የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 መጋቢት ገጽ 20-25
  • በእምነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በእምነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሥራ ስንመርጥ
  • የትዳር ጓደኛ ስንመርጥ
  • ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ሲሰጠን
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ጥርጣሬን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን አድርግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 መጋቢት ገጽ 20-25

የጥናት ርዕስ 12

መዝሙር 119 ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል

በእምነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ

“የምንመላለሰው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም።”—2 ቆሮ. 5:7

ዓላማ

ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎችን ስናደርግ በእምነት መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?

1. ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሕይወቱ መለስ ብሎ ሲያስብ እርካታ የተሰማው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ሞት እንደሚጠብቀው ተረድቷል፤ ሕይወቱን መለስ ብሎ ሲያስብ ግን እርካታ ይሰማዋል። “ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ እምነትን ጠብቄአለሁ” በማለት ተናግሯል። (2 ጢሞ. 4:6-8) ጳውሎስ ራሱን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመስጠት ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ አድርጓል፤ ይሖዋ እንደተደሰተበትም እርግጠኛ ነው። እኛም አምላክ የሚደሰትበት ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንፈልጋለን። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

2. በእምነት መመላለስ ሲባል ምን ማለት ነው?

2 ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ሲናገር “የምንመላለሰው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም” ብሏል። (2 ቆሮ. 5:7) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘መመላለስ’ የሚለው ቃል አንድ ሰው የሚመርጠውን የሕይወት ጎዳና ሊያመለክት ይችላል። በማየት ብቻ የሚመላለስ ሰው ውሳኔ የሚያደርገው የሚያየውን፣ የሚሰማውን ወይም በስሜት ሕዋሶቹ የሚያገኘውን መረጃ ብቻ መሠረት በማድረግ ነው። በአንጻሩ ግን በእምነት የሚመላለስ ሰው ውሳኔውን የሚመራለት በይሖዋ ላይ ያለው እምነት ነው። የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ አምላክ ወሮታ እንደሚከፍለው እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠቅመው ያለውን ጠንካራ እምነት ያሳያሉ።—መዝ. 119:66፤ ዕብ. 11:6

3. በእምነት መመላለስ ምን ጥቅሞች ያስገኛል? (2 ቆሮንቶስ 4:18)

3 እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ውሳኔዎች ከስሜት ሕዋሶቻችን ባገኘነው መረጃ ላይ ተመሥርተው የሚደረጉ ናቸው። ተለቅ ያሉ ውሳኔዎችን ስናደርግ ግን የምናየውን ወይም የምንሰማውን ብቻ ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ለምን? ከስሜት ሕዋሶቻችን የምናገኘው መረጃ የተሳሳተ የሚሆንበት ጊዜ አለ። የምናገኘው መረጃ የተሳሳተ ባይሆንም እንኳ በማየት ብቻ የምንመላለስ ከሆነ ከአምላክ ፈቃድ ወይም ምክር ጋር የሚጋጭ ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን። (መክ. 11:9፤ ማቴ. 24:37-39) በእምነት የምንመላለስ ከሆነ ግን የምናደርገው ውሳኔ “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው” ይሆናል። (ኤፌ. 5:10) የአምላክን ምክር መከተል ውስጣዊ ሰላምና እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (መዝ. 16:8, 9፤ ኢሳ. 48:17, 18) እስከ መጨረሻው በእምነት መመላለሳችንን ከቀጠልን ደግሞ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን።—2 ቆሮንቶስ 4:18⁠ን አንብብ።

4. አንድ ሰው የሚመላለሰው በእምነት ይሁን በማየት የሚታወቀው በምንድን ነው?

4 የምንመላለሰው በእምነት ይሁን በማየት የምናውቀው እንዴት ነው? ይህን ለማወቅ የሚረዳን ዋናው ቁም ነገር ‘ውሳኔያችንን የሚመራው ምንድን ነው?’ የሚለው ነው። የምንመራው በምናየው ነገር ብቻ ነው? ወይስ በይሖዋ ላይ ባለን እምነት እንዲሁም ከእሱ በምናገኘው ምክር? በሦስት ወሳኝ አቅጣጫዎች በእምነት መመላለስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት፦ ሥራ ስንመርጥ፣ የትዳር ጓደኛ ስንመርጥ እና ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች ሲሰጡን። ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ነገሮችን በዝርዝር እንመለከታለን።

ሥራ ስንመርጥ

5. ሥራ ስንመርጥ ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ምንድን ነው?

5 ሁላችንም ለራሳችንና ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ማቅረብ እንፈልጋለን። (መክ. 7:12፤ 1 ጢሞ. 5:8) አንዳንድ ሥራዎች ጥሩ ገቢ ያስገኛሉ። የዕለት ተዕለት ወጪዎችን ከመሸፈን ባለፈ ተቀማጭ የሚሆን ገንዘብ ለመቆጠብ ያስችሉን ይሆናል። አንዳንድ ሥራዎች የሚያስገኙት ገቢ ግን ከእጅ ወደ አፍ ነው፤ ለቤተሰባችን የግድ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ከማሟላት ብዙም ላያልፍ ይችላል። ሥራ ስንመርጥ ‘ምን ያህል ገቢ ያስገኛል?’ የሚለውን ማሰባችን የሚጠበቅ ነው። ይሁንና አንድ ሰው ግምት ውስጥ የሚያስገባው ብቸኛው መሥፈርት ይህ ከሆነ በዋነኝነት በማየት እየተመላለሰ ነው።

6. ሥራ ስንመርጥ በእምነት እንደምንመላለስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 13:5)

6 በእምነት የምንመላለስ ከሆነ ሥራው ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይነካብን እንደሆነም ግምት ውስጥ እናስገባለን። እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህ ሥራ ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች እንዳደርግ ይጠይቅብኛል?’ (ምሳሌ 6:16-19) ‘የአምልኮ እንቅስቃሴዎቼን ይነካብኛል? ከቤተሰቤ ረዘም ላለ ጊዜ እንድርቅስ ያደርገኛል?’ (ፊልጵ. 1:10) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ‘አዎ’ ከሆነ ሥራ ማግኘት ከባድ ቢሆንም እንኳ ሥራውን አለመቀበላችን ጥበብ ይሆናል። በእምነት ስለምንመላለስ ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን እርግጠኞች መሆናችንን የሚያሳይ ውሳኔ እናደርጋለን።—ማቴ. 6:33፤ ዕብራውያን 13:5⁠ን አንብብ

7-8. በደቡብ አሜሪካ የሚኖር አንድ ወንድም በእምነት እንደሚመላለስ ያሳየው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 በደቡብ አሜሪካ የሚኖር ሃቪየርa የተባለ ወንድም በእምነት የመመላለስን አስፈላጊነት ከራሱ ተሞክሮ ተምሯል። እንዲህ ብሏል፦ “አንድ የሥራ አጋጣሚ አግኝቼ አመለከትሁ። ሥራው በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ ሲሆን ደሞዙ በፊት ከነበረኝ በእጥፍ ይጨምራል፤ በዚያ ላይ የምወደው የሥራ ዓይነት ነው።” ሆኖም ሃቪየር አቅኚ መሆን በጣም ይፈልግ ነበር። አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “የመሥሪያ ቤቱ ትልቅ የሥራ ኃላፊ ጋ ቀርቤ ቃለ መጠይቅ እንዳደርግ ተመረጥኩ። ሁሌም የሚበጀኝን የሚያውቀው ይሖዋ እንደሆነ ስለምተማመን ቃለ መጠይቁን ከማድረጌ በፊት እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ቀድሞ ከነበረኝ የተሻለ ሥራ ማግኘት ባልጠላም ሥራው ለመንፈሳዊ ግቦቼ እንቅፋት እንዲሆንብኝ አልፈለግሁም።”

8 ሃቪየር ታሪኩን ሲቀጥል እንዲህ ብሏል፦ “ቃለ መጠይቁ ላይ የሥራ ኃላፊው፣ በየጊዜው ተጨማሪ ሰዓት መሥራት እንደሚጠበቅብኝ ነገረኝ። በአገልግሎቴ ምክንያት ይህን ማድረግ እንደማልችል በአክብሮት ነገርኩት።” ሃቪየር ይህን የሥራ እድገት ሳይቀበል ቀረ። ከሁለት ሳምንት በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ሙሉ ሰዓቱን የማይዝበት ሥራ አገኘ። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶ ከአቅኚነቴ ጋር የሚስማማ ሥራ ሰጥቶኛል። ለይሖዋና ለወንድሞቼ ተጨማሪ ሰዓት መስጠት የሚያስችለኝ ሥራ በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል።”

አንድ የሥራ ኃላፊ፣ ሄልሜት ያደረገንና የሥራ ልብስ የለበሰን አንድ ወንድም ማንም ወደሌለበት ቢሮ ሲወስደው። የሥራ እድገት ሊሰጠው እንደሚፈልግ ለወንድም እየነገረው ነው።

የተሻለ የሥራ አጋጣሚ ስታገኝ ምርጫህ ይሖዋ ለአንተ የሚበጀውን እንደሚያውቅ ያለህን ጠንካራ እምነት ያሳያል? (ከአንቀጽ 7-8⁠ን ተመልከት)


9. ከትሬዞ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

9 አሁን ያለን ሥራ በእምነት እንዳንመላለስ እንቅፋት እንደሆነብን ብናስተውልስ? በኮንጎ የሚኖረውን የትሬዞን ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “አዲሱ ሥራዬ፣ ቢኖረኝ ብዬ ስመኘው የነበረው ዓይነት ነው። ደሞዙ በፊት ከነበረኝ በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን አንቱ የሚያስብል ሥራ ነው።” ይሁንና ትሬዞ ተጨማሪ ሰዓት ይሠራ ስለነበር በተደጋጋሚ ስብሰባ መቅረት ጀመረ። በዚያ ላይ የሥራ ባልደረቦቹ የማጭበርበር ድርጊቶችን እንዲሸፋፍንላቸው ጫና ያደርጉበት ነበር። ትሬዞ ይህን ሥራ መልቀቅ ቢፈልግም ‘ሥራ ብፈታስ?’ የሚለው ነገር አሳሰበው። ታዲያ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ዕንባቆም 3:17-19 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ገቢዬ ቢቀንስም እንኳ ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚንከባከበኝ እንዳስተውል ረዳኝ። ስለዚህ መልቀቂያዬን አስገባሁ።” አሁን የደረሰበትን መደምደሚያ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ቀጣሪዎች፣ ጥሩ እስከከፈሉህ ድረስ ማንኛውንም ነገር ሌላው ቀርቶ የቤተሰብ ሕይወትህንና መንፈሳዊ እንቅስቃሴህን እንኳ መሥዋዕት እንደምታደርግ ይሰማቸዋል። ከይሖዋ እና ከቤተሰቤ ጋር ያለኝን ዝምድና ጠብቄ መኖር በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ከአንድ ዓመት በኋላ በይሖዋ እርዳታ ተስማሚ ሥራ አገኘሁ፤ ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት የሚያስችለኝ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቤን ለማስተዳደር በቂ ገቢ ያስገኝልኛል። ለይሖዋ ቅድሚያ ስንሰጥ ለጊዜውም ቢሆን የገንዘብ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ ይንከባከበናል።” አዎ፣ በይሖዋ ምክርና እሱ በገባልን ቃል የምንተማመን ከሆነ በእምነት መመላለሳችንን እንቀጥላለን፤ እሱም ይባርከናል።

የትዳር ጓደኛ ስንመርጥ

10. የትዳር ጓደኛ የሚመርጥ ሰው በማየት ብቻ የሚመላለሰው ምን ካደረገ ነው?

10 ትዳር የይሖዋ ስጦታ ነው፤ ለማግባት መፈለግም ተፈጥሯዊ ነገር ነው። አንዲት እህት የትዳር ጓደኛ ስትመርጥ የግለሰቡን ስብዕና፣ ቁመናውን፣ ያተረፈውን ስም፣ የገንዘብ አያያዙን፣ ያሉበትን የቤተሰብ ኃላፊነቶች እንዲሁም ትወደው እንደሆነ ግምት ውስጥ ታስገባ ይሆናል።b እነዚህ አስፈላጊ መሥፈርቶች ናቸው። ይሁንና ግምት ውስጥ የምታስገባው እነዚህን ነገሮች ብቻ ከሆነ በማየት እየተመላለሰች ነው።

11. የትዳር ጓደኛ ከመምረጥ ጋር በተያያዘ በእምነት መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 7:39)

11 ይሖዋ፣ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን የእሱን መመሪያ ተከትለው የትዳር ጓደኛ ሲመርጡ ሲያይ ምንኛ ይኮራ ይሆን! ለምሳሌ፣ “አፍላ የጉርምስና ዕድሜን” ሳያልፉ መጠናናት መጀመር እንደሌለባቸው የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ። (1 ቆሮ. 7:36) የትዳር ጓደኛ ሲመርጡ ደግሞ በዋነኝነት ግምት ውስጥ የሚያስገቡት ይሖዋ የገለጻቸውን ከጥሩ ባል ወይም ከጥሩ ሚስት የሚጠበቁ ባሕርያት ነው። (ምሳሌ 31:10-13, 26-28፤ ኤፌ. 5:33፤ 1 ጢሞ. 5:8) የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰው ለፍቅር ጓደኝነት ቢጠይቃቸው በ1 ቆሮንቶስ 7:39 ላይ የሚገኘውን “በጌታ ብቻ” እንድናገባ የተሰጠውን ምክር ይከተላሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ከማንም በላይ ስሜታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ማድረግ የሚችለው ይሖዋ እንደሆነ በመተማመን በእምነት መመላለሳቸውን ይቀጥላሉ።—መዝ. 55:22

12. ከሮሳ ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

12 በኮሎምቢያ የምትኖረውን ሮሳ የተባለች አቅኚ ተሞክሮ እንመልከት። በሥራዋ ምክንያት ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰው ጋር በተደጋጋሚ ትገናኝ ነበር። በኋላም ሰውየው ለፍቅር እንደሚፈልጋት ማሳየት ጀመረ። ሮሳም ይህ ግለሰብ ማርኳት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ጥሩ ሰው ይመስል ነበር። በማኅበረሰቡ ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፤ መጥፎ አመል የለውም። እኔን የሚይዝበትን መንገድም ወድጄው ነበር። የይሖዋ ምሥክር አለመሆኑ እንጂ የወደፊት ባሌ ቢኖረው ብዬ የምመኛቸው ነገሮች ሁሉ ነበሩት። የፍቅር ጥያቄውን እንቢ ማለት በጣም ከብዶኝ ነበር። ምክንያቱም ያ ወቅት ብቸኝነት የተሰማኝና ማግባት የፈለግሁበት ጊዜ ነበር። በእውነት ቤት ደግሞ የሚሆነኝን ሰው አላገኘሁም።” ይሁንና ሮሳ በምታየው ነገር ላይ ብቻ አላተኮረችም። ይህ ውሳኔ ከይሖዋ ጋር ያላትን ወዳጅነት የሚነካው እንዴት እንደሆነ በጥሞና አሰበችበት። ስለዚህ ከግለሰቡ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራት አደረገች። በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችም ተጠመደች። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ላይ ተጋበዘች። አሁን ልዩ አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው። ሮሳ “ይሖዋ ልቤን በሐሴት ሞልቶታል” ብላለች። ስሜታችንን ከሚነኩ ነገሮች ጋር በተያያዘ በእምነት መመላለስ ቀላል ባይሆንም ሁሌም የሚክስ ነው።

ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ሲሰጠን

13. ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ሲሰጠን በማየት እንድንመላለስ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል?

13 አምልኳችንን ስለምናከናውንበት መንገድ በየጊዜው ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች ይሰጡናል። መመሪያው የሚመጣው ከጉባኤያችን ሽማግሌዎች፣ ከወረዳ የበላይ ተመልካች፣ ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከበላይ አካሉ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግን መመሪያዎቹ የተሰጡበት ምክንያት አይገባን ይሆናል። እኛን የሚታየን መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ ሊሆን ይችላል። አልፎ ተርፎም መመሪያውን በሰጡት ወንድሞች ድክመት ላይ ማተኮር ልንጀምር እንችላለን።

14. ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ሲሰጠን በእምነት ለመመላለስ ምን ሊረዳን ይችላል? (ዕብራውያን 13:17)

14 በእምነት የምንመላለስ ከሆነ ይሖዋ ድርጅቱን እንደሚመራና ያለንበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ እንተማመናለን። በመሆኑም በፍጥነትና በደስታ መመሪያውን እንታዘዛለን። (ዕብራውያን 13:17⁠ን አንብብ።) ታዛዥ መሆናችን ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እንገነዘባለን። (ኤፌ. 4:2, 3) አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ፍጹም ባይሆኑም እንኳ ለታዛዥነታችን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች ነን። (1 ሳሙ. 15:22) መታረም ያለበት ነገር ካለ ደግሞ ይሖዋ በራሱ ጊዜ ያስተካክለዋል።—ሚክ. 7:7

15-16. አንድ ወንድም ከድርጅቱ ስላገኘው አንድ መመሪያ ጥርጣሬ ቢያድርበትም በእምነት ለመመላለስ የረዳው ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 በእምነት መመላለስ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ፔሩ ውስጥ በስፋት የሚነገረው ስፓንኛ ቢሆንም ብዙ ነዋሪዎች የአገሬውን ቋንቋዎች ይናገራሉ። ከእነዚህ አንዱ ኬችዋ ነው። ኬችዋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ለበርካታ ዓመታት፣ የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን እየፈለጉ ያነጋግሩ ነበር። ሆኖም መንግሥት ያወጣውን ደንብ ለማክበር ሲባል ኬችዋ ተናጋሪዎችን በሚያገኙበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ተደረገ። (ሮም 13:1) በዚህ ጊዜ አንዳንዶች ይህ ለውጥ ለሥራው እንቅፋት እንዳይፈጥር ሰግተው ነበር። ይሁንና ወንድሞች ማስተካከያዎቹን ተግባራዊ ሲያደርጉ ይሖዋ ጥረታቸውን እንደባረከላቸው አስተውለዋል፤ ኬችዋ ተናጋሪ የሆኑ ብዙ ሰዎች ማግኘት ችለዋል።

16 በኬችዋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ኬቨን ስጋት ተፈጥሮባቸው ከነበሩ ወንድሞች አንዱ ነው። “‘በዚህ አያያዝ፣ ኬችዋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን እንዴት ልናገኝ ነው?’ ብዬ አሰብኩ” ብሏል። ይሁንና ኬቨን ምን አደረገ? እንዲህ ብሏል፦ “ምሳሌ 3:5⁠ን አስታወስኩ። ስለ ሙሴም አሰብኩ። እስራኤላውያንን ከግብፅ እየመራ አውጥቶ እንዲወስዳቸው የታዘዘው፣ ከኋላቸው ከሚያሳድዷቸው ግብፃውያን ማምለጥ የሚችሉበት ምንም መውጫ ያለው ወደማይመስል ቦታ ነበር። ሙሴ ግን ታዘዘ፤ ይሖዋም ለታዛዥነቱ አስደናቂ በሆነ መንገድ ባርኮታል።” (ዘፀ. 14:1, 2, 9-11, 21, 22) ኬቨን አገልግሎቱን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እንዴት እንደባረከን ሳይ በጣም ይደንቀኛል። ከዚህ በፊት አገልግሎት ላይ በእግራችን ረጅም መንገድ እንጓዝ ነበር። እንደዚያም ሆኖ አገልግሎት ላይ አንድ ወይም ሁለት ኬችዋ ተናጋሪዎችን ብቻ የምናገኝበት ጊዜ ነበር። አሁን ትኩረት የምናደርገው የቋንቋው ተናጋሪዎች በብዛት በሚገኙባቸው ክልሎች ላይ ነው። በውጤቱም አገልግሎት ላይ የምናወያያቸው፣ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግላቸው እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸው ሰዎች ብዛት ጨምሯል። በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሰዎች ብዛትም አድጓል።” በእርግጥም በእምነት ስንመላለስ ይሖዋ ምንጊዜም ይባርከናል።

ኬችዋ ተናጋሪ የሆነ ሰው፣ አገልግሎት ላይ ካሉ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ጋር ሲነጋገር። የአንድ ሰው ቤት እያሳያቸው ነው።

ወንድሞች አገልግሎት ላይ ያገኟቸው ብዙ ሰዎች የቋንቋው ተናጋሪዎች በብዛት የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ጠቁመዋቸዋል (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት)


17. ከዚህ ርዕስ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

17 በሦስት ወሳኝ አቅጣጫዎች በእምነት መመላለስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች በእምነት መመላለሳችንን መቀጠል አለብን። ይህም የመዝናኛ ምርጫችንን እንዲሁም ትምህርትንና የልጅ አስተዳደግን በተመለከተ የምናደርገውን ውሳኔ ያካትታል። ማንኛውንም ውሳኔ ስናደርግ በምናየው ነገር ብቻ መመራት የለብንም። ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና፣ ምክሩን እንዲሁም እኛን ለመንከባከብ የገባውን ቃልም ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። እንዲህ ከሆነ “በአምላካችን በይሖዋ ስም ለዘላለም [መሄድ]” እንችላለን።—ሚክ. 4:5

በእምነት መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?

  • ሥራ ስንመርጥ

  • የትዳር ጓደኛ ስንመርጥ

  • ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ሲሰጠን

መዝሙር 156 በእምነት ዓይኔ

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ አንቀጽ ላይ ምክሩ የተጻፈው ለማግባት እያሰበች ካለች እህት አንጻር ነው። ሆኖም ይኸው ምክር ለማግባት ለሚያስቡ ወንድሞችም ይሠራል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ