማስጀመር በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
2. “ከአምላክ ቃል ጋር ተዋወቅ” የሚለውን ክፍል በአገልግሎታችን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
2 ጥያቄ 8ን በመጠቀም እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “ብዙዎች ‘በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራና ሥቃይ ተጠያቂው አምላክ ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። [በአንዳንድ ክልሎች ጥያቄውን ለግለሰቡ በቀጥታ ማሳየት ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።] እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።” ከቀረቡት ጥቅሶች መካከል አንዳንዶቹን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካነበብክ በኋላ አብራራለት። ግለሰቡ ፍላጎት ካሳየ በመግቢያው ላይ የተዘረዘሩትን 20 ጥያቄዎች በማሳየት በሚቀጥለው ጊዜ የምትወያዩበትን ጥያቄ አስመርጠው። አሊያም ደግሞ በተወያያችሁበት ርዕስ ላይ ሰፋ ያለ ሐሳብ የያዘ የማስጠኛ ጽሑፍ ልታበረክትለት ትችላለህ።
3. የክርስትናን እምነት የማይከተሉ ሰዎች ባሉበት ክልል ስንሰብክ “ከአምላክ ቃል ጋር ተዋወቅ” በሚለው ክፍል ተጠቅመን ውይይት መጀመር የምንችለው እንዴት ነው?
3 የክርስትናን እምነት የማይከተሉ ሰዎች ባሉበት ክልል ስንሰብክ ጥያቄ 4 እንዲሁም ከጥያቄ 13 እስከ 17 ይበልጥ ሊረዱን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በጥያቄ 17 ላይ ያለውን ሐሳብ በመጠቀም እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “ለቤተሰብ ጠቃሚ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ከሰዎች ጋር አጠር ያለ ውይይት እያደረግን ነው። በዛሬው ጊዜ ቤተሰቦች ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ይሰማዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ‘ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር’ የሚለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ብዙ ባለትዳሮች ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። [ይህ ሐሳብ የተወሰደው ከኤፌሶን 5:33 መሆኑን መጥቀስ አያስፈልግህም። ከአንዲት ሴት ጋር ስትነጋገር ደግሞ በኤፌሶን 5:28 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በቃልህ ልትነግራት ትችላለህ።] በትዳር ውስጥ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ይመስልሃል?”
4. የክርስትናን እምነት ከማይከተል ሰው ጋር ያደረግኸውን ውይይት ስትደመድም ምን ማድረግ ትችላለህ?
4 ውይይታችሁን ስትደመድሙ፣ በሌላ ጊዜ ተገናኝታችሁ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ። በተወያያችሁበት ጥያቄ ሥር በተጠቀሱት ሌሎች ጥቅሶች ላይ መነጋገር እንደምትችሉ ልትገልጽ ትችላለህ። ተስማሚ ጊዜ መርጠህ፣ ስትወያዩባቸው የነበሩት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ እንደሆኑ ለግለሰቡ ንገረው። ከግለሰቡ ጋር ቀደም ሲል ያደረጋችሁትን ውይይትና ግለሰቡ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን አመለካከት ከግምት በማስገባት ትኩረቱን ሊስብ እንደሚችል የምታስበውን ጽሑፍ አበርክትለት።—የታኅሣሥ 2013 የመንግሥት አገልግሎታችንን አባሪ ተመልከት።