የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ግንቦት ገጽ 20-25
  • የይሖዋ ስም—ኢየሱስ የሰጠው ቦታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ ስም—ኢየሱስ የሰጠው ቦታ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ”
  • ‘የሰጠኸኝ የራስህ ስም’
  • “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው”
  • “ሕይወቴን . . . አሳልፌ እሰጣታለሁ”
  • ‘የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜያለሁ’
  • የይሖዋ ስም—ልንሰጠው የሚገባው ቦታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • “የይሖዋን ስም አወድሱ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ቤዛው ምን ያስተምረናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • “የምታገለግሉትን . . . ምረጡ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ግንቦት ገጽ 20-25

የጥናት ርዕስ 22

መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!

የይሖዋ ስም—ኢየሱስ የሰጠው ቦታ

“ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”—ዮሐ. 17:26

ዓላማ

ኢየሱስ የይሖዋን ስም ያሳወቀው እንዲሁም የቀደሰውና ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው?

1-2. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ምን አድርጓል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

ጊዜው ሐሙስ ምሽት፣ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ነው። ኢየሱስ አልፎ የሚሰጥበት፣ ሸንጎ ፊት የሚቀርብበት፣ የሚፈረድበት፣ የሚሠቃይበትና የሚገደልበት ጊዜ ተቃርቧል። ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሰገነት ላይ ልዩ ራት በልቶ ጨርሷል። ራት ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ አበረታች የሆኑ የስንብት ቃላት ተናገረ። ከዚያም ሰገነቱን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ኢየሱስ ትልቅ ትርጉም ያለው ጸሎት አቀረበ። ይህን ጸሎት ሐዋርያው ዮሐንስ በጽሑፍ አስፍሮልናል፤ ጸሎቱ ዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ይገኛል።

2 ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት በወቅቱ አሳስቦት ስለነበረው ነገር ምን ይገልጽልናል? ይህ ጸሎት ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ትልቅ ቦታ የሰጠው ነገር ምን እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት።

“ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ”

3. ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ስም ምን ተናግሯል? ምን ማለቱስ ነበር? (ዮሐንስ 17:6, 26)

3 ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ “ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ” ብሏል። እንዲያውም የይሖዋን ስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዳሳወቀ ሁለት ጊዜ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:6, 26⁠ን አንብብ።) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? የማያውቁትን ስም እንደነገራቸው መግለጹ ነበር? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አይሁዳውያን ስለነበሩ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ቀድሞውንም ቢሆን ያውቃሉ። ይህ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ይገኛል። በመሆኑም ኢየሱስ ስለ አምላክ መጠሪያ ስም ሳይሆን ስሙ ስለሚወክለው አካል መናገሩ ነበር። ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ማንነት ይበልጥ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል። ይህም ሲባል ዓላማዎቹን፣ ሥራዎቹንና ባሕርያቱን ሌላ ማንም ሊያደርግ በማይችለው መንገድ ገልጦላቸዋል ማለት ነው።

4-5. (ሀ) የአንድን ሰው ስም ማወቅ ምንን እንደሚያካትት በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የይሖዋን ስም ያወቁት እንዴት ነው?

4 ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በጉባኤህ ውስጥ ዳዊት የተባለ ሽማግሌ አለ እንበል፤ ዳዊት ሐኪም ነው። ይህን ወንድም ለረጅም ዓመት ታውቀዋለህ። ሆኖም አንድ ቀን ድንገተኛ የጤና እክል አጋጥሞህ ይህ ወንድም ወደሚሠራበት ሆስፒታል ተወሰድክ። እሱም የሕክምና ሙያውን ተጠቅሞ ሕይወትህን አተረፈልህ። አሁን ለዳዊት ያለህ ፍቅር እንደሚጨምር ምንም ጥያቄ የለውም። የእሱ ስም ሲነሳ ወደ አእምሮህ የሚመጣው የጉባኤያችሁ ሽማግሌ መሆኑ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሕይወትህን ያተረፈልህ ሐኪም መሆኑም ትዝ ይልሃል።

5 በተመሳሳይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የይሖዋን ስም ያውቁት ነበር። ሆኖም በኢየሱስ አገልግሎት የተነሳ ይህ ስም የበለጠ ትርጉም ሰጥቷቸዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ በሚናገረውም ሆነ በሚያደርገው ነገር ሁሉ የአባቱን ማንነት አንጸባርቋል። ስለዚህ ሐዋርያቱ የኢየሱስን ትምህርቶች በማዳመጥና ሰዎችን የሚይዝበትን መንገድ በማየት ይሖዋን ይበልጥ “ማወቅ” ችለዋል።—ዮሐ. 14:9፤ 17:3

‘የሰጠኸኝ የራስህ ስም’

6. ይሖዋ ለኢየሱስ ስሙን ሰጥቶታል ሲባል ምን ማለት ነው? (ዮሐንስ 17:11, 12)

6 ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው።” (ዮሐንስ 17:11, 12⁠ን አንብብ።) ታዲያ ይህ ሲባል ኢየሱስ “ይሖዋ” ተብሎ ይጠራል ማለት ነው? አይደለም። ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ ስለ ይሖዋ ስም ሲናገር ‘የራስህ ስም’ እንዳለ ልብ በል። ስለዚህ የይሖዋ ስም የኢየሱስ መጠሪያ አልሆነም። ታዲያ ኢየሱስ የአምላክ ስም እንደተሰጠው ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ የይሖዋ ወኪልና ቃል አቀባይ ነው። የመጣው በአባቱ ስም ሲሆን በእሱ ስም ድንቅ ሥራዎችን አከናውኗል። (ዮሐ. 5:43፤ 10:25) በተጨማሪም ኢየሱስ የሚለው ስም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው። በእርግጥም የይሖዋ ስም ከኢየሱስ ስም ጋር የቅርብ ተዛማጅነት አለው።

7. ኢየሱስ በይሖዋ ስም የተናገረው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

7 ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ አምባሳደር የአገሪቱን መሪ እንዲወክል ስለተሾመ በመሪው ስም ሊናገር ይችላል። ስለዚህ አምባሳደሩ የሚናገራቸው ቃላት የመሪውን ያህል ክብደት አላቸው። በተመሳሳይም ኢየሱስ የይሖዋ ወኪል ስለሆነ በእሱ ስም ለሕዝቡ ተናግሯል።—ማቴ. 21:9፤ ሉቃስ 13:35

8. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የይሖዋን ስም የተሸከመው እንዴት ነው? (ዘፀአት 23:20, 21)

8 ኢየሱስ “ቃል” እንደመሆኑ መጠን ለሌሎች መላእክትና ለሰዎች መረጃና መመሪያ በማስተላለፍ የይሖዋ ቃል አቀባይ ሆኖ አገልግሏል። (ዮሐ. 1:1-3) እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ይሖዋ እነሱን እንዲመራ የተጠቀመበት መልአክ ኢየሱስ ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ ለእስራኤላውያን ይህን መልአክ እንዲታዘዙ ሲነግራቸው “ምክንያቱም እሱ ስሜን ተሸክሟል” ብሏቸዋል።a (ዘፀአት 23:20, 21⁠ን አንብብ።) ኢየሱስ የይሖዋን ስም “ተሸክሟል” ሲባል ይሖዋን እንደሚወክል እንዲሁም የአባቱን ስም በማስከበርና በማስቀደስ ረገድ ግንባር ቀደም እንደሆነ ያመለክታል።

“አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው”

9. ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ምን ዓይነት ቦታ ይሰጥ ነበር? አብራራ።

9 እስካሁን እንዳየነው ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። ወደ ምድር ከመጣ በኋላም ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ባደረገው ነገር ሁሉ አሳይቷል። ኢየሱስ በአገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” በማለት ይሖዋን ጠይቆታል። አባቱም ወዲያውኑ ከሰማይ በሚያስገመግም ድምፅ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” ብሎ መለሰለት።—ዮሐ. 12:28

10-11. (ሀ) ኢየሱስ የይሖዋን ስም ያከበረው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) የይሖዋ ስም መቀደስና ከነቀፋ ነፃ መሆን ያስፈለገው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስም የአባቱን ስም አክብሯል። እንዴት? አንዱ መንገድ የአባቱን አስደናቂ ባሕርያትና ሥራዎች ለሌሎች በማሳወቅ ነው። ሆኖም የአባቱን ስም ለማክበር ሌላም ነገር አድርጓል። የይሖዋ ስም መቀደስና ከነቀፋ ነፃ መሆን ያስፈልገው ነበር።b ኢየሱስ ለተከታዮቹ የጸሎት ናሙናውን ባስተማረበት ጊዜ የዚህን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።”—ማቴ. 6:9

11 የይሖዋ ስም መቀደስና ከነቀፋ ነፃ መሆን ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን ዲያብሎስ በኤደን ገነት ይሖዋ አምላክን ተሳድቧል፤ እንዲሁም ስሙን አጥፍቷል። ሰይጣን፣ ይሖዋ እንደዋሸና አዳምንና ሔዋንን ጥሩ ነገር እንደነፈጋቸው ተናግሯል። (ዘፍ. 3:1-5) በተጨማሪም ሰይጣን፣ ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ጠቁሟል። ሰይጣን እነዚህን የሐሰት ክሶች በመሰንዘር የይሖዋን ስም አጥፍቷል። ከጊዜ በኋላም በኢዮብ ዘመን ሰይጣን፣ ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉት ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። ከዚህም ሌላ ይህ ስም አጥፊ ይሖዋን ከልቡ የሚወድና በመከራ ውስጥ እሱን ማገልገሉን የሚቀጥል ሰው እንደሌለ ገልጿል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) ከይሖዋና ከሰይጣን ማን ውሸታም እንደሆነ ለማረጋገጥ ጊዜ ያስፈልግ ነበር።

ኢየሱስ በብዙ ሕዝብ ፊት የተራራ ስብከቱን ሲያቀርብ።

ኢየሱስ ለተከታዮቹ የአምላክን ስም የመቀደስን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)


“ሕይወቴን . . . አሳልፌ እሰጣታለሁ”

12. ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ካለው ፍቅር በመነሳት ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል?

12 ኢየሱስ ይሖዋን ስለሚወደው ስሙን ለመቀደስና ከነቀፋ ለማንጻት ሲል የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ “ሕይወቴን . . . አሳልፌ እሰጣታለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 10:17, 18) አዎ፣ ለይሖዋ ስም ሲል ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ ነበር።c የመጀመሪያዎቹ ሁለት ፍጹማን ሰዎች ማለትም አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር በማበር ለይሖዋ ጀርባቸውን ሰጥተዋል። ኢየሱስ ግን በተቃራኒው ወደ ምድር ለመምጣትና ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ፈቃደኛ ነበር። ኢየሱስ በሕይወቱ በሙሉ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ይህን አድርጓል። (ዕብ. 4:15፤ 5:7-10) በመላው ሕይወቱ፣ እንዲያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። (ዕብ. 12:2) በዚህ መንገድ ለይሖዋና ለስሙ ያለውን ፍቅር አስመሥክሯል።

13. የሰይጣንን ውሸታምነት ማጋለጥ የሚችል ከኢየሱስ የተሻለ ሌላ ማንም የለም የምንለው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ኢየሱስ ሕይወቱን የመራበት መንገድ ውሸታም የሆነው ይሖዋ ሳይሆን ሰይጣን መሆኑን በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል! (ዮሐ. 8:44) በሕይወት ከኖረ ከማንኛውም አካል የበለጠ ኢየሱስ ይሖዋን ያውቀዋል። ሰይጣን ካነሳው ክስ መካከል አንዱም እንኳ እውነት ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ይህን ማወቁ አይቀርም ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ በቁርጠኝነት ለይሖዋ ስም ጥብቅና ቆሟል። ይሖዋ የተወው በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥም እንኳ ለአፍቃሪ አባቱ ጀርባውን ከመስጠት ይልቅ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል።—ማቴ. 27:46d

ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ።

ኢየሱስ ሕይወቱን የመራበት መንገድ ውሸታም የሆነው ሰይጣን እንጂ ይሖዋ አለመሆኑን በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል! (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)


‘የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜያለሁ’

14. ይሖዋ ኢየሱስን ለታማኝነቱ ወሮታውን የከፈለው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ባቀረበው ጸሎት ላይ ‘እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜያለሁ’ ሊል ችሏል። ይሖዋ ለታማኝነቱ ወሮታውን እንደሚከፍለው ተማምኖ ነበር። (ዮሐ. 17:4, 5) አባቱም ቢሆን አላሳፈረውም። ኢየሱስ ሞቶ እንዲቀር አልፈቀደም። (ሥራ 2:23, 24) ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት በሰማይ ላይ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል። (ፊልጵ. 2:8, 9) በኋላም ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል። ይህ መንግሥት ምን ያከናውናል? የጸሎት ናሙናው ሁለተኛ ክፍል መልሱን ይሰጠናል፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።”—ማቴ. 6:10

15. ኢየሱስ ሌላስ ምን ያከናውናል?

15 በቅርቡ ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ከአምላክ ጠላቶች ጋር ይዋጋል፤ እንዲሁም ክፉዎችን ያጠፋል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-16) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣንን ወደ “ጥልቁ” ይወረውረዋል፤ በዚያም ሰይጣን የሞተ ያህል ከእንቅስቃሴ ውጭ ይሆናል። (ራእይ 20:1-3) ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት በምድር ላይ ሰላምን መልሶ ያሰፍናል፤ የሰው ልጆችንም ወደ ፍጽምና ይመልሳቸዋል። የሞቱትን ያስነሳል። መላዋን ምድር ገነት ያደርጋታል። የይሖዋ ዓላማ ይፈጸማል!—ራእይ 21:1-4

16. በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ሕይወት ምን ይመስላል?

16 በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ምን እንደሚፈጸም መጠበቅ እንችላለን? የሰዎች ኃጢአትና አለፍጽምና ይወገዳል። የሰው ልጆች በቤዛው አማካኝነት ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው መጠየቅ አያስፈልጋቸውም። መካከለኛም ሆነ የክህነት አገልግሎት አያስፈልጋቸውም። በተጨማሪም “የመጨረሻው ጠላት፣ [አዳማዊ] ሞት ይደመሰሳል።” መቃብሮች ባዶ ይሆናሉ። ሙታን ተነስተዋል። በምድር ላይ የሚኖር ሁሉም ሰው ፍጹም ሆኗል።—1 ቆሮ. 15:25, 26

17-18. (ሀ) በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ምን ይከናወናል? (ለ) ኢየሱስ መግዛቱን የሚያቆምበት ጊዜ ሲደርስ ምን ያደርጋል? (1 ቆሮንቶስ 15:24, 28) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ሌላስ ምን ይከናወናል? በዚያ ወቅት አንድ ልዩ ነገር ይፈጸማል። ከይሖዋ ስም መቀደስ ጋር በተያያዘ የተነሳው ክርክር እልባት ያገኛል። እንዴት? ሰይጣን በኤደን ገነት ይሖዋ ውሸታም እንደሆነና አገዛዙ በፍቅር ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ተናግሮ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ስም እሱን በሚያከብሩት ሰዎች ሲቀደስ ኖሯል። በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ደግሞ የይሖዋ ስም ሙሉ በሙሉ ከነቀፋ ነፃ ይሆናል። አፍቃሪ አባት መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያስመሠክራል።

18 በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ የሰይጣን ክስ ውሸት መሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይረጋገጣል። ኢየሱስ መግዛቱን የሚያቆምበት ጊዜ ሲደርስ ምን ያደርጋል? እሱም እንደ ሰይጣን በይሖዋ ላይ ያምፅ ይሆን? በፍጹም! (1 ቆሮንቶስ 15:24, 28⁠ን አንብብ።) ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ መልሶ ያስረክባል። ለይሖዋ ይገዛል። አዎ፣ ከሰይጣን በተቃራኒ ኢየሱስ ይሖዋን ስለሚወደው ሁሉንም ነገር አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው።

ኢየሱስ በሰማይ ላይ አክሊሉን ለይሖዋ ሲያስረክብ።

ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ላይ መንግሥቱን ለይሖዋ መልሶ በፈቃደኝነት ያስረክባል (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)


19. ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ምን ዓይነት ቦታ ይሰጣል?

19 በእርግጥም ይሖዋ ለኢየሱስ የራሱን ስም ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም! ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን አስመሥክሯል። ታዲያ ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ምን ዓይነት ቦታ ይሰጣል? ከምንም ነገር አስበልጦ ይመለከተዋል። ለዚህ ስም ሲል ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል፤ በሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ያለውን ነገር ሁሉ ለይሖዋ መልሶ ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል። እኛስ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በቀጣዩ ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመለከታለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የይሖዋን ስም ያሳወቃቸው እንዴት ነው?

  • ኢየሱስ የይሖዋ ስም ተሰጥቶታል የተባለው ከምን አንጻር ነው?

  • ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ሲል ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል? ለምንስ?

መዝሙር 16 ያህ ልጁን ሾሟል አወድሱት

a መላእክትም ይሖዋን ወክለው በእሱ ስም ለሰዎች መልእክት ያስተላለፉበት ጊዜ አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ሐሳቦችን የተናገሩት መላእክት ሆነው ሳለ ይሖዋ ራሱ እንደተናገረ ተደርጎ የተገለጸው ለዚህ ነው። (ዘፍ. 18:1-33) ቅዱሳን መጻሕፍት ሙሴ ሕጉን የተቀበለው ከይሖዋ እንደሆነ ቢናገሩም ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ ይሖዋ በእሱ ስም ሕጉን እንዲያስተላልፉ መላእክትን እንደተጠቀመ ይገልጻሉ።—ዘሌ. 27:34፤ ሥራ 7:38, 53፤ ገላ. 3:19፤ ዕብ. 2:2-4

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “መቀደስ” ሲባል ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ወይም ቅዱስ አድርጎ መመልከት ማለት ነው። “ከነቀፋ ነፃ ማድረግ” ሲባል ደግሞ የአንድን ሰው ስም ከተሰነዘረበት የሐሰት ክስ ነፃ ማውጣት ወይም የተሰነዘሩበት ክሶች ውሸት መሆናቸውን ማረጋገጥ ማለት ነው።

c የኢየሱስ ሞት የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድም ከፍቷል።

d በሚያዝያ 2021 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30-31 ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ