ሌሎች አንድን ታላቅ ሀብት እንዲያውቁ መርዳት
1 የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ከምንሰብክባቸው ዓላማዎች አንዱ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች የአምላክን ቃል የላቀ ጥቅም እንዲገነዘቡት መርዳት ሊሆን ይገባል። (ፊል. 3:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ጽሑፎቻችን የመንግሥቱን መልእክት በማሠራጨቱ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። ለምሳሌ ያህል ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመማራቸው ምክንያት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ ረድቷቸዋል።
2 አገልግሎታችን ጽሑፍ ለመውሰድ ፈቃደኛ ለሆነ ሁሉ ጽሑፍ በማደል ብቻ አያበቃም። መልዕክቱን በሚስብ መንገድ ካቀረብንና ሰውየው የሚናገረውን ነገር ልብ ብለን ካዳመጥን በኋላ ‘ከቅዱሳን ጽሑፎች በመጥቀስ በሚገባ ማስረዳት’ ያስፈልገናል። — ሥራ 17:2
3 እንደዚህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መግቢያዎቻችን ሰዎቹ ለመጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ ላለው መልእክት እውነተኛ ፍላጎት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ለማወቅ መንገድ ይከፍቱልናል።
እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “ወደ ቤትዎ የመጣነው በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን ነገሮች ትርጉም ለመወያየት ነው። ብዙ ሰዎች አምላክ አኗኗራችንን በተመለከተ ላወጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኙት የአቋም ደረጃዎች ደንታ የሌላቸው እየሆኑ መጥተዋል። ይህም ሥነ ምግባር እያዘቀጠ እንዲሄድ ከማድረጉም በላይ ሰዎች እርስ በርሳቸው ባላቸው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህንን ነገር አስተውለውታል? [አስተያየቱን እንዲሰጥ ፍቀድለት። የተከሰቱትን አንዳንድ ነገሮች ልትጠቅስለት ትችላለህ።] እስቲ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ የተጠቀሱትን ሰዎች ጠባይ ይመልከቱና በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ ይህ እንደሆነና እንዳልሆነ ይንገሩኝ። [አንብብ። አስተያየቱን እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሚያሳምን ምክንያት ያለ ይመስልዎታል?” ፍላጎት ካሳየ ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 12ና 13 ላይ ያለውን ስዕል አሳየውና በአንቀጽ 12ና 13 ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ያሳየው ፍላጎት ያን ያህል ካልሆነ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም የተባለውን ትራክት ልትሰጠው ትችላለህ።
4 በሩን የከፈተው ወላጅ ከሆነ ውይይታችንን በዚህ መንገድ ለመጀመር እንችላለን፦
◼ “በቤተሰብ ሕይወት ላይ የሚደርሱትን ችግሮች እንዴት በተሻለ መንገድ ለመቋቋም እንደምንችል ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር እየተወያየን ነበር። ሁላችንም ትዳራችን የተሳካ እንዲሆን የምንችለውን ያህል ለማድረግ ብንጥርም የበለጠ መልካም ውጤት እንድናገኝ ሊረዳን የሚችል ነገር ብናገኝ ደስ ይለናል፤ አይደለም እንዴ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ መመሪያ ይሰጠናል። ለምሳሌ በቆላስይስ 3:12–14 ላይ እንዲህ ይላል። [አንብብለት።] ስለዚህ የተቃና የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ‘የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ’ የሚል ርዕስ ባለው ምዕራፍ ላይ የተብራራውን እስቲ ይመልከቱት።” ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 238 አንቀጽ 3ን አንብብለት። “ለመጽሐፉ ማሳተሚያ አስተዋፅዖ ይሆን ዘንድ አምስት ብር ብቻ በመክፈል መጽሐፉን ቢወስዱ ደስ ይለኛል።” ሰውየው ሥራ ይዞ ከሆነ ወይም መጽሐፉን ለመውሰድ ቢያቅማማ በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ የሚሰጥ በቅርቡ የወጣ አንድ መጽሔት ወይም በቤተሰብህ ኑሮ ተደሰት የሚለውን ትራክት ለማበርከት ሞክር።
5 ዓላማችን ስለ መንግሥቲቱ የተሟላ ምስክርነት መስጠት መሆኑን ፈጽሞ ለመርሳት አንፈልግም። (ማቴ. 24:14) በዚህ ታሪካዊ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስና ባሉን ጥሩ ጥሩ ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎች በሚገባ በመጠቀም የይሖዋን ዓላማ ስንፈጽም ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። — ገላ. 6:9