በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና የተደረገው ትልቅ ስብሰባ፣ 1925
1925—የዛሬ መቶ ዓመት
“ክርስቲያኖች በዚህ ዓመት የሚፈጸሙትን ክንውኖች በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል” በማለት የጥር 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ ይናገራል። ሆኖም መጽሔቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ክርስቲያኖች በዚህ ዓመት ስለሚፈጸመው ነገር በጣም ከመጨነቃቸው የተነሳ ጌታ እንዲያከናውኑ የሚፈልገውን ሥራ በደስታ ከማከናወን ወደኋላ ሊሉ አይገባም።” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በ1925 ምን ይፈጸማል ብለው ይጠብቁ ነበር? የጠበቁት ነገር ባይፈጸምም በጌታ ሥራ መጠመዳቸውን የቀጠሉትስ እንዴት ነው?
የዘገየ ተስፋ
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1925 ምድር ተመልሳ ገነት እንደምትሆን ይጠብቁ ነበር። ለምን? ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም አልበርት ሽሮደር እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ወቅት ከክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች መካከል ቀሪዎቹ የመንግሥቱ ክፍል ለመሆን ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ እንዲሁም እንደ አብርሃምና ዳዊት ያሉት የጥንት ታማኞች ትንሣኤ አግኝተው መኳንንት ሆነው እንደሚሾሙና የአምላክ መንግሥት ክፍል ሆነው ምድርን እንደሚያስተዳድሩ እንጠብቅ ነበር።” ዓመቱ እየተገባደደ ሲሄድ ተስፋቸው ባለመፈጸሙ አንዳንዶች ለሐዘን ተዳረጉ፤ ደግሞም ይህ መሆኑ አያስገርምም።—ምሳሌ 13:12
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የጠበቁት ነገር ባይፈጸምም ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ በስብከቱ ሥራ መጠመዳቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም ስለ ይሖዋ የመመሥከር ኃላፊነታቸውን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ ሄደ። እውነትን በስፋት ለማሰራጨት ያከናወኑትን ሥራ እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
የሬዲዮ ስርጭት ተስፋፋ
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ባለፈው ዓመት WBBR የሬዲዮ ጣቢያን በመጠቀም ከፍተኛ ስኬት አግኝተው ስለነበር ሌላ ትልቅ የሬዲዮ ጣቢያ ገነቡ፤ ይህ ጣቢያ የተገነባው በቺካጎ፣ ኢሊኖይ አቅራቢያ ነው። የአዲሱ የሬዲዮ ጣቢያ ስም WORD ነበር። በሬዲዮ ጣቢያው የግንባታ ሥራ የተካፈለ ራልፍ ሌፍለር የተባለ የሬዲዮ መሐንዲስ እንዲህ ብሏል፦ “ቀዝቃዛ በሆኑት የክረምት ምሽቶች WORD ከአድማስ እስከ አድማስ ይሰማ ነበር።” ለምሳሌ 5,000 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በፓይለት ስቴሽን፣ አላስካ የሚኖር አንድ ቤተሰብ አባላት ከመጀመሪያዎቹ ስርጭቶች አንዱን አዳምጠው ነበር። ስርጭቱን ካዳመጡ በኋላ፣ አበረታች መንፈሳዊ ፕሮግራም በማዘጋጀታቸው በጣቢያው ውስጥ ለሚሠሩት ሰዎች የምስጋና ደብዳቤ ጻፉላቸው።
በስተ ግራ፦ በባታቪያ፣ ኢሊኖይ የሚገኙት የWORD የሬዲዮ ጣቢያ የማሰራጫ ማማዎች
በስተ ቀኝ፦ ራልፍ ሌፍለር በሬዲዮ ጣቢያው ውስጥ ሲሠራ
የሬዲዮ ጣቢያውን አስደናቂ ተደራሽነት አስመልክቶ የታኅሣሥ 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል፦ “የ5,000 ዋት አቅም ያለው WORD ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉ ትላልቅ የሬዲዮ ጣቢያዎች አንዱ ነው። ከአትላንቲክ ዳርቻ እስከ ፓስፊክ ዳርቻ እንዲሁም ከኩባ እስከ አላስካ ሰሜናዊ ጫፍ ድረስ ስርጭቱ ጥርት ብሎ ይሰማል። እውነትን ሰምተው የማያውቁ ብዙ ሰዎች የሬዲዮ ፕሮግራሙን በመስማታቸው ለመልእክቱ ፍላጎት አሳይተዋል።”
ጆርጅ ኔሽ
በዚያ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ካናዳ ውስጥም በሬዲዮ ተጠቅመው ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት እያደረጉ ነበር። በ1924 CHUC የተባለው የሬዲዮ ጣቢያ በሳስካቱን፣ ሳስካችዋን ተገነባ። ይህ የሬዲዮ ጣቢያ ካናዳ ውስጥ ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሃይማኖታዊ የሬዲዮ ጣቢያዎች አንዱ ነው። ይህ የሬዲዮ ጣቢያ በጣም ትንሽ ስለነበር በ1925 ወደ ሌላ ቦታ መዛወር አስፈለገው። በመሆኑም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሬዲዮ ጣቢያውን ወደ ሪጀንት ሕንፃ አዛወረው፤ በሳስካቱን የሚገኘው ይህ ሕንፃ ቀደም ሲል ቲያትር ቤት የነበረ ሲሆን ድርጅቱ ለዚሁ ዓላማ ገዝቶ አድሶት ነበር።
ለዚህ የሬዲዮ ጣቢያ ምስጋና ይግባውና ሰዎች ተራርቀው በሚኖሩበት በሳስካችዋን ያሉ በርካቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን መስማት ችለዋል። ለምሳሌ ርቆ በሚገኝ አንድ ከተማ የምትኖር ግራሃም የተባለች ሴት አንድ የሬዲዮ ስርጭት ካዳመጠች በኋላ ደብዳቤ ጽፋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲላኩላት ጠየቀች። ወንድም ጆርጅ ኔሽ እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ የእውነት ጥማት እንዳላት ስለተሰማን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባለውን መጽሐፍ ሁሉንም ጥራዞች ላክንላት።” ብዙም ሳይቆይ ይህች ሴት ይበልጥ ርቀው ወደሚገኙ ቦታዎች የመንግሥቱን መልእክት ማስፋፋት ጀመረች።
በግንዛቤያችን ላይ የተደረገ ማስተካከያ
የመጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ “የብሔሩ መወለድ” የሚል ወሳኝ ርዕስ ይዞ ወጣ። ይህ ርዕስ በጣም አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ሰይጣን ድርጅት እንዳለው ከተገነዘቡ ጥቂት ቆይተዋል፤ ድርጅቱ በሰማይ ላይ ያሉ የማይታዩ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታትንና በምድር ላይ ያለውን የሃይማኖት፣ የንግድና የፖለቲካ ሥርዓት ያቀፈ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ሆኖም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በዚህ ርዕስ አማካኝነት ይሖዋም ድርጅት እንዳለው የወንድማማች ማኅበሩ እንዲገነዘብ አደረገ፤ ይህ ድርጅት ከሰይጣን ድርጅት ፍጹም ተቃራኒ ነው። (ማቴ. 24:45) በተጨማሪም ታማኙ ባሪያ፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 እንደተወለደ እንዲሁም በዚህ ዓመት ‘በሰማይ በተነሳው ጦርነት’ ምክንያት ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ እንደተባረሩና እንቅስቃሴያቸው በምድር ላይ እንደተገደበ ገለጸ።—ራእይ 12:7-9
አንዳንዶች ይህን አዲስ ግንዛቤ መቀበል ከበዳቸው። በመሆኑም መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፦ “ከመጠበቂያ ግንብ አንባቢዎች መካከል እዚህ ላይ በተጻፈው ሐሳብ የማይስማሙ ካሉ ተረጋግተው ጌታን እንዲጠብቁና ንጹሕ ልብ ይዘው እንዲቀጥሉ እናበረታታቸዋለን።”
ሆኖም ቶም ኤር የተባለ በብሪታንያ የሚኖር ኮልፖርተር አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ርዕስ አስመልክቶ ምን እንደተሰማቸው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች ስለ ራእይ 12 በተሰጠው ማብራሪያ በጣም ተደስተዋል። መንግሥቱ በሰማይ ላይ እንደተቋቋመ ስንገነዘብ ይህን ምሥራች ለሌሎች ለማካፈል ይበልጥ ጉጉት አደረብን። ሥራችንን እንድናጧጡፍ አነሳስቶናል፤ በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቦቹን ወደ ታላላቅ ነገሮች እየመራቸው ያለው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ረድቶናል።”
ስለ ይሖዋ መመሥከር
በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በኢሳይያስ 43:10 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ በደንብ ያውቁታል፦ “‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘አዎ፣ የመረጥኩት አገልጋዬ ናችሁ።’” ሆኖም ከ1925 በፊት ይህ ጥቅስ በጽሑፎቻችን ላይ እምብዛም ተጠቅሶ አያውቅም ነበር። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ተቀየረ። በ1925 ኢሳይያስ 43:10ን እና 12ን የሚያብራሩ 11 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ወጡ!
በነሐሴ 1925 መገባደጃ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና ትልቅ ስብሰባ አደረጉ። በታተመው የስብሰባ ፕሮግራም ላይ ወንድም ራዘርፎርድ እንዲህ የሚል የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፏል፦ “ወደዚህ ስብሰባ የመጣነው ከጌታ . . . ብርታት ለማግኘት ነው፤ የእሱ ምሥክሮች ለመሆን የሚያስችል አዲስ ጉልበት አግኝተን ወደ መስኩ እንመለሳለን።” ስምንት ቀን በፈጀው ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎቹ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ይሖዋ እንዲመሠክሩ ማበረታቻ ተሰጣቸው።
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 29 ወንድም ራዘርፎርድ “ለተግባር የሚያነሳሳ ጥሪ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። በንግግሩ ላይ የመመሥከርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ለሕዝቦቹ . . . ‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ . . . እኔም አምላክ ነኝ’ ብሏቸዋል። ከዚያም በማያሻማ መንገድ እንዲህ የሚል ግልጽ ትእዛዝ ሰጣቸው፦ ‘ለሕዝቦች ምልክት አቁሙ።’ የጌታ መንፈስ ካላቸውና የእሱ ምሥክሮች ከሆኑት [ከሕዝቦቹ] በስተቀር ለሕዝቦች ምልክት የሚያቆም በምድር ላይ ማንም የለም።”—ኢሳ. 43:12፤ 62:10
የተስፋ መልእክት የተባለው ትራክት
ወንድም ራዘርፎርድ ንግግሩን ካቀረበ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ “የተስፋ መልእክት” የተባለውን የአቋም መግለጫ በአንድ ድምፅ ተቀበሉ። የአቋም መግለጫው “ሰላም፣ ብልጽግና፣ ጤንነት፣ ሕይወት፣ ነፃነትና ዘላለማዊ ደስታ” የሚያስገኘው ብቸኛው እውነተኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ይገልጻል። ይህ የአቋም መግለጫ ከጊዜ በኋላ ወደተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በትራክት መልክ ታትሟል። አርባ ሚሊዮን ገደማ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ “የይሖዋ ምሥክሮች” በሚለው ስም መጠራት የጀመሩት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነው። ሆኖም ስለ እሱ የመመሥከር ኃላፊነታቸውን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዷል።
ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሶ መጠየቅ
በዓለም ዙሪያ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ቀደም ሲል ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰው እንዲጠይቁ የሚሰጣቸው ማበረታቻም እየጨመረ ሄደ። የተስፋ መልእክት የተባለውን ትራክት ለማሰራጨት ዘመቻ ከተካሄደ በኋላ ቡለቲንa እንዲህ የሚል መመሪያ ይዞ ወጣ፦ “ለቤቱ ባለቤቶች ጽሑፍ ባይበረከትላቸውም እንኳ የተስፋ መልእክት የተባለው ትራክት ወደተሰራጨባቸው ቤቶች ተመልሳችሁ ሂዱ።”
የጥር 1925 ቡለቲን በፕላኖ፣ ቴክሳስ የሚኖር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የላከውን የሚከተለውን ሪፖርት አካቶ ነበር፦ “በተደጋጋሚ የተሸፈነ ክልል ብዙውን ጊዜ ከአዲስ ክልል የበለጠ ውጤታማ መሆኑ አስገርሞናል። በክልላችን ውስጥ የሚገኝ አንድ ትንሽ መንደር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ አምስት ጊዜ ተሸፍኗል። . . . በቅርቡ እህት ሄንድሪክስ እና እናቴ ይህን ክልል በድጋሚ ሸፍነውት ነበር፤ [ከመቼውም ጊዜ] ይበልጥ ብዙ መጻሕፍት አበርክተዋል።”
በፓናማ የሚኖር አንድ ኮልፖርተር ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከቤታቸው ያባረሩኝ ብዙዎቹ ሰዎች ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ ጊዜ ስመለስ የአመለካከት ለውጥ ያሳያሉ። በዚህ ዓመት አገልግሎቴ በዋነኝነት ያተኮረው ቀደም ሲል ያነጋገርኳቸውን ሰዎች ተመልሼ በመጠየቅ ላይ ነው። ከአንዳንዶቹ ሰዎች ጋር አስደሳች ውይይት ማድረግ ችያለሁ።”
የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ
ወንድም ራዘርፎርድ ለሁሉም ኮልፖርተሮች በላከው ዓመታዊ ደብዳቤ ላይ ያለፈውን ዓመት እንቅስቃሴ ጠቅለል አድርጎ የገለጸ ከመሆኑም ሌላ ከፊታቸው ስለሚጠብቃቸው ሥራ ተናገረ። እንዲህ ብሏል፦ “ባሳለፍነው ዓመት በሐዘን ተውጠው የነበሩ ብዙ ሰዎችን የማጽናናት መብት አግኝታችኋል። ይህ ሥራ ልባችሁን አስደስቶታል። . . . ከፊታችሁ ያለው ዓመት ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ ለመመሥከር እንዲሁም ለሕዝቦች ምልክት ለማቆም የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይሰጣችኋል። . . . ድምፃችንን አንድ ላይ አስተባብረን ለአምላካችንና ለንጉሣችን የውዳሴ መዝሙር መዘመራችንን እንቀጥል።”
ወንድሞች በ1925 መገባደጃ ላይ በብሩክሊን ያሉትን ሕንፃዎች ለማስፋፋት ዕቅድ እያወጡ ነበር። ቀጣዩ ዓመት ማለትም 1926 ድርጅቱ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ካከናወናቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ሁሉ ትልቁ የተጀመረበት ዓመት ነው።
በአዳምስ ስትሪት፣ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የተካሄደው ግንባታ፣ 1926
a አሁን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ተብሎ ይጠራል።