የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 የካቲት ገጽ 14-19
  • የይሖዋን ይቅርታ መኮረጅ የምትችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋን ይቅርታ መኮረጅ የምትችለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስሜትህን ችላ አትበለው
  • ስሜትህን አክመው
  • አዎንታዊ ስሜቶችን አዳብር
  • ይቅር ባይ መሆን በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ አተኩር
  • ‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 የካቲት ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 8

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

የይሖዋን ይቅርታ መኮረጅ የምትችለው እንዴት ነው?

“ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላ. 3:13

ዓላማ

ይህ ርዕስ፣ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ለማለት የትኞቹን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ እንደምንችል ያብራራል።

1-2. (ሀ) አንድን ሰው ይቅር ማለት የሚከብደን በተለይ መቼ ሊሆን ይችላል? (ለ) ዴኒስ ይቅር ባይነት ያሳየችው እንዴት ነው?

ሌሎችን ይቅር ማለት ይከብድሃል? ብዙዎቻችን ይከብደናል፤ በተለይ አንድ ሰው የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር ከባድ የስሜት ጉዳት ካስከተለብን ግለሰቡን ይቅር ማለት ሊከብደን ይችላል። ይሁንና የደረሰብንን የስሜት ጉዳት አሸንፈን ይቅር ባይ መሆን እንችላለን። ለምሳሌ ዴኒስa የተባለች እህታችን አስደናቂ ይቅር ባይነት ያሳየችው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በ2017 ዴኒስ እና ቤተሰቧ አዲስ የተከፈተውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለመጎብኘት ሄደው ነበር። ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ሳሉ አንድ ሹፌር መኪናውን መቆጣጠር ስላቃተው መኪናቸውን ገጨው። ዴኒስ በአደጋው ራሷን ሳተች። በኋላ ላይ ስትነቃ ልጆቿ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ ባለቤቷ ብራያን ደግሞ እንደሞተ አወቀች። ዴኒስ ስለዚያ ወቅት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በሐዘን ተዋጥኩ፤ ግራ ተጋባሁ።” በኋላ ላይ ዴኒስ፣ ሹፌሩ አደጋውን ያደረሰው በአልኮል ወይም በዕፅ ተጽዕኖ ሥር ሆኖ አሊያም ትኩረቱ ተከፋፍሎ እንዳልሆነ ተገነዘበች። ከዚያም ይሖዋ የአእምሮ ሰላም እንዲሰጣት ጸለየች።

2 አደጋውን ያደረሰው ሹፌር፣ ነፍስ በማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ። ጥፋተኛ ነው ተብሎ ከተፈረደበት ሊታሰር ይችላል። ይሁንና ፍርድ ቤቱ ለዴኒስ፣ በሰውየው ላይ የሚተላለፈው ፍርድ በዋነኝነት የተመካው እሷ በምትሰጠው ምሥክርነት ላይ እንደሆነ አሳወቃት። ዴኒስ እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወቴ ውስጥ እጅግ አስከፊ የሆነውን ያንን ወቅት እንዳስታውስ በመገደዴ አንድ ሰው ቁስሌን ከፍቶ ጨው እንደነሰነሰብኝ ተሰማኝ።” ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ዴኒስ በቤተሰቧ ላይ ከፍተኛ ሥቃይ ባስከተለው ሰው ፊት ተቀምጣ ምሥክርነት እንድትሰጥ ፍርድ ቤት ቀረበች። ታዲያ ዴኒስ ምን አለች? ዳኛው ለግለሰቡ ምሕረት እንዲያሳዩት ጠየቀች።b ተናግራ ስትጨርስ ዳኛው ማልቀስ ጀመሩ። እንዲህ ብለዋል፦ “ዳኛ ሆኜ በሠራሁባቸው 25 ዓመታት፣ ችሎት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሰምቼ አላውቅም። የተበዳይ ቤተሰቦች ለበዳይ ምሕረት እንዳሳይ ጠይቀውኝ አያውቁም። ፍቅርና ይቅርታ የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ሰምቼ አላውቅም።”

3. ዴኒስ ይቅር ባይ እንድትሆን ያነሳሳት ምንድን ነው?

3 ዴኒስ ይቅር ባይ እንድትሆን የረዳት ምንድን ነው? በይሖዋ ይቅርታ ላይ ማሰላሰሏ ነው። (ሚክ. 7:18) ይሖዋ ላሳየን ይቅርታ አድናቆት ካለን ሌሎችን ይቅር ለማለት እንነሳሳለን።

4. ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል? (ኤፌሶን 4:32)

4 ይሖዋ፣ እሱ እኛን በነፃ ይቅር እንዳለን ሁሉ እኛም ሌሎችን በነፃ ይቅር እንድንል ይፈልጋል። (ኤፌሶን 4:32⁠ን አንብብ።) ጉዳት ያደረሱብንን ሰዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (መዝ. 86:5፤ ሉቃስ 17:4) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይበልጥ ይቅር ባይ ለመሆን የሚረዱንን ሦስት ነገሮች እንመለከታለን።

ስሜትህን ችላ አትበለው

5. በምሳሌ 12:18 መሠረት አንድ ሰው በደል ሲያደርስብን ምን ሊሰማን ይችላል?

5 በተለይ የቅርብ ጓደኛችን ወይም የቤተሰባችን አባል በንግግሩ ወይም በድርጊቱ ሲበድለን ከባድ የስሜት ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። (መዝ. 55:12-14) አንዳንድ ጊዜ፣ የደረሰብን የስሜት ሥቃይ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በስለት እንደተወጋን ያህል ሊሰማን ይችላል። (ምሳሌ 12:18⁠ን አንብብ።) የተጎዳውን ስሜታችንን ለማፈን ወይም ችላ ለማለት እንሞክር ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ማድረግ፣ በስለት ከተወጋን በኋላ ስለቱን እዚያው ቁስሉ ውስጥ እንደመተው ሊቆጠር ይችላል። በተመሳሳይም የተጎዳውን ስሜታችንን ችላ ካልነው ሊያገግም አይችልም።

6. አንድ ሰው ሲበድለን ምን ማድረግ ሊቀናን ይችላል?

6 አንድ ሰው ሲበድለን በመጀመሪያ የሚቀናን መበሳጨት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ ልንቆጣ እንደምንችል ይናገራል። ሆኖም ይህ ስሜት እንዲቆጣጠረን እንዳንፈቅድ ያስጠነቅቀናል። (መዝ. 4:4፤ ኤፌ. 4:26) ለምን? ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ስሜት ወደ ድርጊት ይመራል። ቁጣ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት አያስገኝም። (ያዕ. 1:20) ይህን ምንጊዜም አስታውስ፦ መቆጣት ተፈጥሯዊ ነው፤ ተቆጥቶ መቆየት ግን የምርጫ ጉዳይ ነው።

መቆጣት ተፈጥሯዊ ነው፤ ተቆጥቶ መቆየት ግን የምርጫ ጉዳይ ነው

7. በደል ሲደርስብን የትኞቹ ስሜቶች ሊሰሙን ይችላሉ?

7 በደል ሲደርስብን ሌሎች የሚያሠቃዩ ስሜቶችም ሊሰሙን ይችላሉ። ለምሳሌ አን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ልጅ እያለሁ አባቴ እናቴን ትቶ ሞግዚቴን አገባ። እንደተጣልኩ ሆኖ ተሰማኝ። ልጆች ሲወልዱ ደግሞ እንደተተካሁ ሆኖ ተሰማኝ። ስለዚህ ‘ማንም አይፈልገኝም’ ከሚል ስሜት ጋር ስታገል ኖሬያለሁ።” ጆርጄት የተባለች እህት፣ ባለቤቷ ታማኝነቱን ባጓደለበት ወቅት ምን እንደተሰማት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ከልጅነታችን አንስቶ ጓደኛሞች ነበርን። አብረን በአቅኚነት አገልግለናል! ስለዚህ ልቤ ተሰበረ።” ናኦሚ የተባለች እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ሊጎዳኝ ይችላል ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር። ስለዚህ ከእኔ ተደብቆ ፖርኖግራፊ ይመለከት እንደነበረ ሲነግረኝ እንዳታለለኝና እንደከዳኝ ሆኖ ተሰማኝ።”

8. (ሀ) ሌሎችን ይቅር ማለት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ሌሎችን ይቅር ስንል የትኞቹን ጥቅሞች እናገኛለን? (“አንድ ሰው ከባድ በደል ፈጽሞብን ከሆነስ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

8 ሌሎች የሚናገሩትን ወይም የሚያደርጉትን ነገር መቆጣጠር አንችልም፤ ሆኖም የምንሰጠውን ምላሽ ለመቆጣጠር መሞከር እንችላለን። ብዙውን ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ምላሽ ይቅር ማለት ነው። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋን እንወደዋለን፤ እሱ ደግሞ ይቅር ባዮች እንድንሆን ይፈልጋል። ተቆጥተን ከቆየንና ይቅር ካላልን የሞኝነት እርምጃ ልንወስድ፣ ምናልባትም ጤንነታችንን ልንጎዳ እንችላለን። (ምሳሌ 14:17, 29, 30) ክርስቲን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በደረሰብኝ የስሜት ጉዳት ላይ በምብሰለሰልበት ጊዜ ፈገግታዬ ይጠፋል። ጤናማ ያልሆነ ምግብ መብላት ይቀናኛል። እንቅልፍ መተኛት እቸገራለሁ፤ እንዲሁም ስሜቴን መቆጣጠር ይከብደኛል። ይህ ደግሞ በትዳሬና ከሌሎች ጋር ባለኝ ዝምድና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።”

አንድ ሰው ከባድ በደል ፈጽሞብን ከሆነስ?

አንድን ሰው ይቅር እንላለን ሲባል ድርጊቱን ስህተት እንዳልሆነ አድርገን እንቆጥረዋለን ወይም ግለሰቡ መጠቀሚያ እንዲያደርገን እንፈቅዳለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያደረብንን ቂምና ብስጭት ለመተው እንመርጣለን ማለት ነው። ይህን በማድረግ፣ ከባድ በደል የፈጸመብን ግለሰብ እኛን መጉዳቱን እንዲቀጥል እንደማንፈቅድለት እናሳያለን። ቂምን መተው ለራሳችን የምንሰጠው ስጦታ እንደሆነ ሊቆጠር ይችላል። ቁስላችን እንዲሽርና ወደፊት መጓዝ እንድንችል ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ በግለሰቡ ላይ ያደረብንን ቂምና ብስጭት ለመተው ብንወስንም እንኳ ግለሰቡ ላደረገው ነገር አሁንም በይሖዋ ፊት ተጠያቂ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም በአንድ ሰው ላይ ያደረብንን ቂምና ብስጭት መተው መዝሙራዊው በመንፈስ መሪነት “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው ሊባል ይችላል። (መዝ. 55:22) ከባድ በደል ያደረሰብንን ሰው ይሖዋ እንደሚፈርድበት በመተማመን ጉዳዩን ለእሱ እንተወዋለን። ደግሞም ይሖዋ አንድን ጉዳይ የሚይዝበት መንገድ እኛ ከምንይዝበት መንገድ በእጅጉ የተሻለ ነው። በመሆኑም በራሳችን ልናደርግ ከምንችለው እጅግ በተሻለ ሁኔታ ይሖዋ ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ ያስተላልፋል።

9. ያደረብንን ቂም መተው ያለብን ለምንድን ነው?

9 የበደለን ሰው ይቅርታ ባይጠይቀንም እንኳ ግለሰቡ ያደረሰብንን ጉዳት መቀነስ እንችላለን። እንዴት? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጆርጄት እንዲህ ብላለች፦ “የተወሰነ ጊዜ ቢወስድብኝም፣ በቀድሞ ባለቤቴ ላይ ያደረብኝን ቂምና ብስጭት መተው ቻልኩ። በውጤቱም ወደር የሌለው ሰላም አገኘሁ።” ያደረብንን ቂም ስንተው ልባችን በምሬት እንዳይጎዳ እንጠብቀዋለን። በተጨማሪም ለራሳችን ስጦታ እንደሰጠን ሊቆጠር ይችላል፤ ጉዳዩን ረስተን ሕይወታችንን በደስታ መቀጠል እንችላለን። (ምሳሌ 11:17) ይሁንና የተሰማህን ስሜት አምነህ ከተቀበልክ በኋላም ይቅር ለማለት ዝግጁ ካልሆንክስ?

ስሜትህን አክመው

10. ስሜታችን እንዲያገግም ለራሳችን ጊዜ መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 የተጎዳውን ስሜትህን ማከም የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እስክታገግም ድረስ ለራስህ ጊዜ በመስጠት ነው። አንድ ሰው ከባድ የአካል ጉዳት ከደረሰበት፣ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ሰውነቱ እስኪያገግም ድረስ ጊዜ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም፣ አንድን ሰው ከልባችን ይቅር ለማለት ዝግጁ ከመሆናችን በፊት ስሜታችን እንዲያገግም ጊዜ መስጠት ሊያስፈልገን ይችላል።—መክ. 3:3፤ 1 ጴጥ. 1:22

ሥዕሎች፦ ጉዳት የደረሰበት አንድ ወንድም ቀስ በቀስ ሲያገግም። 1. የሕክምና ባለሙያዎች አምቡላንስ ውስጥ ሲያስገቡት። 2. በድጋሚ መራመድ እንዲችል ሕክምና ሲደረግለት። 3. ብቻውን በደንብ ሲራመድ።

ልክ እንደ አካላዊ ጉዳት ሁሉ ስሜታዊ ጉዳትም እንዲድን ተገቢው እንክብካቤና ጊዜ ያስፈልገዋል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)


11. ጸሎት ይቅር ባይ ለመሆን የሚረዳህ እንዴት ነው?

11 ወደ ይሖዋ በመጸለይ ይቅር ባይ ለመሆን እንዲረዳህ ጠይቀው።c ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አን ጸሎት የረዳት እንዴት እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በቤተሰባችን ውስጥ ያለነው ሁላችንም ለሠራናቸው አግባብ ያልሆኑ ነገሮች ይሖዋ ይቅር እንዲለን ጠየቅኩት። ከዚያም ለአባቴና ለአዲሷ ሚስቱ ደብዳቤ በመጻፍ ይቅር እንዳልኳቸው ነገርኳቸው።” አን እንዲህ ማድረግ ቀላል እንዳልነበር ተናግራለች። ሆኖም እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን ይቅርታ ለመኮረጅ ጥረት ማድረጌ አባቴንና ሚስቱን ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማር እንደሚያነሳሳቸው ተስፋ አደርጋለሁ።”

12. ስሜታችንን ከማመን ይልቅ በይሖዋ መታመን ያለብን ለምንድን ነው? (ምሳሌ 3:5, 6)

12 ስሜትህን ከማመን ይልቅ በይሖዋ ታመን። (ምሳሌ 3:5, 6⁠ን አንብብ።) ይሖዋ ለእኛ የሚበጀን ምን እንደሆነ ምንጊዜም ያውቃል። (ኢሳ. 55:8, 9) ደግሞም መቼም ቢሆን የሚጎዳንን ነገር እንድናደርግ አይጠይቀንም። በመሆኑም ይሖዋ ይቅር ባይ እንድንሆን የሚያበረታታን እንዲህ ማድረጋችን ስለሚጠቅመን እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 40:4፤ ኢሳ. 48:17, 18) በሌላ በኩል ግን ስሜታችንን የምናምነው ከሆነ ጨርሶ ይቅር ማለት ሊከብደን ይችላል። (ምሳሌ 14:12፤ ኤር. 17:9) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ናኦሚ እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ባለቤቴ ፖርኖግራፊ በመመልከቱ እሱን ይቅር አለማለቴ ተገቢ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። ይቅር ብለው ድጋሚ ይጎዳኛል ወይም ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰብኝ ይረሳዋል ብዬ ፈርቼ ነበር። ደግሞም ይሖዋ ስሜቴን ይረዳልኛል ብዬ አስቤ ነበር። ይሁንና ይሖዋ ስሜቴን ይረዳልኛል ማለት ከስሜቴ ጋር ይስማማል ማለት እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ምን ዓይነት ስሜት እንደሚሰማኝ እንዲሁም ስሜቴ እስኪያገግም ጊዜ እንደሚወስድ ይረዳል። ያም ቢሆን ይቅር ባይ እንድሆን ይጠብቅብኛል።”d

አዎንታዊ ስሜቶችን አዳብር

13. በሮም 12:18-21 መሠረት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 ከባድ የስሜት ጉዳት ያደረሰብንን ሰው ይቅር በምንልበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ ዳግመኛ ላለማንሳት መወሰናችን ብቻ በቂ አይደለም። ጉዳት ያደረሱብን ክርስቲያን ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ከሆኑ ግባችን ሰላም መፍጠር ነው። (ማቴ. 5:23, 24) ብስጭታችንን በምሕረት፣ ቅሬታችንን ደግሞ በይቅርታ ለመተካት እንመርጣለን። (ሮም 12:18-21⁠ን አንብብ፤ 1 ጴጥ. 3:9) እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?

14. ምን ለማድረግ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

14 በደል ላደረሰብን ሰው የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋ የሰዎችን መልካም ጎን ለማየት ይመርጣል። (2 ዜና 16:9፤ መዝ. 130:3) ብዙውን ጊዜ፣ የሰዎችን መልካም ጎን ለማየት ጥረት ካደረግን የምናየው መልካም ጎናቸውን ነው፤ መጥፎ ጎናቸውን ለማየት ጥረት ካደረግን ደግሞ የምናየው መጥፎ ጎናቸውን ነው። የሰዎችን መልካም ጎን ለማየት ጥረት የምናደርግ ከሆነ እነሱን ይቅር ማለት ይቀለናል። ለምሳሌ ጄረድ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ወንድም ያደረሰብኝን በደል ከምወድለት በርካታ ነገሮች ጋር ሳነጻጽር እሱን ይቅር ማለት ቀላል ይሆንልኛል።”

15. በደል ላደረሰብን ሰው ‘ይቅር ብዬሃለሁ’ ብለን መንገራችን ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

15 ልናደርግ የምንችለው ሌላው አስፈላጊ ነገር ለግለሰቡ ይቅር እንዳልነው መንገር ነው። ለምን? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ናኦሚ ምን እንዳለች ልብ በል፦ “ባለቤቴ ‘ይቅር ብለሽኛል?’ ብሎ ጠየቀኝ። እኔ ግን ‘ይቅር ብዬሃለሁ’ የሚሉትን ቃላት ከአፌ ማውጣት ተናነቀኝ። በዚህ ጊዜ ባለቤቴን ከልቤ ይቅር እንዳላልኩት ተገነዘብኩ። ውሎ አድሮ ‘ይቅር ብዬሃለሁ’ የሚሉትን ቃላት ከአፌ ማውጣት ቻልኩ። ባለቤቴ እነዚህን ቃላት ሲሰማ እንባ ተናነቀው፤ እኔም ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በእሱ ላይ ያለኝን እምነት መልሼ መገንባት ችያለሁ፤ አሁን እንደ ቀድሞው የቅርብ ወዳጆች ሆነናል።”

16. ስለ ይቅር ባይነት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

16 ይሖዋ ይቅር ባዮች እንድንሆን ይፈልጋል። (ቆላ. 3:13) ያም ቢሆን ሌሎችን ይቅር ማለት ሊከብደን ይችላል። ሆኖም ስሜታችንን ችላ ከማለት ይልቅ ለማከም ጥረት ካደረግን ይቅር ማለት እንችላለን። ከዚያም አዎንታዊ የሆኑ ስሜቶችን ማዳበር እንችላለን።—“ይቅርታ ለማድረግ የሚረዱ ሦስት እርምጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ይቅርታ ለማድረግ የሚረዱ ሦስት እርምጃዎች

በጭንቀት የተዋጠች አንዲት እህት በመስኮት ወደ ውጭ ስትመለከት።

ስሜትህን ችላ አትበለው

  • የተጎዳውን ስሜታችንን ችላ ካልነው ያገግማል ብለን መጠበቅ አንችልም።

ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የታየችው እህት አጥብቃ ስትጸልይ።

ስሜትህን አክመው

  • ስሜትህ እስኪያገግም ለራስህ ጊዜ ስጠው።

  • ይሖዋ ቂምን ለማሸነፍ እንዲረዳህ ጠይቀው።

  • ስሜትህን ከማመን ይልቅ በይሖዋ ታመን።

እህትና ባለቤቷ ደስተኛ ሆነው።

አዎንታዊ ስሜቶችን አዳብር

  • ለግለሰቡ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት አድርግ።

  • ይቅር ለማለት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው።

  • ለግለሰቡ ይቅር እንዳልከው ንገረው።

ይቅር ባይ መሆን በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ አተኩር

17. ይቅር ባይ መሆናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

17 ይቅር ባይ ለመሆን የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን። አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ መሐሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን እንመስላለን እንዲሁም እናስደስተዋለን። (ሉቃስ 6:36) ሁለተኛ፣ ይሖዋ በደግነት ላሳየን ይቅርታ አመስጋኞች መሆናችንን እናሳያለን። (ማቴ. 6:12) ሦስተኛ፣ ጤንነታችን ይሻሻላል፤ ከሌሎች ጋር ያለን ወዳጅነትም ይጠናከራል።

18-19. ሌሎችን ይቅር ማለታችን ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

18 ሌሎችን ይቅር ስንል ያልተጠበቁ በረከቶችን ልናገኝ እንችላለን። ለምሳሌ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዴኒስ ምን በረከት እንዳገኘች እንመልከት። ዴኒስ ከጊዜ በኋላ እንደተረዳችው፣ አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ሕይወቱን ለማጥፋት አስቀድሞ ወስኖ ነበር። ሆኖም ዴኒስ ባሳየችው ይቅርታ ልቡ በጥልቅ ስለተነካ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ።

19 እኛም አንድን ሰው ይቅር ማለት በሕይወታችን ውስጥ ልናደርጋቸው ከምንችላቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ ከባዱ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል፤ ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ልናደርጋቸው ከምንችላቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ የሚክሰው እሱ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 5:7) እንግዲያው ሁላችንም የይሖዋን ይቅርታ ለመኮረጅ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።

አንድ ሰው ሲበድልህ . . .

  • ስሜትህን ችላ ማለት የሌለብህ ለምንድን ነው?

  • ስሜትህን ለማከም ምን ሊረዳህ ይችላል?

  • አዎንታዊ ስሜቶችን ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 125 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው”

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።

c “በነፃ ይቅር እንድል” እና “እንታረቅ” ለሚሉት ኦሪጅናል መዝሙሮች የተዘጋጁትን ቪዲዮዎች jw.org ላይ ተመልከት።

d ፖርኖግራፊ መመልከት ኃጢአትና ጎጂ ድርጊት ቢሆንም ጥፋተኛ ያልሆነው ወገን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ፍቺ እንዲፈጽም መሠረት አይሆንም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ