በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በአገልግሎት ላይ ያገኘነው ሰው ፍላጎት ካሳየ ግለሰቡ ቤቱ በሚገኝበት ጊዜ ላይ ተመልሰን በመሄድ የዘራነውን የእውነት ዘር ማጠጣት እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 3:6) ይህን ለማድረግ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ከግለሰቡ ጋር ከመለያየታችን በፊት ተመልሰን የምንመጣበትን ጊዜ ቀጠሮ በመያዝ ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት እንጥላለን። ከዚህ በተጨማሪ በድጋሚ ስንገናኝ ልንወያይበት የምንችል አንድ ጥያቄ ማንሳታችን ጠቃሚ ነው። ይህም ያነጋገርነው ሰው ተመልሰን የምንመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንዲጠብቅ ያደርገዋል፤ ያነሳንለት ጥያቄ መልስ ባበረከትንለት ጽሑፍ ላይ የሚገኝ ከሆነ ደግሞ ጽሑፉን ለማንበብ ይበልጥ ይነሳሳል። ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት መጣል ግለሰቡን በድጋሚ ማነጋገር ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል፤ ምክንያቱም የምንወያይበትን ርዕሰ ጉዳይ አስቀድመን መርጠናል፤ ግለሰቡም ቢሆን ስለ ምን ጉዳይ እንደምንነጋገር ግራ አይገባውም። በድጋሚ ስንገናኝ ወደ እሱ የመጣነው ቀደም ሲል ያነሳንለትን ጥያቄ ለመመለስ እንደሆነ ከጠቆምነው በኋላ ወደ ውይይታችን መግባት እንችላለን።
በዚህ ወር እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦
መግቢያ ስትዘጋጁ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ልትወያዩበት የምትችሉትን አንድ ጥያቄም አዘጋጁ። ከዚያም አብረዋችሁ ለሚያገለግሉት አስፋፊዎች ጥያቄውን ንገሯቸው።