‘የመንፈስን አንድነት ጠብቁ’
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል፦ “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።”—ኤፌ. 4:2, 3
በመካከላችን ያለው አንድነት ‘የመንፈስ አንድነት’ ተብሎ ተጠርቷል። ይህም ሲባል ይህ አንድነት የሚመነጨው በሥራ ላይ ካለው የአምላክ ኃይል ነው ማለት ነው። ሆኖም ጳውሎስ እንደገለጸው ይህ አንድነት ሊጠበቅ የሚገባው ነገር ነው። ይህ የማን ኃላፊነት ነው? እያንዳንዱ ክርስቲያን “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል።
ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ ሰው አዲስ መኪና ሰጠህ እንበል። መኪናውን መንከባከብ የማን ኃላፊነት ነው? መልሱ ግልጽ ነው። መኪናውን በአግባቡ ባለመያዝህ ምክንያት ቢበላሽ ስጦታውን የሰጠህን ሰው ተጠያቂ ማድረግ አትችልም።
በተመሳሳይም ክርስቲያናዊ አንድነታችን ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ቢሆንም እያንዳንዳችን ይህን አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን። ከአንድ ወንድም ወይም ከአንዲት እህት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ከሌለን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ለጉዳዩ እልባት በመስጠት የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ የበኩሌን አስተዋጽኦ እያደረግኩ ነው?’
አንድነትን ለመጠበቅ “ልባዊ ጥረት አድርጉ”
ጳውሎስ እንደገለጸው የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። በተለይ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቅር ካሰኙን ይህ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንድነትን ለመጠበቅ የግድ ጉዳዩን አንስተን ግለሰቡን ማነጋገር ይኖርብናል? እንዲህ ማድረግ ላይጠበቅብን ይችላል። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ጉዳዩን ማንሳቴ አንድነት ለማስፈን ያስችላል ወይስ ችግሩን ያባብሰዋል?’ አንዳንድ ጊዜ ጉዳዩን መተው ወይም ይቅር ማለት የጥበብ አካሄድ ነው።—ምሳሌ 19:11፤ ማር. 11:25
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ጉዳዩን ማንሳቴ አንድነት ለማስፈን ያስችላል ወይስ ችግሩን ያባብሰዋል?’
ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 4:2) አንድ ማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህ አገላለጽ “እንደ ማንነታቸው ተቀበሏቸው” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ገልጿል። ይህም ሲባል የእምነት አጋሮቻችን ልክ እንደ እኛ ኃጢአተኛ እንደሆኑ አምነን እንቀበላለን ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ “አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ጥረት እናደርጋለን። (ኤፌ. 4:23, 24) ሆኖም ማናችንም አዲሱን ስብዕና ፍጹም በሆነ መንገድ መልበስ አንችልም። (ሮም 3:23) ይህን እውነታ አምነን ከተቀበልን እርስ በርሳችን መቻቻል፣ ይቅር መባባልና ‘የመንፈስን አንድነት መጠበቅ’ ቀላል ይሆንልናል።
ከሌሎች ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ስንፈታ ወይም ጉዳዩን ስንተወው ‘አንድ ላይ የሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ’ በጉባኤያችን ውስጥ ይሰፍናል። በኤፌሶን 4:3 ላይ ‘አንድ ላይ የሚያስተሳስረው ማሰሪያ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቆላስይስ 2:19 ላይ “ጅማቶች” ተብሎ ተተርጉሟል። ጅማቶች አንድን አጥንት ከሌላ አጥንት ጋር የሚያያይዙ ጠንካራ ሕብረ ሕዋሳት ናቸው። በተመሳሳይም ሰላምና ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር በመካከላችን አለመግባባት ቢፈጠርም ከእነሱ ጋር ተቀራርበን እንድንኖር ይረዳናል።
እንግዲያው አንድ የእምነት አጋርህ ቅር ሲያሰኝህ፣ ሲያናድድህ ወይም ሲያበሳጭህ በድክመቶቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ በርኅራኄ ዓይን ተመልከተው። (ቆላ. 3:12) ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን አንተም ሌሎችን ቅር ያሰኘህበት ጊዜ ይኖራል። ይህን ማስታወስህ “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” የበኩልህን አስተዋጽኦ እንድታደርግ ይረዳሃል።