የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ግንቦት ገጽ 26-31
  • የይሖዋ ስም—ልንሰጠው የሚገባው ቦታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ ስም—ልንሰጠው የሚገባው ቦታ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች”
  • “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”
  • ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች
  • የይሖዋ ስም—ኢየሱስ የሰጠው ቦታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • “የይሖዋን ስም አወድሱ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • “የምታገለግሉትን . . . ምረጡ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ግንቦት ገጽ 26-31

የጥናት ርዕስ 23

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

የይሖዋ ስም—ልንሰጠው የሚገባው ቦታ

“‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’ ይላል ይሖዋ።”—ኢሳ. 43:10

ዓላማ

የይሖዋን ስም በመቀደስና ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን በማድረግ በኩል የእኛ ድርሻ ምንድን ነው?

1-2. ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ በምን ማወቅ እንችላለን?

ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ከሁሉ የላቀ ቦታ ይሰጣል። ለአባቱ ስም ጥብቅና በመቆም ረገድ ግንባር ቀደም ነው። ባለፈው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ኢየሱስ ለይሖዋ ስምና ስሙ ለሚወክላቸው ነገሮች ሁሉ ሲል ለመሞት ፈቃደኛ ነበር። (ማር. 14:36፤ ዕብ. 10:7-9) የሺው ዓመት ግዛት ካበቃ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ለይሖዋ ስም መቀደስ ሲል ያለውን ሥልጣን ሁሉ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል። (1 ቆሮ. 15:26-28) ከዚህም ሌላ፣ ኢየሱስ ለአምላክ ስም ያለው ፍቅር ከአባቱ ጋር ስላለው ዝምድና ብዙ የሚነግረን ነገር አለ። ለአምላክ ስም ሲል ያደረገው ነገር ሁሉ ይሖዋን በጣም እንደሚወደው ያረጋግጣል።

2 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በአባቱ ስም ነው። (ዮሐ. 5:43፤ 12:13) የአባቱን ስም ለተከታዮቹ አሳውቋል። (ዮሐ. 17:6, 26) በይሖዋ ስም አስተምሯል፤ እንዲሁም በስሙ ተአምራት ፈጽሟል። (ዮሐ. 10:25) እንዲያውም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው” ብሏል። (ዮሐ. 17:11) ታዲያ ኢየሱስ ለይሖዋ ስም ይህን ያህል ቦታ የሚሰጥ ከመሆኑ አንጻር አንድ ሰው የይሖዋን ስም የማያውቅ ወይም የማይጠቀም ከሆነ እንዴት የክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ ነኝ ሊል ይችላል?

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን የይሖዋን ስም ከፍ አድርገን በመመልከት የኢየሱስን ፈለግ እንከተላለን። (1 ጴጥ. 2:21) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ የሚሰብኩት ሰዎች በይሖዋ ስም የተጠሩት ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። (ማቴ. 24:14) በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ ለይሖዋ ስም ምን ዓይነት ቦታ ልንሰጥ እንደሚገባ እንማራለን።

“ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች”

4. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ምን ተልእኮ ሰጥቷቸዋል? (ለ) ይህ ተልእኮ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

4 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ስለዚህ ምሥራቹ ከእስራኤል ውጭም ይሰበካል ማለት ነው። ውሎ አድሮ በሁሉም ብሔራት ውስጥ ያሉ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። (ማቴ. 28:19, 20) ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ነው ያለው። ታዲያ እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት የይሖዋን ስም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? ወይስ የኢየሱስ ምሥክሮች ብቻ ነው የሚሆኑት? በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ ያለው ዘገባ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳናል።

5. በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ባደረጉት ስብሰባ ላይ ሁሉም ሰዎች የይሖዋን ስም ማወቅ እንደሚያስፈልጋቸው የታየው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 በ49 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች፣ ያልተገረዙ አሕዛብ ክርስቲያን ለመሆን ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ለመወያየት ተሰብስበው ነበር። በስብሰባው መደምደሚያ ላይ የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ የሚከተለውን ሐሳብ ተናገረ፦ “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ [ጴጥሮስ] በሚገባ ተርኳል።” ያዕቆብ የተናገረው ስለ ማን ስም ነበር? ነቢዩ አሞጽ የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን የማደርገው የቀሩት ሰዎች፣ ከብሔራት ከመጡት በስሜ የተጠሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት . . . ይሖዋ ተናግሯል።” (ሥራ 15:14-18) እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ስለ ይሖዋ መማር ብቻ ሳይሆን ‘በስሙም ይጠራሉ።’ ይህም ማለት የአምላክን ስም ይሸከማሉ እንዲሁም በዚያ ስም ተለይተው ይታወቃሉ ማለት ነው።

ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ካሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጋር ሲነጋገር። ሁለቱ ወንድሞች የተከፈተ ጥቅልል ይዘው እያዳመጡት ነው።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ስብሰባ ባደረገበት ወቅት እነዚያ ታማኝ ወንዶች፣ ክርስቲያኖች ለአምላክ ስም የሚሆኑ ሰዎች መሆን እንዳለባቸው በግልጽ ተረድተው ነበር (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)


6-7. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው ጉዳይ ምንድን ነው?

6 የኢየሱስ ስም ትርጉም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ነው። ደግሞም ይሖዋ እምነት ያላቸውን ሰዎች ለማዳን ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ነው። (ማቴ. 20:28) ቤዛውን በመክፈል የሰው ልጆች እንዲድኑና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።—ዮሐ. 3:16

7 ይሁንና መጀመሪያውኑ የሰው ልጆች አዳኝ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? በኤደን ገነት ውስጥ በተከሰተው ነገር የተነሳ ነው። ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ በማመፃቸው የተነሳ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን አጥተዋል። (ዘፍ. 3:6, 24) ይሁንና ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን ከማዳን ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ አለ። የይሖዋ ስም ጠፍቷል። (ዘፍ. 3:4, 5) ስለዚህ የአዳምና የሔዋን ዘሮች መዳን ማግኘታቸው ይበልጥ አንገብጋቢ ከሆነው ጉዳይ ማለትም ከይሖዋ ስም መቀደስ ጋር ተያያዘ። ኢየሱስ የይሖዋ ወኪል በመሆኑና ስሙን በመሸከሙ የይሖዋን ስም በመቀደስ በኩል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

አንድ ሰው የይሖዋን ስም የማያውቅ ወይም የማይጠቀም ከሆነ እንዴት የክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ ነኝ ሊል ይችላል?

8. በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ምን ሊገነዘቡ ይገባል?

8 በኢየሱስ ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ፣ አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ የመዳናቸው ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ እውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል። (ዮሐ. 17:3) በተጨማሪም ልክ እንደ ኢየሱስ በይሖዋ ስም ተለይተው ይታወቃሉ። የዚህ ስም መቀደስ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ሊገነዘቡ ይገባል። መዳናቸው የተመካው በዚህ ላይ ነው። (ሥራ 2:21, 22) ስለዚህ የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች በሙሉ ስለ ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን ስለ ይሖዋም መማር ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ የተመዘገበውን ጸሎቱን በሚከተሉት ቃላት መደምደሙ ተገቢ ነው፦ “እኔን የወደድክበት ፍቅር እነሱም እንዲኖራቸው እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”—ዮሐ. 17:26

“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”

9. ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ሁሉም እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች የይሖዋ ስም መቀደስ ሊያሳስባቸው ይገባል። (ማቴ. 6:9, 10) የይሖዋን ስም ከስሞች ሁሉ አስበልጠው ሊመለከቱት ይገባል። ይህ ደግሞ በተግባር የሚገለጽ ነገር ነው። ይሁንና የይሖዋን ስም በመቀደስ እንዲሁም ሰይጣን ከሰነዘረበት ነቀፋ ነፃ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው?

10. በኢሳይያስ መጽሐፍ ከምዕራፍ 42 እስከ 44 ላይ የትኛው ምሳሌያዊ ችሎት ተገልጿል? (ኢሳይያስ 43:9፤ 44:7-9) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 የይሖዋን ስም በመቀደስ ረገድ የምንጫወተው ሚና በኢሳይያስ መጽሐፍ ከምዕራፍ 42 እስከ 44 ላይ ተገልጿል። በእነዚህ ምዕራፎች ላይ አማልክት በምሳሌያዊ ሁኔታ ችሎት ፊት እንደቀረቡ ተደርጎ ተገልጿል። ይሖዋ ‘አማልክት ነን’ የሚሉ ሁሉ አምላክ ስለመሆናቸው ማስረጃ እንዲያቀርቡ ይጠይቃቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ አማልክት የሚናገሩት ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ምሥክሮች እንዲቀርቡ ይጠይቃል። ሆኖም ምሥክር ሊቀርብ አልቻለም።—ኢሳይያስ 43:9፤ 44:7-9⁠ን አንብብ።

ሥዕሎች፦ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የይሖዋን ስም ለማስቀደስ የበኩላቸውን ድርሻ ሲወጡ መላእክት ከምድር በላይ ሲበርሩ ይታያል። 1. አንድ ባልና ሚስት በጋሪ ምሥክርነት ሲካፈሉ። 2. አንዲት ወጣት እህት አብራት ለምትማር ልጅ የ​jw.org የአድራሻ ካርድ ስትሰጥ። 3. አንድ ወንድም የሕዝብ መጓጓዣ ውስጥ ሆኖ ለአንድ ሰው ሲመሠክር። 4. አንድ ወንድም እጁ በካቴና ታስሮ ጭምብል ያጠለቁ ፖሊሶች ሲወስዱት። 5. የሆስፒታል አልጋ ላይ ያለች አንዲት እህት ስለ ደም ያላትን አቋም ለአንድ ሐኪም ስታስረዳ።

በምንናገረውና በምናደርገው ነገር በምሳሌያዊው ችሎት ፊት ምሥክርነት መስጠት እንችላለን (አንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት)


11. በኢሳይያስ 43:10-12 ላይ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ብሏቸዋል?

11 ኢሳይያስ 43:10-12⁠ን አንብብ። ይሖዋ ሕዝቦቹን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ . . . እኔም አምላክ ነኝ።” ይሖዋ “ከእኔ ሌላ አምላክ አለ?” የሚለውን ጥያቄ እንዲመልሱ ጠይቋቸዋል። (ኢሳ. 44:8) እኛም ለዚህ ጥያቄ መልስ የመስጠት ልዩ መብት አግኝተናል። ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን እንመሠክራለን። የእሱ ስም ከሌሎች ስሞች ሁሉ በላይ ነው። ይሖዋን ከልባችን እንደምንወደው እንዲሁም ሰይጣን ምንም ዓይነት ጫና ቢያሳድርብን ለይሖዋ ታማኞች እንደምንሆን በአኗኗራችን እናሳያለን። በዚህ መንገድ የእሱን ስም ለመቀደስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።

12. በኢሳይያስ 40:3, 5 ላይ የሚገኘው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው?

12 ከይሖዋ ስም ጎን ስንቆም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መከተላችን ነው። ኢሳይያስ አንድ ሰው ‘የይሖዋን መንገድ እንደሚጠርግ [ወይም ‘እንደሚያዘጋጅ፣’ ግርጌ]’ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳ. 40:3) ይህ ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው? አጥማቂው ዮሐንስ ለኢየሱስ መንገድ አዘጋጅቷል። ኢየሱስ ደግሞ የመጣውም ሆነ የተናገረው በይሖዋ ስም ነው። (ማቴ. 3:3፤ ማር. 1:2-4፤ ሉቃስ 3:3-6) ያው ትንቢት “የይሖዋ ክብር ይገለጣል” ይላል። (ኢሳ. 40:5) ይህ የሆነው እንዴት ነው? ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ የይሖዋን ማንነት ፍጹም በሆነ መንገድ ከማንጸባረቁ የተነሳ ይሖዋ ራሱ ወደ ምድር እንደመጣ ሊቆጠር ይችላል።—ዮሐ. 12:45

13. የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የይሖዋ ምሥክሮች ነን። የይሖዋን ስም ተሸክመናል፤ እንዲሁም ስለ አስደናቂ ሥራዎቹ ለምናገኘው ሰው ሁሉ እንናገራለን። ይሁንና ስለ ይሖዋ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመሥከር ኢየሱስ የይሖዋን ስም በመቀደስ ረገድ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚናም ማሳወቅ ይኖርብናል። (ሥራ 1:8) ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ምሥክር ኢየሱስ ነው፤ እኛ ደግሞ የእሱን ምሳሌ እንከተላለን። (ራእይ 1:5) ነገር ግን እያንዳንዳችን ለይሖዋ ስም ምን ዓይነት ቦታ ልንሰጥ ይገባል?

ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች

14. በመዝሙር 105:3 ላይ እንደተገለጸው ስለ ይሖዋ ስም ምን ይሰማናል?

14 በይሖዋ ስም እንኮራለን። (መዝሙር 105:3⁠ን አንብብ።) ይሖዋ በስሙ ስንኩራራ በጣም ደስ ይለዋል። (ኤር. 9:23, 24፤ 1 ቆሮ. 1:31፤ 2 ቆሮ. 10:17) ‘በይሖዋ መኩራራት’ ሲባል እሱ አምላካችን በመሆኑ መኩራት ማለት ነው። የእሱን ስም ማክበርና ከስሙ ጎን መቆም መቻላችንን እንደ ትልቅ መብት እንቆጥረዋለን። ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ለሚማሩ ልጆች፣ ለጎረቤቶቻችን እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለመናገር ፈጽሞ ማፈር የለብንም! ዲያብሎስ ስለ ይሖዋ ስም ለሌሎች መናገራችንን እንድናቆም ይፈልጋል። (ኤር. 11:21፤ ራእይ 12:17) እንዲያውም ሰይጣንና እሱ የሚጠቀምባቸው ሐሰተኛ ነቢያት ሰዎች የይሖዋን ስም እንዲረሱ ማድረግ ይፈልጋሉ። (ኤር. 23:26, 27) እኛ ግን ለይሖዋ ስም ያለን ፍቅር “ቀኑን ሙሉ” በስሙ ሐሴት እንድናደርግ ያነሳሳናል።—መዝ. 5:11፤ 89:16

15. የይሖዋን ስም መጥራት ሲባል ምን ማለት ነው?

15 የይሖዋን ስም መጥራታችንን እንቀጥላለን። (ኢዩ. 2:32፤ ሮም 10:13, 14) የይሖዋን ስም መጥራት የአምላክን መጠሪያ ስም ከማወቅና ከመጠቀም ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ስለ አምላክ ማንነት እውቀት እንቀስማለን፤ በእሱ ላይ እምነት እናዳብራለን፤ እንዲሁም እርዳታና መመሪያ ለማግኘት ወደ እሱ ዘወር እንላለን። (መዝ. 20:7፤ 99:6፤ 116:4፤ 145:18) ከዚህም ሌላ፣ ስለ ስሙና ስለ ባሕርያቱ ለሌሎች እንናገራለን። የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ይችሉ ዘንድ ንስሐ እንዲገቡና እርምጃ እንዲወስዱ እናበረታታቸዋለን።—ኢሳ. 12:4፤ ሥራ 2:21, 38

16. ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ለይሖዋ ስም ስንል መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ነን። (ያዕ. 5:10, 11) በመከራ ውስጥ ለይሖዋ ታማኞች ሆነን ስንቀጥል ሰይጣን ውሸታም መሆኑን እናጋልጣለን። በኢዮብ ዘመን ሰይጣን የይሖዋ አገልጋዮችን በተመለከተ “[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል” የሚል ክስ ሰንዝሯል። (ኢዮብ 2:4) ሰይጣን፣ ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉት ሕይወት አልጋ በአልጋ እስከሆነላቸው ድረስ ብቻ እንደሆነና መከራ ሲያጋጥማቸው ይሖዋን እንደሚተዉት ተናግሯል። ታማኙ ኢዮብ ይህ ክስ ውሸት መሆኑን አሳይቷል። እኛም በተመሳሳይ ሰይጣን ምንም ዓይነት ጥቃት ቢሰነዝርብን ለይሖዋ ፈጽሞ ጀርባችንን እንደማንሰጥ ማሳየት እንችላለን፤ ይህ ልዩ መብት ነው። ይሖዋ ለስሙ ሲል እንደሚጠብቀን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 17:11

17. በ1 ጴጥሮስ 2:12 መሠረት ለይሖዋ ስም ክብር ማምጣት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

17 ለይሖዋ ስም አክብሮት እናሳያለን። (ምሳሌ 30:9፤ ኤር. 7:8-11) ይሖዋን ስለምንወክልና ስሙን ስለተሸከምን ስሙን ልናስከብር ወይም ልናሰድብ እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 2:12⁠ን አንብብ።) በመሆኑም በአነጋገራችንና በምግባራችን ይሖዋን ለማስከበር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ በማድረግ፣ አለፍጽምናችን በፈቀደልን መጠን ለስሙ ክብር ማምጣት እንችላለን።

18. ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

18 ከራሳችን ስም ይበልጥ የይሖዋ ስም ያሳስበናል። (መዝ. 138:2) ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለይሖዋ ስም ባለን ፍቅር የተነሳ በዙሪያችን ባሉት ሰዎች ዘንድ መጥፎ ስም ሊሰጠን ይችላል።a ኢየሱስ የይሖዋን ስም ለማክበር ሲል እንደ ወንጀለኛ ተዋርዶ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። ‘የሚደርስበትን ውርደት ከምንም አልቆጠረም’፤ ይህም ሲባል ሌሎች ለእሱ ያላቸው አመለካከት ከመጠን በላይ አላሳሰበውም ማለት ነው። (ዕብ. 12:2-4) ትኩረቱ ያረፈው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ነው።—ማቴ. 26:39

19. ስለ ይሖዋ ስም ምን ይሰማሃል? ለምንስ?

19 በይሖዋ ስም እንኮራለን፤ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን በመጠራታችንም ክብር ይሰማናል። ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ ስለምንሰጥ የሚሰነዘርብንን ማንኛውንም ነቀፋ ለመቋቋም ፈቃደኞች ነን። ከራሳችን ስም እንኳ ይበልጥ የይሖዋ ስም ያሳስበናል። እንግዲያው፣ ሰይጣን ምንም ዓይነት ጥቃት ቢሰነዝርብን የይሖዋን ስም ማወደሳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ስናደርግ፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ እኛም ለይሖዋ ስም ከሁሉ የላቀ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • የኢየሱስ ተከታዮች ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው?

  • በዛሬው ጊዜ በየትኛው ምሳሌያዊ ችሎት ፊት ምሥክሮች ሆነን ቀርበናል?

  • ለይሖዋ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 10 ይሖዋ አምላካችንን አወድሱ!

a ታማኙ ኢዮብ እንኳ ሦስቱ ጓደኞቹ ስሙን ባጠፉ ጊዜ እይታው ተዛብቷል። መጀመሪያ ላይ ኢዮብ ልጆቹንና ንብረቱን ሁሉ ቢያጣም እንኳ “ኃጢአት አልሠራም ወይም አምላክን በደል ሠርቷል ብሎ አልወነጀለም።” (ኢዮብ 1:22፤ 2:10) ሆኖም ጓደኞቹ ኃጢአት እንደሠራ በመግለጽ ክስ ሲሰነዝሩበት ‘እንዳመጣለት’ መናገር ጀመረ። የይሖዋን ስም ከመቀደስ ይልቅ ለራሱ ስም ጥብቅና ለመቆም ቅድሚያ ሰጥቷል።—ኢዮብ 6:3፤ 13:4, 5፤ 32:2፤ 34:5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ