ክርስቲያናዊ ሕይወት
በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ በርካታ ሰዎች፣ ስለ አምላክ እውነቱን ለማወቅ ፍለጋ ላይ ናቸው ሊባል ይችላል። (ኢሳ 55:6) ለእነዚህ ሰዎች እውነትን ደረጃ በደረጃ ማስተማር እንድንችል ደግሞ በተደጋጋሚ ተመልሰን በመሄድ ልናነጋግራቸው ይገባል። ሰዎች የሚያጋጥማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ የተለያየ ነው፤ በመሆኑም የሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግ የምንጠቀምበትን ዘዴ እንደየሰዉ ሁኔታ መለዋወጥ አለብን። ዋናው ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር መሆኑን መርሳት የለብንም፤ ለዚህም ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን እንዲሁም በእያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ ወቅት አንድ ግብ ለማሳካት መጣራችን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ያስችለናል።
ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
በአጭር ጊዜ ምናልባትም በጥቂት ቀናት ውስጥ ተመልሰህ ለመሄድ ጥረት አድርግ።—ማቴ 13:19
ወዳጃዊ ስሜትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ አነጋግራቸው። ዘና ያለ መንፈስ እንዲኖር አድርግ
ስትገናኙ ሞቅ ባለ መንገድ ሰላምታ አቅርብ። ግለሰቡን በስሙ እየጠራህ አነጋግረው። ተመልሰህ የመጣህበትን ምክንያት ግለጽለት፤ ለምሳሌ ባለፈው ውይይታችሁ ላይ ያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ፣ አዲስ መጽሔት ለመስጠት፣ ድረ ገጻችንን ለማስተዋወቅ፣ ቪዲዮ ለማሳየት አሊያም መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናበትን መንገድ ለመጠቆም ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ አንተ ከተዘጋጀህበት የተለየ ርዕሰ ጉዳይ ካነሳ፣ በዚያ ላይ መወያየት ትችላላችሁ።—ፊልጵ 2:4
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ሐሳብ በመናገር፣ ምናልባትም ጽሑፍ በመስጠት በግለሰቡ ልብ ውስጥ የተከልከውን የእውነት ዘር ውኃ አጠጣው። (1ቆሮ 3:6) ከግለሰቡ ጋር ወዳጃዊ ግንኙነት እንዲኖርህ ጥረት አድርግ
ለቀጣዩ ተመላልሶ መጠየቅ መሠረት ጣል