የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ኅዳር ገጽ 16-21
  • ሩኅሩኅ የሆነውን ሊቀ ካህናታችንን ኢየሱስን አስቡ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሩኅሩኅ የሆነውን ሊቀ ካህናታችንን ኢየሱስን አስቡ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ውድ ልጅ ወደ ምድር መጣ
  • ኢየሱስ የሰዎችን ስሜት ይረዳ ነበር
  • በዛሬው ጊዜ የሊቀ ካህናታችንን ምሳሌ መከተል
  • ሊቀ ካህናታችን ሊረዳህ ይችላል
  • ቤዛው ምን ያስተምረናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ኢየሱስ በምድር ላይ ካሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት የምናገኘው ትምህርት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ኅዳር ገጽ 16-21

የጥናት ርዕስ 46

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

ሩኅሩኅ የሆነውን ሊቀ ካህናታችንን ኢየሱስን አስቡ

“ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለም።”—ዕብ. 4:15

ዓላማ

ኢየሱስ አዛኝና ሩኅሩኅ መሆኑ ከሁሉ የተሻለ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ያስቻለው እንዴት ነው? እኛስ ከእሱ የክህነት አገልግሎት ምን ጥቅም እናገኛለን?

1-2. (ሀ) ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር የላከው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (ዕብራውያን 5:7-9)

ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ይሖዋ አምላክ ውድ ልጁን ወደ ምድር ላከው። ለምን? አንዱ ምክንያት የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት እርግማን ለመቤዠትና ሰይጣን ያደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 3:8) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ሰው ሆኖ የሚያሳልፈው ጊዜ አዛኝ፣ ሩኅሩኅና የሌሎችን ስሜት የሚረዳ ሊቀ ካህናት ለመሆን ይበልጥ እንደሚያዘጋጀው ያውቃል። ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ሆኖ ማገልገል የጀመረው በ29 ዓ.ም. ከተጠመቀ በኋላ ነው።a

2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ኢየሱስ ምድር ላይ ያሳለፈው ጊዜ ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ያስቻለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ኢየሱስ ለዚህ ኃላፊነት ‘ፍጹም እንዲሆን’ የተደረገው እንዴት እንደሆነ ያለንን ግንዛቤ ማስፋታችን በኃጢአታችን ወይም በድክመታችን የተነሳ በምንደቆስበት ጊዜም እንኳ ወደ ይሖዋ መቅረብ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል።—ዕብራውያን 5:7-9ን አንብብ።

የአምላክ ውድ ልጅ ወደ ምድር መጣ

3-4. ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ የትኞቹን ትላልቅ ለውጦች አስተናግዷል?

3 ብዙዎቻችን ያለንበት ሁኔታ ተለውጦ ያውቃል። ለምሳሌ የምንወደውን መኖሪያችንን ትተን እንዲሁም ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ርቀን በሌላ ቦታ ለመኖር ተገደን እናውቅ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ለውጦች ተፈታታኝ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም የኢየሱስን ያህል ትልቅ ለውጥ ያስተናገደ አንድም ሰው የለም። በሰማይ ሳለ ከሌሎች መላእክት ሁሉ የላቀ ቦታ ነበረው። በይሖዋ ፍቅር ተከቦ ይኖር የነበረ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ “ቀኝ” ሆኖ በማገልገሉ ሁልጊዜ ይደሰት ነበር። (መዝ. 16:11፤ ምሳሌ 8:30) ያም ቢሆን ፊልጵስዩስ 2:7 እንደሚለው በፈቃደኝነት ‘ራሱን ባዶ አደረገ’፤ በሰማይ የነበረውን የላቀ ቦታ ትቶ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ለመኖር ወደ ምድር መጣ።

4 ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት የነበረውን ሁኔታም ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ካቀረቡት መሥዋዕት እንደምንረዳው የተወለደው በድሃ ቤተሰብ ውስጥ ነው። (ዘሌ. 12:8፤ ሉቃስ 2:24) ክፉው ንጉሥ ሄሮድስ የኢየሱስን መወለድ ሲያውቅ ሊያስገድለው ሞክሮ ነበር። ቤተሰቡ ከእሱ ለማምለጥ ሲል ለተወሰነ ጊዜ ያህል በግብፅ ስደተኛ ሆኖ ኖሯል። (ማቴ. 2:13, 15) ኢየሱስ በሰማይ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ለውጥ ነው!

5. ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ምን ተመልክቷል? ይህስ ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት እንዲሆን የረዳው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ሲሠቃዩ ተመልክቷል። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን እንደቀመሰ ጥርጥር የለውም፤ አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍም የሞተው በዚያ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ከሥጋ ደዌ በሽተኞች፣ ከዓይነ ስውራን፣ ከሽባዎች እንዲሁም ልጆቻቸውን በሞት ካጡ ወላጆች ጋር ተገናኝቷል፤ ለእነሱም ራርቶላቸዋል። (ማቴ. 9:2, 6፤ 15:30፤ 20:34፤ ማር. 1:40, 41፤ ሉቃስ 7:13) እርግጥ ነው፣ ሰማይ ላይ በነበረበት ጊዜም በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ይመለከት ነበር። ሆኖም ምድር ላይ ከመጣ በኋላ የሰው ልጆችን ሥቃይ በአዲስ መልክ ተመልክቷል። (ኢሳ. 53:4) ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ጊዜ የሰው ልጆችን ስሜት፣ መከራና ሥቃይ እንዲረዳ አስችሎታል። እሱ ራሱም እንደ ጭንቀት፣ ድካምና ሐዘን ያሉ የሰው ልጆች የሚያስተናግዷቸውን ስሜቶች አስተናግዷል።

ኢየሱስ ከበሽታቸው እንዲፈውሳቸው በሚለምኑት ሰዎች ተከቦ። በርኅራኄ ተነሳስቶ የአንድን የታመመ አረጋዊ ሰው እጅ ይይዛል።

ኢየሱስ በዙሪያው ያሉት ሰዎች ስሜትና መከራ በጥልቅ ያሳስበው ነበር (አንቀጽ 5ን ተመልከት)


ኢየሱስ የሰዎችን ስሜት ይረዳ ነበር

6. ነቢዩ ኢሳይያስ የተጠቀመባቸው ዘይቤያዊ አገላለጾች ስለ ኢየሱስ ርኅራኄ ምን ያስተምሩናል? (ኢሳይያስ 42:3)

6 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የደካሞችንና ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን ስሜት ይረዳ ነበር። በዚህ መንገድ፣ ስለ እሱ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ፣ የበለጸጉና ጠንካራ የሆኑ ሰዎች ከለመለመ የአትክልት ቦታ ወይም ግርማ ሞገስ ከተላበሱ ትላልቅ ዛፎች ጋር የተመሳሰሉበት ጊዜ አለ። (መዝ. 92:12፤ ኢሳ. 61:3፤ ኤር. 31:12) ድሆችና የተጎሳቆሉ ሰዎች ግን ከተቀጠቀጠ ሸንበቆና ከሚጨስ የጧፍ ክር ጋር ተመሳስለዋል፤ ሁለቱም ነገሮች ለሰዎች ጥቅም አይሰጡም። (ኢሳይያስ 42:3ን አንብብ፤ ማቴ. 12:20) ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ መሪነት እነዚህን ዘይቤያዊ አገላለጾች የተጠቀመው ኢየሱስ በሌሎች ዘንድ እንደ ዋጋ ቢስ ለሚቆጠሩ ተራ ሰዎች የሚያሳየውን ፍቅርና ርኅራኄ ለማመልከት ነው።

7-8. ኢየሱስ የኢሳይያስ ትንቢት እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት ነው?

7 ወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ “የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም” የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል። ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት አንዳንዶቹ እንደተቀጠቀጠ ሸንበቆ ያሉ የተጨቆኑ ሰዎችንና ሊጠፋ እንደተቃረበ የሚጨስ የጧፍ ክር ያሉ ተስፋ ቢስ የሆኑ ሰዎችን በእጅጉ ጠቅመዋቸዋል። ከእነዚህም መካከል መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ የወረሰው ሰው ይገኝበታል። ይህ ሰው ‘ተፈውሼ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር እቀላቀላለሁ’ የሚል ተስፋ አልነበረውም። (ሉቃስ 5:12, 13) ኢየሱስ መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት ሰውም አግኝቶ ነበር። ይህ ሰው፣ ሌሎች ሞቅ ያለ ጭውውት ሲያደርጉ እያየ እሱ ምንም ነገር መረዳት ሲያቅተው ምን ሊሰማው እንደሚችል አስበው። (ማር. 7:32, 33) ሆኖም ይህ ብቻ አይደለም።

8 በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ አይሁዳውያን፣ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው በራሳቸው ወይም በወላጆቻቸው ኃጢአት ምክንያት እንደሆነ ያምኑ ነበር። (ዮሐ. 9:2) መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች በዚህ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ሰዎች ስለሚበድሏቸው ዋጋ ቢስ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ኢየሱስ እየተሠቃዩ ያሉ ሰዎችን በመፈወስና በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት መልሶ እንዲቀጣጠል በማድረግ የኢሳይያስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። ታዲያ ይህ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

9. ዕብራውያን 4:15, 16 በሰማይ ላይ ያለው ሊቀ ካህናታችን ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች እውነተኛ ርኅራኄ እንደሚያሳይ የሚያጎላው እንዴት ነው?

9 ዕብራውያን 4:15, 16ን አንብብ። ኢየሱስ ለእኛም ምንጊዜም እንደሚራራልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህ ምን ማለት ነው? ሩኅሩኅ የሆነ ሰው ሌሎች የሚደርስባቸውን መከራና የሚሰማቸውን ሐዘን ሲመለከት ስሜቱ ይነካል። “ርኅራኄ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል የሌላን ሰው ስሜትና ሥቃይ መጋራትን ያመለክታል። (ዕብራውያን 10:34​ንም ተመልከት፤ እዚያ ላይ ጳውሎስ ተመሳሳይ የግሪክኛ ግስ ተጠቅሟል።) ስለ ኢየሱስ ተአምራት የሚገልጹት ዘገባዎች፣ ኢየሱስ የሌሎችን ሥቃይ ሲመለከት ምን ያህል ስሜቱ እንደተነካ ያሳያሉ። ሰዎችን የፈወሰው ግዴታ እንዳለበት ተሰምቶት አይደለም። ከልቡ ያስብላቸው ነበር፤ ሊረዳቸውም ፈልጓል። ለምሳሌ የሥጋ ደዌ በሽተኛውን በፈወሰበት ወቅት ተአምሩን ከሩቅ መፈጸም ይችል ነበር፤ ሆኖም ሰውየውን ለመዳሰስ ተነሳስቷል፤ ምናልባትም ይህ ሰው ለብዙ ዓመታት ሰው ነክቶት አያውቅ ይሆናል። ኢየሱስ መስማት የተሳነውንም ሰው የፈወሰው ከሕዝብ መሃል አውጥቶ ገለል ወዳለ ስፍራ በመውሰድ ነው። በተጨማሪም አንድ ፈሪሳዊ የኢየሱስን እግር በእንባዋ ያጠበችውንና በፀጉሯ ያደረቀችውን ንስሐ የገባች ሴት ሲያቃልላት ኢየሱስ ጥብቅና ቆሞላታል። (ማቴ. 8:3፤ ማር. 7:33፤ ሉቃስ 7:44) ኢየሱስ በሕመም ይሠቃዩ የነበሩ እንዲሁም ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችን አላገለላቸውም። ከዚህ ይልቅ ወደ እሱ እንዲመጡ ጋብዟቸዋል፤ እንዲሁም በርኅራኄ አጽናንቷቸዋል። ኢየሱስ ለእኛም እንዲህ ያለ ርኅራኄ እንደሚያሳየን መተማመን እንችላለን።

በዛሬው ጊዜ የሊቀ ካህናታችንን ምሳሌ መከተል

10. በዛሬው ጊዜ መስማት የተሳናቸውን ሰዎችና ዓይነ ስውራንን ለመርዳት የትኞቹን መንፈሳዊ ዝግጅቶች መጠቀም እንችላለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን የሌሎችን ስሜት በመረዳት እንዲሁም ፍቅርና ርኅራኄ በማሳየት ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት እናደርጋለን። (1 ጴጥ. 2:21፤ 3:8) መስማት የተሳናቸውንና ዓይነ ስውራንን መፈወስ እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ሆኖም በመንፈሳዊ ልንረዳቸው እንችላለን። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ከ100 በሚበልጡ የምልክት ቋንቋዎች ይገኛሉ። በተጨማሪም የማየት ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲባል የብሬይል ጽሑፎች ከ60 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች፣ የቪዲዮ የድምፅ መግለጫዎች ደግሞ ከ100 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ። እነዚህ ዝግጅቶች መስማት የተሳናቸውን ሰዎችና ዓይነ ስውራንን ወደ ይሖዋና ወደ ልጁ እንዲቀርቡ ይረዷቸዋል።

ሥዕሎች፦ 1. ወንድሞችና እህቶች በምልክት ቋንቋ በሚካሄድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ በምልክት ቋንቋ ሲዘምሩ። 2. አንዲት ዓይነ ስውር እህት መጽሐፍ ቅዱስን በብሬይል ስታነብ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛሉ

በስተ ግራ፦ ከ100 በላይ የምልክት ቋንቋዎች

በስተ ቀኝ፦ ከ60 በላይ ቋንቋዎች በብሬይል

(አንቀጽ 10ን ተመልከት)


11. የይሖዋ ድርጅት ልክ እንደ ኢየሱስ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው? (የሐዋርያት ሥራ 2:5-7, 33) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

11 የይሖዋ ድርጅት ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለመርዳት ጥረት ያደርጋል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ በጴንጤቆስጤ በዓል ላይ የተገኙ ሰዎች በሙሉ ‘እያንዳንዳቸው በገዛ ቋንቋቸው’ ምሥራቹን መስማት እንዲችሉ መንፈስ ቅዱስን እንዳፈሰሰ አስታውስ። (የሐዋርያት ሥራ 2:5-7, 33ን አንብብ።) ድርጅቱም የእሱን አመራር በመከተል ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያዘጋጃል። ከእነዚህ ቋንቋዎች አንዳንዶቹ በጥቂት ሰዎች ዘንድ ብቻ የሚነገሩ ናቸው። ለምሳሌ የአሜሪካ ሕንዶች የሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ቋንቋዎች የሚነገሩት በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ በሚኖሩ ጥቂት ሰዎች ነው። ሆኖም በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ሲባል ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ከ160 በላይ በሚሆኑት ጽሑፎቻችን ተዘጋጅተዋል። ጽሑፎቻችን ከ20 በሚበልጡ የሮማኒ ቋንቋዎችም ይገኛሉ። እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩት በምሥራቃዊና ደቡብ ምሥራቃዊ አውሮፓ የሚኖሩ ጥቂት ሕዝቦች ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ መድልዎ ይፈጸምባቸዋል። እንዲህ ያሉ ቋንቋዎችን የሚናገሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእውነት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሥዕሎች፦ 1. አንዲት የአሜሪካ ሕንድ እህት በቋንቋዋ የተዘጋጀን መጽሐፍ ቅዱስ እቅፍ አድርጋ። 2. አንዲት ሮማኒ እህትና ሴት ልጇ በአንዲት ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ በደስታ ሲካፈሉ።

በስተ ግራ፦ የአሜሪካ ሕንዶች የሚጠቀሙባቸው ከ160 በላይ ቋንቋዎች

በስተ ቀኝ፦ ከ20 በላይ የሮማኒ ቋንቋዎች

(አንቀጽ 11ን ተመልከት)


12. የይሖዋ ድርጅት ተግባራዊ እርዳታ የሚያደርገው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

12 የይሖዋ ድርጅት ምሥራቹን ለማስፋፋት የሚደረጉትን እንዲህ ያሉ ጥረቶች ከማደራጀት በተጨማሪ በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ያበረክታል። ለዚህም ሲባል በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት ራሳቸውን ያቀርባሉ። በተጨማሪም ድርጅቱ፣ ሰዎች አምላክ ለእነሱ ስላለው ፍቅር መማር እንዲችሉ ቀለል ያሉ የስብሰባ አዳራሾችን ያዘጋጃል።

ሊቀ ካህናታችን ሊረዳህ ይችላል

13. ኢየሱስ በየትኞቹ መንገዶች ይረዳናል?

13 ጥሩ እረኛችን የሆነው ኢየሱስ ለእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ፍላጎት ትኩረት ይሰጣል። (ዮሐ. 10:14፤ ኤፌ. 4:7) በሚያጋጥመን የሕይወት ውጣ ውረድ የተነሳ እንደሚጨስ የጧፍ ክር ወይም እንደተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንደሆንን የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። ባለብን ከባድ ሕመም፣ በሠራነው ስህተት ወይም ከእምነት አጋራችን ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ከሚሰማን ሥቃይ አሻግረን በማየት ተስፋችን ላይ ማተኮር ሊከብደን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚመለከትና ውስጣዊ ስሜትህን እንደሚረዳ አስታውስ። የኢየሱስ ርኅራኄ አንተን ለመርዳት እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። ለምሳሌ ስትደክም መንፈስ ቅዱስን ተጠቅሞ ሊያበረታህ ይችላል። (ዮሐ. 16:7፤ ቲቶ 3:6) በተጨማሪም ኢየሱስ ‘ስጦታ የሆኑትን ሰዎችና’ ሌሎች የእምነት አጋሮችህን በመጠቀም ሊያበረታታህ፣ ሊደግፍህና ሊረዳህ ይችላል።—ኤፌ. 4:8

14. ተስፋ ስንቆርጥ ምን ማድረግ እንችላለን?

14 ሕይወት ሲጨልምብህ ወይም መንፈስህ ሲደቆስ፣ ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን ሆኖ ስለሚጫወተው ሚና አሰላስል። ይሖዋ ወደ ምድር የላከው ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጠን ብቻ ሳይሆን ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች የሚጋፈጧቸውን ችግሮች ይበልጥ መረዳት እንዲችል ብሎ እንደሆነ አስታውስ። በኃጢአታችን ወይም በድክመታችን የተነሳ ተስፋ ስንቆርጥ ኢየሱስ “በሚያስፈልገን ጊዜ” እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው።—ዕብ. 4:15, 16

15. ከይሖዋ መንጋ የራቀ ሰው ወደ ጉባኤ ለመመለስ እንዴት እርዳታ እንዳገኘ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

15 በተጨማሪም ኢየሱስ ሕዝቦቹ ከይሖዋ መንጋ የራቁ ሰዎችን ለመፈለግና ለመርዳት ጥረት ሲያደርጉ ይመራቸዋል። (ማቴ. 18:12, 13) የስቴፋኖንb ተሞክሮ እንመልከት። ስቴፋኖ ከጉባኤ ከተወገደ ከ12 ዓመታት በኋላ በስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰነ። እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው ቢያስጨንቀኝም ከይሖዋ አፍቃሪ ቤተሰብ ጋር መልሼ መቀላቀል ፈልጌ ነበር። ያነጋገሩኝ ሽማግሌዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ። የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማኝ ጊዜ ነበር፤ ተስፋ ለመቁረጥ የተቃረብኩባቸው ጊዜያትም አሉ። ሆኖም ወንድሞች ይሖዋና ኢየሱስ እንድጸና እንደሚፈልጉ አስታወሱኝ። ውገዳው ሲነሳልኝ መላው ጉባኤ እኔንም ሆነ ቤተሰቤን ሞቅ አድርጎ ተቀበለን። በኋላም ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። በአሁኑ ወቅት በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን እያገለገልን ነው።” አፍቃሪው ሊቀ ካህናታችን ንስሐ የገቡ ሰዎች ወደ ጉባኤ ለመመለስ እርዳታ ሲያገኙ ምንኛ ይደሰት ይሆን!

16. ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት ስላለን አመስጋኝ የሆንከው ለምንድን ነው?

16 ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ወቅት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ሰዎች በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እርዳታ ሰጥቷቸዋል። ዛሬም በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ እርዳታ እንደሚሰጠን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ደግሞ ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን አለፍጽምናና ኃጢአት ከሚያስከትለው መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ያወጣቸዋል። አምላካችን ይሖዋ በታላቅ ፍቅርና ምሕረት ተነሳስቶ ልጁን ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናታችን አድርጎ ስለሾመልን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት ከሁሉ የተሻለ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ያዘጋጀው እንዴት ነው?

  • ኢሳይያስ 42:3 በኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

  • ሊቀ ካህናታችን በዛሬው ጊዜ እየረዳን ያለው እንዴት ነው?

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

a ኢየሱስ የአይሁድን ሊቀ ካህናት የተካው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥቅምት 2023 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ አምልኮ የማቅረብ መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው” የሚለውን ርዕስ ገጽ 26 ከአን. 7-9ን ተመልከት።

b ስሙ ተቀይሯል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ