ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ፍላጎት ለመቀስቀስ ተመልሶ መሄድ
1 አንዳንድ ጊዜ ለምሥራቹ መጠነኛ ፍላጎት የሚያሳዩ ነገር ግን ሥራ ስለበዛባቸው ሊያነጋግሩን ያልቻሉ ሰዎች እናገኛለን። ለእነዚህ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማካፈል በሌላ ጊዜ ተመልሰን ለማነጋገር ጥረት እናደርጋለንን? ወይም ደግሞ ከቤቱ ባለቤት ጋር ጥሩ ውይይት አድርገን ነገር ግን ምንም ጽሑፍ አልወሰደ ይሆናል። ከእሱ ጋር ስለ እውነት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ተመልሰን እንሄዳለንን?
2 የአገልግሎት ክልላችንን አጣርተን መሸፈንና ያገኘናቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ሁሉ ተከታትለን መርዳት በጣም አስፈላጊ ነው። ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርገው መጽሐፍ ወይም መጽሔቶችን ለወሰዱ ሰዎች ብቻ ነውን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አንዳንድ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ቸል ብለን እያለፍን ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ጽሑፍ ስላልወሰደ ብቻ ተጨማሪ መንፈሳዊ ማበረታቻ አያስፈልገውም ብለን ልንፈርድበት አንፈልግም። (ከሮሜ 14:4 ጋር አወዳድር።) ምናልባት እኛ ካነጋገርነው በኋላ የቤቱ ባለቤት የተናገርነውን ነገር ሊያስብበት ወይም እሱን ለማነጋገር ያደረግነውን ጥረት ሊያደንቅ ይችላል። ተመልሰን በምንሄድበት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ሊቀበለን ይችል ይሆናል።
3 ከዚህ በፊት ባነጋገርከው ጊዜ ሥራ በዝቶበት የነበረውን ሰው ተመልሰህ ስታነጋግር እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “እርስዎን እንደገና በማግኘቴ ደስ ብሎኛል። ባለፈው ጊዜ መጥቼ ሳለ ሥራ ስለበዛብዎት ልንነጋገር አልቻልንም ነበር። እርስዎ ሥራ እንደሚበዛብዎት እመለከታለሁ። ስለዚህ ንግግሬን አሳጥራለሁ። ስለራስዎና ስለሚያፈቅሯቸው ሰዎች ጤንነት እንደሚያስቡ ምንም አያጠራጥርም። ሆኖም አምላክ ማንኛውንም በሽታ ለማጥፋት ቃል እንደገባ ያውቁ ነበርን? ይህ አስደሳች ተስፋ አይደለምን? [የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በዚህ “እነሆ! ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” በተባለው ብሮሹር በአንቀጽ 4 ላይ ያለውን ነጥብ ልብ ይበሉ።” ጊዜ ካለህ አንቀጹን አንብብና ከዚያም በገጽ 4 መጨረሻ ላይ ካሉት በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው ሁኔታ ከሚገልጹት ጥቅሶች አንዱን ተወያዩበት። የቤቱ ባለቤት ፈቃደኛ ከሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትጀምርለት ትችል ይሆናል።
4 ቀደም ሲል ትራክት ወስዶ የነበረውን ሰው በድጋሚ በምታነጋግርበት ጊዜ ቀጥሎ ያለውን በሚመስል አንድ ሐሳብ ልትጠቀም ትችላለህ፦
◼ “ባለፈው ጊዜ መጥቼ ሳነጋግርዎት በእርግጥ ዓለምን የሚገዛው ማን ነው? የሚለውን አንድ ትራክት ወስደው ነበር። ይህን ዓለም ሰይጣን የሚገዛው መሆኑን ማመን አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታልን? [የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በገጽ 6 ላይ ያለው የመጀመሪያ አንቀጽ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ።” አንቀጹን አንብብና እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- “ሰይጣን እኛን ለማሳሳት የሚፈልገው ለምንድን ነው?” የቤቱ ባለቤት መልስ ከሰጠ በኋላ በገጽ 3 ላይ ያለውን አራተኛውን አንቀጽ አብራችሁ ተወያዩበት። ትራክቱን አንድ በአንድ በመመርመር ልትቀጥሉ ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለውን ብሮሹር ልታስተዋውቀውና በገጽ 13 አንቀጽ 8 ላይ ያለውን ሐሳብ ልታወያየው ትፈልግ ይሆናል።
5 ምንም እንኳን ያሳዩት ፍላጎት መጠነኛ ቢሆንም በስብከት ሥራችን ያገኘነውን እንዲህ ያለውን ፍላጎት ተከታትለን ለመርዳትና ይሆናል የሚል አመለካከት ለመያዝ ጥሩ ምክንያት አለን። ለሌሎች አሳቢ በመሆን እውነትን እንዲማሩ ለመርዳት መገፋፋት በጣም አስፈላጊ ነው። የይሖዋ ድርጅት ሌሎች ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁዎች እንዲሆኑ ለመርዳት የሚያስችለንን ጽሑፍና የአቀራረብ ዘዴ ታዘጋጅልናለች። — ማቴዎስ 5:3
6 መጠነኛ ፍላጎት ካለው ሰው ጋር አስደሳች ውይይት አድርገህ ከነበረ ፍላጎቱን ለመኮትኮት ተመልሰህ ማነጋገሩን ቸል አትበል። ይህም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምርና በሕይወት መንገድ እንዲጓዝ ሊያደርገው ይችላል። በዚህ ሕይወት አድን በሆነው ሥራ በትጋት መካፈላቸውን እንዲቀጥሉ ሁሉንም እናበረታታለን። — 1 ጢሞቴዎስ 4:16