የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ግንቦት ገጽ 8-13
  • ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር በሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር በሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ በምሕረት ይቅር ይለናል
  • ይሖዋ ተስፋ ይሰጠናል
  • ይሖዋ እንዳንፈራ ይረዳናል
  • ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ግንቦት ገጽ 8-13

የጥናት ርዕስ 20

መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን

ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር በሉ

“የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . ይወደስ።”—2 ቆሮ. 1:3

ዓላማ

ይሖዋ ግዞተኞቹን አይሁዳውያን ካጽናናበት መንገድ የምናገኛቸውን ትምህርቶች እንመረምራለን።

1. ግዞተኞቹ አይሁዳውያን የነበሩበትን ሁኔታ ግለጽ።

በባቢሎን የነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። የትውልድ አገራቸው ስትጠፋ ተመልክተዋል። በእነሱም ሆነ በአባቶቻቸው ኃጢአት የተነሳ ከቤታቸው ተወስደው ወደ ባዕድ አገር ተልከዋል። (2 ዜና 36:15, 16, 20, 21) ግዞተኞቹ ባቢሎን ውስጥ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ለማከናወን የሚያስችል መጠነኛ ነፃነት እንደነበራቸው አይካድም። (ኤር. 29:4-7) ያም ቢሆን ሕይወት ለእነሱ ቀላል አልነበረም፤ ደግሞም በዚያ መኖር የሚመርጡት ነገር እንዳልሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። እነዚህ ግዞተኞች፣ ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ምን ተሰምቷቸው ነበር? አንድ ታማኝ ግዞተኛ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “በባቢሎን ወንዞች አጠገብ፣ በዚያ ተቀምጠን ነበር። ጽዮንን ባስታወስናት ጊዜ አለቀስን።” (መዝ. 137:1) ቅስማቸው የተሰበረው ግዞተኞች ማጽናኛ ያስፈልጋቸው ነበር። ይሁንና ማጽናኛ ማግኘት የሚችሉት ከየት ነው?

2-3. (ሀ) ይሖዋ ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን ምን አድርጎላቸዋል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ነው። (2 ቆሮ. 1:3) አፍቃሪ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ወደ እሱ የሚቀርቡትን ሰዎች በሙሉ ማጽናናት ያስደስተዋል። ይሖዋ ከግዞተኞቹ መካከል አንዳንዶቹ እሱ የሰጣቸውን ተግሣጽ ተቀብለው ወደ እሱ እንደሚመለሱ ያውቅ ነበር። (ኢሳ. 59:20) በመሆኑም አይሁዳውያን በግዞት ከመወሰዳቸው ከመቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስን በመንፈሱ በመምራት በስሙ የተጠራውን መጽሐፍ እንዲጽፍ አድርጓል። የመጽሐፉ ዓላማ ምን ነበር? ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል፦ “‘አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ’ ይላል አምላካችሁ።” (ኢሳ. 40:1) አዎ፣ በኢሳይያስ መጽሐፍ አማካኝነት ይሖዋ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን የሚያስፈልጋቸውን ማጽናኛ ሰጥቷቸዋል።

3 እንደ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ሁሉ እኛም አልፎ አልፎ ማጽናኛ ያስፈልገናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ ግዞተኞቹን ያጽናናባቸውን ሦስት መንገዶች እንመለከታለን፦ (1) ንስሐ የገቡትን ሕዝቦቹን ይቅር እንደሚላቸው ቃል ገብቷል፤ (2) ለሕዝቦቹ ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም (3) እንዳይፈሩ ረድቷቸዋል። እነዚህን ነጥቦች ስንመረምር፣ ይሖዋ ከተናገራቸው የሚያጽናኑ ቃላት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።

ይሖዋ በምሕረት ይቅር ይለናል

4. ይሖዋ መሐሪ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 55:7)

4 ይሖዋ “የምሕረት አባት” ነው። (2 ቆሮ. 1:3) ንስሐ የገቡትን ግዞተኞች ይቅር እንደሚል ቃል በገባበት ወቅት ይህን ባሕርይ አሳይቷል። (ኢሳይያስ 55:7⁠ን አንብብ።) እንዲህ ብሏል፦ “በዘላለማዊ ታማኝ ፍቅር ምሕረት አሳይሻለሁ።” (ኢሳ. 54:8) ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምሕረት ያሳያቸው እንዴት ነው? አይሁዳውያን በብሔር ደረጃ ድርጊታቸው ያስከተለውን መዘዝ መቅመስ ቢኖርባቸውም ይሖዋ ባቢሎን ውስጥ እስከ መጨረሻው እንደማይኖሩ ቃል ገብቶላቸዋል። በግዞት የሚቆዩት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። (ኢሳ. 40:2) እነዚህ ቃላት ንስሐ የገቡ ግዞተኞችን በእጅጉ እንዳጽናኗቸው ምንም ጥያቄ የለውም።

5. ከግዞተኞቹ አይሁዳውያን ይበልጥ በይሖዋ ምሕረት ላይ እምነት ለመጣል የሚያበቃ ምክንያት አለን የምንለው ለምንድን ነው?

5 ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያሳየው ይቅርታ ብዙ ነው። በዛሬው ጊዜ ከግዞተኞቹ አይሁዳውያን ይበልጥ በዚህ እውነታ ላይ እምነት ለመጣል የሚያበቃ ተጨማሪ ምክንያት አለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ለይሖዋ ይቅርታ መሠረት የሆነው ምን እንደሆነ እናውቃለን። ኢሳይያስ ትንቢቱን ከተናገረ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች በሙሉ ቤዛ እንዲሆን ሲል የሚወደውን ልጁን ወደ ምድር ልኮታል። ይህ መሥዋዕት ኃጢአታችን “እንዲደመሰስ” ማለትም ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ የሚያስችል መሠረት ይሆናል። (ሥራ 3:19፤ ኢሳ. 1:18፤ ኤፌ. 1:7) የምናገለግለው አምላክ ምንኛ መሐሪ ነው!

6. በይሖዋ ምሕረት ላይ ትኩረት ማድረጋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 በጥፋተኝነት ስሜት የምንዋጥ ከሆነ ይሖዋ በኢሳይያስ 55:7 ላይ የተናገራቸው ቃላት ሊያጽናኑን ይችላሉ። አንዳንዶቻችን ንስሐ ከገባን በኋላም ቀደም ሲል በሠራነው ኃጢአት የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። በተለይ አሁንም ስህተታችን ያስከተለውን መዘዝ እየቀመስን ከሆነ የጥፋተኝነት ስሜት ሊያስቸግረን ይችላል። ይሁንና ኃጢአታችንን ተናዘንና አካሄዳችንን አስተካክለን ከሆነ ይሖዋ ይቅር እንዳለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ይቅር ሲለን ደግሞ ኃጢአታችንን ላለማስታወስ ይመርጣል። (ከኤርምያስ 31:34 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ይሖዋ ቀደም ሲል የሠራናቸውን ኃጢአቶች እያስታወሰ የማይኖር ከሆነ እኛም እንደዚያ ልናደርግ አይገባም። ይሖዋ ትኩረት የሚያደርገው በአሁኑ ወቅት እያከናወንን ባለነው ነገር ላይ እንጂ ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ አይደለም። (ሕዝ. 33:14-16) በቅርቡ ደግሞ፣ የምሕረት አባት የሆነው አምላካችን ስህተቶቻችን ካስከተሉብን መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ያወጣናል።

አንድ ወንድም በልበ ሙሉነት ሲራመድ። ሥዕሎች፦ ቀደም ሲል ያደርጋቸው የነበሩትን ነገሮች አሁን ከሚያደርጋቸው ነገሮች ጋር የሚያነጻጽሩ ትዕይንቶች። ቀደም ሲል የሠራቸው ስህተቶች፦ 1. ዓመፅ የሚንጸባረቅበት የቪዲዮ ጌም ይጫወት ነበር። 2. ከመጠን በላይ ይጠጣና ያጨስ ነበር። 3. ኮምፒውተሩ ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ያይ ነበር። አሁን እያደረገ ያለው ነገር፦ 1. የስብሰባ አዳራሹን ሲያጸዳ። 2. ከአንዲት አረጋዊት እህት ጋር ሲነጋገር። 3. በመስክ አገልግሎት ሲካፈል።

ይሖዋ ትኩረት የሚያደርገው ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ እያከናወንን ባለነው ነገር ላይ ነው (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7. የፈጸምነውን ኃጢአት ሸሽገን ከሆነ የሽማግሌዎችን እርዳታ እንድንጠይቅ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

7 የፈጸምነውን ከባድ ኃጢአት በመሸሸጋችን የተነሳ ሕሊናችን የሚቆረቁረን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ የሽማግሌዎችን እርዳታ እንድንጠይቅ ያበረታታናል። (ያዕ. 5:14, 15) ይሁንና ስህተታችንን መናዘዝ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። ሆኖም ንስሐ ከገባን እንዲሁም ይሖዋና እሱ እኛን እንዲረዱን የሾማቸው ሰዎች ፍቅርና ምሕረት እንደሚያሳዩን ካስታወስን እነዚህን ታማኝ ወንዶች ቀርበን ለማነጋገር እንነሳሳለን። አርተርa የተባለ ወንድም ከባድ የሕሊና ወቀሳ ባጋጠመው ወቅት የይሖዋ ምሕረት ያጽናናው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ለአንድ ዓመት ያህል ፖርኖግራፊ እመለከት ነበር። ሆኖም ስለ ሕሊና የሚናገር አንድ ንግግር ከሰማሁ በኋላ ኃጢአቴን ለባለቤቴ እና ለሽማግሌዎች ተናዘዝኩ። እንዲህ ካደረግኩ በኋላ እፎይታ ተሰማኝ። ሆኖም የሠራሁት ስህተት አሁንም ይጸጽተኝ ነበር። ሽማግሌዎቹ ይሖዋ እንዳልተወኝ አስታወሱኝ። እሱ ተግሣጽ የሚሰጠን ስለሚወደን ነው። ሽማግሌዎቹ የተናገሯቸው ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ልቤን ነኩት፤ እንዲሁም አስተሳሰቤን እንዳስተካክል ረዱኝ።” በአሁኑ ጊዜ አርተር አቅኚና የጉባኤ አገልጋይ ነው። ንስሐ እስከገባን ድረስ ይሖዋ ምሕረት እንደሚያሳየን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

ይሖዋ ተስፋ ይሰጠናል

8. (ሀ) ይሖዋ ለግዞተኞቹ ምን ተስፋ ሰጥቷቸዋል? (ለ) በኢሳይያስ 40:29-31 መሠረት ተስፋ ንስሐ የገቡትን አይሁዳውያን የሚረዳቸው እንዴት ነው?

8 ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ያሉበት ሁኔታ ተስፋ ያለው አይመስልም ነበር። የባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት የሚታወቀው በግዞት የያዛቸውን ሰዎች ባለመልቀቅ ነበር። (ኢሳ. 14:17) ሆኖም ይሖዋ ለሕዝቦቹ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ሕዝቦቹ ነፃ እንዲወጡ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፤ ደግሞም ምንም ነገር እሱን ሊያግደው አይችልም። (ኢሳ. 44:26፤ 55:12) በይሖዋ ዓይን ባቢሎን እንደ አቧራ ነበር። (ኢሳ. 40:15) እፍ ሲባል በኖ ይጠፋል። ታዲያ ተስፋ ግዞተኞቹን የሚረዳቸው እንዴት ነው? ያጽናናቸዋል። ግን ይህ ብቻ አይደለም። ኢሳይያስ “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ . . . ኃይላቸው ይታደሳል” በማለት ጽፏል። (ኢሳይያስ 40:29-31⁠ን አንብብ።) አዎ፣ ተስፋ ኃይላቸውን ያድስላቸዋል፤ “እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ ይወጣሉ።”

9. ግዞተኞቹ፣ ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት መጣል የሚችሉት ለምንድን ነው?

9 በተጨማሪም ይሖዋ ለግዞተኞቹ፣ እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት ለመጣል የሚረዳ ምክንያት ሰጥቷቸዋል። እንዴት? ከዚያ በፊት የተፈጸሙትን ትንቢቶች ለማሰብ ሞክር። አሦር የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት ድል እንዳደረገና ሕዝቡን በግዞት እንደወሰደ ያውቃሉ። (ኢሳ. 8:4) ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ሲያጠፉና ነዋሪዎቿን በግዞት ሲወስዷቸው ተመልክተዋል። (ኢሳ. 39:5-7) ንጉሥ ሴዴቅያስ ዓይኑ የታወረውና በግዞት የተወሰደውም በእነሱ ዘመን ነው። (ኤር. 39:7፤ ሕዝ. 12:12, 13) ይሖዋ የተናገረው ትንቢት በሙሉ ተፈጽሟል። (ኢሳ. 42:9፤ 46:10) ይህን ሁሉ ማየታቸው ይሖዋ ነፃ እንደሚወጡ የሰጣቸው ተስፋም እንደሚፈጸም ያላቸውን እምነት አጠናክሮላቸው መሆን አለበት።

10. በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ተስፋችን ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆንልን ምን ይረዳናል?

10 ምን ትምህርት እናገኛለን? በሐዘን በምንዋጥበት ጊዜ ተስፋ ሊያጽናናንና ኃይላችንን ሊያድስልን ይችላል። የምንኖረው በአስጨናቂ ዘመን ውስጥ ነው፤ ጠላቶቻችንም ኃያላን ናቸው። ያም ቢሆን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ይሖዋ ግሩም ተስፋ ሰጥቶናል፤ እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም እንደምንኖር ቃል ገብቶልናል። ይህ ተስፋ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል። አለዚያ አንድን ውብ መልክዓ ምድር በቆሸሸ መስኮት አሻግሮ የመመልከት ያህል ተስፋችን ሊደበዝዝብን ይችላል። በምሳሌያዊ ሁኔታ መስኮቱን በማጽዳት ተስፋችን ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረንን ግሩም ሕይወት በዓይነ ሕሊናችን ለመሣል አዘውትረን ጊዜ መመደብ እንችላለን። ስለ ተስፋችን የሚናገሩ ጽሑፎችን ማንበብ፣ ቪዲዮዎችን መመልከት እንዲሁም መዝሙሮችን ማዳመጥ እንችላለን። በተጨማሪም በጉጉት የምንጠብቃቸውን ተስፋዎች አስመልክቶ ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን።

11. ከባድ የጤና እክሎች ያሉባት አንዲት እህት ኃይሏ እንዲታደስ የረዳት ምንድን ነው?

11 ተስፋ ጆይ የተባለችን እህት ያጽናናትና ያበረታታት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ጆይ ከባድ የጤና እክሎች አሉባት። እንዲህ ብላለች፦ “ችግሩ ከአቅሜ በላይ እንደሆነብኝ በሚሰማኝ ጊዜ ይሖዋ ስሜቴን እንደሚረዳልኝ በመገንዘብ የውስጤን አውጥቼ ወደ እሱ እጸልያለሁ። ይሖዋም በምላሹ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ ይሰጠኛል።” (2 ቆሮ. 4:7) በተጨማሪም ጆይ ‘ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” በማይልበት’ አዲስ ዓለም ውስጥ ራሷን ለመሣል ጥረት ታደርጋለች። (ኢሳ. 33:24) እኛም በተመሳሳይ ልባችንን በይሖዋ ፊት ካፈሰስን እንዲሁም በተስፋችን ላይ ትኩረት ካደረግን ኃይላችንን ማደስ እንችላለን።

12. ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንድንጥል የሚረዳ ምን ምክንያት አለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ይሖዋ ለግዞተኞቹ እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዲጥሉ የሚረዳ ብዙ ምክንያት እንደሰጣቸው ሁሉ ለእኛም እንዲሁ አድርጎልናል። በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ስላሉት ትንቢቶች ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ “በከፊል ብርቱ፣ በከፊል ደግሞ ደካማ” የሆነ የዓለም ኃያል መንግሥት ሲገዛ እያየን ነው። (ዳን. 2:42, 43) ከዚህም ሌላ “በተለያየ ስፍራ . . . የምድር ነውጥ” እየተከሰተ እንዳለ እንሰማለን፤ “ለብሔራት ሁሉ” ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራም እየተካፈልን ነው። (ማቴ. 24:7, 14) እነዚህና ሌሎች ትንቢቶች ሲፈጸሙ ማየታችን ይሖዋ የሰጠን የሚያጽናኑ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

አንዲት እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እያነበበች ስታሰላስል። ሥዕሎች፦ 1. አንድ ባልና ሚስት በጽሑፍ ጋሪ አጠገብ ቆመው አንድን ሰው ሲያነጋግሩ። 2. አንድ አባትና ልጁ የተፈጥሮ አደጋ ያስከተለውን ውድመት ሲያዩ። 3. አንድ ድንጋይ በዳንኤል ምዕራፍ 2 ላይ የተጠቀሰውን ናቡከደነጾር በሕልሙ ያየውን ግዙፍ ምስል እግሮች ሲመታ። 4. ሰዎች ገነት በሆነችው ምድር ላይ ተደስተው ሲኖሩ።

በዛሬው ጊዜ ሲፈጸሙ የምናያቸው ትንቢቶች ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)


ይሖዋ እንዳንፈራ ይረዳናል

13. (ሀ) አይሁዳውያን ነፃ በሚወጡበት ጊዜ አካባቢ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ለ) በኢሳይያስ 41:10-13 መሠረት ይሖዋ ግዞተኞቹን አይሁዳውያን ያጽናናቸው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ ለግዞተኞቹ ግሩም ተስፋ በመስጠት ቢያጽናናቸውም እንኳ ነፃ በሚወጡበት ጊዜ አካባቢ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው ያውቅ ነበር። ይሖዋ አይሁዳውያን በግዞት በሚቆዩበት ጊዜ ማብቂያ አካባቢ አንድ ኃያል ንጉሥ በዙሪያቸው ያሉትን ብሔራት እንደሚያወድምና በባቢሎን ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 41:2-5) ታዲያ ይህ አይሁዳውያኑን ሊያስፈራቸው ይገባል? ይሖዋ እንዲህ በማለት ለሕዝቦቹ አስቀድሞ ማጽናኛ ሰጥቷቸዋል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።” (ኢሳይያስ 41:10-13⁠ን አንብብ።) ይሖዋ “እኔ አምላክህ ነኝ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? አይሁዳውያኑ ሊያመልኩት እንደሚገባ መናገሩ አልነበረም፤ ምክንያቱም ቀድሞውንም ይህን ያውቃሉ። ከዚህ ይልቅ አሁንም ከጎናቸው እንደሆነ እያስታወሳቸው ነበር።—መዝ. 118:6

14. ይሖዋ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን እንዳይፈሩ የረዳበት ሌላኛው መንገድ ምንድን ነው?

14 ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለግዞተኞቹ፣ ገደብ የለሽ ኃይልና እውቀት እንዳለው በማስታወስ እንዳይፈሩ ረድቷቸዋል። ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ቀና ብለው በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ እንዲያዩ ጋብዟቸዋል። ከዋክብትን መፍጠር ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ኮከብ በስም እንደሚያውቅ ነገራቸው። (ኢሳ. 40:25-28) ይሖዋ የእያንዳንዱን ኮከብ ስም የሚያውቅ ከሆነ የእያንዳንዱን አገልጋዩን ስም እንደሚያውቅ ምንም ጥያቄ የለውም! ደግሞም ይሖዋ ከዋክብትን ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል ካለው ሕዝቦቹን ለመርዳት የሚያስችል ኃይል እንደሚኖረው ግልጽ ነው። በእርግጥም ግዞተኞቹ አይሁዳውያን የሚፈሩበት ወይም የሚጨነቁበት ምንም ምክንያት የለም።

15. ይሖዋ አይሁዳውያን ግዞተኞችን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቦቹን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር አዘጋጅቷቸዋል። በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ጥቂት ቀደም ብሎ አምላክ ሕዝቦቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” (ኢሳ. 26:20) ይህ ጥቅስ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው ንጉሥ ቂሮስ ባቢሎንን በተቆጣጠረበት ወቅት ሊሆን ይችላል። አንድ ጥንታዊ የግሪክ ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጸው፣ ቂሮስ ወደ ባቢሎን በገባበት ወቅት “[ወታደሮቹ] ከቤት ውጭ ያገኙትን ሰው በሙሉ እንዲገድሉ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር።” የባቢሎን ነዋሪዎች ምን ያህል ፈርተው ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር! ሆኖም ግዞተኞቹ አይሁዳውያን የይሖዋን መመሪያ መከተላቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸው ሊሆን ይችላል።

16. የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ከልክ በላይ መጨነቅ የሌለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 ምን ትምህርት እናገኛለን? በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ መከራ ከፊታችን ይጠብቀናል። ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ግራ በመጋባትና በፍርሃት ይዋጣሉ። የይሖዋ ሕዝቦች ግን አይፈሩም። ይሖዋ አምላካችን እንደሆነ እናውቃለን። ‘መዳናችን እየቀረበ እንደሆነ’ ስለምናውቅ ቀጥ ብለን እንቆማለን። (ሉቃስ 21:28) ግንባር የፈጠሩ ብሔራት ጥቃት በሚሰነዝሩብን ጊዜም እንኳ ጸንተን እንቆማለን። ይሖዋ መላእክታዊ ጥበቃ ያደርግልናል፤ እንዲሁም ሕይወት አድን የሆነ መመሪያ ይሰጠናል። እንዲህ ያለውን መመሪያ የምናገኘው በምን መንገድ ሊሆን ይችላል? ይህን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለውን መመሪያ የምናገኘው በጉባኤያችን አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ደህንነት የምናገኝበት “ውስጠኛው ክፍል” የሚያመለክተው ጉባኤዎቻችንን ሊሆን ይችላል። ከፊታችን ለሚጠብቀን ነገር መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር መቀራረብ፣ ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን በፈቃደኝነት መታዘዝ እንዲሁም ድርጅታችንን እየመራ ያለው ይሖዋ እንደሆነ መተማመን ይኖርብናል።—ዕብ. 10:24, 25፤ 13:17

በታላቁ መከራ ወቅት ወንድሞችና እህቶች አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ። በመስኮት ወደ ውጭ እያዩ ነው፤ አንደኛው ወንድም በጨለማ ወደተዋጠው ሰማይ ይጠቁማል።

ይሖዋ እኛን ለማዳን ባለው ኃይልና ችሎታ ላይ ካሰላሰልን በታላቁ መከራ ወቅት ከልክ በላይ አንጨነቅም (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)b


17. ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት የምትችለው እንዴት ነው?

17 ግዞተኞቹ አይሁዳውያን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ማጽናኛ ሰጥቷቸዋል። ለእኛም እንደዚያው ያደርግልናል። እንግዲያው ነገ ምንም ይዞ ቢመጣ ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለትህን ቀጥል። አዎ፣ ታላቅ በሆነው ምሕረቱ ላይ እምነት ይኑርህ። ተስፋህ ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆን አድርግ። ይሖዋ አምላክህ ስለሆነ የምትፈራበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አስታውስ።

የሚከተሉት ጥቅሶች የሚያጽናኑህ እንዴት ነው?

  • ኢሳይያስ 55:7

  • ኢሳይያስ 40:29-31

  • ኢሳይያስ 41:10-13

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች አንድ ላይ ተሰብስበዋል። ይሖዋ ባለው ኃይል እንዲሁም ሕዝቦቹ በየትኛውም የምድር ክፍል ቢኖሩ እነሱን ለመጠበቅ ባለው ችሎታ ላይ እምነት አላቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ