የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ጥር ገጽ 14-19
  • ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርግ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተሟላ መረጃ አግኝ
  • የይሖዋን አመለካከት ከግምት አስገባ
  • አማራጮቹን ገምግም
  • ለስኬት የሚያበቃ ውሳኔ አድርግ
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የአምላክን አስተሳሰብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • ጥርጣሬን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ጥር ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 3

መዝሙር 35 ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ’

ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርግ

“የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው፤ እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ማወቅም ማስተዋል ነው።”—ምሳሌ 9:10

ዓላማ

እውቀትን፣ ማስተዋልንና ጥልቅ ግንዛቤን ተጠቅመን ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

1. ሁላችንም ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

በየዕለቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ያስፈልገናል። አንዳንዶቹን ውሳኔዎች ማድረግ ቀላል ነው፤ ለምሳሌ ‘ቁርስ ምን ልብላ’ ወይም ‘ስንት ሰዓት ልተኛ’ የሚለውን መወሰን ቀላል ነው። አንዳንዶቹን ውሳኔዎች ማድረግ ግን ከባድ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ውሳኔዎች በጤንነታችን፣ በደስታችን፣ በወዳጅ ዘመዶቻችን ወይም በአምልኳችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። እኛንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን ማድረግ እንፈልጋለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ውሳኔዎቻችን ይሖዋን የሚያስደስቱ እንዲሆኑ እንፈልጋለን።—ሮም 12:1, 2

2. ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?

2 ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ (1) የተሟላ መረጃ ማግኘት፣ (2) ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ከግምት ማስገባት እንዲሁም (3) አማራጮቹን መገምገም ይኖርብሃል። ይህ ርዕስ እነዚህን እርምጃዎች ያብራራል፤ እንዲሁም የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስገነዝበናል።—ምሳሌ 2:11

የተሟላ መረጃ አግኝ

3. ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የተሟላ መረጃ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

3 ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳህ የመጀመሪያው እርምጃ የተሟላ መረጃ ማግኘት ነው። ለምን? ለምሳሌ አንድ ታማሚ ያጋጠመውን ከባድ የጤና ችግር አስመልክቶ ሐኪሙን አማከረ እንበል። ሐኪሙ በመጀመሪያ ታማሚውን ሳይመረምረው ወይም ጥያቄዎችን ሳይጠይቀው ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚሰጠው ይወስናል? እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። አንተም በመጀመሪያ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት ካደረግክ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ። ይሁንና የተሟላ መረጃ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

4. በምሳሌ 18:13 መሠረት የተሟላ መረጃ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 ብዙውን ጊዜ፣ ጥያቄዎችን መጠየቃችን የተሟላ መረጃ ለማግኘት ይረዳናል። ለምሳሌ አንድ ግብዣ ላይ እንድትገኝ ተጠርተሃል እንበል። በግብዣው ላይ ብትገኝ ይሻላል? ጋባዡን ወይም የተዘጋጀውን ግብዣ በተመለከተ የማታውቅ ከሆነ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይኖርብሃል፦ “ግብዣው የሚካሄደው መቼና የት ነው? ስንት ሰዎች ይገኛሉ? ግብዣውን በኃላፊነት የሚከታተለው ማን ነው? እነማን ይገኛሉ? በግብዣው ላይ ምን ምን ይደረጋል? የአልኮል መጠጥ ይቀርባል?” የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ይረዳሃል።—ምሳሌ 18:13⁠ን አንብብ።

አንድ ወጣት ወንድም በስልኩ የደረሰውን ግብዣ አስመልክቶ ጓደኞቹን ሲጠይቃቸው፤ እነሱም ግብዣው ላይ ተጠርተዋል።

ጥያቄዎችን በመጠየቅ የተሟላ መረጃ አግኝ (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)a


5. የተሟላ መረጃ ካገኘህ በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

5 ቀጥሎም ያገኘኸውን መረጃ ከግምት በማስገባት አጠቃላይ ሁኔታውን በጥንቃቄ አጢን። ለምሳሌ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮት የሌላቸው ሰዎች በግብዣው ላይ እንደሚገኙ ወይም ደግሞ የአልኮል መጠጥ እንደሚቀርብና ግብዣውን በኃላፊነት የሚከታተል ሰው እንደማይኖር ብትገነዘብስ? ግብዣው መረን ወደለቀቀ ድግስ ሊቀየር የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? (1 ጴጥ. 4:3) በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብዣው የሚደረግበት ሰዓት ከጉባኤ ስብሰባህ ወይም ከአገልግሎት ፕሮግራምህ ጋር የሚጋጭ ቢሆንስ? አጠቃላይ ሁኔታውን ካጤንክ በኋላ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። ሆኖም መውሰድ ያለብህ ሌላም እርምጃ አለ። ስለ ጉዳዩ አንተ ያለህን አመለካከት አውቀሃል፤ ይሁንና ይሖዋ ያለው አመለካከትስ ምንድን ነው?—ምሳሌ 2:6

የይሖዋን አመለካከት ከግምት አስገባ

6. በያዕቆብ 1:5 መሠረት የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

6 አመለካከቱን ለማወቅ እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ይሖዋ አንድ ውሳኔ እሱን የሚያስደስት መሆን አለመሆኑን ለማስተዋል የሚያስችል ጥበብ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። እንዲህ ያለውን ጥበብ “ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል።”—ያዕቆብ 1:5⁠ን አንብብ።

7. የይሖዋን አመለካከት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

7 የይሖዋን አመራር ለማግኘት ከጸለይክ በኋላ መልሱን ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ጉዞ ላይ እያለህ መንገድ ጠፍቶብህ የአካባቢው ነዋሪ የሆነን አንድ ሰው እርዳታ ጠየቅክ እንበል። ግለሰቡ ገና መልስ ሳይሰጥህ በፊት ትተኸው ትሄዳለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። የሚሰጥህን መመሪያ በጥንቃቄ ታዳምጣለህ። በተመሳሳይም ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጥህ ከጸለይክ በኋላ ካለህበት ሁኔታ ጋር የሚያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ጥረት በማድረግ ይሖዋ የሚሰጥህን ምላሽ ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በአንድ ግብዣ ላይ ለመገኘት ወይም ላለመገኘት በምትወስንበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ መረን ስለለቀቀ ድግስ፣ ስለ መጥፎ ጓደኝነት እንዲሁም ከግል ምርጫችን ይልቅ የመንግሥቱን ጉዳዮች ስለማስቀደም የሚናገረውን ሐሳብ ከግምት ልታስገባ ትችላለህ።—ማቴ. 6:33፤ ሮም 13:13፤ 1 ቆሮ. 15:33

8. የይሖዋን አመለካከት የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ለማግኘት እርዳታ የሚያስፈልግህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 አንዳንድ ጊዜ ግን፣ የይሖዋን አመለካከት የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ለማግኘት እርዳታ ሊያስፈልግህ ይችላል። በዚህ ጊዜ ተሞክሮ ካለው ወንድም ወይም እህት ምክር ማግኘት ትችላለህ። ይሁንና በራስህ ምርምር ማድረግህም በእጅጉ ይጠቅምሃል። ምርምር ለማድረግ እንዲረዱን ታስበው በተዘጋጁት ጽሑፎች ለምሳሌ በምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች እና ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ሐሳቦችን ማግኘት ትችላለህ። ምርምር በምታደርግበት ጊዜ ግብህ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ መሆኑን አትዘንጋ።

ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የታየው ወጣት ወንድም “ለዘላለም በደስታ ኑር!” ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 35⁠ን ሲያነብ።

የይሖዋን አመለካከት ከግምት አስገባ (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)b


9. ውሳኔያችን ይሖዋን የሚያስደስት ስለመሆኑ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 5:17)

9 ውሳኔያችን ይሖዋን የሚያስደስት ስለመሆኑ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋን በሚገባ ማወቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ [ማወቅ] ማስተዋል ነው” ይላል። (ምሳሌ 9:10) አዎ፣ እውነተኛ ማስተዋል የሚገኘው የይሖዋን ባሕርያት፣ ዓላማውን እንዲሁም እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች ከማወቅ ነው። ‘ስለ ይሖዋ ከማውቀው ነገር አንጻር እሱን የሚያስደስተው ውሳኔ የትኛው ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።—ኤፌሶን 5:17⁠ን አንብብ።

10. ከቤተሰቦቻችን ፍላጎት ወይም ከባሕላችን የበለጠ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ትልቅ ቦታ መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

10 አንዳንድ ጊዜ፣ ይሖዋን ለማስደሰት ስንል በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች የሚያሳዝን ውሳኔ ማድረግ ሊኖርብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ወላጆች በአሳቢነት ተነሳስተው ሴት ልጃቸው ሀብታም ባል እንድታገባ ጫና ያሳድሩባት ይሆናል፤ ሆኖም ግለሰቡ በመንፈሳዊ ጠንካራ ላይሆን ይችላል። ልጃቸው የተመቻቸ ሕይወት እንድትመራ መፈለጋቸው የሚያስገርም ነገር አይደለም። ሆኖም ‘ይህ ሰው መንፈሳዊነቴን እንዳጠናክር ይረዳኛል?’ ብላ ራሷን መጠየቅ ይኖርባታል። ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት አለው? ማቴዎስ 6:33 መልሱን ይሰጠናል። ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን መፈለግ’ እንዳለባቸው ይናገራል። ወላጆቻችንንም ሆነ በማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች የምናከብር ቢሆንም ዋነኛው ፍላጎታችን ይሖዋን ማስደሰት ነው።

አማራጮቹን ገምግም

11. ያሉህን አማራጮች ለመገምገም የሚረዳህ በፊልጵስዩስ 1:9, 10 ላይ የተጠቀሰው የትኛው ባሕርይ ነው?

11 ከውሳኔህ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከግምት ካስገባህ በኋላ ያሉህን አማራጮች መገምገም ይኖርብሃል። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10⁠ን አንብብ።) ጥልቅ ግንዛቤ እያንዳንዱ አማራጭ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት እንድታስተውል ይረዳሃል። አንዳንድ ጊዜ ውሳኔውን ማድረግ ቀላል ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ውሳኔዎች ግን ጥቁርና ነጭ አይደሉም። ጥልቅ ግንዛቤ ውስብስብ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንድታደርግ ይረዳሃል።

12-13. ጥልቅ ግንዛቤ ከሥራ ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው?

12 አንድ ምሳሌ እንመልከት። ቤተሰብህን ለማስተዳደር የሚያስችል ሥራ እየፈለግክ ነው እንበል። ሁለት ሥራዎችን አገኘህ። ስለ ሥራዎቹ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት አደረግክ። የሥራውን ዓይነት፣ የሥራ ሰዓቱን፣ ወደ ሥራ ቦታው ለመሄድ የሚፈጅብህን ጊዜ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን አጣራህ። ሁለቱም ሥራዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጩ አይደሉም። ከሥራው ዓይነት ወይም ከደሞዙ አንጻር አንደኛው ሥራ የተሻለ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ከግምት ልታስገባቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ።

13 ለምሳሌ ሥራው ከጉባኤ ስብሰባ ሰዓት ጋር ይጋጭብሃል? ወይም ደግሞ ሥራው የቤተሰብህን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችልህን ጊዜ ይሻማብሃል? እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅህ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ማለትም መንፈሳዊነትህንና ቤተሰብህን ከቁሳዊ ነገሮች እንድታስቀድም ይረዳሃል። በዚህ መንገድ ይሖዋ የሚባርከው ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ።

14. ጥልቅ ግንዛቤና ፍቅር ሌሎችን እንዳናሰናክል የሚረዱን እንዴት ነው?

14 በተጨማሪም ጥልቅ ግንዛቤ ውሳኔያችን በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንድናስብ ያነሳሳናል፤ ይህም ‘ሌሎችን ከማሰናከል’ ይጠብቀናል። (ፊልጵ. 1:10) እንደ አለባበስና አጋጌጥ ካሉ የግል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የሆነ ዓይነት አለባበስ ወይም አጋጌጥ እንወድ ይሆናል። ይሁንና ምርጫችን በጉባኤ ውስጥ ወይም ከጉባኤው ውጭ ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ቅር የሚያሰኝ ቢሆንስ? ጥልቅ ግንዛቤ ስሜታቸውን እንድናከብር ይረዳናል። ፍቅር “የሌላውን ሰው ጥቅም” እንድንፈልግና ልከኛ እንድንሆን ያነሳሳናል። (1 ቆሮ. 10:23, 24, 32፤ 1 ጢሞ. 2:9, 10) በዚህ መንገድ ለሌሎች ያለንን ፍቅርና አክብሮት የሚያንጸባርቅ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።

15. አንድ ትልቅ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ምን ማሰብ ይኖርብሃል?

15 ትልቅ ውሳኔ የምታደርግ ከሆነ ውሳኔውን በሥራ ላይ ማዋል ምን እንደሚጠይቅ አስብ። ኢየሱስ ‘ወጪያችንን እንድናሰላ’ አሳስቦናል። (ሉቃስ 14:28) እንግዲያው ውሳኔውን ስኬታማ ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ፣ ገንዘብ ወይም ጥረት እንደሚጠይቅብህ አስላ። ምናልባትም እያንዳንዱ የቤተሰብህ አባል ያደረግከውን ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ከቤተሰብህ ጋር መወያየት ትችል ይሆናል። በዚህ መንገድ ዕቅድ ማውጣትህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ስታደርግ በውሳኔህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንዳለብህ ወይም ሌላ አማራጭ ብትከተል የተሻለ እንደሚሆን ትገነዘብ ይሆናል። ደግሞም ከቤተሰብህ አባላት ጋር መወያየትህና የሚሰጡህን ሐሳብ ማዳመጥህ ውሳኔውን ስኬታማ ለማድረግ እንዲተባበሩህ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ምሳሌ 15:22

ለስኬት የሚያበቃ ውሳኔ አድርግ

16. ለስኬት የሚያበቃ ውሳኔ እንድታደርግ የሚረዱህ የትኞቹ እርምጃዎች ናቸው? (“ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ውሳኔዎች ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

16 ከላይ የተጠቀሱትን እርምጃዎች ከተከተልክ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ዝግጁ ነህ ማለት ነው። የተሟላ መረጃ አግኝተሃል፤ እንዲሁም ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱህን መሠረታዊ ሥርዓቶች መርምረሃል። አሁን ይሖዋ ውሳኔህን ስኬታማ እንዲያደርግልህ መጸለይ ትችላለህ።

ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ውሳኔዎች ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

አንድ ወጣት ወንድም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ሊወስዳቸው የሚችላቸውን እርምጃዎች የሚያሳዩ ሥዕሎች፦ 1. በአጉሊ መነፅር ይመለከታል። 2. ይጸልያል። ዴስኩ ላይ መጽሐፍ ቅዱስና ታብሌት አለ። 3. ዴስኩ ላይ የተቀመጠውን ሚዛን በትኩረት ይመለከታል።
  • የተሟላ መረጃ አግኝ፦ ጥያቄዎችን ጠይቅ፤ ከዚያም አጠቃላይ ሁኔታውን አጢን (ምሳሌ 18:13)

  • የይሖዋን አመለካከት ከግምት አስገባ፦ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መርምር (ኤፌ. 5:17፤ ያዕ. 1:5)

  • አማራጮቹን ገምግም፦ ውሳኔው በአንተም ሆነ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስብ፤ እንዲሁም ውሳኔውን በሥራ ላይ ለማዋል ምን እንደሚጠይቅ አስላ (ፊልጵ. 1:9, 10)

17. ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው?

17 ከዚህ ቀደም በርካታ ጥሩ ውሳኔዎችን አድርገህ ይሆናል። ይሁንና ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ቁልፉ በራስህ ማስተዋል ወይም ተሞክሮ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ጥበብ መታመን ነው። እውነተኛ እውቀት፣ ማስተዋልና ጥልቅ ግንዛቤ ሊሰጥህ የሚችለው እሱ ብቻ ነው፤ ጥበብ የእነዚህ ነገሮች ውጤት ነው። (ምሳሌ 2:1-5) ይሖዋ እሱን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን እንድታደርግ ይረዳሃል።—መዝ. 23:2, 3

ጥሩ ውሳኔዎችን ከማድረግ ጋር በተያያዘ ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን ትምህርት እናገኛለን?

  • ምሳሌ 18:13

  • ኤፌሶን 5:17

  • ፊልጵስዩስ 1:9, 10

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

a የሥዕሉ መግለጫ፦ የተወሰኑ ወጣት ወንድሞችና እህቶች በስልካቸው ላይ ስለደረሳቸው ግብዣ ይወያያሉ።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንደኛው ወንድም በግብዣው ላይ ለመገኘት ከመወሰኑ በፊት ምርምር ያደርጋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ