የሚደረግልህ የጤና ምርመራ
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ግለሰቦች ስለሚያደርጉት ሕክምናና ምርምራ ሐሳብ አያቀርብም ወይም ውሳኔ አያስተላልፍም። ይሁን አንጂ አንዳንድ ድርጊቶች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብርሃን ሲታዩ አጠያያቂ ከሆኑ በእነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ይደረጋል። ከዚያም እያንዳንዱ ግለሰብ ሁኔታውን አመዛዝኖ ምን አንደሚያደርግ ሊወስን ይችላል።
ውድ ወንድሞች፦ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላችሁን ሐሳብ ባውቅ ደስ ይለኛል። የጤና ችግር ያለባቸውን ሕመምተኞች የምትመረምር አንዲት ሴት ጥሩ ምርመራ የምታደርግ ትመስላለች፤ ሆኖም የምትጠቀምበት ዘዴ አጠራጠረኝ። . . . ምርመራ አድርጋ በሽታው ይህ ነው ትላለች። ከዚያም ምን ዓይነት መድኃኒት ወይም ምን ያህል መጠን ማዘዝ እንደሚገባት ለማወቅ በበሽተኛው እጢ አጠገብ ባለ ቆዳ ወይም በአንድ የአካል ክፍል ላይ አንድ ብልቃጥ ታደርጋለች። በሽተኛው ክንዱን ወደ ላይ እንዲያነሣ ታደርግና ወደ ታች ለመጎተት ትሞክራለች። የመድኃኒቱ ዓይነት ወይም መጠን የበሽተኛውን ክንድ ወደ ታች ለመጎተት በሚያስፈልጋት ኃይል መጠን ይወሰናል። ንድፈ ሐሳቡ ኤሌክትሮኖች ከመድኃኒቱ ተነሥተው በብልቃጡ የብረት ክዳን በኩል ወደ አንድ የአካል ክፍል በመዝለቅ ያንን ክፍል ያጠነክሩታል የሚል ነው። ይህ በበትር አማካኝነት ውኃ ያለበትን መሬት ለማወቅ እንደሚደረግ ጥንቆላ ያለ ነገር ይሆን?
ይህ ደብዳቤ አንዳንዶች የሚያስፈልጋቸውን የአመጋገብ ዘዴ ለመወሰን፣ ስሜታዊ ጉዳዮችን ለማመዛዘን፣ ትውስታዎችን ለመገምገምና በዕለታዊ ሕይወት የሚያጋጥሙ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚጠቀሙበትን ልማድ አስመልክቶ ከኦሪገን ዩ ኤስ ኤ የተላከ ነበር። ልማዱ የቱንም ያህል ቢስፋፋም የደብዳቤው ጸሐፊ ጥርጣሬ ትክክል ነውን?
ለጤንነትህ ምንም ነገር ትከፍላለህን?
ከጥንት ጀምሮ ሰዎች ለምን እንደሚታመሙና እንዴት ሊድኑ እንደሚችል ለመረዳት ሲጥሩ ኖረዋል። እስራኤላውያን ኃጢአተኛ መሆናቸውን በማወቃቸው ተጠቅመዋል። ብዙ በሽታዎች እንዳይዟቸውና እንዳያስተላለፉ የሚረዱ ሕጎችም አምላክ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 5:2፤ 11:39, 40፤ 13:1–4፤ 15:4–12፤ ዘዳግም 23:12–14) ይህም ሆኖ የአምላክ ሕዝቦች በጊዜያቸው ከነበሩ ብቃት ካላቸው ሐኪሞች እርዳታ ፈልገዋል።—ኢሳይያስ 1:6፤ 38:31፤ ማርቆስ 2:17፤ 5:25, 26፤ ሉቃስ 10:34፤ ቆላስይስ 4:14
ይህ በጥንት ባቢሎንና ግብፅ የነበሩት ሕዝቦች ከሚያደርጉት ነገር እንዴት የተለየ ነበር! የእነሱ “ዶክተሮች” ተፈጥሮያዊ ከሆኑ ነገሮች የተቀመሙ አንዳንድ መድኃኒቶች ነበሯቸው፤ ሆኖም ብዙዎቹ የእነሱ “ሕክምናዎች” በአሁኑ ወቅት እንደ ማጭበርበሪያ ተደርገው ይታያሉ። በጥንት ሥዕላዊ አጻጻፍ የተጻፈ አንድ የግብፃውያን ጽሑፍ አንድ ሐኪም ከአሳማ ዓይኖች፣ ከአንቲሞኒ፣ ከቀይ ማቅለሚያ ንጥረ ነገርና ከማር በተቀመመ መድኃኒት እውርን እንዳከመ ይናገራል። ይህ ያልተጣሩ ነገሮች ቅልቅል በሕመምተኛው ጆሮ ውስጥ ተጨመረ! በድሮ ዘመን ጥቅም አግኝተንበታል ይሉ የነበሩ ሰዎች ይህ ዘዴ “በእርግጥም ግሩም” እንደነበረ ይናገራሉ። እንግዳነቱ ወይም ምሥጢራዊነቱ ይበልጥ ማርኳቸው ይሆናል።
ባቢሎናውያንና ግብፃውያን ብዙውን ጊዜ መናፍስታዊ ኃይሎችን ይለምኑ ነበር።a ቄስና ሐኪም ሆኖ የሚያገለግለው ግለሰብ የሆነ ኃይል ከበሽተኛው ወደ ሌላ ፍጡር ተዛውሮ ለውጥ ያመጣል ብሎ በማመን በበግ አፍንጫ ላይ እንዲተነፍስ በሽተኛውን ይጠይቅ ነበር። በጉ ይታረዳል፤ ጉበቱ የበሽተኛውን ሕመምና የወደፊት ሁኔታ ያሳውቃል ይባላል።—ኢሳይያስ 47:1, 9–13፤ ሕዝቅኤል 21:21
እርግጥ በጥንትዋ እስራኤል ውስጥ የነበሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሐኪሞች በመናፍስታዊ ድርጊቶች አይጠቀሙም ነበር። አምላክ በጥበብ የሚከተለውን አዟቸው ነበር፦ “ምዋርተኛም፣ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ . . . ጠንቋይም፣ በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።” (ዘዳግም 18:10–12፤ ዘሌዋውያን 19:26፤ 20:27) ይኸው ትእዛዝ ዛሬ ባሉ የአምላክ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ ይሠራል። ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
በቅርብ ዓመታት ብዙ ሰዎች ትኩረታቸውን “አማራጭ” የምርመራ ቴክኒኮችና ሕክምናዎች ወደሚባሉት አዙረዋል። ይህ በመሠረቱ የግል ምርጫ ነው። (ማቴዎስ 7:1፤ ከሮሜ 14:3,4 ጋር አወዳድር።) እርግጥ ማንኛውም ክርስቲያን በአጠያያቂ የጤና ጉዳዮች በጣም ከመያዙ የተነሣ ብቸኛው ሕይወት ማዳኛ መንገድ አገልግሎት ሆኖ ሳለ እነዚህ ጉዳዮች አገልግሎትን እንዲጋርዱ ቢደረግ ያሳዝናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) መጽሐፍ ቅዱስ በአዲሱ ዓለም በቅጠላ ቅጠሎች፣ በተመጣጠኑ ምግቦች፣ ወይም በማንጻት ሥርዓቶች አማካይነት በሚደረግ ሕክምና በሽታ ተፈውሶ ፍጹም ጤንነት ይገኛል አይልም። በእርግጥ የተሟላ ፈውስ የሚገኘው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው።—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 22:1, 2
በነገሩ ውስጥ የሚገቡት የትኞቹ ኃይሎች ናቸው?
አንድ ክርስቲያን ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የጡንቻ ፍተሻ በተመለከተ የግል ውሳኔ ሲያደርግ ግምት ውስጥ ሊያስገባቸው የሚገቡት ነገሮች ምንድን ናቸው?
አንዳንድ የጡንቻዎች መፈተሻ ዘዴዎች የተለመደው ሕክምና ክፍል ናቸው፤ ስለ ተገቢነታቸውም የሚጠራጠሩ አይኖሩም። ለምሳሌ ያህል የሽባነት በሽታ ጡንቻዎችን ያላላል፤ ስለዚህ የሚደረገው ሕክምና ኪኒሲዮሎጂ የሚባለው “የጡንቻዎችና የእንቅስቃሴያቸው ጥናት” ይሆናል። እንደዚህ ዓይነቱ ኪኒሲዮሎጂ ጭንቅላታቸው ውስጥ ደም የፈሰሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት በሚሰጥ ሕክምናም ረገድ ይሠራበታል። አብዛኞቹ ሰዎች ይህ ዓይነቱን ምርመራና ሕክምና ይቀበላሉ።
በመክፈቻው ላይ በተጠቀሰው ደብዳቤ የተጠቆመው የጡንቻ ምርመራስ እንዴት ነው? ይህ ዓይነቱ “ኪኒሲዮሎጂ” የተወሰኑ ምግቦች፣ ቅጠላ ቅጠሎች ወይም ቪታሚኖች ሰውን ይጠቅሙ ወይም ይጎዱ እንደሆነ ለመመርመር ይሠራበታል። ብዙውን ጊዜ እንደሚደረገው ግለሰቡ ክንዱን ወደ ላይ ያነሳና መርማሪው የሰውዬውን የጡንቻ ብርታት ለመፈተሽ ወደ ታች ይጫነዋል። ከዚያም ምርመራው የሚደረግበት ሰው ምግብ ወይም ሌላ ነገር በአፉ ውስጥ፣ በሆዱ ወይም በእጁ ላይ ያስቀምጣል። ቀጥሎ የክንዱ ጡንቻዎች እንደገና ይሞከራሉ። ያ ዓይነት ምግብ ካስፈለገው ክንዱ ይበረታል፤ ካላስፈለገው ግን ጡንቻዎቹ ይዝላሉ ይባላል።b
ይህን የሞከሩ አንዳንዶች ሙከራው እንደሚሠራና ውጤቱ በሰውነታችን ውስጥ ባሉ ኃይሎች ላይ አማካኝነት እንደሚመጣ ያምናሉ። የሚከሰቱና ሊታዩ የሚችሉ ዘመናዊ ሳይንስ ያልደረሰባቸው ብዙ ነገሮች አሉ በማለት ይናገራሉ። ስለዚህ ምንም እንኳን ሐኪሞች ያልደረሱበት ወይም የማይቀበሉት ቢሆንም በሰውነታችን ውስጥ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ወይም በሰውነታችን ውስጥ ባሉት ኃይሎችና በአንዳንድ ንጥረ ነገሮች መካከል ለውጦች ይካሄዳሉ ይላሉ።
በሌላ በኩል አፕላይድ ኪኒሲዮሎጂ የተባለው መጽሐፍ “አንዳንድ ጊዜ [መጻሕፍት] እንደ ምግብ ወይም ቅጠላ ቅጠል ያሉ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች አንድ ነገር በእጅ በመያዝ ወይም ጡንቻዎችን በመፈተን ሊገመገሙ ይችላሉ በማለት ያስተምራሉ። የዚህ ዓይነቱን ሙከራ አስተማማኝነት የሚያረጋግጥ መረጃ የለም። መርማሪው ስለ አንዳንድ ምግብ ነክ ንጥረ ነገሮች ያለው እምነት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ የጡንቻ ምርመራ ሲያደርግ በምርመራው ሂደት ወቅት ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ ሳንካ ይሆንበታል። “በእጅ የጡንቻ ምርመራ በማድረግ ልምድ ያለው መርማሪ ምርመራውን ቀስ ብሎ በመለዋወጥ ምርመራ የሚደረግለትን ሰው ጡንቻ በራሱ ምርጫ ደካማ ወይም ብርቱ ሊያስመስለው ይችላል።”
ተጠንቀቁ!
ይሁንና አንዳንድ የጡንቻ ፍተሻ ከዚህም አልፎ ይሄዳል። ለምሳሌ “ምትክ ምርመራ” የሚባለውን እንውሰድ። ይህ በሽማግሌ ወይም በጣም ደካማ በሆነ ሕፃን ምትክ ሆኖ በሚሠራ ሰው ላይ ሊሞከር ይችላል። ምትኩ ሕፃኑን ሲነካ መርማሪው የምትኩን ክንድ ይመረምራል። ይህ በለማዳ እንስሳትም ላይ ተሠርቶበታል፤ የምትኩ እጅ ኮሊና ጀርመን ሼፐርድ በተባሉ የውሻ ዘሮች ወይም በሌላ በሽተኛ እንስሳ ላይ አርፎ ተመርምሯል።
በእነዚህ ልማዶች ላይ ለመፍረድ አንፈልግም፤ ይሁን እንጂ ‘ከነዚህ ውጤቶች በስተጀርባ ከአካል ውስጥ የሚወጡ ኃይሎች ይኖራሉን?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። ሳይንቲስቶች የኮስሚክ ጨረሮች፣ ማይክሮዌቮችና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮማግኔቲክ ጨረሮች መኖራቸውን አረጋግጠዋል። ሆኖም ፍጡራን በሙሉ እንዲያውም ሕፃናትና የቤት አንስሳት ከውስጣቸው ሊወጣ የሚችልና በሁለተኛው ሰው ላይ ለውጥ የሚያስከትል ኃይል አላቸውን? ባቢሎናውያን ከፍጡራን ላይ ኃይል ወጥቶ በግ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብለው ያስቡ ነበር። ‘በዛሬው ጊዜ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ተመሳሳይ ነገር ይከሰታል ብዬ አምናለሁን? ወይስ ለውጦቹ ሌላ ትርጉም አላቸው?’ ብለህ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ።
አንዳንድ ፈዋሾች በጥምዝምዝ ብረቶች ወይም በፔንዱለሞች የግለሰቦችን “ኃይል” እንለካለን ይላሉ። የፈዋሹ “የኃይል መስክ” በበሽተኛው ላይ ለውጥ ሲያስከትል እነዚህ ነገሮች ይንቀሳቀሳሉ ይባላል። በአንድ ወቅት ተመራማሪ ሳይንቲስት የነበረች በዚህ መስክ መርማሪና ጸሐፊ የሆነች አንዲት ሴት አንዳንዴ በፔንዱለም በመጠቀም ትመረምራለች። ደግሞም በግለሰቦች ዙሪያ ያለ “ሰብዓዊ የኃይል መስክ” ወይም ባለ ቀለም የብርሃን አክሊል የተባለ ነገር ማየት እንደምትችል ትናገራለች። በአካል ውስጥ ያሉ እብጠቶችን፣ የደም ሴሎችን ወይም ማይክሮቦችን ለማየትና ያለፈውን ጊዜ ለመመርመር “ውስጥን የማየት ችሎታን” እጠቀማለሁ ትላለች።c
ከዚህ በፊት እንደተገለጸው የክንድን ብርታት በመፈተሽ ኃይልን መለካት ስሜትን ለመመርመር ተሠርቶበታል። አንድ በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ጥቂት የስሜት ምርመራ ማድረግ ከፈለግህ ድምፅ በማሰማት ‘ችግር አለብህ?’ በማለት ጠይቅና እንደገና መርምር። አልፎ አልፎ ይህ ለምርመራ ሲባል የተሰጠው ምግብ ለበሽተኛው ጠቃሚ ካልሆነ ክንዱን ያዳክማል።” አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱን ምርመራ “ልዩ የአካል፣ የስሜት ወይም የመንፈስ መቃወስ የሚከሰትበትን ዕድሜ ለመመርመር” ይጠቀማሉ። በተጨማሪም በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ነገሮች በተመለከተ ‘ላድርግ ወይም አላድርግ’ የሚል ውሳኔ ለማድረግ ይጠቀሙበታል።
ብዙዎቹ እንዲህ ያለውን የጡንቻ ምርመራ (ኪኒሶሎጂ) የሚያደርጉ ልማዱ አሁን ከተገለጸው እንደሚለይ ማለትም ከመናፍስትነት ጋር እንደማይያያዝ ወይም የስሜት ምርመራ እንደማያካሂዱ ሊናገሩ ይችላሉ። ሆኖም የሚያደርጉት ነገር ባልተለመዱ መንገዶች ወይም ልዩ ኃይል አለን በሚሉ ሰዎች ብቻ ሊሞከር የሚችል በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ እንዳለ በሚያምኑት ኃይል ላይ የተመሠረተ ነውን?
ክርስቲያኖች እነዚህን ጉዳዮች በቀላሉ አይመለከቷቸውም። አምላክ እስራኤላውያንን ሲመክር፦ “መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም [ከተፈጥሮ በላይ በሆነ ኃይል መጠቀማችሁንም ሆነ አዓት] . . . የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም” ብሏል። (ኢሳይያስ 1:13) ሕዝቡ አምላካቸውን ሲከዱ ‘ምዋርተኞችና አስማተኞች ሆኑ።’ (2 ነገሥት 17:17፤ 2 ዜና መዋዕል 33:1–6) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ልዩ ሥነ ሥርዓቶችን በማከናወን አንድ ዓይነት እውቀት ለማግኘት ይጥሩ ነበር፤ ከዚያም “ከተፈጥሮ በላይ ከሆነው ኃይል” ጋር ተነጋገሩ።—ዘካርያስ 10:2
አንዳንድ የጡንቻ ፍተሻ በሽተኛውንም ሆነ መርማሪውን አይጎዳ ይሆናል። ሆኖም በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አንዳንዶቹ ውስጥን እንደ ማየት፣ ምሥጢራዊ የብርሃን አክሊልና የፔንዱለም አጠቃቀም ያሉ ከሰው በላይ ወይም ከተፈጥሮ በላይ የሆኑ ዘዴዎችን የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ክርስቲያኖች ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች መጠቀም የለባቸውም። እንዲያውም የሰይጣንን ጥልቅ ነገሮች ለማወቅ ስለማይጓጉ እንደዚህ ዓይነቶቹን ነገሮች አይሞክሩም። (ራእይ 2:24) ከዚህ ይልቅ የአምላክ ቃል ከሚያወግዘው መናፍስትነት ጋር የተያያዘ ከሚመስል ከማንኛውም ነገር ለመጠንቀቅ ጥሩ ምክንያት አለ።—ገላትያ 5:19–21
መርማሪው ስለሚያደርገው ነገር ራሱ ኃላፊ ሲሆን የየግለሰቡን አባባል ወይም ዘዴ ትክክል ነው ወይም አይደለም ብለን ለመፍረድ አንፈልግም። ይህን ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ አንዳንድ ሰዎች ከሰው በላይ በሆነ ኃይል እንደሚጠቀሙ ቢሰማህም ብዙዎቹ በዚህ ድርጊት የሚካፈሉት በመናፍስትነት እንደሚሳተፉ ምንም ሳያስቡ በየዋህነት እንደሚያደርጉት ግልጽ ነው። ተስፋ ቆርጠው ጥሩ ጤንነት ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም በዚህ ድርጊት ይካፈሉ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ኋላ ላይ የሕክምና ዘዴው ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅም ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ አንፃር ሲታይ ሊደረግ እንደማይገባው ታይቷቸዋል።
ለመድገም ያህል እያንዳንዱ ግለሰብ እንዲህ ዓይነቶቹን የግል ጉዳዮች አስመልክቶ የራሱን ውሳኔ መወሰን አለበት። ይሁንና ክርስቲያኖች ይህን የአምላክ ምክር ማስታወስ አለባቸው፦ “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።” (ምሳሌ 14:15) ይህ ይጠቅማሉ የሚባሉ አንዳንድ የጤና ምርመራ ዘዴዎችንም ይጨምራል።
ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮችን ከእውነተኛው አምልኮ ለማዘናጋት ይፈልጋል። ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በሌሎች ጉዳዮች በመሳብ ይህን ቢያደርግ ደስ ይለዋል። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ ከሰው በላይ በሆኑ ወይም በሚመስሉ ወደ መናፍስትነት ሊስቡ በሚችሉ ነገሮች ቢማረኩ ደስ ይለዋል።—1 ጴጥሮስ 5:8
ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም እንኳን ይሖዋ አምላክ ስለ መናፍስትነት ያለው አመለካከት አልተለወጠም። ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰው አምላክ እስራኤላውያንን “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም” በእነርሱ ዘንድ እንዳይገኝ አዟቸው ነበር። “ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ . . . በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን።”—ዘዳግም 18:10–13
ታዲያ በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው ክርስቲያኖች ‘መጋደላችን . . . በሰማያዊ ስፍራ ካለ መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር ስለሆነ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ’ ያለማቋረጥ መልበሱ ምንኛ ጥበብ ነው!—ኤፌሶን 6:11, 12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ብዙ ሰዎች ቃልቻዎችን፣ ጠንቋዮችን ወይም ተመሳሳይ ፈዋሾችን ያማክራሉ። ቃልቻ “በሽተኞችን ለማዳን አስማት ለማድረግና ድርጊቶችን ለመቆጣጠር በጥንቆላ የሚጠቀም ሰው ነው።” ጠንቋዮች ወይም ቃልቻዎች ቅጠላ ቅጠሎችን (ምሥጢራዊ ኃይሎችን በመለመን) ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ሊቀላቅሉ ይችላሉ። ጥንቁቅ የሆነ ታማኝ ክርስቲያን ፈውስ የሚያመጡ ቢመስሉም ከእንደዚህ ዓይነቶቹ የመናፍስትነት ድርጊቶች ይርቃል።—2 ቆሮንቶስ 2:11፤ ራእይ 2:24፤ 21:8፤ 22:15
b ይህ አጠቃላይ የሆነ መግለጫ ሲሆን የምርመራው ሂደት ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ምርመራ የሚደረግለት ሰው አውራ ጣቱንና መሃል ጣቱን አንድ ላይ አድርጎ እንዲጫን ሊጠየቅና መርማሪው ለማለያየት ሊሞክር ይችላል።
c ሴትየዋ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “እነዚህ ተአምር የሚመስሉ ለውጦች እንዴት ሊመጡ ቻሉ? . . . እኔ የምጠቀምበት ዘዴ እጅ መጫን፣ የእምነት ፈውስ ወይም መንፈሳዊ ፈውስ ይባላል። ምሥጢራዊ ሳይሆን በጣም ግልጽ የሆነ ዘዴ ነው . . . ሁሉም ሰው በሥጋዊ አካሉ ዙሪያ ያለና የሚሰርፅ የኃይል መስክ ወይም የብርሃን አክሊል አለው። ይህ የኃይል መስክ ከጤና ጋር በቅርብ የተዛመደ ነው። . . . ነገሮችን የመለየት ከፍተኛ ስሜት የማየት ችሎታህን ሳትጠቀም አንድን ነገር በአእምሮህ የምታጣራበት ‘የእይታ’ ዓይነት ነው። የፈጠራ ሐሳብ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ከተራ ማስተዋል በላቀ መንገድ ነገሮችን የመለየት ችሎታ በመባል ይጠራል።”