ጽሑፍ የተበረከተላቸውን ሰዎች ሁሉ ተከታትለህ እርዳ
1 ኢየሱስ ተከታዮቹን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ተግተው እንዲሠሩ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 28:19) ይህም ጽሑፎችን በማበርከት ብቻ የሚከናወን አይደለም። ሰዎች በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ለመርዳት እንፈልጋለን። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተጨማሪ እርዳታ ለመስጠት ተመልሰን መሄድ አለብን።
2 በመጀመሪያ ጉብኝትህ ወቅት ከመጽሔቶችህ በአንዱ ውስጥ በሚገኝ አንድ ርዕስ ተጠቅመህ አነጋግረህ ከነበረ ተመልሰህ ስትሄድም በዚያው ርዕስ ላይ መወያየቱ ጥሩ ይሆናል፦
◼ “ባለፈው ጊዜ መጥቼ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ በሚረዳ ከመጠበቂያ ግንብ (ወይም ከንቁ!) ላይ ባለ አንድ ርዕስ ላይ ተነጋግረን ነበር። አምላክ ለሰው ልጆች የተሻለ ጊዜ ለማምጣት ያለው ዓላማ ከንጉሣዊ መስተዳድሩ ጋር የተያያዘ ነው። ሚክያስ 4:3, 4 ይህ መንግሥት ሁሉንም ጦርነቶች እንደሚያስቆም አምላክ የሰጠውን ተስፋ መዝግቧል።” ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ “እነሆ!” የተባለውን ብሮሹር አስተዋውቀህ በሽፋኑ ላይ ያለውን ሥዕላዊ መግለጫ አሳየው። የመጀመሪያውን አንቀጽና ለአንቀጹ የተሰጡትን ጥቅሶች (በገጽ 4 ላይ) አንብብለት። ከጥቅሶቹ መካከል አንዱ ሚክያስ 4:3, 4 መሆኑን አሳየው። ውይይቱን በአንቀጽ 2 ላይ ለመቀጠል ተመልሰህ ስለምትመጣበት ሁኔታ ተነጋገሩ።
3 ሰውዬው ኮንትራት ለመግባት ዝግጁ ካልሆነ ስሙን በመጽሔት ደንበኞችህ መመዝገቢያ ላይ ለመመዝገብ ትወስን ይሆናል፦
◼ “ባለፈው ጊዜ በተውኩልዎት መጽሔቶች እንደተደሰቱ ስለገለጹ በቅርቡ የወጡትን እትሞች ለማግኘት የሚፈልጉ ይመስለኛል። በተለይ ይህ ርዕስ ያስደስትዎታል ብዬ አምናለሁ።” ይስበዋል ብለህ ያሰብከውን ርዕስ አሳየው። ወደፊት የሚወጡትን እትሞች ይዠልዎት ብመጣስ? ብለህ ጥያቄ አቅርብለት።
4 በመጀመሪያው ቀን ትራክት አበርክተህለት ከነበረ ባበረከትኸው ትራክት ላይ ልታወያየው ካለዚያም በቅርብ ጊዜ በወጣ መጽሔት ወይም ብሮሹር ላይ የሚገኝ አንድ ተስማሚ ነጥብ በመጥቀስ ታነጋግረው ይሆናል።
ለምሳሌ “ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት” የሚለውን ትራክት አበርክተህ ከነበረ እንዲህ በል፦
◼ “ባለፈው ጊዜ መጥቼ ሳለ አምላክ የተሻለ ዓለም ለማምጣት ስለሰጠው ተስፋ ተነጋግረን ነበር። እንደተወያየነው የተሻሉ ሁኔታዎች የሚመጡት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ነው። ሰላም የሰፈነበት የዚህ አዲስ ዓለም ክፍል ለመሆን ምን ማድረግ የሚፈለግብን ይመስልዎታል?” ሰውዬው ሐሳብ እንዲሰጥ ፍቀድለት፤ ከዚያም በመዝሙር 37:9, 11, 29 ላይ ባሉት ሐሳቦች ላይ ማወያየትህን ቀጥል።
5 ያበረከትከው ብሮሹር ከነበረና አብራችሁ እንዴት ማጥናት እንደምትችሉ ለማሳየት አጋጣሚው ካልነበረህ ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ እንዴት እንደምታጠኑት ለማሳየት እቅድ አውጣ።
ለምሳሌ “መንግሥት” የሚለውን ብሮሹር አብርክተህ ከነበረ ሰውዬው የራሱን ቅጂ እንዲያመጣ ጠይቅውና እንዲህ በለው፦
◼ “ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ይሰብከው ስለነበረው መልእክት ዋና ቁም ነገር ገጽ 3 ምን እንደሚል እንመልከት።” ከዚያም በገጽ 3 ላይ ስላለው ሐሳብ አጠር ያለ ማብራሪያ ስጥ። የበለጠ ለማወቅ ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ እንደሚያስብ ሰውዬውን ጠይቀው። ከዚያም እንዲህ በል:- “የአምላክ መንግሥት ለምን እንደምታስፈልገን መገንዘባችን በጣም አስፈላጊ ነው። ተስፋ ማድረግ ያለብን በአምላክ መንግሥት ላይ ብቻ መሆን ያለበት ለምን እንደሆነ ለመወያየት ተመልሼ ብመጣ ደስ ይለኛል።”
6 ልዩ ልዩ ብሮሹሮችና የተለያዩ ርዕሶችን የያዙ መጽሔቶች አሉን። እጠቀምበታለሁ ብለህ ባቀድከው ብሮሹር ወይም መጽሔት ላይ ሰዎችን የሚስቡ ነጥቦች ፈልግ። ይህን ማድረግህ ኢየሱስ ስላዘዛቸው ነገሮች የበለጠ ለማወቅ ከልብ የሚፈልጉትን ሰዎች ማበረታታት እንድትችል ይረዳሃል። — ማቴ. 28:20