ሰዎች ጦርነትን ማስቀረት አይችሉም
ጦርነት እና ግጭት የሚቀረው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ የሚያስወግደው’ አምላክ እንጂ ሰዎች እንዳልሆኑ ይናገራል።—መዝሙር 46:9
አምላክ የዓለም መንግሥታትን ያጠፋል
አምላክ በአንድ ጦርነት አማካኝነት የዓለም መንግሥታትን ያጠፋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጦርነት “የአርማጌዶን ጦርነት” በማለት ይጠራዋል።a (ራእይ 16:16) በዚያ ወቅት ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ “ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚካሄደው ጦርነት” ይሰበሰባሉ። (ራእይ 16:14) አርማጌዶን አምላክ ጦርነቶችን ሁሉ ለማስወገድ የሚያካሂደው ጦርነት ነው።
አምላክ የዓለምን መንግሥታት በራሱ መንግሥት ይተካቸዋል። ይህ መንግሥት የሚገዛው ከሰማይ ሲሆን ፈጽሞ አይጠፋም። (ዳንኤል 2:44) አምላክ የዚህ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን መርጦታል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ማቴዎስ 28:18) ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምራቸው ስለዚህ መንግሥትb መናገሩ ነበር። (ማቴዎስ 6:9, 10) ሁሉም የሰው ልጆች፣ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድረው አንድ ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ሥር በአንድነት ይኖራሉ።
በዓለም ላይ ካሉ መሪዎች በተለየ መልኩ ኢየሱስ ሥልጣኑን የራሱን ጥቅም ለማራመድ አይጠቀምበትም። እሱ ፍትሐዊና ከአድልዎ ነፃ ስለሆነ ማንም ሰው በዘሩ፣ በብሔሩ ወይም በጎሣው ምክንያት ግፍ አይፈጸምበትም። (ኢሳይያስ 11:3, 4) በተጨማሪም ሰዎች መብታቸውን ለማስከበር መታገል አያስፈልጋቸውም። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የእያንዳንዱ ሰው ደህንነት ያሳስበዋል። “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋል። . . . ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:12-14
የአምላክ መንግሥት የጦር መሣሪያዎችን ከምድር ላይ ጠራርጎ ያስወግዳል። (ሚክያስ 4:3) ከዚህም ሌላ፣ መዋጋታቸውን ወይም የሌሎችን ሰላም ማደፍረሳቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ያልሆኑ ክፉ ሰዎችን ያጠፋል። (መዝሙር 37:9, 10) ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ምንም ዓይነት ስጋት ሳይሰማው ወደ የትኛውም የምድር ክፍል መሄድ ይችላል።—ሕዝቅኤል 34:28
ሰዎች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የተመቻቸ ሕይወት ይመራሉ። ለግጭት መንስኤ የሆኑትን እንደ ድህነት፣ ረሃብና የመኖሪያ ቤት እጦት ያሉ ችግሮች ያስወግዳል። ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ እና ገንቢ የሆነ ምግብ ያገኛል፤ እንዲሁም የሚኖርበት ምቹ ቤት ይኖረዋል።—መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 65:21-23
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ ጦርነት ያስከተላቸው ጉዳቶች በሙሉ ይስተካከላሉ። ይህም አካላዊ ጉዳቶችን ብቻ ሳይሆን ጦርነት የሚያስከትላቸውን አእምሯዊና ስሜታዊ ቁስሎችም ያካትታል። የሞቱ ሰዎችም እንኳ ተነስተው በምድር ላይ ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 25:8፤ 26:19፤ 35:5, 6) ሞት የነጠላቸው ቤተሰቦች ዳግመኛ ይሰባሰባሉ። “ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል” ከተባሉት መካከል ጦርነት ያስከተላቸው መጥፎ ትዝታዎችም ይካተታሉ።—ራእይ 21:4
አምላክ ኃጢአትን ያስወግዳል
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሁሉም ሰዎች የሚያመልኩት ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋንc ነው፤ እሱ “የፍቅርና የሰላም አምላክ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ሰዎች አብረው በሰላም መኖር የሚችሉበትን መንገድ ይማራሉ። (ኢሳይያስ 2:3, 4፤ 11:9) የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ የሚያውሉ ሁሉ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ይወጣሉ።—ሮም 8:20, 21
አምላክ ሰይጣንንና አጋንንቱን ያጠፋል
የአምላክ መንግሥት የጦርነት ጠንሳሽ የሆኑትን ሰይጣንንና አጋንንቱን ያጠፋል። (ራእይ 20:1-3, 10) እነሱ የሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ ሲወገድ “ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7
አምላክ ጦርነትንና ግጭትን ለማስወገድ የገባው ቃል እንደሚፈጸም እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እሱ ጦርነትን ለማስወገድ ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አለው።
አምላክ ጦርነትንና ዓመፅን ለማስወገድ የሚያስችል ጥበብም ሆነ ኃይል አለው። (ኢዮብ 9:4) እሱ ማድረግ የማይችለው ምንም ነገር የለም።—ኢዮብ 42:2
አምላክ ሰዎች ሲሠቃዩ ማየት አይፈልግም። (ኢሳይያስ 63:9) በተጨማሪም “ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው ይጠላል።”—መዝሙር 11:5
አምላክ ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል፤ እሱ ሊዋሽ አይችልም።—ኢሳይያስ 55:10, 11፤ ቲቶ 1:2
አምላክ ወደፊት እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል
አምላክ ጦርነትን ያስወግዳል
a “የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ አንብብ።
b የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።
c ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18