የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ታኅሣሥ ገጽ 14-19
  • ይሖዋን በትሕትናው ምሰሉት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን በትሕትናው ምሰሉት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ ነው
  • ይሖዋ ምክንያታዊ ነው
  • ይሖዋ ታጋሽ ነው
  • ይሖዋ ምስኪኖችን በአክብሮት ይይዛቸዋል
  • የይሖዋንና የኢየሱስን አስተሳሰብ ኮርጁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ አጣጥም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ታኅሣሥ ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 50

መዝሙር 48 በየዕለቱ ከይሖዋ ጋር መሄድ

ይሖዋን በትሕትናው ምሰሉት

“የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።”—ኤፌ. 5:1

ዓላማ

የይሖዋን ትሕትና መኮረጅ የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመለከታለን።

1. የይሖዋ ትሕትና አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለሥልጣናትን ስታስብ ትሑቶች እንደሆኑ ይሰማሃል? እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። ሆኖም ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ ትሑት ነው። (መዝ. 113:5-8) በትሕትና ረገድ ይሖዋን የሚወዳደር የለም፤ እሱ ሌሎችን በንቀት ዓይን አይመለከትም። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የይሖዋ ትሕትና የተንጸባረቀባቸውን አራት ግሩም ባሕርያቱን እንመለከታለን። በተጨማሪም ኢየሱስ የአባቱን ትሕትና የኮረጀው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። እነዚህን ነገሮች መመርመራችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብና ትሕትናውን በላቀ ሁኔታ እንድንኮርጅ ይረዳናል።

ይሖዋ በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ ነው

2. መዝሙር 62:8 ስለ ይሖዋ ምን ይናገራል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

2 ብዙውን ጊዜ፣ ኩራተኛ ሰዎችን መቅረብ ከባድ ነው። ትዕቢተኛ ስለሆኑ ሌሎችን በአክብሮት አይዙም፤ በመሆኑም ሰዎች ይርቋቸዋል። ይሖዋ ግን ከእነዚህ ሰዎች ፍጹም የተለየ ነው! የሰማዩ አባታችን ትሑት በመሆኑ ወደ እሱ እንድንቀርብና የሚያሳስበንን ነገር እንድንነግረው ጋብዞናል። (መዝሙር 62:8ን አንብብ።) አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹ የሚያሳስባቸውን ነገር ለመስማት እንደሚፈልግ ሁሉ ይሖዋም የአገልጋዮቹን ጸሎት በደስታ ያዳምጣል። እንዲያውም እንዲህ ያሉ ጸሎቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው እንዲገኙ አድርጓል። ይህም ይሖዋ ጸሎታችንን ለመስማት ምን ያህል እንደሚጓጓ ያሳያል። (ኢያሱ 10:12-14፤ 1 ሳሙ. 1:10-18) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆንን ቢሰማንስ?

አንድ ትንሽ ልጅ በአሻንጉሊት አውሮፕላኑ ሲጫወት የአበባ ማስቀመጫውን ተሳስቶ እንደሰበረው ሲናገር አባቱ በትዕግሥት ያዳምጠዋል።

አንድ ልጅ ሲጫወት የአበባ ማስቀመጫ ሰብሯል፤ አባቱ የይሖዋን ትሕትና በመኮረጅ እያዳመጠው ነው (አንቀጽ 2ን ተመልከት)


3. ይሖዋ አዘውትረህ ወደ እሱ በጸሎት እንድትቀርብ እንደሚፈልግ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

3 የይሖዋ ፍቅር የሚገባን ሰዎች እንዳልሆንን ቢሰማንም እንኳ ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ ይሖዋን ከሩኅሩኅ አባት ጋር አመሳስሎታል። ልጁ ንስሐ ከገባ በኋላም በድጋሚ ከቤተሰቡ ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ተሰምቶት ነበር። ይሁንና ልጁ ወደ ቤት ሲመለስ አባትየው ምን ተሰማው? ኢየሱስ እንደተናገረው አባትየው ልጁን ገና ከሩቅ ሲመለከተው “እየሮጠ [ሄዶ] አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” (ሉቃስ 15:17-20) ይሖዋ ልክ እንደዚህ አባት ነው። ልባቸው የተሰበረና የበደለኝነት ስሜት ወይም ጭንቀት ያደቀቃቸው አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት እንደሰማ ሙሉ ትኩረቱን እንዲሰጣቸው ትሕትናው ያነሳሳዋል። (ሰቆ. 3:19, 20) ይሖዋ በርኅራኄ ተነሳስቶ እነሱን ለማጽናናት በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደ እነሱ ይሮጣል፤ እንደሚወዳቸውም ያረጋግጥላቸዋል። (ኢሳ. 57:15) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ወደ እኛ “የሚሮጠው” እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ እንዲህ የሚያደርገው በሽማግሌዎች፣ አማኝ በሆኑ የቤተሰባችን አባላት እንዲሁም በሌሎች የእምነት አጋሮቻችን አማካኝነት ነው። (ያዕ. 5:14, 15) ይሖዋ እንዲህ ያለውን እርዳታ የሚያደርግልን ወደ እሱ እንድንቀርብ ስለሚፈልግ ነው።

4. ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ልክ እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ትሑት ነው። በዚህም ምክንያት፣ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሰዎች በቀላሉ ይቀርቡት ነበር። ወደ እሱ ቀርበው ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ነፃነት ይሰማቸው ነበር። (ማር. 4:10, 11) እንዲሁም በአንድ ጉዳይ ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ሲጋብዛቸው እውነተኛ ስሜታቸውን ይነግሩት ነበር። (ማቴ. 16:13-16) ስህተት በሚሠሩበት ጊዜም በፍርሃት አይንቀጠቀጡም ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ደግ፣ መሐሪና ታጋሽ እንደሆነ ያውቃሉ። (ማቴ. 17:24-27) ኢየሱስ አባቱን በሚገባ በመምሰሉ የተነሳ ተከታዮቹ እሱን በማየት ይሖዋን የበለጠ ማወቅ ችለዋል። (ዮሐ. 14:9) ይሖዋ በዘመኑ ከነበሩት ጨካኝ፣ ኩሩና አሳቢነት የጎደላቸው የሃይማኖት መሪዎች በተለየ ትሑትና በቀላሉ የሚቀረብ እንደሆነ ተገንዝበዋል።

5. ትሕትና በቀላሉ የምንቀረብ ለመሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

5 እኛስ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ትሕትናን ማዳበራችን በቀላሉ የምንቀረብ እንድንሆን ያስችለናል። ትሕትና እንደ ምቀኝነት፣ ኩራትና ቂመኝነት ካሉ ባሕርያት እንድንርቅ ይረዳናል፤ እነዚህ ባሕርያት ሌሎች እንዲርቁን ያደርጋሉ። በአንጻሩ ግን ትሕትና ደግ፣ ትዕግሥተኛና ይቅር ባይ እንድንሆን ይረዳናል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ሌሎች ወደ እኛ እንዲቀርቡ ያደርጋሉ። (ቆላ. 3:12-14) በተለይ ሽማግሌዎች በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው፣ ወንድሞች እንዲቀርቧቸው መጀመሪያ ሊያገኟቸው ይገባል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ሳያስፈልግ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በስብሰባዎች ከመካፈል ይልቅ በአካል ለመገኘት ጥረት ያደርጋሉ። እንዲሁም ሁኔታቸው በፈቀደ መጠን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ከቤት ወደ ቤት ያገለግላሉ። ወንድሞችና እህቶች ከሽማግሌዎች ጋር ከተቀራረቡ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው እነሱን ማነጋገር ቀላል ይሆንላቸዋል።

ይሖዋ ምክንያታዊ ነው

6-7. ይሖዋ አገልጋዮቹን ሰምቶ ሐሳቡን እንደቀየረ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

6 ኩራተኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያታዊ አይደሉም። ይሖዋ ግን ከማንም የላቀ እውቀትና ችሎታ ቢኖረውም ትሑት ስለሆነ ምክንያታዊ ወይም እሺ ባይ ነው። የሙሴን እህት ሚርያምን የያዘበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እሷና አሮን የይሖዋ ወኪል በሆነው በሙሴ ላይ አጉረምርመው ነበር። በመሆኑም ሚርያም ለይሖዋ አክብሮት ሳታሳይ ቀርታለች ሊባል ይችላል። ይሖዋም ባደረገችው ነገር ተቆጥቶ በሥጋ ደዌ መታት። በዚህ ጊዜ አሮን ሙሴን ተማጸነላት፤ ሙሴ ደግሞ እህቱን እንዲፈውስለት ይሖዋን ጠየቀው። ታዲያ ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን አይቀይሩም። ይሖዋ ግን ትሑት ስለሆነ ሐሳቡን በመቀየር ሚርያምን ፈውሷታል።—ዘኁ. 12:1-15

7 ይሖዋ ከንጉሥ ሕዝቅያስ ሁኔታ ጋር በተያያዘም ትሕትና አሳይቷል። ይሖዋ በነቢዩ አማካኝነት ሕዝቅያስን እንደሚሞት ነገረው። በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ይሖዋ እንዲፈውሰው እንባውን እያፈሰሰ ተማጸነ። በምላሹም ይሖዋ በሕዝቅያስ ሕይወት ላይ 15 ዓመት በመጨመር ምሕረት አሳየው። (2 ነገ. 20:1, 5, 6) በእርግጥም ይሖዋ ትሑት ስለሆነ ሩኅሩኅና እሺ ባይ ነው።

8. ኢየሱስ ምክንያታዊ እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ። (ማርቆስ 3:1-6)

8 ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሌሎችን ከመርዳት ወደኋላ አላለም። ለምሳሌ ርኅራኄ የለሽ የሆኑት ጠላቶቹ ቢቃወሙትም በሰንበት ቀን ሰዎችን ፈውሷል። (ማርቆስ 3:1-6ን አንብብ።) ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ከሆነ በኋላም ጉባኤውን በሚይዝበት መንገድ ምክንያታዊ ነው። ለምሳሌ በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ወቅት አካሄዱን የሚያስተካክልበት አጋጣሚ በመስጠት ትዕግሥት ያሳየዋል።—ራእይ 2:2-5

9. ምክንያታዊነትን ማዳበርና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 እኛስ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ያዕ. 3:17) ለምሳሌ ምክንያታዊ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ባያቀብጧቸውም እንኳ ከአቅማቸው በላይ አይጠብቁባቸውም። በዘፍጥረት 33:12-14 ላይ ያለው ዘገባ እንደሚያሳየው ያዕቆብ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። በተጨማሪም ትሑትና ምክንያታዊ የሆኑ ወላጆች አንዱን ልጃቸውን ከሌላው ጋር አያወዳድሩም። የጉባኤ ሽማግሌዎችም ምክንያታዊ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ የሽማግሌዎች አካል በአብላጫ ድምፅ ባጸደቀው ውሳኔ በመስማማት ነው። (1 ጢሞ. 3:2, 3) እንዲሁም ሁላችንም፣ የእኛ አመለካከት የተለየ ቢሆንም እንኳ የሌሎችን አመለካከት ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ሮም 14:1) በእርግጥም በጉባኤ ውስጥ ያለ ሁሉም ሰው ‘ምክንያታዊነቱ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን’ ጥረት ማድረግ አለበት።—ፊልጵ. 4:5

ሥዕሎች፦ አንድ ወንድም ከትናንሽ ልጆቹ ጋር በደስታ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል። 1. ልጁ ለአንድ ሰው “ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተባለውን ብሮሹር ሲያበረክት ፈገግ ብሎ ያየዋል። 2. በኋላ ላይ ሴት ልጁ ለአንዲት ሴት የjw.org የአድራሻ ካርድ ስትሰጥ በፈገግታ ያያታል።

አንድ አባት በአገልግሎት ላይ ከልጆቹ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው (አንቀጽ 9ን ተመልከት)


ይሖዋ ታጋሽ ነው

10. ይሖዋ ትዕግሥት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

10 ኩሩ ሰዎች መጠበቅ እንደማይወዱ አስተውለህ ሊሆን ይችላል። ኩራት ታጋሽ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። ይሖዋ ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! እሱ ከማንም ይበልጥ ታጋሽ ነው። ለምሳሌ በኖኅ ዘመን ይሖዋ ክፉዎችን ከማጥፋቱ በፊት 120 ዓመት እንደሚታገሥ ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 6:3) በመሆኑም ኖኅ ልጆቹን ለማሳደግና በቤተሰቡ እርዳታ መርከቡን ለመሥራት የሚያስችል ጊዜ አግኝቷል። በኋላም የይሖዋ ወኪል የሆነ መልአክ፣ አብርሃም የሰዶምንና የገሞራን ጥፋት አስመልክቶ ጥያቄዎችን ሲጠይቀው በትዕግሥት አዳምጦታል። ኩራተኛ ሰው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመው ‘አንተ እኔን የምትጠይቀኝ ማን ሆነህ ነው?’ ብሎ ሊመልስ ይችላል። ሆኖም ያ መልአክ የይሖዋን ምሳሌ በመከተል አብርሃምን በትዕግሥት ይዞታል።—ዘፍ. 18:20-33

11. በ2 ጴጥሮስ 3:9 ላይ እንደተጠቀሰው ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ትዕግሥት እያሳየ ያለው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ በዛሬው ጊዜም ትዕግሥት እያሳየ ነው። መጨረሻውን ለማምጣት የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ እየጠበቀ ነው። ይሖዋ እየታገሠ ያለው ለምንድን ነው? “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።” (2 ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ።) ታዲያ የይሖዋ ትዕግሥት ውጤት አስገኝቷል? እንዴታ! ቅን ልብ ያላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ እሱ መቅረብ ችለዋል። ወደፊትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች እንዲህ እንደሚያደርጉ ተስፋ እናደርጋለን። ሆኖም የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ አለው። ይሖዋ ሰዎችን ቢወድም ልል አይደለም። ክፋት ለዘላለም እንዲቀጥል አይፈቅድም።—ዕን. 2:3

12. ኢየሱስ የይሖዋን ትዕግሥት የኮረጀው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ኢየሱስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የይሖዋን ትዕግሥት ኮርጇል። ኢየሱስ፣ ሰይጣን የይሖዋንም ሆነ የታማኝ ሰዎችን ስም ሲያጠፋ ተመልክቷል። (ዘፍ. 3:4, 5፤ ኢዮብ 1:11፤ ራእይ 12:10) በተጨማሪም በሰዎች ላይ ይህ ነው የማይባል መከራ ሲደርስ አይቷል። ኢየሱስ “የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ” ምንኛ ይጓጓ ይሆን! (1 ዮሐ. 3:8) ኢየሱስ ይህን ለማድረግ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ የረዳው ምንድን ነው? አንዱ ነገር ትሑት መሆኑ ነው። ጊዜውን የመወሰን ሥልጣን ያለው ይሖዋ እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል።—ሥራ 1:7

13. ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው? ለምንስ?

13 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለሐዋርያቱ ትዕግሥት አሳይቷቸዋል። ለምሳሌ ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በተደጋጋሚ ቢከራከሩም ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። ከዚህ ይልቅ ለእነሱ ትዕግሥት ማሳየቱን ቀጥሏል። (ሉቃስ 9:46፤ 22:24-27) ውሎ አድሮ አስፈላጊውን ለውጥ እንደሚያደርጉ ተማምኖ ነበር። አንተስ በተደጋጋሚ አንድ ዓይነት ስህተት ሠርተህ ታውቃለህ? ከሆነ፣ እንዲህ ያለ ትሑትና ታጋሽ ንጉሥ ስላለህ አመስጋኝ አይደለህም?

14. ትዕግሥት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

14 እኛስ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ስናዳብር በአስተሳሰባችንና በምግባራችን ይሖዋን ይበልጥ እንመስላለን። (1 ቆሮ. 2:16) ታዲያ የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? አቋራጭ መንገድ የለውም። የወንጌል ዘገባዎችን ማንበብ ይኖርብናል። ከዚያም ያነበብነው ታሪክ የኢየሱስን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቀው እንዴት እንደሆነ ጊዜ ወስደን ማሰላሰል አለብን። በተጨማሪም የኢየሱስን ትሕትናና ትዕግሥት ለመኮረጅ እንዲረዳን ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል። የክርስቶስን አስተሳሰብ ስናዳብር ለራሳችንም ሆነ ለእምነት አጋሮቻችን ይበልጥ ትዕግሥት በማሳየት ይሖዋን እየመሰልን እንሄዳለን።—ማቴ. 18:26-30, 35

ይሖዋ ምስኪኖችን በአክብሮት ይይዛቸዋል

15. በመዝሙር 138:6 ላይ በተገለጸው መሠረት ይሖዋ ምን አድርጓል?

15 መዝሙር 138:6ን አንብብ። ትሑት የሆኑ ሰዎች በጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እውቅና የተሰጣቸው መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! ባለፉት ዘመናት፣ አንዳንዶች ዝቅ አድርገው ቢመለከቷቸውም ይሖዋ ያከበራቸውን ሰዎች ምሳሌ እንመልከት። አንዳንዶቹ ወደ አእምሯችን ቶሎ ላይመጡልን ይችላሉ፤ ሆኖም ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቧል። ለምሳሌ በጥንት ዘመን የኖረች ዲቦራ የተባለች ሞግዚት ነበረች። ይሖዋ ሙሴን ስለ እሷ እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል። ዲቦራ በይስሐቅና በያዕቆብ ቤት ውስጥ በድምሩ ለ125 ዓመት ያህል በታማኝነት አገልግላለች። ስለዚህች ታማኝ ሴት የምናውቀው ነገር የተወሰነ ቢሆንም ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበረች ይሖዋ በቃሉ ውስጥ እንዲጻፍ አድርጓል። (ዘፍ. 24:59፤ 35:8 ግርጌ) ከዘመናት በኋላ ይሖዋ እረኛ የነበረውን ዳዊትን የእስራኤል ብሔር ንጉሥ በማድረግ ከፍ ከፍ አድርጎታል። (2 ሳሙ. 22:1, 36) ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ አምላክ ለተወሰኑ እረኞች መላእክት ልኮ መሲሑ በቤተልሔም መወለዱን በማብሰር አክብሯቸዋል፤ ይህን ምሥራች የሰሙት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እነሱ ነበሩ። (ሉቃስ 2:8-11) በተጨማሪም ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደሱ በወሰዱት ጊዜ ይሖዋ ለአረጋውያኑ ለስምዖንና ለሐና ልጁን የማየት መብት በመስጠት አክብሯቸዋል። (ሉቃስ 2:25-30, 36-38) በእርግጥም “ይሖዋ ከፍ ያለ ቢሆንም ትሑት የሆነውን ሰው ይመለከታል።”

16. ኢየሱስ ሌሎችን በሚይዝበት መንገድ አባቱን የመሰለው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ልክ እንደ አባቱ ኢየሱስም ምስኪን የሆኑ ሰዎችን በአክብሮት ይይዛቸው ነበር። ‘ላልተማሩና ተራ ለሆኑ ሰዎች’ ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯል። (ሥራ 4:13፤ ማቴ. 11:25) በተጨማሪም ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን ፈውሷል፤ እነሱን የፈወሰበት መንገድም ለእነሱ ክብር እንዳለው የሚያሳይ ነው። (ሉቃስ 5:13) ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን ሥራ ሠርቷል። (ዮሐ. 13:5) ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት ደግሞ ያኔ የነበሩትንም ሆነ ወደፊት የሚመጡትን ትሑት ተከታዮቹን በሙሉ ከሁሉ የላቀ ሥራ በመስጠት አክብሯቸዋል፤ ይህም ሥራ ሌሎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መርዳት ነው።—ማቴ. 28:19, 20

17. ሌሎችን እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 እኛስ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ሰዎች አስተዳደጋቸው፣ የቆዳ ቀለማቸው ወይም የትምህርት ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ሰው ምሥራቹን በመስበክ እንደምናከብራቸው እናሳያለን። በተጨማሪም ያለን ችሎታ ወይም ኃላፊነት ምንም ይሁን ምን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን በማሰብ እናከብራቸዋለን። (ፊልጵ. 2:3) ይሖዋ በእነዚህም ሆነ በሌሎች መንገዶች በትሕትና ሌሎችን ለማክበር ‘ቀዳሚ ስንሆን’ ይደሰታል።—ሮም 12:10፤ ሶፎ. 3:12

ሁለት እህቶች ማረሚያ ቤት ውስጥ ለታሰረች ሴት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመሩ።

ምሥራቹን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች በመስበክ የይሖዋን ትሕትና መኮረጅ እንችላለን (አንቀጽ 17ን ተመልከት)a


18. የይሖዋን ትሕትና መኮረጅ የምትፈልገው ለምንድን ነው?

18 አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ትሕትና ለመኮረጅ ጥረት ስናደርግ በቀላሉ የምንቀረብ፣ ምክንያታዊና ታጋሽ እንሆናለን። እንዲሁም ልክ እንደ ይሖዋ ሌሎችን በአክብሮት እንይዛለን። እያንዳንዳችን ትሑት ወደሆነው አምላካችን ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት ስናደርግ በእሱ ዓይን ይበልጥ ውድ እንሆናለን።—ኢሳ. 43:4

ትሕትና የሚረዳህ እንዴት ነው?

  • በቀላሉ የምትቀረብ ለመሆን

  • ምክንያታዊ ለመሆን

  • ታጋሽ ለመሆን

መዝሙር 159 ለይሖዋ ክብር ስጡ

a የሥዕሉ መግለጫ፦ እህቶች እስረኞችን በማስተማር የይሖዋን ትሕትና ሲኮርጁ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ