የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w22 ሐምሌ ገጽ 14-19
  • ሁላችንንም የሚመለከት ጥንታዊ ትንቢት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሁላችንንም የሚመለከት ጥንታዊ ትንቢት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት እነማን ናቸው?
  • ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
  • ትንቢቱ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
  • ለ1 የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት
    አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
  • የእባቡ ዘር፣ እንዴት ተጋለጠ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ስምምነት
    መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
  • ይሖዋ ዓላማውን ይገልጣል
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
w22 ሐምሌ ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 30

ሁላችንንም የሚመለከት ጥንታዊ ትንቢት

“በአንተና በሴቲቱ መካከል . . . ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ።”—ዘፍ. 3:15

መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!

ማስተዋወቂያa

1. አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ምን አደረገ? (ዘፍጥረት 3:15)

አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ አንድ አስደናቂ ትንቢት በመናገር ለዘሮቻቸው ተስፋ ሰጠ። ይህ ትንቢት በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል።—ጥቅሱን አንብብ።

2. ይህን ትንቢት አስደናቂ የሚያደርገው ምንድን ነው?

2 ይህ ትንቢት የሚገኘው በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ሆኖም ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ በሆነ መልኩ ከዚህ ትንቢት ጋር ተያያዥነት አላቸው። የአንድ መጽሐፍ ስፌት ሁሉንም ገጾች ሰብስቦ እደሚያያይዝ ሁሉ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢትም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ በአንድ የጋራ መልእክት እንዲያያዙ ያደርጋል። ይህ መልእክት ዲያብሎስንና ክፉ የሆኑ ተከታዮቹን የሚደመስስ አንድ አዳኝ እንደሚላክ የሚገልጽ ነው።b ይህ ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ በጣም አስደሳች ነው!

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት እነማን ናቸው? ትንቢቱ የሚፈጸመው እንዴት ነው? እንዲሁም ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት ነው?

በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት እነማን ናቸው?

ምስሎች፦ “በዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት።” 1. እባቡ፦ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ሰይጣን። 2. የእባቡ ዘር፦ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት። 3. ሴቲቱ፦ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት። 4. የሴቲቱ ዘር፦ ኢየሱስ ክርስቶስና አብረውት የሚገዙት ቅቡዓን በሰማይ ላይ ክብር ተላብሰው። ምስሎቹ በአንቀጽ 4, 5, 7 እና 8 በድጋሚ ይገኛሉ።

4. እባቡ ማን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

4 በዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት “እባቡ፣” የእባቡ “ዘር፣” “ሴቲቱ” እና የሴቲቱ ‘ዘር’ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የእያንዳንዳቸውን ማንነት ለማወቅ ይረዳናል።c በመጀመሪያ ‘የእባቡን’ ማንነት እንመልከት። እውነተኛ እባብ፣ ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ የተናገረውን ነገር ሊረዳ አይችልም። በመሆኑም ይሖዋ ፍርዱን ያስተላለፈው ማሰብ በሚችል ፍጡር ላይ መሆን አለበት። ይህ ፍጡር ማን ነው? ራእይ 12:9 ማንነቱን በግልጽ ይነግረናል። ጥቅሱ “የጥንቱ እባብ” ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ በቀጥታ ይናገራል። ይሁንና የእባቡ ዘር ማን ነው?

መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ሰይጣን።

እባቡ

ሰይጣን ዲያብሎስ፤ ራእይ 12:9 “የጥንቱ እባብ” እሱ እንደሆነ ይገልጻል (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

5. የእባቡ ዘር እነማንን ያካትታል?

5 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ “ዘር” የሚለውን ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። ይህም ሲባል አንዳንዶች አንድን አካል በጣም ከመምሰላቸው የተነሳ እንደ ልጆቹ ይቆጠራሉ እንደማለት ነው። ከዚህ አንጻር የእባቡ ዘር እንደ ሰይጣን ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን የሚቃወሙ መንፈሳዊ ፍጥረታትን እና ሰዎችን ያካትታል። ይህም በኖኅ ዘመን በሰማይ ላይ የነበራቸውን ቦታ የተዉትን መላእክትና እንደ አባታቸው እንደ ዲያብሎስ ዓይነት ባሕርይ ያላቸውን ክፉ ሰዎች ይጨምራል።—ዘፍ. 6:1, 2፤ ዮሐ. 8:44፤ 1 ዮሐ. 5:19፤ ይሁዳ 6

ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት።

የእባቡ ዘር

ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን የሚቃወሙ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታትና ሰዎች (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

6. “ሴቲቱ” ሔዋን ልትሆን የማትችለው ለምንድን ነው?

6 ቀጥሎ ደግሞ ‘የሴቲቱን’ ማንነት እንመልከት። ሴቲቱ ሔዋን ልትሆን አትችልም። ለምን? አንድ ምክንያት ብቻ እንመልከት። ትንቢቱ የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ ‘እንደሚጨፈልቀው’ ይናገራል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው እባቡ ሰይጣን ነው። ሰይጣን ደግሞ መንፈሳዊ ፍጡር ስለሆነ የሔዋን ዘር የሆነ ማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው እሱን ሊጨፈልቀው አይችልም። ታዲያ ሰይጣን የሚጠፋው እንዴት ነው?

7. ራእይ 12:1, 2, 5, 10 እንደሚያሳየው በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ማን ነች?

7 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ማንነት በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። (ራእይ 12:1, 2, 5, 10⁠ን አንብብ።) ሴቲቱ በምድር ላይ ያለች ሴት አይደለችም። ጨረቃ ከእግሯ ሥር አለች፤ በራሷም ላይ 12 ከዋክብት ያሉት አክሊል አድርጋለች። ሴቲቱ አስደናቂ ልጅ ማለትም የአምላክን መንግሥት ወልዳለች። መንግሥቱ ያለው በሰማይ ነው፤ በመሆኑም ሴቲቱም ያለችው በሰማይ ላይ መሆን አለበት። ሴቲቱ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ታመለክታለች።—ገላ. 4:26

ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት።

ሴቲቱ

ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈው የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

8. የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ማን ነው? የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነውስ መቼ ነው? (ዘፍጥረት 22:15-18)

8 የአምላክ ቃል የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ማን እንደሆነ ለማወቅም ይረዳናል። የዘሩ ዋነኛ ክፍል የሚመጣው ከአብርሃም የትውልድ መስመር እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፍጥረት 22:15-18⁠ን አንብብ።) ልክ ትንቢቱ እንደሚለው ኢየሱስ የመጣው ከዚህ ታማኝ ሰው የትውልድ ሐረግ ነው። (ሉቃስ 3:23, 34) ሆኖም ይህ ዘር ሰይጣን ዲያብሎስን ጨፍልቆ ከሕልውና ውጭ ማድረግ ስላለበት ተራ ሰው ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ የአምላክ ልጅ ሆነ። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ሆነ። (ገላ. 3:16) ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳ በኋላ ይሖዋ “የክብርና የሞገስ ዘውድ” ደፋለት፤ እንዲሁም ‘ሥልጣንን ሁሉ በሰማይና በምድር’ ሰጠው። ከተሰጠው ሥልጣን መካከል ‘የዲያብሎስን ሥራ የማፍረስ’ ሥልጣን ይገኝበታል።—ዕብ. 2:7፤ ማቴ. 28:18፤ 1 ዮሐ. 3:8

ኢየሱስ ክርስቶስና አብረውት የሚገዙት ቅቡዓን በሰማይ ላይ ክብር ተላብሰው።

የሴቲቱ ዘር

ኢየሱስ ክርስቶስ እና አብረውት የሚገዙት 144,000 ቅቡዓን (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

9-10. (ሀ) የሴቲቱ ዘር ሌላ ማንን ያካትታል? የሴቲቱ ዘር ክፍል የሚሆኑትስ መቼ ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

9 ይሁንና ይህ ዘር ሁለተኛ ክፍልም አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአይሁዳውያንና ለአሕዛብ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ሐሳብ የዘሩን ሁለተኛ ክፍል ማንነት ለማወቅ ይረዳናል፤ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ በተስፋውም ቃል መሠረት ወራሾች ናችሁ።” (ገላ. 3:28, 29) ይሖዋ አንድን ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባው ያ ሰው የሴቲቱ ዘር ክፍል ይሆናል። በመሆኑም የሴቲቱ ዘር ኢየሱስን እና አብረውት የሚገዙትን 144,000 ቅቡዓን ያካትታል። (ራእይ 14:1) ሁሉም አባታቸውን ይሖዋ አምላክን ይመስላሉ።

10 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሱትን ገጸ ባሕርያት ማንነት ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ይሖዋ ይህ ትንቢት ደረጃ በደረጃ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ በአጭሩ እንመለከታለን።

ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

11. የሴቲቱ ዘር “ተረከዙ” የቆሰለው በምን መንገድ ነው?

11 በዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው ትንቢት መሠረት እባቡ የሴቲቱን ዘር “ተረከዙን” ያቆስለዋል። ሰይጣን አይሁዳውያንን እና ሮማውያንን በማነሳሳት የአምላክን ልጅ እንዲገድሉት ባደረገበት ጊዜ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። (ሉቃስ 23:13, 20-24) የተረከዝ ቁስል አንድን ሰው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከእንቅስቃሴ ውጭ እንደሚያደርገው ሁሉ ኢየሱስም ሞቶ ለሦስት ቀናት ያህል መቃብር ውስጥ መቆየቱ ለጊዜው ከእንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆን አድርጎታል።—ማቴ. 16:21

12. የእባቡ ራስ የሚጨፈለቀው መቼ እና እንዴት ነው?

12 በዘፍጥረት 3:15 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም ከተፈለገ ኢየሱስ መቃብር ውስጥ መቅረት የለበትም። ለምን? ምክንያቱም በትንቢቱ መሠረት የሴቲቱ ዘር የእባቡን ዘር ይጨፈልቃል። ይህ እንዲሆን ኢየሱስ ከተረከዝ ቁስሉ ማገገም አለበት። ደግሞም አገግሟል! ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ትንሣኤ አግኝቶ የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር ሆነ። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ ሰይጣንን ጨፍልቆ ከሕልውና ውጭ ያደርገዋል። (ዕብ. 2:14) ክርስቶስና ተባባሪ ገዢዎቹ የእባቡን ዘር ማለትም የአምላክን ጠላቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ላይ ጠራርገው ያጠፋሉ።—ራእይ 17:14፤ 20:4, 10d

ከዘፍጥረት 3:15 አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉልህ ክንውኖች

ከዘፍጥረት 3:15 አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉልህ ክንውኖችን የሚያሳይ የጊዜ ሰሌዳ። ሀ. 1943 ዓ.ዓ.፦ አብርሃም በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ሲመለከት። ለ. 29 ዓ.ም.፦ ኢየሱስ፣ ዮሐንስ ካጠመቀው በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባ። ሐ. 33 ዓ.ም. ፋሲካ፦ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ። መ. 33 ዓ.ም. ጴንጤቆስጤ፦ በክርስቶስ ተከታዮች ራስ ላይ “የእሳት ምላሶች“ ይታያሉ። ሠ. 1914 ዓ.ም. ገደማ፦ ኢየሱስ ሰይጣንን እና አጋንንቱን ከሰማይ ሲያባርራቸው። ረ. የሺው ዓመት መጨረሻ፦ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ እሳት ሐይቅ ሲወረወሩ።
  1. ሀ. 1943 ዓ.ዓ.

    አምላክ የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ከአብርሃም የትውልድ ሐረግ እንደሚመጣ የገባው ቃል መፈጸም ጀመረ። (ዘፍ. 12:1-3፤ 22:15-18)

  2. ለ. 29 ዓ.ም.

    ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ፤ በዚህ ጊዜ የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ሆነ። (ማቴ. 3:16፤ ገላ. 3:16)

  3. ሐ. 33 ዓ.ም. ፋሲካ

    ኢየሱስ ተረከዙ ቆሰለ፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በኋላ አገገመ። (ማቴ. 16:21፤ 26:1, 2)

  4. መ. 33 ዓ.ም. ጴንጤቆስጤ

    የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል ከሚሆኑት ሰዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ተቀቡ። (ሥራ 2:1-4፤ ገላ. 3:29)

  5. ሠ. 1914 ገደማ

    ሰይጣን ከሰማይ ተባረረ፤ በሴቲቱ ዘር ላይ የሚደርሰው ስደትም ተፋፋመ። (ራእይ 12:9, 12, 17)

  6. ረ. የሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ

    ሰይጣን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጨፈለቃል። (ራእይ 20:7, 10)

ትንቢቱ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

13. የዚህ ትንቢት ፍጻሜ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

13 ራስህን የወሰንክ የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ከዚህ ትንቢት ፍጻሜ እየተጠቀምክ ነው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል። የአባቱንም ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም በእሱ አማካኝነት ይሖዋ አምላክን ማወቅና መውደድ ችለናል። በተጨማሪም ከኢየሱስ ትምህርቶች እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ጉባኤን ከሚመራበት መንገድ ጥቅም አግኝተናል። የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ አስተምሮናል። ደግሞም ሁላችንም ከኢየሱስ ሞት ማለትም ከተረከዙ መቁሰል ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ የደሙን ዋጋ ‘ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻን’ ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል።—1 ዮሐ. 1:7

14. ይሖዋ በኤደን የተናገረው ትንቢት ወዲያውኑ እንዳልተፈጸመ እንዴት እናውቃለን? አብራራ።

14 ይሖዋ በኤደን ያንን ትንቢት ሲናገር የተጠቀመባቸው ቃላት ትንቢቱ የሚፈጸመው በዚያ ወቅት እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ሴቲቱ ተስፋ የተሰጠበትን ዘር እስክታስገኝ፣ ዲያብሎስ ተከታዮቹን እስኪያሰባስብ እንዲሁም በሁለቱ ቡድኖች መካከል ጠላትነት እስኪፈጠር ጊዜ ያስፈልጋል። ስለዚህ ትንቢት ማወቃችን ይጠቅመናል። ምክንያቱም ትንቢቱ፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም የይሖዋን አገልጋዮች እንደሚጠላ ያሳያል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። (ማር. 13:13፤ ዮሐ. 17:14) በተለይ ባለፉት 100 ዓመታት ይሄኛው የትንቢቱ ክፍል ሲፈጸም በግልጽ ተመልክተናል። እንዴት?

15. ዓለም ለአምላክ ሕዝቦች ያለው ጥላቻ የጨመረው ለምንድን ነው? ሰይጣንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም የምንለውስ ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ በ1914 መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ከሰማይ ተባረረ። አሁን እንቅስቃሴው በምድር አካባቢ ተገድቦ መጥፊያውን እየተጠባበቀ ነው። (ራእይ 12:9, 12) ሆኖም የሚጠብቀው እጁን አጣጥፎ አይደለም። ሰይጣን መጥፊያው መቅረቡን ስላወቀ በከፍተኛ ቁጣ ተሞልቷል፤ ቁጣውንም በአምላክ ሕዝቦች ላይ እየተወጣ ነው። (ራእይ 12:13, 17) በመሆኑም ዓለም ለአምላክ ሕዝቦች ያለው ጥላቻ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨምሯል። ሆኖም ሰይጣንን እና ተከታዮቹን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። (ሮም 8:31) እስካሁን እንደተመለከትነው በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት አብዛኛው ክፍል ፍጻሜውን አግኝቷል። ስለዚህ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን እንችላለን።

16-18. ከርተስ፣ ኡርሱላ እና ጄሲካ ዘፍጥረት 3:15⁠ን መረዳታቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?

16 በዘፍጥረት 3:15 ላይ ይሖዋ የሰጠን ተስፋ፣ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል። በጉዋም ሚስዮናዊ ሆኖ የሚያገለግለው ከርተስ እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋ ያለኝን ታማኝነት የሚፈትኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሕይወቴ ውስጥ አጋጥመውኛል። ሆኖም በዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው ትንቢት ላይ ማሰላሰሌ በሰማዩ አባቴ ላይ ያለኝን እምነት ይዤ እንድቀጥል ረድቶኛል።” ከርተስ፣ ይሖዋ ከፈተናዎቻችን ሁሉ የሚገላግለንን ቀን በጉጉት ይጠባበቃል።

17 በባቫሪያ የምትኖር ኡርሱላ የተባለች እህት ዘፍጥረት 3:15⁠ን መረዳቷ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፉን እንድታምን እንደረዳት ገልጻለች። ሌሎቹ ትንቢቶች በሙሉ ከዚህ ትንቢት ጋር ያላቸውን ተያያዥነት ስትገነዘብ በጣም ተደነቀች። እንዲህ ብላለች፦ “የሰው ልጆች ያለተስፋ እንዳይቀሩ ሲል ይሖዋ ወዲያውኑ እርምጃ እንደወሰደ ሳውቅ ልቤ በጥልቅ ተነካ።”

18 በማይክሮኔዥያ የምትኖረው ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን እንዳገኘሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገነዘብ የተሰማኝን ስሜት እስካሁን አስታውሳለሁ! በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ተረዳሁ። ይህም በአሁኑ ጊዜ የምንመራው አስቸጋሪ ሕይወት እውነተኛው ሕይወት እንዳልሆነ እንድገነዘብ ረዳኝ። በተጨማሪም ትንቢቱ ይሖዋን ማገልገሌ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት፣ ወደፊት ደግሞ ከአሁኑም የበለጠ አስደሳች ሕይወት ለማግኘት እንደሚረዳኝ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል።”

19. የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍል እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

19 እስካሁን እንደተመለከትነው ዘፍጥረት 3:15 ፍጻሜውን እያገኘ ነው። የሴቲቱ ዘርና የእባቡ ዘር ማንነት በግልጽ ታውቋል። የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነው ኢየሱስ ከተረከዝ ቁስሉ አገግሟል። እንዲያውም አሁን ግርማ የተላበሰና የማይሞት ሕይወት ያለው ንጉሥ ነው። በሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል ውስጥ የሚካተቱትን ሰዎች የመምረጡ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው። የትንቢቱ የመጀመሪያ ክፍል ፍጻሜውን ስላገኘ የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍልም እንደሚፈጸም ማለትም የእባቡ ራስ እንደሚጨፈለቅ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሰይጣን ከሕልውና ውጭ ሲሆን ታማኝ የሰው ልጆች በሙሉ እፎይ ይላሉ! እስከዚያው ድረስ ግን ተስፋ አትቁረጡ። አምላካችን እምነት የሚጣልበት ነው። በሴቲቱ ዘር አማካኝነት ‘ለምድር ብሔራት ሁሉ’ የተትረፈረፈ በረከት ያፈስላቸዋል።—ዘፍ. 22:18

በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ልታብራራ ትችላለህ?

  • “እባቡ፣” የእባቡ ዘር፣ “ሴቲቱ” እና የሴቲቱ ዘር እነማን ናቸው?

  • ትንቢቱ እስካሁን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

  • የትንቢቱ ፍጻሜ በግለሰብ ደረጃ የጠቀመህ እንዴት ነው?

መዝሙር 23 ይሖዋ መግዛት ጀምሯል

a በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ካልገባን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። ስለዚህ ትንቢት ማጥናታችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል፤ እንዲሁም እሱ የገባውን ቃል በሙሉ እንደሚፈጽም ይበልጥ እንድንተማመን ያደርገናል።

b በአዲስ ዓለም ትርጉም ተጨማሪ መረጃ ለ1 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c “በዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d “ከዘፍጥረት 3:15 አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉልህ ክንውኖች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ