ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ስታገኝ ተመልሰህ ጠይቃቸው
1 ብዙዎቻችን መጽሔቶችንና ብሮሹሮችን በማሰራጫት በኩል ተሳክቶልናል። ተመልሰን መሄዳችንና ሰዎች ተጨማሪ ፍላጎት እንዲያሳዩ ለማነቃቃት መሞከራችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ስናደርግ የተሳካ ውጤት ማግኘታችንና አለማግኘታችን የተመካው ተመላልሶ መጠየቅ ከማድረጋችን በፊት በምናደርገው ዝግጅት ላይ ነው።
2 ዝግጅት የሚጀምረው ከቤት ወደ ቤት መዝገባችን ላይ ዝርዝር ሁኔታዎችን በመያዝ ነው። መጀመሪያ ላይ ስትገናኙ በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተወያይታችሁ እንደነበርና ሰውዬው ምን ተሰምቶት እንደነበር በማስታወሻህ ላይ ጻፍ። ተመልሰህ ስትሄድ ምን ብለህ ውይይት እንደምትጀምር ሳይቀር በማስታወሻ መያዝ ትፈልግ ይሆናል።
3 ለምሳሌ የሚያዝያ 15 “መጠበቂያ ግንብ” ን አበርክተህ ከነበረ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አጠር ያለ አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ፦
◼ “በቀደም ዕለት መጥቼ ሳለ በዛሬው ጊዜ እምነት የሚጣልበት አመራር ከየት ማግኘት እንደሚቻል ተወያይተን ነበር። ከዚህ ሐሳብ ጋር በተያያዘ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የሚለው ይህ ብሮሹር ወደፊት የሚፈጸሙትን አስተማማኝ የአምላክ ተስፋዎች እንዴት እንደሚያስረዳ ልብ ብለው ይመልከቱ።” ከዚያም በክፍል 10 ገጽ 22 መግቢያ ላይ ባሉት ሐሳቦች ተጠቅመህ የአምላክ ፈቃድ በምድር ሲሆን በረከት የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ አስረዳው።
4 ብሮሹር ስታበረክት የምትጠቀምበት ሌላው አቀራረብ እንዲህ ሊሆን ይችላል፦
◼ “ባለፈው ጊዜ የዚህች ምድር የወደፊት ዕጣ ምን እንደሚሆን ባደረግነው አጠር ያለ ውይይት ተደስቻለሁ። እዚህ ላይ እንደሚታየው አምላክ ከዚህች ምድር ላይ ክፋትንና መከራን ሲያጠፋ ምን ዓይነት ኑሮ ይኖራል ብለው ይገምታሉ? [የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? — እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ? በሚለው ብሮሹር በገጽ 31 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው።] በገጽ 29, 30 ላይ ያሉት እነዚህ ጥቅሶች ሁሉ የአምላከ መንግሥት የምታመጣቸውን በረከቶች እንደሚገልጹ ይመልከቱ። [አንድ ጥቅስ ምረጥና ቀጥታ ከብሮሹሩ ላይ አንብብለት።] ይህን ብሮሹር ቢወስዱ ደስ ይለኛል።”
5 ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ ሰውዬው የራሱን ሃይማኖታዊ ጽሑፍ እንደሚያገኝና ሌላ ሃይማኖታዊ ጽሑፍ እንደማያስፈልገው አድርጎ እንደሚያስብ ይነግርህ ይሆናል። እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “ሃይማኖታችን ምንም ቢሆን ሁላችንም ስጋት የሚፈጥሩብን እንደ ወንጀል፣ ከባድ ሕመምና የአካባቢ ሁኔታዎች የመሳሰሉ አንድ ዓይነት ችግሮች አሉብን። አይደለም እንዴ? [ሐሳብ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ለእነዚህ ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ይኖራል ብለው ያስባሉ? [2 ጴጥሮስ 3:13] የጽሑፎቻችን ዓላማ በመጠበቂያ ግንብ በገጽ 2 ላይ ተገልጿል። [የመረጥከውን አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር አንብብለት።] ጽሑፎቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጠቃሚ መልእክቶችን ስለያዙ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ብዙ ሰዎች እነርሱን ማንበብ ያስደስታቸዋል።” ከዚያም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማችን ልታስረዳው ትችላለህ።
6 እንዲህ ባለ አቀራረብ ትጠቀም ይሆናል፦
◼ “በቀደም ዕለት መጥቼ ሳለ ዓለማችን ወደፊት ስለሚኖራት ሁኔታ ተነጋግረን ነበር። ስለዚህ ዜና ምን ይሰማዎታል? [በቅርቡ የተሰራጩ አሳሳቢ የሆኑ ዜናዎችን ጥቀስ።] ሰዎች እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን ሲሰሙ ይህ ዓለም መጨረሻው ምን ይሆን ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። አያደርግም እንዴ? እነዚህ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ እንደተተነበየው ‘በመጨረሻው ቀን’ እንደምንኖር ያመለክታሉ ብለን እናምናለን።” ጎላ ብለው የሚታዩትን ሐሳቦች ካነበብክ በኋላ በጥቅሱ ላይ ከተገለጹት ባሕርያት ጋር የሚመሳሰል ጠባይ ያላቸው ሰዎችን አይቶ ያውቅ እንደሆነ ልትጠይቅው ትችላለህ። ምክንያቱን ማስረዳት ከተባለው መጽሐፍ በገጽ 234–8 ላይ ካሉት ንዑስ ርዕሶች በአንዱ ላይ መወያየታችሁን ቀጥሉ።
7 በደንብ ከተዘጋጀንና ሌሎችን ለመርዳት እውነተኛ ፍላጎት ካሳየን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንደሚሰሙን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። — ዮሐ. 10:27, 28