-
ሁላችንም መጽናኛ ያስፈልገናልመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 5
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ማጽናኛ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?
ሁላችንም መጽናኛ ያስፈልገናል
ትንሽ ልጅ እያለህ የወደቅክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ምናልባት እጅህ ቆስሎ ወይም ጉልበትህ ተላልጦ ይሆናል። እናትህ እንዴት እንዳባበለችህ ወይም እንዳጽናናችህ ትዝ ይልሃል? ምናልባት ቁስሉን ጠራርጋ በፋሻ አስራልህ ይሆናል። ብታለቅስም እናትህ እቅፍ አድርጋ በሚያጽናኑ ቃላት ስታባብልህ ሕመምህን ወዲያውኑ ረስተኸው ይሆናል። በዚያ ዕድሜ ላይ በቀላሉ መጽናናት ይቻላል።
ይሁን እንጂ እያደግን ስንሄድ ሕይወት ይበልጥ እየተወሳሰበ ይሄዳል። የሚያጋጥሙን ችግሮች ከባድ ስለሚሆኑ በቀላሉ መጽናናት አንችልም። የሚያሳዝነው ነገር የትልልቅ ሰዎች ችግር ፋሻ በማሰር ወይም እናት በምትሰጠው ፍቅር የሚፈታ አይደለም። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
ከሥራ ተባረህ ታውቃለህ? ከሆነ በዚህ ምክንያት የተሰማህን ድንጋጤ መቼም ቢሆን አትረሳው ይሆናል። ሁሊያን ከሥራ መባረሩን በሰማ ጊዜ በጣም ደንግጦ እንደነበር ይናገራል። ‘ቤተሰቤን የማስተዳድረው እንዴት ነው? ድርጅቱ፣ ብዙ ዓመት ከለፋሁለት በኋላ እንዴት እንደማይረባ ነገር አውጥቶ ይጥለኛል?’ የሚሉት ጥያቄዎች አስጨንቀውት ነበር።
ወይም ትዳርህ በመፍረሱ በጣም ደንግጠህ ይሆናል። ራኬል እንዲህ ብላለች፦ “ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ባሌ በድንገት ጥሎኝ ሄደ፤ በዚህ ወቅት በከፍተኛ ሐዘን ተዋጥኩ። ልቤ በሐዘን ተሰበረ። ሐዘኑ ያስከተለብኝ ስሜታዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ሥቃይም ጭምር ነበር። ፍርሃት ለቀቀብኝ።”
ወይም ደግሞ ምንም መሻሻል የማያሳይ ከባድ የጤና ችግር ይኖርብህ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ፣ “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” በማለት እንደተናገረው እንደ ታማኙ ኢዮብ ይሰማህ ይሆናል። (ኢዮብ 7:16) ምናልባት አንተም “አንዳንድ ጊዜ፣ ሞቴን ቁጭ ብዬ እየጠበቅሁ እንዳለሁ ይሰማኛል” በማለት እንደተናገሩት በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንዳሉት እንደ ሉዊስ ይሰማህ ይሆናል።
አሊያም ደግሞ የምትወደውን የቤተሰብህን አባል በሞት በማጣትህ መጽናኛ ማግኘት አስፈልጎህ ይሆናል። ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ በሚያሳዝን ሁኔታ በአውሮፕላን አደጋ ሲሞት መጀመሪያ ላይ መቀበል ከብዶኝ ነበር። ከዚያም ሐዘኑ ይሰማኝ ጀመር፤ ስሜቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም የሚሰማትን ስሜት አስመልክቶ ‘በአንቺም ውስጥ ትልቅ ሰይፍ ያልፋል’ በማለት ከገለጸው ጋር ይመሳሰላል።”—ሉቃስ 2:35
ሮበርት፣ ሉዊስ፣ ራኬልና ሁሊያን የደረሰባቸው ነገር እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም መጽናናት ችለዋል። ከማንም በላይ መጽናኛ መስጠት ከሚችለው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ መጽናኛ አግኝተዋል። ታዲያ አምላክ መጽናኛ የሚሰጠው እንዴት ነው? ለአንተስ የሚያስፈልግህን መጽናኛ ይሰጥህ ይሆን?
-
-
አምላክ የሚያጽናናን እንዴት ነው?መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 5
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ማጽናኛ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?
አምላክ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋንa ‘በሚደርስብን መከራ ሁሉ የሚያጽናናን’ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በማለት ገልጾታል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) በመሆኑም አምላክ ሊሰጠን ከሚችለው እርዳታ በላይ የሆነ ነገር ወይም በሰማይ ያለው አባታችን በሚሰጠን ማጽናኛ ሊወገድ የማይችል ምንም ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል።
እርግጥ ነው፣ አምላክ የሚሰጠውን ማጽናኛ ለማግኘት ከእኛ የሚጠበቅ ነገር አለ። አንድ ሐኪም፣ ለመታየት ቀጠሮ ይዘን ወደ እሱ ካልሄድን እንዴት ሊያክመን ይችላል? ነቢዩ አሞጽ “ሁለት ሰዎች በቀጠሮ ሳይገናኙ አብረው ይጓዛሉ?” በማለት ጠይቋል። (አሞጽ 3:3 የግርጌ ማስታወሻ) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ይመክረናል።—ያዕቆብ 4:8
ታዲያ አምላክ ወደ እኛ እንደሚቀርብ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? አንደኛ አምላክ እኛን መርዳት እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ተናግሯል። (ሣጥኑን ተመልከት።) ሁለተኛ፣ በዘመናችንም ሆነ በጥንት ዘመን አምላክ ያጽናናቸው ሰዎች አሉ።
በዛሬው ጊዜ የአምላክን እርዳታ ማግኘት እንደሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ሁሉ ንጉሥ ዳዊትም በተደጋጋሚ ከባድ ችግር አጋጥሞታል። በአንድ ወቅት “እርዳታ ለማግኘት ወደ አንተ በምጮኽበት ጊዜ ልመናዬን ስማ” በማለት ይሖዋን ተማጽኖ ነበር። ታዲያ አምላክ መልስ ሰጠው? አዎን። ዳዊት አክሎም “ከእሱ እርዳታ ስላገኘሁ ልቤ ሐሴት ያደርጋል” ብሏል።—መዝሙር 28:2, 7
ኢየሱስ የሚያለቅሱትን በማጽናናት ረገድ የሚጫወተው ሚና
አምላክ፣ ኢየሱስ መጽናኛ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና እንዲኖረው አድርጓል። አምላክ ለኢየሱስ ከሰጠው ሥራዎች መካከል ‘ልባቸው የተሰበረውን መጠገን’ እና ‘የሚያለቅሱትን ሁሉ ማጽናናት’ ይገኙበታል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው ኢየሱስ ‘ለደከሙና ሸክም ለከበዳቸው’ ሰዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።—ማቴዎስ 11:28-30
ኢየሱስ ለሰዎች ጥበብ ያዘለ ምክር በመስጠት፣ እነሱን በደግነት በመያዝ አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹን ከበሽታቸው በመፈወስ አጽናንቷቸዋል። አንድ ቀን የሥጋ ደዌ በሽተኛ የሆነ አንድ ሰው ኢየሱስን “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ተማጸነው። ኢየሱስም በርኅራኄ ተገፋፍቶ “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። (ማርቆስ 1:40, 41) ከዚያም ሰውየው ከበሽታው ተፈወሰ።
በዛሬው ጊዜ የአምላክ ልጅ በምድር ላይ ስለሌለ እኛን በግለሰብ ደረጃ ሊያጽናናን አይችልም። ይሁን እንጂ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው አባቱ ይሖዋ መጽናኛ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሁንም እየረዳ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3) አምላክ ሰዎችን ለማጽናናት የሚጠቀምባቸውን አራት ዋና ዋና መንገዶች እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ። “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።”—ሮም 15:4
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ። ኢየሱስ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ መላው የክርስቲያን ጉባኤ ሰላም አግኝቶ ነበር። ለምን? “መላው ጉባኤ ይሖዋን በመፍራትና መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ ጋር በመስማማት ይኖር ስለነበር [ነው]።” (የሐዋርያት ሥራ 9:31) የአምላክ ኃይል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ከፍተኛ ኃይል አለው። አምላክ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚገኝን ሰው ለማጽናናት ሊጠቀምበት ይችላል።
ጸሎት። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ” በማለት ይመክረናል። አክሎም እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
የእምነት አጋሮቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን መጽናኛ ለማግኘት በእርግጥ ልንታመንባቸው የምንችል እውነተኛ ጓደኞቻችን ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እምነት ባልደረቦቹ ሲናገር ‘በችግርና በመከራ’ ወቅት “የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል” ብሏል።—ቆላስይስ 4:11፤ 1 ተሰሎንቄ 3:7
ይሁንና ‘እነዚህ ነገሮች፣ ችግር በሚያጋጥመኝ ወቅት በእርግጥ ያጽናኑኛል?’ የሚለው ነገር ያሳስብህ ይሆናል። እስቲ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ያጋጠማቸውን ነገር እንመልከት። እነዚህ ሰዎች “እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ” የሚለው አምላክ የሰጠው አስደሳች ተስፋ አሁንም እንደሚፈጸም እርግጠኛ ሆነዋል፤ አንተም ይህንን ማረጋገጥ ትችላለህ።—ኢሳይያስ 66:13
a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።
-
-
ችግር ሲያጋጥመን ማጽናኛ ማግኘትመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 5
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ማጽናኛ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?
ችግር ሲያጋጥመን ማጽናኛ ማግኘት
ችግርና መከራ በተለያየ መልኩ ያጋጥመናል። እርግጥ ስለ ሁሉም ዓይነት ችግር እያነሳን መወያየት አንችልም፤ ሆኖም ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን አራት ምሳሌዎች አንድ በአንድ እንመልከት። የተለያየ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች ከአምላክ እውነተኛ መጽናኛ ያገኙት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።
ከሥራ መባረር
“ያገኘሁትን ማንኛውንም ሥራ ሳልመርጥ መሥራትን የተማርኩ ሲሆን በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች የምናወጣውን ወጪ ቀነስን።”—ጆናታን
ሴት የተባለ አንድ ከሥራ የተባረረ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ከሥራ የተባረርነው በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው።a ለሁለት ዓመታት ያህል የኖርነው ቤተሰብ በሚያደርግልን እርዳታና አንዳንድ ተባራሪ ሥራዎችን እየሠራን ነበር። በዚህም የተነሳ ባለቤቴ ፕሪሲላ የመንፈስ ጭንቀት ያዛት፤ እኔም ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ተሰማኝ።
“ሁኔታውን ለመቋቋም የረዱን ነገሮች አሉ። ፕሪሲላ፣ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:34 ላይ የተናገረውን ሐሳብ ዘወትር ታስታውስ ነበር። ኢየሱስ እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች ስላሉት ስለ ነገ መጨነቅ እንደሌለብን ተናግሯል። በተጨማሪም ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረቧ በጽናት ለመቀጠል የሚያስችል ብርታት ሰጥቷታል። እኔን ያጽናናኝ ደግሞ መዝሙር 55:22 ነው። እንደ መዝሙራዊው ሁሉ እኔም ሸክሜን በይሖዋ ላይ ጣልኩ፤ እሱም ደግፎኛል። አሁን ሥራ ያለኝ ቢሆንም ኢየሱስ በማቴዎስ 6:20-22 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሯችንን ቀላል አድርገናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳችን ይበልጥ ተቀራርበናል።”
ጆናታን ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አነስተኛ በሆነው የቤተሰባችን ንግድ ላይ ኪሳራ ሲደርስ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ፍርሃት አድሮብኝ ነበር። የኢኮኖሚው ቀውስ የ20 ዓመት ልፋታችንን መና አስቀርቶታል። ከባለቤቴ ጋር ስለ ገንዘብ መጨቃጨቅ ጀመርን። ክሬዲት ካርዳችን ተቀባይነት አያገኝም ብለን ስለፈራን በክሬዲት ካርዳችን እንኳ መግዛት አልቻልንም።
“ይሁን እንጂ አምላክ በቃሉና በመንፈሱ አማካኝነት ጥሩ ውሳኔዎች እንድናደርግ ረድቶናል። ያገኘሁትን ማንኛውንም ሥራ ሳልመርጥ መሥራትን የተማርኩ ሲሆን በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች የምናወጣውን ወጪ ቀነስን። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የእምነት አጋሮቻችን ድጋፍ አልተለየንም። ለራሳችን ያለንን ግምት እንዳናጣ የረዱን ሲሆን ሁኔታው በጣም ከባድ በሚሆንብን ጊዜ ደግሞ የእርዳታ እጃቸውን ዘርግተውልናል።”
የትዳር መፍረስ
ራኬል እንዲህ ብላለች፦ “ባሌ በድንገት ጥሎኝ ሲሄድ ስሜቴ በጣም ተጎድቶና ተናድጄ ነበር። በከባድ ሐዘንም ተዋጥኩ። ይሁን እንጂ ወደ አምላክ ቀረብኩ፤ እሱም አጽናንቶኛል። በየዕለቱ ወደ እሱ እጸልይ ስለነበር የአምላክ ሰላም ልቤን ጠብቆልኛል። የተሰበረውን ልቤን እንደጠገነልኝ ተሰምቶኛል።
“ደግሞም ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ያደረብኝን ንዴትና ቂም ማሸነፍ ችያለሁ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም 12:21 ላይ ‘በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ’ በማለት የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ አደረኩ።
“‘ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው።’ . . . አሁን አዳዲስ ግቦች አውጥቼ ትኩረቴን በዚያ ላይ አድርጌያለሁ።”—ራኬል
“አንድ አስተዋይ ጓደኛዬ የሰጠኝ ምክር ያለፈውን በመርሳት ወደ ፊት እንድቀጥል ረድቶኛል። መክብብ 3:6 ላይ ያለውን ‘ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው’ የሚለውን ጥቅስ አሳየኝ። ምክሩ ጠንከር ያለ ቢሆንም በወቅቱ የሚያስፈልገኝ ይህ ነበር። አሁን አዳዲስ ግቦች አውጥቼ ትኩረቴን በዚያ ላይ አድርጌያለሁ።”
ኤልዛቤት እንዲህ ብላለች፦ “ትዳራችሁ ሲፈርስ ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋችኋል። ምንጊዜም ድጋፍ የምታደርግልኝ የምወዳት ጓደኛ አለችኝ። አብራኝ ታለቅስና ታጽናናኝ ነበር፤ እንደማልፈለግ ሳይሆን ተወዳጅ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ታደርግ ነበር። ይሖዋ የውስጤ ቁስል እንዲሽር ለመርዳት በእሷ እንደተጠቀመ ይሰማኛል።”
ሕመም ወይም እርጅና
“ከጸለይኩ በኋላ የአምላክ መንፈስ ብርታት ሲሰጠኝ ይሰማኛል።”—ሉዊስ
በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ሉዊስ ከባድ የልብ ሕመም ስላለባቸው ከአንዴም ሁለቴ ሞት አፋፍ ደርሰው ነበር። አሁን በየቀኑ ለ16 ሰዓታት ኦክሲጂን ይሰጣቸዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ዘወትር ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ከጸለይኩ በኋላ የአምላክ መንፈስ ብርታት ሲሰጠኝ ይሰማኛል። ጸሎት በጽናት ለመቀጠል የሚያስፈልገኝን ድፍረት ይሰጠኛል፤ ምክንያቱም በይሖዋ ላይ እምነት አለኝ፤ እንዲሁም እንደሚያስብልኝ አውቃለሁ።”
በ80ዎቹ ዓመታት ውስጥ የሚገኙት ፔትራ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “መሥራት የምፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ግን ምን ያደርጋል አቅም የለኝም። ጉልበቴ እየደከመ መሄዱን አምኖ መቀበል በጣም ከብዶኛል። በጣም ይደክመኛል፣ እንዲሁም ያለ መድኃኒት መኖር አልችልም። ብዙ ጊዜ የማስበው፣ ኢየሱስ የሚቻል ከሆነ ሊደርስበት የነበረው መከራ እንዲያልፍለት አባቱን የተማጸነበትን መንገድ ነው። ይሖዋ በዚህ ወቅት ለኢየሱስ ብርታት ሰጥቶታል፤ እኔንም ያበረታኛል። በየዕለቱ የማቀርበው ጸሎት እንደ መድኃኒት ሆኖልኛል። ወደ አምላክ ከጸለይኩ በኋላ ቀለል ይልልኛል።”—ማቴዎስ 26:39
ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት መልቲፕል ስክለሮሲስ ከሚባል የነርቭ በሽታ ጋር ሲታገል የኖረው ሁሊያንም እንደዚሁ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “በቢሮ ወንበር ፋንታ የአካል ጉዳተኞች ወንበር መጠቀም ጀምሬያለሁ። ይሁን እንጂ ሕይወቴን ሌሎችን ለማገልገል ስለምጠቀምበት ዋጋ እንዳለኝ ይሰማኛል። ሌሎችን መርዳት ሥቃይን የሚያስታግስ ሲሆን ይሖዋም በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ እንደሚያበረታን የገባውን ቃል ይፈጽማል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኔም ‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ’ ብዬ ከልቤ መናገር እችላለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:13
የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት
አንቶኒዮ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ በመኪና አደጋ በሞተ ጊዜ መጀመሪያ ላይ ማመን አቅቶኝ ነበር። አባቴ ምንም ያጠፋው ነገር አልነበረም፤ የተገጨው በእግረኞች መንገድ ላይ እየሄደ ሳለ ነው። ይሁን እንጂ ምንም ማድረግ አልቻልኩም። አባቴ ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ለአምስት ቀናት ራሱን እንደሳተ ቆይቷል። በእናቴ ፊት ላለማልቀስ እንደምንም ብዬ ራሴን እቆጣጠር ነበር፤ ብቻዬን ስሆን ግን ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። ‘ለምን? ለምን?’ እያልኩ ራሴን በተደጋጋሚ እጠይቅ ነበር።
“በእነዚያ እጅግ አሳዛኝ ቀናት ስሜቴን ለመቆጣጠር እንዲረዳኝና ሰላም እንዲሰጠኝ ዘወትር ይሖዋን እለምነው ነበር። ደግሞም ቀስ በቀስ እየተረጋጋሁ መጣሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ‘ያልተጠበቁ ክስተቶች’ ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ የሚናገር መሆኑን አስታወስኩ። አምላክ ስለማይዋሽ አባቴን ዳግመኛ በትንሣኤ እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ።”—መክብብ 9:11፤ ዮሐንስ 11:25፤ ቲቶ 1:2
“የአውሮፕላን አደጋው የልጃችንን ሕይወት ቢቀጥፍም ከልጃችን ጋር ያሳለፍናቸው አስደሳች ጊዜያት አሁንም ከአእምሯችን አልጠፉም።”—ሮበርት
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሮበርትም ይህን ሐሳብ ይጋራል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የተጠቀሰውን የአእምሮ ሰላም አግኝተናል። ይህን ያገኘነው ለይሖዋ በመጸለያችን ነው። እንዲህ ያለው ውስጣዊ ሰላም ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለዜና ዘጋቢዎች በተረጋጋ መንገድ ለመናገር አስችሎናል። የአውሮፕላን አደጋው የልጃችንን ሕይወት ቢቀጥፍም ከልጃችን ጋር ያሳለፍናቸው አስደሳች ጊዜያት አሁንም ከአእምሯችን አልጠፉም። በዚህ ላይ ለማተኮር ጥረት እናደርጋለን።
“የእምነት አጋሮቻችን ስለ እምነታችን ተረጋግተን ስንናገር በቴሌቪዥን እንዳዩን ሲነግሩን ይህን ማድረግ የቻልነው በእነሱ ጸሎት እንደሆነ ገልጸንላቸዋል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የላኳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሚያጽናኑ መልእክቶች ይሖዋ በእነሱ አማካኝነት እየደገፈን እንደሆነ እንዳምን አድርገውኛል።”
ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች አምላክ የተለያዩ ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ላጋጠሟቸው ሰዎች መጽናኛ መስጠት እንደሚችል ያሳያሉ። አንተንስ ሊያጽናናህ ይችላል? በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህ መከራ ምንም ሆነ ምን፣ አንተም በመከራህ ወቅት መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ።b ታዲያ ይሖዋ እንዲረዳህ ለምን በጸሎት አትጠይቀውም? እሱ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3
-