ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙ መግቢያዎች
አስተያየት:- በመስክ አገልግሎት በምትሰማራበት ጊዜ የምትጠቀምበትን የመግቢያ ዓይነት ለመምረጥ ሦስት ነገሮችን በጥንቃቄ እንድታስብባቸው ያስፈልጋል:- (1) ለሰዎች እንድንነግራቸው የታዘዝነው መልእክት “ይህ የመንግሥት ምሥራች” ነው። (ማቴ. 24:14 አዓት) ስለ መንግሥቲቱ በቀጥታ በማንነጋገርበትም ጊዜ ቢሆን ሰዎች የአምላክ መንግሥት እንደምታስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ መርዳት ወይም ስለዚህች መንግሥት እንዳይመረምሩ እንቅፋት የሚሆኑባቸውን መሰናክሎች ማስወገድ እንደሚገባን ማስታወስ ይኖርብናል። (2) የሰዎችን ልብ ለመንካት የሚረዳን ለሰዎች ደህንነት ያለን ልባዊ አሳቢነት ነው። ኢየሱስንም የሰዎችን ልብ ለመንካት ያስቻለው ይህ ባሕርይ ነው። (ማር. 6:34) እንዲህ ያለው ሰዎችን የመርዳት እውነተኛ ፍላጎት በጥሩ ፈገግታ፣ የወዳጅነት መንፈስ በማሳየት፣ እነርሱ በሚናገሩበት ጊዜ ለማዳመጥ ፈቃደኛ በመሆንና ተስማሚ መልስ በመስጠት ይገለጻል። በተጨማሪም ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያደፋፍሩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የምናነጋግራቸውን ሰዎች አመለካከት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንችላለን። አንደኛ ቆሮንቶስ 9:19–23 ሐዋርያው ጳውሎስ የአቀራረብ ዘዴውን ምሥራቹን ከሚነግራቸው ሰዎች ሁኔታ ጋር ያስማማ እንደነበር ያሳያል። (3) በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች እንግዶች የመጡበትን ምክንያት ከመናገራቸው በፊት አንዳንድ ሥርዓቶችን እንዲፈጽሙ ይጠበቅባቸዋል። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ደግሞ የቤት ባለቤቶች ሳይጋበዙ የመጡ እንግዶች ቶሎ ብለው የመጡበትን ምክንያት እንዲናገሩ ይፈልጋሉ።—ከሉቃስ 10:5 ጋር አወዳድር።
ጥሩ ልምድ ያላቸው አንዳንድ ምሥክሮች እንዴት ውይይት እንደሚጀምሩ ቀጥሎ ከቀረቡት መግቢያዎች ማየት ይቻላል። አንተ የምትጠቀምባቸው መግቢያዎች ብዙ ጊዜ ውይይት ለመጀመር የማይረዱ ሆነው ካገኘሃቸው ከዚህ በታች ከቀረቡት መግቢያዎች አንዳንዶቹን ሞክር። ይህን በምታደርግበት ጊዜ በራስህ አነጋገር ለመጠቀም እንደምትፈልግ አያጠራጥርም። በተጨማሪም ሰዎችን ቀርቦ በማነጋገር የተሳካ ውጤት ካገኙ በጉባኤህ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ምክር ብትጠይቅ ልትጠቀም ትችላለህ።
አርማጌዶን
● ‘ብዙ ሰዎች የአርማጌዶን ጉዳይ ያሳስባቸዋል። የዓለም መሪዎች ይህን ቃል አጠቃላይ የሆነ የኑክሌር ጦርነትን ለማመልከት ሲጠቀሙበት ሰምተዋል። እርስዎ አርማጌዶን ለሰው ዘር ምን ትርጉም አለው ብለው ያምናሉ? . . . በእርግጥ አርማጌዶን የሚለው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ለቃሉ ከሚሰጠው የተለምዶ ፍቺ ፈጽሞ የተለየ ነው። (ራእይ 16:14, 16) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከመጪው ጥፋት ለመትረፍ ከፈለግን በግላችን ልናደርጋቸው የምንችላቸው ነገሮች እንዳሉ ይገልጻል። (ሶፎ. 2:2, 3)’ (በገጽ 43–47 ላይ “አርማጌዶን” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)
መጽሐፍ ቅዱስ/አምላክ
● ‘ጤና ይስጥልኝ። የመጣሁት ለጥቂት ደቂቃዎች አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት ልነግርዎት ነው። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ ምን እንደሚል ይመልከቱ። (እንደ ራእይ 21:3, 4 ያሉትን ጥቅሶች አንብብ።) ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዎታል? ነገሩ ጥሩ አይመስልዎትም?’
● ‘በኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራዊ እርዳታዎች ከየት ማግኘት እንደሚቻል ለጐረቤቶቻችን እየነገርናቸው ነው። በቀደሙት ዘመናት ሰዎች አንድ ዓይነት መፍትሔ ለመፈለግ መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡ ነበር። አሁን ግን የሰዎች አስተሳሰብ በተለወጠበት ጊዜ ላይ እንኖራለን። ስለዚህ ነገር ምን ይሰማዎታል? እርስዎ መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱት እንደ አምላክ ቃል አድርገው ነው ወይስ በሰዎች እንደተጻፈ እንደ አንድ ጥሩ መጽሐፍ ብቻ? . . . የአምላክ ቃል ከሆነስ ይህን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል ብለው ያስባሉ?’ (ከገጽ 56–67 ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)
● ‘እቤት ስላገኘሁዎት ደስ ብሎኛል። ለጐረቤቶቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ (ወይም ከቅዱሳን ጽሑፎች) ያገኘሁትን ሐሳብ እያካፈልኩ ነው። ለመሆኑ . . . ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? (ወደ መነጋገሪያ ርዕስህ የሚያስገባ አንድ ጥያቄ ጠይቅ።)’
● ‘ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ እያበረታታናቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ትልልቅ ለሆኑ ጥያቄዎች የሚሰጣቸው መልሶች ብዙ ጊዜ ሰዎችን ያስገርማቸዋል። ለምሳሌ . . . (መዝ. 104:5፤ ወይም ዳን. 2:44፤ ወይም ሌላ)’
● ‘በዛሬው ዕለት ጐረቤቶቻችንን ለአጭር ጊዜ እያነጋገርን ነው። ካነጋገርናቸው ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በአምላክ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ በአምላክ ማመን አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። እርስዎስ ምን ይሰማዎታል? . . . መጽሐፍ ቅዱስ የግዙፉን ጽንፈ ዓለም ታላቅነት እንድንመለከት ያበረታታናል። (መዝ. 19:1) እነዚህን ሰማያዊ አካላት በሥርዓቱና በሕጉ የሚመራቸው አምላክ ለእኛም ጠቃሚ መመሪያ ሰጥቶናል። (መዝ. 19:7–9)’ (በተጨማሪ በገጽ 146–152፤ 83–87 ላይ “አምላክ” እና “ፍጥረት” በሚሉት ዋና ርዕሶች ሥር ተመልከት።)
ወንጀል/ደህንነት
● ‘ጤና ይስጥልኝ። ከሰዎች ጋር ስለ ግል ደህንነታቸው ጉዳይ እየተነጋገርን ነው። በአካባቢያችን ብዙ ወንጀል ይፈጸማል፣ ይህም በሕይወታችን ላይ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። እርስዎንና እኔን የመሰሉ ሰዎች በጨለማ ያለ ሥጋት ለመጓዝ የምንችልበት ዘመን የሚመጣ ይመስልዎታል? (ወይም ለዚህ ችግር እውነተኛ መፍትሔ የሚሰጥ አለ ብለው ያስባሉ?) . . . (ምሳሌ 15:3፤ መዝ. 37:10, 11)’
● ‘ —— እባላለሁ። የምኖረው በዚህ አካባቢ ነው። ዛሬ ጠዋት ወደዚህ በመምጣት ላይ ሳለሁ ሰዎች ስለ (በአካባቢው የተፈጸመ ወንጀል ወይም ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ጥቀስ) ሲነጋገሩ ሰማሁ። ስለተፈጸመው ነገር ምን ይሰማዎታል? . . . ሕይወታችን ዋስትና እንዲኖረው ሊረዳ የሚችል ነገር ያለ ይመስልዎታል? . . . (ምሳሌ 1:33፤ 3:5, 6)’
ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎች
● ‘እንደምን አመሹ። —— እባላለሁ። የምኖረው በዚህ አካባቢ ነው። (የአካባቢውን ስም ወይም የቀበሌውን ቁጥር ተናገር) ባለፈው ምሽት በቴሌቪዥን የተላለፈውን ዜና ተከታትለዋል? . . . በተለይ ስለ (አንዱን ወቅታዊ የሆነ አሳሳቢ ጉዳይ ጥቀስና) የተነገረውን። ስለዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት? . . . ሰዎች ይህ ዓለም ወዴት እያመራ ነው? ብለው ሲጠይቁ መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻ ቀን’ በሚለው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር እናምናለን። እስቲ ይህን በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ የሚገኝ ዝርዝር መግለጫ ይመልከቱ።’ (በተጨማሪ ገጽ 234–243ን ተመልከት።)
● ‘በዚህ ሳምንት ውስጥ ይህንን ዜና በጋዜጣ ላይ አንብበዋል? (ከጋዜጣ ላይ ቆርጠህ ያወጣኸውን አሳያቸው።) ስለዚህ ዜና ምን አስተያየት አለዎት? . . . ’
● ‘አንድ ነገር ልጠይቅዎት እፈልጋለሁ። ምርጫ ቢሰጥዎ ዓለማችንን ካጋጠሟት ብዙ ችግሮች በቅድሚያ እንዲወገድ የሚፈልጉት የትኛውን ነው? (የቤቱን ባለቤት በከፍተኛ ደረጃ ያሳሰበው ምን እንደሆነ ከተረዳህ በኋላ ይህንን ያሳሰበውን ነገር ለውይይቱ መሠረት አድርገህ ተጠቀም።)’
የሥራ/የመኖሪያ ቤት ችግር
● ‘ከጐረቤቶችዎ ጋር እያንዳንዱ ሰው ሥራና ቤት እንዲኖረው መደረግ ስላለበት ነገር ስንነጋገር ነበር። ሰብዓዊ መንግሥታት ይህን ያሟላሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው ብለው ያምናሉን? . . . እነዚህ ችግሮች ሁሉ እንዴት መፍትሔ ማግኘት እንደሚችሉ የሚያውቅ አለ። እርሱም የሰው ዘር ፈጣሪ ነው። (ኢሳ. 65:21–23)’
● ‘ስለ አንድ ጥሩ መንግሥት የሚገልጽ ሐሳብ ለጐረቤቶቻችን እየነገርን ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ከምግባረ ብልሹነት ነፃ የሆነ፣ ለሁሉም ሰው ሥራና ጥሩ መኖሪያ ቤት የሚያዘጋጅ መንግሥት እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህን ሁሉ ሊያደርግ የሚችለው ምን ዓይነት መንግሥት ነው ብለው ያስባሉ? . . . (መዝ. 97:1, 2፤ ኢሳ. 65:21–23)’ (በገጽ 152–157 ላይ “መስተዳድር” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር የተገለጸውን ተመልከት።)
ቤተሰብ/ልጆች
● ‘የቤተሰብን ችግር እንዴት መወጣት እንደሚቻል ለማወቅ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር እየተወያየን ነው። ሁላችንም የምንችለውን ያህል ለማድረግ እንሞክራለን። ይሁን እንጂ ከአሁኑ የተሻለ የተሳካ ውጤት ለማግኘት የሚረዳን ነገር ብናገኝ ደስ ይለናል፤ አይደለም እንዴ? . . . (ቆላ. 3:12, 18–21) መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰባችን የወደፊት ኑሮ ጥሩ ተስፋ ይሰጠናል። (ራእይ 21:3, 4)’
● ‘ሁላችንም ልጆቻችን ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸው እንፈልጋለን። ነገር ግን ዛሬ በዓለም ያለውን ችግር ስንመለከት ደስተኛ ኑሮ ይገኛል ብሎ ለመጠበቅ የሚያስችል ጥሩ ምክንያት ያለ ይመስልዎታል? . . . ልጆቻችንስ ባደጉ ጊዜ ምን ዓይነት ዓለም ያጋጥማቸዋል ብለው ያስባሉ? . . . አምላክ ይህችን ምድር አስደሳች የመኖሪያ ሥፍራ እንደሚያደርጋት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝ. 37:10, 11) ይሁን እንጂ ልጆቻችን በምድር ላይ በደስታ ለመኖር መቻላቸው በአብዛኛው ዛሬ እኛ በምናደርገው ምርጫ ላይ የተመካ ነው። (ዘዳ. 30:19)’
የወደፊቱ ጊዜ/ሳይሰጉ መኖር
● ‘እንደምን አደሩ። ደህና ነዎት? . . . ወደፊት ስለሚኖረው መልካም ጊዜ ለጐረቤቶቻችን ለመንገር ጥረት እያደረግን ነው። እርስዎስ የወደፊቱ ኑሮ ጥሩ የሚሆን ይመስልዎታል? . . . በአንዳንድ ሁኔታዎች የተነሣ ከአሁኑ የተሻለ የወደፊት ኑሮ እንደሚመጣ ለማመን ከባድ ይሆንብዎታል? . . . በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚ ሐሳብ እንደሚሰጥ ተገንዝቤአለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ በዘመናችን ያለውን ሁኔታ በትክክል ከመግለጹም በላይ ይህ ሁሉ ሁኔታ ምን ትርጉም እንዳለውና ውጤቱም ምን እንደሚሆን ይነግረናል። (ሉቃስ 21:10, 11, 31)’
● ‘ጤና ይስጥልኝ —— እባላለሁ። አንተስ? . . . እንደ አንተ ያሉ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ ለወደፊቱ ጊዜ ስለያዘልን ተስፋ የሚናገረውን እንዲመረምሩ እያበረታታሁ ነው። (እንደ ራእይ 21:3, 4 የመሳሰሉትን ጥቅሶች አንብብ።) ይህ ነገር መልካም ሆኖ አይታይህም?’
የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
● ‘የመጣሁት ቋሚ የሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመስጠት እንደምችል ለመግለጽ ነው። ፈቃድዎ ከሆነ ለጥቂት ደቂቃዎች ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በየቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር እንዴት እንደሚያጠኑ ባሳይዎት ደስ ይለኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከቀረቡት ርዕሶች መካከል የፈለግነውን መርጠን ልንወያይበት እንችላለን። (በማስጠኛው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን የርዕሶች ዝርዝር አሳይ።) ከእነዚህ ርዕሶች መካከል በተለይ ለማወቅ የሚፈልጉት ስለየትኛው ነው?’
● ‘ለጐረቤቶቻችን ይህን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተዘጋጀ መጽሐፍ እያሳየናቸው ነው። (አሳይ) ከዚህ ቀደም አይተውት ያውቃሉ? . . . ጥቂት ደቂቃ ካለዎት በራስዎ መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በመጽሐፉ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ላሳይዎ እችላለሁ።’
የፍትሕ መጓደል/መከራ
● ‘አምላክ በሰዎች ላይ ስለደረሰው የፍትሕ መጓደልና መከራ ግድ ይኖረው ይሆን? ብለው አስበው ያውቃሉ? . . . (መክ. 4:1፤ መዝ. 72:12–14)’ (በተጨማሪም “መከራ” እና “ማበረታቻ” በሚሉት ዋና ርዕሶች ሥር ያለውን ተመልከት።)
መንግሥት
● ‘ከጐረቤቶቼ ጋር በምነጋገርበት ጊዜ ብዙዎቹ ጎረቤቶቼ ዛሬ ያጋጠሙንን ትልልቅ ችግሮች ማለትም ወንጀልንና ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን (ወይም ሌሎች በሰዎች አእምሮ የሚጉላሉ ችግሮችን) ሊያስወግድላቸው በሚችል መንግሥት ሥር መኖር እንደሚፈልጉ ልገነዘብ ችያለሁ። በእርግጥም ይህ የሚፈለግ ነገር ነው፤ እርስዎስ በዚህ አይስማሙም? . . . በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ የመሰለ መንግሥት ይገኛል? . . . ብዙ ሰዎች እነዚህን ችግሮች የምታስወግድላቸው መንግሥት እንድትመጣ ሲጸልዩ ቆይተዋል። እርስዎም ይህች መንግሥት እንድትመጣ ጸልየው እንደሚያውቁ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ይህች መንግሥት መስተዳድር እንደሆነች አይገነዘቡም። (ዳን. 2:44፤ መዝ. 67:6, 7፤ ሚክ. 4:4)’ (በተጨማሪም በገጽ 226–233 እና 152–157 “መንግሥት” እና “መስተዳድር” በሚሉት ዋና ርዕሶች ሥር ያለውን ተመልከት።)
● ‘ጐረቤቶቻችንን አንድ ጥያቄ እየጠየቅናቸው ነው። እርስዎም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢሰጡ ደስ ይለናል። እንደሚያውቁት ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ፣ ፈቃዱም በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር እንድትሆን እንድንጸልይ አስተምሮናል። በእርግጥ ይህ ጸሎት መልስ አግኝቶ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ የሚሆን ይመስልዎታል? . . . (ኢሳ. 55:10, 11፤ ራእይ 21:3–5)’
● ‘ሁላችንንም ስለሚነካ አንድ ጉዳይ ከጐረቤቶቼ ጋር እየተወያየሁ ነው። የምንመርጠው የአምላክን መንግሥት ነው ወይስ የሰውን አገዛዝ? ዛሬ ከሚታየው የዓለም ሁኔታ አንጻር ሲታይ ሰዎች እስከዛሬ ካመጧቸው የበለጡ ነገሮች እንደሚያስፈልጉን አይሰማዎትም? . . . (ማቴ. 6:9, 10፤ መዝ. 146:3–5)’
የመጨረሻ ቀኖች
● ‘የመጣነው በዛሬው ጊዜ በዓለም ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉት ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸው ለመወያየት ነው። ብዙ ሰዎች ለአምላክና አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ላሰፈራቸው የአኗኗር ሥርዓቶች የነበራቸው አክብሮት በጣም እየቀነሰ መጥቷል። ይህም በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል። ፈቃድዎ ከሆነ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ የተመዘገበውን መግለጫ ላንብብልዎትና ከዘመናችን ሁኔታ ጋር ይስማማ ወይም አይስማማ እንደሆነ ይንገሩኝ። (አንብበው) . . . ወደፊት የተሻለ ሁኔታ ይመጣል ብሎ ለመጠበቅ ጥሩ ምክንያት ያለ ይመስልዎታል? (2 ጴጥ. 3:13)’
● ‘ብዙ ሰዎች የዚህ ዓለም መጥፊያ እየተቃረበ ነው ብለው ያምናሉ። ይህ የአሁኑ ጊዜ “የመጨረሻ ቀን” እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ዓለም ጥፋት ለመዳንና ገነት በምትሆን ምድር ላይ እንዴት ለመኖር እንደምንችል የሚናገር መሆኑን ያውቃሉ? (ሶፎ. 2:2, 3)’ (በተጨማሪ በገጽ 234–243 ላይ “የመጨረሻ ቀኖች” በሚል ዋና ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)
እንዲሁም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለመግቢያነት ስለሚያገለግሉ ሐሳቦች በተሰጠው ዝርዝር ላይ “ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎች” በሚል ርዕስ የቀረበውን ሐሳብ ተመልከት።
ሕይወት/ደስታ
● ‘ስለ ሕይወት ትርጉም አጥብቀው የሚያስቡ ሰዎችን ለማግኘት ጐረቤቶቻችንን እያነጋገርን ነው። አብዛኞቹ ሰዎች መጠነኛ ደስታ አላቸው። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ብዙ ችግሮችም አሉባቸው። በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ ሕይወታችን በጣም አጭር እንደሆነ እንገነዘባለን። ሕይወታችን በዚህ በአሁኑ ዕድሜ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ታስቦ ነበር? ምን ይመስልዎታል? . . . (አምላክ በኤደን ውስጥ ለሰው ልጅ የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ግለጽ፤ ከዚያም ዮሐንስ 17:3ን እና ራእይ 21:3, 4ን ጥቀስ።)’ (በተጨማሪ በገጽ 243–248 ላይ “ሕይወት” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ያለውን ተመልከት።)
● ‘ዛሬ ጎረቤቶቻችን “የዘላለም ሕይወት” የሚለውን አነጋገር ከመጽሐፍ ቅዱስ በሚያነቡበት ጊዜ ምን እንደሚታሰባቸው እየጠየቅን ነው። ይህ አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 40 ጊዜ ያህል የተጠቀሰ በመሆኑ ትኩረታችንን ይስባል። ይህ ዓይነቱ ሕይወት ለእኛ ምን ትርጉም አለው? . . . እንዴትስ ልናገኘው እንችላለን? (ዮሐ. 17:3፤ ራእይ 21:4)’
● ‘በአሁኑ ጊዜ ያለው የኑሮ ሁኔታ ከልብ ከሚያሳስባቸው ሰዎች ጋር እየተነጋገርን ነው። አብዛኞቻችን በሕይወት መኖራችን ያስደስተናል። ይሁን እንጂ ብዙዎች እውነተኛ ደስታ ያለበት ሕይወት ማግኘት ይቻል ይሆን? ብለው ይጠይቃሉ። እርስዎስ ስለዚህ ነገር ምን ይሰማዎታል? . . . በዛሬው ጊዜ ለደስታ መጥፋት ምክንያት የሆነው ዋነኛ ችግር ምንድን ነው ይላሉ? . . . (መዝ. 1:1, 2፤ የቤቱን ባለቤት ስላሳሰበው ጉዳይ የሚገልጹ ሌሎች ተስማሚ ጥቅሶችን ጥቀስ።)’
ፍቅር/ደግነት
● ‘ብዙ ሰዎች እውነተኛ ፍቅር ከዓለም ላይ መጥፋቱ በጣም እንዳሳሰባቸው ተገንዝበናል። እርስዎስ እንደዚህ ይሰማዎታል? . . . ይህ የሆነው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ? . . . መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሁኔታ አስቀድሞ እንደተናገረ ያውቃሉ? (2 ጢሞ. 3:1–4) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የኖረበትንም ምክንያት ጭምር ይገልጻል። (1 ዮሐ. 4:8)’
● ‘ —— እባላለሁ። ከጐረቤቶችዎ አንዱ ነኝ። የመጣሁት በጣም ስላሳሰበኝ ስለ አንድ ጉዳይ ከጐረቤቶቼ ጋር ለአጭር ጊዜ ለመነጋገር ስለፈለግሁ ነው። ይህን ጉዳይ እርስዎም እንዳስተዋሉት እርግጠኛ ነኝ። ደግ መሆን ብዙ ወጪ አይጠይቅም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ደግነት እየጠፋ የሄደ ይመስላል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዴት ሊኖር ቻለ ብለው ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? . . . (ማቴ. 24:12፤ 1 ዮሐ. 4:8)’
እርጅና/ሞት
● ‘ለምን እንደምናረጅና እንደምንሞት ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? አንዳንድ የባሕር ዔሊዎች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይኖራሉ። አንዳንድ ዛፎች ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ኖረዋል። ሰዎች ግን 70 እና 80 ዓመት ብቻ ይኖሩና ይሞታሉ። ይህ ለምን ሆነ? ብለው ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? . . . (ሮሜ 5:12) ይህ ሁኔታ ይለወጥ ይሆን? . . . (ራእይ 21:3, 4)’
● ‘ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ነው ወይስ ከሞት በኋላ ሌላ ነገር አለ? ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? . . . መጽሐፍ ቅዱስ ስለሞት ያለንን ማንኛውንም ጥያቄ በግልጽ ይመልስልናል። (መክ. 9:5, 10) እምነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ተስፋ እንዳላቸውም ይገልጻል። (ዮሐ. 11:25)’ (በተጨማሪም በገጽ 97–104 እንዲሁም 118 ላይ “ሞት” እና “ማበረታቻ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።)
ጦርነት/ሰላም
● ‘በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የኑክሌር ጦርነት ይነሣ ይሆናል የሚል ሥጋት አላቸው። በዚህች ምድር ላይ እውነተኛ ሰላም ሰፍኖ ለማየት የምንችል ይመስልዎታል? . . . (መዝ. 46:8, 9፤ ኢሳ. 9:6, 7)’
● ‘ከጦርነት ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚፈልጉ ሰዎችን እየፈለግሁ ነው። በዚህ መቶ ዘመን ብቻ ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ጦርነቶች ተደርገዋል። አሁን ደግሞ የኑክሌር ጦርነት ሥጋት በፊታችን ተጋርጧል። እንዲህ የመሰለውን ጦርነት ለማስቀረት ምን የሚያስፈልግ ይመስልዎታል? . . . ሰላማዊ ዓለም ሊያመጣ የሚችለውስ ማን ነው? . . . (ሚክ. 4:2–4)’
● ‘ማንኛውም ሰው ዓለም ሰላም እንድትሆን እንደሚፈልግ ሲናገር እንሰማለን። አብዛኞቹ የዓለም መሪዎችም ይህንኑ ሲናገሩ ይሰማል። ታዲያ በምድር ላይ ሰላም ማግኘት አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? . . . (ራእይ 12:7–12)’
ብዙ ሰዎች:- ‘የራሴ ሃይማኖት አለኝ’ በሚሉበት ጊዜ
● ‘እንደምን አደሩ። በዚህ ሕንጻ ውስጥ (ወይም በዚህ አካባቢ) የሚኖሩትን ቤተሰቦች እያነጋገርን ነው። አብዛኞቹ ሰዎች የራሳቸው ሃይማኖት እንዳላቸው ነግረውናል። እርስዎም የራስዎ ሃይማኖት እንዳለዎት አያጠራጥርም። . . . ይሁን እንጂ የየራሳችን ሃይማኖት ያለን ቢሆንም እንኳ እንደ ኑሮ ውድነት፣ ወንጀል፣ ሕመምና የመሳሰሉት ችግሮች በጋራ እየታገሉን ነው። አይደለም? . . . ለእነዚህ ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ የሚገኝ ይመስልዎታል? . . . (2 ጴጥ. 3:13 ወዘተ)’
ብዙ ሰዎች:- ‘ሥራ አለብኝ’ በሚሉበት ጊዜ
● ‘ጤና ይስጥልን። አንድ ትልቅ መልእክት ይዘን በዚህ አካባቢ የሚኖሩትን ሁሉንም ሰዎች እያነጋገርን ነው። ሥራ ያለብዎት መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ ስለዚህ መልእክቱን በአጭሩ እነግርዎታለሁ።’
● ‘ሰላም። —— እባላለሁ። ወደዚህ የመጣሁበት ምክንያት ስለ አምላክ መንግሥት በረከቶች ልነግርዎትና እኛም ከእነዚህ በረከቶች እንዴት ተካፋዮች ልንሆን እንደምንችል እንድንወያይ ነው። ነገር ግን አሁን እንደማየው ሥራ ላይ ነዎት (ወይም ከቤት ሊወጡ ነው።) አንድ አጠር ያለ ሐሳብ ነግሬዎት ብንለያይስ?’
በተደጋጋሚ በተሠራበት የአገልግሎት ክልል
● ‘እቤት ስላገኘሁዎት ደስ ብሎኛል። በዚህ አካባቢ ሳምንታዊ ጉብኝታችንን እያደረግን ነው። የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘር ስለምታደርጋቸው አስደናቂ ነገሮች ተጨማሪ ነገር ልናካፍልዎት እንፈልጋለን።’
● ‘ጤና ይስጥልኝ። በድጋሚ መገናኘታችን ያስደስታል። ቤተሰብ ሁሉ ደህና ነው? . . . አንድ ነገር ልነግርዎት ነው ጎራ ያልሁት። እርሱም . . . ’
● ‘እንደምን አደሩ። ደህና ነዎት? . . . ከእርስዎ ጋር የምነጋገርበትን ሌላ አጋጣሚ ለማግኘት ስፈልግ ነበር። (ከዚህ በኋላ ለመወያየት የፈለግኸውን ርዕሰ ጉዳይ ተናገር።)’