እሁድ፣ ነሐሴ 31
ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው . . . ይረዱታል።—ዳን. 12:10
የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጨርሶ የማታውቀውን ቦታ ለመጎብኘት አስበሃል እንበል። ሆኖም አብሮህ የሚጓዘው ጓደኛህ አካባቢውን በደንብ ያውቀዋል። የት እንዳላችሁ እንዲሁም እያንዳንዱ መንገድ ወዴት እንደሚያመራ ጠንቅቆ ያውቃል። ጓደኛህ አብሮህ ለመምጣት በመስማማቱ በጣም እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም ይሖዋ በጊዜ ሰሌዳ ላይ የቱ ጋ እንዳለን እንዲሁም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ያውቃል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን ይሖዋ እንዲረዳን በትሕትና ልንጠይቀው ይገባል። (ዳን. 2:28፤ 2 ጴጥ. 1:19, 20) እንደ ማንኛውም ጥሩ ወላጅ፣ ይሖዋ ልጆቹ ወደፊት ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል። (ኤር. 29:11) ሆኖም ከሰብዓዊ ወላጆች በተለየ መልኩ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ትንቢት መናገር ይችላል። ወሳኝ የሆኑ ክንውኖች ከመከሰታቸው በፊት እንድናውቅ ሲል ትንቢቶች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል።—ኢሳ. 46:10፤ w23.08 8 አን. 3-4
ሰኞ፣ መስከረም 1
እንደ ንጋት ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ከላይ ይወጣልናል።—ሉቃስ 1:78
አምላክ ለኢየሱስ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ለመፍታት የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት በራሳችን ፈጽሞ ልናሸንፋቸው የማንችላቸውን ችግሮች የመቅረፍ ኃይል እንዳለው ያሳያሉ። ለምሳሌ የሰው ልጆች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የሆነውን በዘር የወረስነውን ኃጢአት እንዲሁም የኃጢአት ውጤት የሆኑትን በሽታንና ሞትን ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው። (ማቴ. 9:1-6፤ ሮም 5:12, 18, 19) “ማንኛውንም ዓይነት” በሽታ የመፈወስ፣ አልፎ ተርፎም ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው የፈጸማቸው ተአምራት ያሳያሉ። (ማቴ. 4:23፤ ዮሐ. 11:43, 44) በተጨማሪም ኃይለኛ ማዕበልን ጸጥ የማሰኘት እንዲሁም ክፉ መናፍስትን የማስወጣት ችሎታ አለው። (ማር. 4:37-39፤ ሉቃስ 8:2) ይሖዋ ለልጁ እንዲህ ያለ ኃይል እንደሰጠው ማወቅ በእርግጥም የሚያጽናና ነው። የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች የሚናገሩት ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የፈጸማቸው ተአምራት በሰማይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በስፋት ስለሚያከናውነው ሥራ ያስተምሩናል። w23.04 3 አን. 5-7
ማክሰኞ፣ መስከረም 2
መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።—1 ቆሮ. 2:10
ጉባኤያችሁ ብዙ አስፋፊዎች ካሉትና ብዙ ጊዜ የመመለስ ዕድል የማታገኙ ከሆነ ተስፋ ልትቆርጡ ትችላላችሁ። ሆኖም መልስ ለመመለስ መሞከራችሁን አታቁሙ። ለእያንዳንዱ ስብሰባ በርከት ያሉ መልሶችን ተዘጋጁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በስብሰባው መጀመሪያ አካባቢ ሐሳብ የመስጠት ዕድል ባታገኙም እንኳ ስብሰባው ሲቀጥል አጋጣሚ ልታገኙ ትችላላችሁ። ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጁ እያንዳንዱ አንቀጽ ከዋናው ጭብጥ ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ በተለያዩ አንቀጾች ላይ የምትሰጡት ሐሳብ መኖሩ አይቀርም። በተጨማሪም ለማስረዳት የሚከብዱ ጥልቅ እውነቶችን በያዙ አንቀጾች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ልትዘጋጁ ትችላላችሁ። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ባሉ አንቀጾች ላይ እጃቸውን የሚያወጡት ሰዎች ቁጥር ያን ያህል ብዙ ላይሆን ይችላል። ይሁንና ሐሳብ የመስጠት ዕድል ሳታገኙ የተወሰኑ ስብሰባዎች ቢያልፉስ? ከስብሰባው በፊት ወደ መሪው ሄዳችሁ በመረጣችሁት አንቀጽ ላይ ሐሳብ የመስጠት ዕድል እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። w23.04 21-22 አን. 9-10