የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ኅዳር ገጽ 22-27
  • “አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ”!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ”!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ሰዎች በይሖዋ ዘንድ ያላቸውን ዋጋ እንዲያውቁ የረዳቸው እንዴት ነው?
  • ይሖዋ በሚያየን መንገድ ራሳችንን ማየት የምንችለው እንዴት ነው?
  • ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ይሖዋ እጅግ ይወድሃል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ኢየሱስ በምድር ላይ ካሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት የምናገኘው ትምህርት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ኅዳር ገጽ 22-27

የጥናት ርዕስ 47

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

“አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ”!

“አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ።”—ዳን. 9:23

ዓላማ

የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ወንድሞችና እህቶች በይሖዋ ዘንድ ያላቸውን እውነተኛ ዋጋ እንዲገነዘቡ መርዳት።

1-2. በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆንን ለመገንዘብ ምን ይረዳናል?

ከይሖዋ ውድ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹ የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል። ምናልባትም እንዲህ የሚሰማቸው ሰዎች ዝቅ አድርገው ስለሚመለከቷቸው ሊሆን ይችላል። አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ፣ በይሖዋ ዘንድ ውድ ዋጋ እንዳለህ መገንዘብ የምትችለው እንዴት ነው?

2 ይሖዋ ሰዎች እንዴት እንዲያዙ እንደሚፈልግ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መመርመርህ ይረዳህ ይሆናል። ልጁ ኢየሱስ ሰዎችን በደግነትና በአክብሮት ይይዝ ነበር። እንዲህ በማድረግ፣ እሱና አባቱ የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማቸውን ምስኪን ሰዎች ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ አሳይቷል። (ዮሐ. 5:19፤ ዕብ. 1:3) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ (1) ኢየሱስ ሰዎች በይሖዋ ዘንድ ያላቸውን ዋጋ እንዲያውቁ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም (2) በአምላክ ዓይን ውድ እንደሆንን ራሳችንን ማሳመን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።—ሐጌ 2:7 ግርጌ

ኢየሱስ ሰዎች በይሖዋ ዘንድ ያላቸውን ዋጋ እንዲያውቁ የረዳቸው እንዴት ነው?

3. ኢየሱስ የእሱን እርዳታ የፈለጉትን የገሊላ ሰዎች የያዛቸው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ገሊላ ውስጥ ባከናወነው ሦስተኛ የስብከት ጉዞ ወቅት በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከእሱ ለመማርና ከበሽታቸው ለመፈወስ ሲሉ ወደ እሱ ይጎርፉ ነበር። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” እንደነበር አስተዋለ። (ማቴ. 9:36) የሃይማኖት መሪዎቻቸው እንደ መሃይም ስለሚቆጥሯቸው ይንቋቸው ነበር፤ እንዲያውም ‘የተረገመ ሕዝብ’ ብለው ይጠሯቸው ነበር። (ዮሐ. 7:47-49) ሆኖም ኢየሱስ ጊዜ ወስዶ እነሱን በማስተማርና ከበሽታቸው በመፈወስ እንደሚያከብራቸው አሳይቷል። (ማቴ. 9:35) በተጨማሪም ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን መርዳት ስለፈለገ ሐዋርያቱን በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ አሠልጥኗቸዋል፤ እንዲሁም የታመሙትን እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 10:5-8

4. ኢየሱስ አድማጮቹን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

4 ኢየሱስ አድማጮቹን በአክብሮትና በደግነት በመያዝ እሱና አባቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን ውድ አድርገው እንደሚመለከቷቸው አሳይቷል። አንተም ይሖዋን እያገለገልክ ቢሆንም በእሱ ዘንድ ያለህን ቦታ ከተጠራጠርክ ኢየሱስ ከእሱ መማር የሚፈልጉትን ምስኪን ሰዎች እንዴት እንደያዛቸው አስብ። እንዲህ ማድረግህ በይሖዋ ዘንድ ያለህን ውድ ዋጋ እንድትገነዘብ ያስችልሃል።

5. ኢየሱስ በገሊላ ያገኛት ሴት የነበረችበትን ሁኔታ ግለጽ።

5 ኢየሱስ ሰዎችን በቡድን ደረጃ ከማስተማር ባለፈ ለግለሰቦችም ትኩረት ሰጥቷል። ለምሳሌ በገሊላ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረች ሴት አገኘ። (ማር. 5:25) በሕጉ መሠረት ርኩስ ስለነበረች እሷን የሚነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ከሰዎች ጋር ያላት ግንኙነት በእጅጉ የተገደበ እንደሚሆን እሙን ነው። በተጨማሪም በሕዝባዊ በዓላት ላይ ተገኝታ ከሌሎች ጋር አምልኮ ማቅረብ አትችልም። (ዘሌ. 15:19, 25) በእርግጥም ይህች ሴት አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ሥቃይ ይደርስባት እንደነበር አያጠራጥርም።—ማር. 5:26

6. ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት የተፈወሰችው እንዴት ነው?

6 በብዙ ሥቃይ ውስጥ የነበረችው ይህች ሴት ኢየሱስ እንዲፈውሳት ፈልጋለች። ሆኖም እንዲፈውሳት አልጠየቀችውም። ለምን? ምናልባት በሕመሟ ምክንያት ኀፍረት ተሰምቷት ወይም ተሸማቃ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በሕጉ መሠረት ርኩስ ሆና ሳለ ሕዝብ መሃል በመግባቷ ኢየሱስ እንደሚቆጣት አስባ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ስላሰበች ሄዳ ልብሱን ነካች። (ማር. 5:27, 28) እምነቷ ክሷታል፤ ከበሽታዋ ተፈወሰች። ከዚያም ኢየሱስ የነካው ማን እንደሆነ ጠየቀ፤ እሷም ያደረገችውን ነገር ሁሉ ተናገረች። ታዲያ ኢየሱስ እንዴት ይይዛት ይሆን?

7. ኢየሱስ እየተሠቃየች የነበረችውን ይህችን ሴት የያዛት እንዴት ነው? (ማርቆስ 5:34)

7 ኢየሱስ ይህችን ሴት በደግነትና በአክብሮት ይዟታል። “በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች” እንደነበር ተመልክቷል። (ማር. 5:33) ስሜቷን በመረዳት በሚያጽናኑ ቃላት አነጋግሯታል። እንዲያውም “ልጄ ሆይ” በማለት ጠርቷታል። ይህ አጠራር አክብሮት ብቻ ሳይሆን ፍቅርና ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ነው። (ማርቆስ 5:34ን አንብብ።) ኢየሱስ አንዲትን ሴት “ልጄ ሆይ” ብሎ እንደጠራ የተገለጸው በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ብቻ ነው። እንዲህ ብሎ የጠራት በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መሆኑን ስላየ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህች ሴት ምን ያህል እፎይታ ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል ገምት። ኢየሱስ በዚህ መንገድ ባያጽናናት ኖሮ አካላዊ ፈውስ ብታገኝም በጥፋተኝነት ስሜት እየተሠቃየች ልትኖር ትችል ነበር። ኢየሱስ ያላትን እውነተኛ ዋጋ፣ ይኸውም የአፍቃሪው የሰማዩ አባቷ ውድ ልጅ እንደሆነች እንድትገነዘብ ረድቷታል።

8. በብራዚል የምትኖር አንዲት እህት ምን ዓይነት ፈተና አጋጥሟታል?

8 በዛሬው ጊዜም አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ስሜታዊ ሥቃይ ከሚያስከትል የጤና ችግር ጋር ይታገላሉ። በብራዚል የዘወትር አቅኚ ሆና የምታገለግለው ማሪያa ስትወለድ ጀምሮ እግርም ሆነ ግራ እጅ የላትም። እንዲህ ብላለች፦ “አካል ጉዳተኛ በመሆኔ የተነሳ ትምህርት ቤት ውስጥ ልጆቹ ሁልጊዜ ያሾፉብኝ ነበር። ስሜት የሚያቆስሉ ቅጽል ስሞች ይሰጡኝ ነበር። ከገዛ ቤተሰቤ ሳይቀር መድልዎ ደርሶብኛል።”

9. ማሪያ በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆነች እንድትገነዘብ የረዳት ምንድን ነው?

9 ማሪያ እርዳታ ያገኘችው እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ወንድሞችና እህቶች ያጽናኗት ሲሆን ይሖዋ እሷን በሚያይበት መንገድ ራሷን እንድታይ ረድተዋታል። እንዲህ ብላለች፦ “የረዱኝን ሰዎች ዘርዝሬ ለመጻፍ ደብተሬ አይበቃኝም። እንዲህ ያለ ግሩም መንፈሳዊ ቤተሰብ ስለሰጠኝ ይሖዋን በሙሉ ልቤ አመሰግነዋለሁ።” የማሪያ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆነች እንድትገነዘብ ረድተዋታል።

10. መግደላዊቷ ማርያም ምን ዓይነት መከራ ነበረባት? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ የረዳት ሌላ ሴትም አለች፤ ይህች ሴት መግደላዊቷ ማርያም ናት። መግደላዊቷ ማርያም በሰባት አጋንንት ተይዛ ነበር! (ሉቃስ 8:2) በአጋንንት ተጽዕኖ ሥር በመሆኗ እንግዳ የሆኑ ነገሮችን ታደርግ እንደነበር ጥያቄ የለውም፤ በዚህ የተነሳም ሌሎች ሳያገሏት አይቀሩም። በዚያ አስከፊ የሕይወቷ ዘመን ማንም እንደማይወዳትና እሷን መርዳት እንደማይችል ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ያሠቃዩአት የነበሩትን አጋንንት አስወጣላት። ከዚያ በኋላ ታማኝ ደቀ መዝሙሩ ሆነች። ኢየሱስ መግደላዊቷ ማርያም በአምላክ ዘንድ ውድ እንደሆነች እንድትገነዘብ በሌላም መንገድ ረድቷታል። እንዴት?

ሥዕሎች፦ 1. መግደላዊቷ ማርያም ሰወር ያለ ቦታ ላይ በጭንቀት ተውጣ ተንበርክካ ሳለ ኢየሱስ ይመለከታታል። 2. መግደላዊቷ ማርያም ከኢየሱስና ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርቱ ጋር አብራ በደስታ ስትጓዝ።

ኢየሱስ መግደላዊቷ ማርያም በይሖዋ ዘንድ ውድ እንደሆነች እንድትገነዘብ የረዳት እንዴት ነው? (አንቀጽ 10-11ን ተመልከት)


11. ኢየሱስ መግደላዊቷ ማርያም በይሖዋ ዘንድ ውድ እንደሆነች እንድታውቅ የረዳት እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

11 ኢየሱስ ለስብከት በሚዘዋወርባቸው ቦታዎች መግደላዊቷ ማርያም አብራው እንድትጓዝ ግብዣ አቅርቦላታል።b በመሆኑም ኢየሱስ ሌሎችን ሲያስተምር የመስማት አጋጣሚ አግኝታለች። በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞት በተነሳ ቀን ተገልጦላታል። በዚያ ቀን ካነጋገራቸው የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዷ እሷ ነች። እንዲያውም ኢየሱስ እሱ ከሞት መነሳቱን ለሐዋርያቱ እንድትናገር ኃላፊነት ሰጥቷታል። በእርግጥም ይሖዋ ውድ አድርጎ እንደሚመለከታት የሚያሳይ ብዙ ማስረጃ አግኝታለች!—ዮሐ. 20:11-18

12. ሊዲያ በአስተዳደጓ ምክንያት ምን ይሰማት ነበር?

12 ልክ እንደ መግደላዊቷ ማርያም በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች ማንም እንደማይወዳቸው ይሰማቸዋል። በስፔን የምትኖር ሊዲያ የተባለች እህት እናቷ እሷን አርግዛ ሳለ ውርጃ ለመፈጸም ታስብ እንደነበር ተናግራለች። ሊዲያ ሕፃን ልጅ እያለች እናቷ ትሰድባት እንዲሁም ችላ ትላት እንደነበር ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወቴ የምፈልገው ነገር በሰዎች ዘንድ መወደድና ተቀባይነት ማግኘት ነበር። ሆኖም እናቴ መጥፎ ሰው እንደሆንኩ ስላሳመነችኝ እንዲህ ያለው ፍቅር ይገባኛል ብዬ አላስብም ነበር።”

13. ሊዲያ በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆነች እንድትገነዘብ የረዳት ምንድን ነው?

13 ሊዲያ እውነትን ከተማረች በኋላ ጸሎት፣ የግል ጥናት እንዲሁም ከእምነት አጋሮቿ ያገኘችው ማበረታቻና ተግባራዊ ድጋፍ በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆነች እንድትገነዘብ አስችሏታል። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ምን ያህል እንደሚወደኝ ብዙ ጊዜ ይነግረኛል። ያሉኝን መልካም ባሕርያት በተደጋጋሚ እያነሳ ያስታውሰኛል። ሌሎች ውድ ጓደኞቼም እንዲህ ያደርጉልኛል።” አንተስ በይሖዋ ዓይን ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንዲገነዘብ ልትረዳው የምትፈልገው ሰው አለ?

ይሖዋ በሚያየን መንገድ ራሳችንን ማየት የምንችለው እንዴት ነው?

14. አንደኛ ሳሙኤል 16:7 ይሖዋ ሰዎችን ስለሚያይበት መንገድ ምን ያስተምረናል? (“ይሖዋ ሕዝቦቹን ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

14 ይሖዋ የሚያይህ ዓለም በሚያይህ መንገድ እንዳልሆነ አስታውስ። (1 ሳሙኤል 16:7ን አንብብ።) በእሱ ዘንድ ያለህን ዋጋ የሚመዝነው በቁመናህ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ባለህ ቦታ ወይም በትምህርት ደረጃህ ላይ ተመሥርቶ አይደለም። (ኢሳ. 55:8, 9) ስለዚህ ዋጋማነትህን ለመለካት የዓለምን መሥፈርቶች ሳይሆን የይሖዋን መሥፈርቶች ተጠቀም። አልፎ አልፎ የዋጋ ቢስነት ስሜት ቢሰማቸውም ይሖዋ ከፍ አድርጎ ስለተመለከታቸው ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ማንበብ ትችላለህ፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ኤልያስ፣ ናኦሚ እና ሐና ይገኙበታል። ይሖዋ በእርግጥ እንደሚወድህና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ ያረጋገጡልህን በሕይወትህ ያጋጠሙህ ነገሮች መጻፍም ትችላለህ። በተጨማሪም በይሖዋ ዘንድ ስላለን ዋጋ የሚገልጹ ጽሑፎችን መመልከት ትችላለህ።c

ይሖዋ ሕዝቦቹን ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው ከእንስሳት ፍጹም የተለዩ አድርጎ ነው። ከእሱ ጋር ዝምድና የመመሥረትና ወዳጆቹ የመሆን ችሎታ ሰጥቶናል። (ዘፍ. 1:27፤ መዝ. 8:5፤ 25:14፤ ኢሳ. 41:8) ይህ እውነታ ብቻ እንኳ ለራሳችን ጥሩ ግምት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው። ይሁንና ለራሳችን ጥሩ ግምት እንዲኖረን የሚያስችለን ሌላም ይበልጥ አሳማኝ የሆነ ምክንያት አለ። ወደ ይሖዋ ከቀረብን፣ ራሳችንን ለእሱ ከወሰንንና እሱን ከታዘዝነው በአምላካችንና በፈጣሪያችን ዘንድ ይበልጥ ውድ እንሆናለን።—ኢሳ. 49:15

15. ይሖዋ ዳንኤልን ‘እጅግ የተወደደ’ አድርጎ የተመለከተው ለምንድን ነው? (ዳንኤል 9:23)

15 ታማኝነትህ በይሖዋ ዘንድ ውድ እንደሚያደርግህ አትዘንጋ። ነቢዩ ዳንኤል በአንድ ወቅት በጣም ተዳክሞና ተስፋ ቆርጦ ነበር፤ ምናልባትም ይህ የሆነው በ90ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ እያለ ሊሆን ይችላል። (ዳን. 9:20, 21) ታዲያ ይሖዋ ያበረታታው እንዴት ነው? አምላክ መልአኩን ገብርኤልን ልኮ ዳንኤል ‘እጅግ የተወደደ ሰው’ እንደሆነና ጸሎቱ እንደተሰማ ነግሮታል። (ዳንኤል 9:23ን አንብብ።) ዳንኤልን በአምላክ ፊት በጣም ውድ ያደረገው ምንድን ነው? በዋነኝነት ለጽድቅ ያለው ፍቅርና ታማኝነቱ ነው። (ሕዝ. 14:14) ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ይህ ዘገባ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው እኛን ለማጽናናት ሲል ነው። (ሮም 15:4) ይሖዋ የአንተንም ጸሎት ይሰማል። ለጽድቅ ያለህን ፍቅርና ለእሱ በታማኝነት የምታቀርበውን አገልግሎትም ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—ሚክ. 6:8 ግርጌዎች፤ ዕብ. 6:10

16. ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባት አድርገህ ለመመልከት ምን ይረዳሃል?

16 ይሖዋን እንደሚወድህ አባትህ አድርገህ ተመልከተው። ይሖዋ ሊረዳህ ይፈልጋል እንጂ በአንተ ላይ ስህተት አይፈላልግም። (መዝ. 130:3፤ ማቴ. 7:11፤ ሉቃስ 12:6, 7) የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች በዚህ ላይ ማሰላሰላቸው ረድቷቸዋል። በስፔን የምትኖረውን ሚሼል የተባለች እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ባለቤቷ ለበርካታ ዓመታት ነጋ ጠባ ይሰድባት ስለነበር እንደማትወደድና ዋጋ ቢስ እንደሆነች ይሰማት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የዋጋ ቢስነት ስሜት ሲሰማኝ ይሖዋ በክንዶቹ ተሸክሞ ፍቅር እንደሚያሳየኝና ጥበቃ እንደሚያደርግልኝ ለማሰብ እሞክራለሁ።” (መዝ. 28:9) በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ሎረን የተባለች እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ በፍቅር ማሰሪያ ወደ ራሱ ከሳበኝ፣ እነዚህን ሁሉ ዓመታት አጠገቡ ጠብቆ ካቆየኝ እንዲሁም ሌሎችን ለማስተማር ጭምር ከተጠቀመብኝ በእርግጥም ዋጋ እንዳለኝና ጠቃሚ እንደሆንኩ አድርጎ እንደሚመለከተኝ ጥያቄ የለውም።”—ሆሴዕ 11:4

17. የይሖዋ ሞገስ እንዳለህ እርግጠኛ ለመሆን ምን ሊረዳህ ይችላል? (መዝሙር 5:12) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 የይሖዋ ሞገስ እንዳለህ ተማመን። (መዝሙር 5:12ን አንብብ።) ዳዊት የይሖዋን ሞገስ ጻድቃንን ከሚከልል “ትልቅ ጋሻ” ጋር አመሳስሎታል። የይሖዋ ሞገስና ድጋፍ ጥበቃ እንደሚያደርግልህ ማወቅህ በዋጋ ቢስነት ስሜት ከመዋጥ ይጠብቅሃል። ታዲያ የይሖዋ ሞገስ እንዳለህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? እስካሁን እንደተመለከትነው ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ይህን ማረጋገጫ ሰጥቶሃል። በተጨማሪም የጉባኤ ሽማግሌዎችን፣ የቅርብ ጓደኞችህን እንዲሁም ሌሎችን በመጠቀም በእሱ ዓይን ውድ እንደሆንክ እንድታስታውስ ያደርጋል። እንዲህ ላሉት ማበረታቻዎች ምን ዓይነት ምላሽ ልትሰጥ ይገባል?

አንዲት እህት ከሌላ እህት ጋር አብራ ለማገልገል በፈገግታ ከስብሰባ አዳራሽ ስትወጣ፤ አብራት ያለችው እህት አቅፋታለች።

የይሖዋ ሞገስ እንዳለን ማወቃችን የዋጋ ቢስነት ስሜትን ለማስወገድ ይረዳናል (አንቀጽ 17ን ተመልከት)


18. ሌሎች ሲያመሰግኑህ ምስጋናቸውን ከልብህ መቀበል የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

18 የሚያውቁህና የሚወዱህ ሰዎች የሚሰጡህን ልባዊ ምስጋና እንደማይገባህ በመቁጠር በቸልታ አትለፈው። ይሖዋ የእሱ ሞገስ እንዳለህ እንድትገነዘብ ለመርዳት እየተጠቀመባቸው ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሚሼል እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች በደግነት ተነሳስተው የሚናገሯቸውን ቃላት ከልቤ መቀበል እንዳለብኝ ቀስ በቀስ እየተማርኩ ነው። አሁንም ቢሆን ያታግለኛል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚፈልገው እንዲህ እንዳደርግ እንደሆነ አውቃለሁ።” ሚሼል ሽማግሌዎች ካደረጉላት ፍቅራዊ እርዳታ ተጠቅማለች። በአሁኑ ወቅት አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው፤ እንዲሁም የቤቴል የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኛ ናት።

19. በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆንክ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ በሰማዩ አባታችን ዘንድ የላቀ ቦታ እንዳለን በደግነት አስታውሶናል። (ሉቃስ 12:24) በመሆኑም ይሖዋ ውድ አድርጎ እንደሚመለከተን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህንን ፈጽሞ መርሳት አይኖርብንም! እንዲሁም ሌሎች በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ መርዳታችንን እንቀጥል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ኢየሱስ ሰዎች በይሖዋ ዓይን ውድ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ የረዳቸው እንዴት ነው?

  • ኢየሱስ ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት የረዳት እንዴት ነው?

  • ራሳችንን ይሖዋ በሚያየን መንገድ ለመመልከት ምን ሊረዳን ይችላል?

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b መግደላዊቷ ማርያም ከኢየሱስ ጋር ይጓዙ ከነበሩት ሴቶች መካከል አንዷ ናት። እነዚህ ሴቶች የገዛ ንብረታቸውን ተጠቅመው ኢየሱስንና ሐዋርያቱን አገልግለዋቸዋል።—ማቴ. 27:55, 56፤ ሉቃስ 8:1-3

c ለምሳሌ ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 24ን ተመልከት፤ እንዲሁም ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት በተባለው መጽሐፍ ላይ “ጥርጣሬ፤ በራስ አለመተማመን” በሚለው ርዕስ ሥር የሚገኙትን ጥቅሶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንብብ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ