የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 መጋቢት ገጽ 14-19
  • በስብከቱ ሥራ የኢየሱስን ቅንዓት ኮርጁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በስብከቱ ሥራ የኢየሱስን ቅንዓት ኮርጁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቅድሚያ የሰጠው ለይሖዋ ፈቃድ ነው
  • ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረት ሰጥቷል
  • በይሖዋ ድጋፍ ተማምኗል
  • ምንጊዜም አዎንታዊ ነበር
  • በአገልግሎትህ ይበልጥ ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በፍቅር ተነሳስታችሁ መስበካችሁን ቀጥሉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 መጋቢት ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 11

መዝሙር 57 ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መስበክ

በስብከቱ ሥራ የኢየሱስን ቅንዓት ኮርጁ

“ጌታ . . . እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ከተማና ቦታ ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱም ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።”—ሉቃስ 10:1

ዓላማ

አገልግሎትህን በቅንዓት ስለማከናወን ከኢየሱስ ምሳሌ የምትማራቸው አራት ነገሮች።

1. የይሖዋን ሕዝቦች ከዓለም የሚለያቸው አንዱ ባሕርይ ምንድን ነው?

የይሖዋ አገልጋዮችን ከአስመሳይ ክርስቲያኖች የሚለያቸው አንዱ ነገር ለአገልግሎት ያላቸው ቅንዓትa ነው። (ቲቶ 2:14) ያም ሆኖ በቅንዓት መስበክ ትግል የሚሆንብህ ጊዜ ሊኖር ይችላል። አንድ ትጉህ የጉባኤ ሽማግሌ “አንዳንድ ጊዜ ለአገልግሎት ምንም ተነሳሽነት አይኖረኝም” በማለት ስሜቱን ሳይሸሽግ ተናግሯል። አንተም እንደ እሱ ተሰምቶህ ያውቅ ይሆናል።

2. ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ጠብቀን መቀጠል ከባድ የሚሆንብን ለምን ሊሆን ይችላል?

2 ከስብከቱ ሥራ ይልቅ በሌሎች የቅዱስ አገልግሎት ዘርፎች ስንካፈል ይበልጥ እንደሰት ይሆናል። ለምን? ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን ስንገነባና ስንጠግን፣ በእርዳታ አገልግሎት ስንካፈል ወይም ወንድሞቻችንን ስናበረታታ የሥራችንን ውጤት ወዲያው እናያለን፤ ይህም እርካታ ያስገኝልናል። ከወንድሞቻችን ጋር ስንሠራ ያለውን ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት መንፈስ እንወደዋለን፤ ወንድሞቻችን የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር እንደሚያደንቁም እናውቃለን። በሌላ በኩል ግን በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ለዓመታት ብንሰብክም ያን ያህል በጎ ውጤት አላገኘን ይሆናል። ወይም የምናገኛቸው ሰዎች መልእክታችንን ይቃወሙ ይሆናል። ወደ መጨረሻው እየተጠጋን ስንሄድ ደግሞ መልእክታችን ከዚህም ይበልጥ ተቃውሞ እንደሚገጥመው እንጠብቃለን። (ማቴ. 10:22) ታዲያ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ማከናወናችንን ለመቀጠል ብሎም ቅንዓታችንን ለመጨመር ምን ሊረዳን ይችላል?

3. በሉቃስ 13:6-9 ላይ የሚገኘው ምሳሌ የኢየሱስን ቅንዓት ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?

3 የኢየሱስን ምሳሌ መመርመራችን በቅንዓት እንድንሰብክ የሚረዳ ቁም ነገር ያስተምረናል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ቅንዓቱ አልበረደም። እንዲያውም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ጨምሯል። (ሉቃስ 13:6-9⁠ን አንብብ።) ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው የወይን አትክልት ሠራተኛ አንዲትን የበለስ ዛፍ ለመንከባከብ ሦስት ዓመት ቢደክምም ፍሬ አላገኘም፤ ኢየሱስም እንዲሁ ለአይሁዳውያን ሦስት ዓመት ያህል ቢሰብክም አብዛኞቹ ጥሩ ምላሽ አልሰጡም። ይሁንና የወይን አትክልት ሠራተኛው በበለስ ዛፏ ተስፋ እንዳልቆረጠ ሁሉ ኢየሱስም በሕዝቡ ተስፋ አልቆረጠም፤ የአገልግሎት እንቅስቃሴውንም አልቀነሰም። እንዲያውም የሰዎችን ልብ ለመንካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል።

4. ኢየሱስ በየትኞቹ አራት አቅጣጫዎች ምሳሌ ይሆነናል?

4 በዚህ ርዕስ ላይ ኢየሱስ በተለይ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው የመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት ቅንዓት ያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ያስተማረውን ነገር ተግባራዊ ማድረጋችንና ፈለጉን መከተላችን በዛሬው ጊዜ ቅንዓታችንን ጠብቀን ለመቀጠል ይረዳናል። ኢየሱስ ምሳሌ የሚሆንባቸውን አራት አቅጣጫዎች ከዚህ በኋላ እናያለን፦ (1) ቅድሚያ የሰጠው የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ነው፤ (2) ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረት ሰጥቷል፤ (3) በይሖዋ ድጋፍ ተማምኗል እንዲሁም (4) ለመልእክቱ ጆሮ የሚሰጡ ሰዎች እንደሚኖሩ ተስፋ በማድረግ አዎንታዊ ሆኖ ቀጥሏል።

ቅድሚያ የሰጠው ለይሖዋ ፈቃድ ነው

5. ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያሳየው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” በቅንዓት የሰበከው አምላክ እንዲሠራ የፈለገው ሥራ ይህ እንደሆነ ስለተገነዘበ ነው። (ሉቃስ 4:43) አገልግሎቱ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። በአገልግሎቱ መገባደጃ ላይም እንኳ “በየከተማውና በየመንደሩ እያስተማረ” ይጓዝ ነበር። (ሉቃስ 13:22) በተጨማሪም በሥራው አብረውት እንዲሆኑ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት አሠልጥኗቸዋል።—ሉቃስ 10:1

6. ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች ቢኖሩብንም የስብከቱ ሥራ ምን ያህል ቦታ አለው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ዛሬም ይሖዋና ኢየሱስ እንድናከናውነው የሚፈልጉት ተቀዳሚው ሥራ ምሥራቹን መስበክ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች በሙሉ ከስብከቱ ሥራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። ለምሳሌ ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን የምንገነባው ወይም በቤቴል የምናገለግለው መስኩ ላይ የሚከናወነውን ሥራ ለመደገፍ ነው። በእርዳታ አገልግሎት የምንካፈለው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ብቻ ሳይሆን የስብከቱን ሥራ ጨምሮ ወደ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ቶሎ እንዲመለሱ ለመርዳት ነው። የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት መገንዘባችንና ይሖዋ እንድናከናውነው የሚፈልገው ዋነኛ ሥራ መሆኑን ማስታወሳችን አዘውትረን በአገልግሎት ለመካፈል ተነሳሽነት ይፈጥርልናል። በሃንጋሪ የሚኖር ያኖሽ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “የስብከቱ ሥራችንን የሚተካ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ እንደሌለ ለማስታወስ እሞክራለሁ፤ ይህ ዋነኛ ሥራችን ነው።”

ፎቶግራፎች፦ 1. አንድ ወንድም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ሲሠራ። 2. ሌላ ወንድም በቤቴል የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ ከቤቱ ሲሠራ። 3. በኋላ ላይ ሁለቱ ወንድሞች በስብከቱ ሥራ አብረው ሲካፈሉ።

ምሥራቹን መስበክ በአሁኑ ወቅት ይሖዋና ኢየሱስ እንድናከናውነው የሚፈልጉት ተቀዳሚ ሥራ ነው (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7. ይሖዋ መስበካችንን እንድንቀጥል የሚፈልገው ለምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4)

7 ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ለማሳደግ የሚረዳን ለሰዎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት መያዝ ነው። እሱ የሚፈልገው በተቻለ መጠን ብዙዎች ምሥራቹን ሰምተው እውነትን እንዲቀበሉ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4⁠ን አንብብ።) ይህን ሕይወት አድን መልእክት ለሌሎች ስንናገር ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን የሚያሠለጥነንም ለዚሁ ነው። ለምሳሌ፣ ሰዎችን ውደዱ—ደቀ መዛሙርት አድርጉ የተባለው ብሮሹር ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግብ ይዘን ጭውውት መጀመር ስለምንችልበት መንገድ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ይዟል። ሰዎች አሁን ላይ ጆሮ ባይሰጡ እንኳ ወደፊት ታላቁ መከራ ከማብቃቱ በፊት ይህን ማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኙ ይሆናል። ዛሬ የምንነግራቸው ነገር ያን ጊዜ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። መስበካችንን ካልቀጠልን ግን ይህ ሊሆን አይችልም።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረት ሰጥቷል

8. ኢየሱስ የትንቢቶችን ፍጻሜ ማወቁ የጊዜ አጠቃቀሙ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል?

8 ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምን ፍጻሜ እንዳላቸው ተረድቶ ነበር። አገልግሎቱ የሚቆየው ለሦስት ዓመት ተኩል ብቻ እንደሆነ ያውቃል። (ዳን. 9:26, 27) መቼ እና እንዴት እንደሚሞትም ከትንቢት ተረድቷል። (ሉቃስ 18:31-34) ኢየሱስ ስለ ትንቢቶች ያወቀው ነገር በጊዜ አጠቃቀሙ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፤ ይኸውም የተሰጠውን ሥራ በተሰጠው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሲል በቅንዓት ሰብኳል።

9. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በቅንዓት እንድንሰብክ የሚያነሳሱን ለምንድን ነው?

9 እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳታችን በቅንዓት እንድንሰብክ ያነሳሳናል። ይህ ሥርዓት የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ እናውቃለን። ዛሬ በዓለም ሁኔታና በሰዎች ባሕርይ ላይ የምናያቸው ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆኑ እናውቃለን። የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል እንዲሁም ሩሲያና አጋሮቿ ጎራ ለይተው ሲፎካከሩ ስናይ መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጻሜው ዘመን” ስለሚነሱ የደቡብና የሰሜን ነገሥታት የሚናገረው ትንቢት እየተፈጸመ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ዳን. 11:40) ዳንኤል 2:43-45 ላይ የምስሉ እግር የሚያመለክተው የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃይል እንደሆነም እናውቃለን። ከዚህ ትንቢት በመነሳት በጣም በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን እንደሚያጠፋ እርግጠኞች ሆነናል። ለፍጻሜው ምን ያህል እንደቀረብን ስለምንረዳ በጥድፊያ ስሜት ለመስበክ እንነሳሳለን።

10. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በየትኞቹ ሌሎች መንገዶች ቅንዓታችን እንዲቀጣጠል ይረዱናል?

10 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች፣ ለሌሎች ለመናገር የሚያጓጓን መልእክትም ይዘዋል። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የምትኖረው ኬሪ “ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸውን አስደሳች ተስፋዎች ሳስብ እውነትን ለሌሎች ለመናገር እገፋፋለሁ” ብላለች። አክላም “ዛሬ ሰዎች ያሉባቸውን ችግሮች ስመለከት ‘እነዚህ ተስፋዎች እኮ ለእኔ የሚያስፈልጉኝን ያህል ለእነሱም ያስፈልጓቸዋል’ ብዬ አስባለሁ” በማለት ተናግራለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የስብከቱ ሥራችን የይሖዋ ድጋፍ እንዳለው ስለሚጠቁሙን ዝም እንዳንል ብርታት ይሰጡናል። በሃንጋሪ የምትኖረው ላይላ እንዲህ ብላለች፦ “በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ ያለው ትንቢት ከውጭ ሲታዩ ምሥራቹን የሚቀበሉ ለማይመስሉ ሰዎችም እንድሰብክ ያነሳሳኛል። በይሖዋ እርዳታ ማንኛውም ሰው ለውጥ ማድረግ እንደሚችል አውቃለሁ።” በዛምቢያ የሚኖረው ክሪስቶፈር ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በማርቆስ 13:10 ላይ እንደተነገረው ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ እየተሰበከ ነው። ለዚህ ትንቢት ፍጻሜ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሌ ክብር እንደሆነ ይሰማኛል።” አንተስ መስበክህን እንድትቀጥል የሚያነሳሳህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የትኛው ነው?

በይሖዋ ድጋፍ ተማምኗል

11. ኢየሱስ በቅንዓት መስበኩን ለመቀጠል በይሖዋ እርዳታ መተማመን ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ሉቃስ 12:49, 53)

11 ኢየሱስ እስከ መጨረሻው በቅንዓት መስበክ የቻለው የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለየው ስለተማመነ ነው። ኢየሱስ ሲሰብክ ዘዴኛ ቢሆንም የመንግሥቱ ምሥራች የተጋጋለ ውዝግብ ሊፈጥርና መራራ ተቃውሞ ሊያስነሳ እንደሚችል ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 12:49, 53⁠ን አንብብ።) የሃይማኖት መሪዎቹ በተደጋጋሚ ሊገድሉት የሞከሩት በመስበኩ የተነሳ ነው። (ዮሐ. 8:59፤ 10:31, 39) ይሁንና ኢየሱስ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሆነ ስላወቀ መስበኩን ቀጥሏል። “የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው። . . . ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም” ብሏል።—ዮሐ. 8:16, 29

12. ኢየሱስ ስደት እያለም መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ተከታዮቹን ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ፣ የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለያቸው መተማመን እንደሚችሉ ደቀ መዛሙርቱን አስታውሷቸዋል። ስደት በሚደርስባቸው ጊዜም እንኳ ይሖዋ እንደሚረዳቸው በተደጋጋሚ አረጋግጦላቸዋል። (ማቴ. 10:18-20፤ ሉቃስ 12:11, 12) ስደት አይቀሬ ከመሆኑ አንጻር ጠንቃቆች እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 10:16፤ ሉቃስ 10:3) ሰዎች መልእክታቸውን መስማት ካልፈለጉ እንዳይጫኗቸው መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 10:10, 11) ስደት ሲደርስባቸው ደግሞ እንዲሸሹ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 10:23) ኢየሱስ በይሖዋ በመታመን በቅንዓት ቢሰብክም ሳያስፈልግ ራሱን ለአደጋ አላጋለጠም።—ዮሐ. 11:53, 54

13. ይሖዋ እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

13 ዛሬም ተቃውሞ እያለም በቅንዓት መስበካችንን ለመቀጠል የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። (ራእይ 12:17) ታዲያ ይሖዋ እንደሚደግፍህ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው? በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ጸሎት ተመልከት። ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንዲጠብቃቸው ይሖዋን ለምኗል፤ ይሖዋም ይህን ልመናውን ሰምቶታል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዘገባ፣ ሐዋርያቱ ስደት እያለም በቅንዓት መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ያትታል። ኢየሱስ ጸሎቱ ላይ ይሖዋ እንዲጠብቃቸው የለመነው ሐዋርያቱን ብቻ ሳይሆን የእነሱን መልእክት ሰምተው እምነት የሚጥሉትን ሰዎችም ጭምር ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንተም ትገኝበታለህ። ይሖዋ ለኢየሱስ ልመና ምላሽ መስጠቱን ቀጥሏል፤ ሐዋርያቱን እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል።—ዮሐ. 17:11, 15, 20

14. በቅንዓት መስበካችንን መቀጠል እንደምንችል እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ወደ ፍጻሜው እየተጠጋን ስንሄድ ምሥራቹን መስበክ ከባድ እየሆነብን ሊመጣ ይችላል። ያም ቢሆን የሚያስፈልገንን ድጋፍ ሁሉ እናገኛለን። (ሉቃስ 21:12-15) ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በተዉልን ምሳሌ መሠረት ሰዎች መልእክታችንን መስማት ካልፈለጉ ምርጫቸውን እናከብርላቸዋለን፤ አላስፈላጊ አተካራ ውስጥም አንገባም። በሥራችን ላይ እገዳ በተጣለባቸው አካባቢዎችም እንኳ ወንድሞቻችን በራሳቸው ሳይሆን ይሖዋ በሚሰጣቸው ብርታት ስለሚተማመኑ ምሥራቹን በቅንዓት መስበካቸውን መቀጠል ችለዋል። ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አገልጋዮቹ ኃይል ሰጥቷቸዋል፤ ዛሬም እሱ በቃ እስኪል ድረስ ‘የስብከቱን ሥራ ሙሉ በሙሉ መፈጸም’ እንድንችል ኃይል ይሰጠናል። (2 ጢሞ. 4:17) ይሖዋ በሚያደርግልህ ድጋፍ ታግዘህ በቅንዓት መስበክህን መቀጠል እንደምትችል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

በሥራችን ላይ እገዳ በሚጣልበት ጊዜም እንኳ ቀናተኛ አስፋፊዎች ትኩረት በማይስብ መልኩ ስለ እምነታቸው መናገር የሚችሉበትን መንገድ ይፈልጋሉ (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)b


ምንጊዜም አዎንታዊ ነበር

15. ኢየሱስ ለአገልግሎቱ አዎንታዊ አመለካከት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ስለ ስብከቱ ሥራ ሁልጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። ለአገልግሎት ያለውን ቅንዓት እንዳያጣ የረዳው ይህ ነው። ለምሳሌ በ30 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ኢየሱስ ብዙዎች ለስብከቱ ሥራ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ታይቶት ነበር፤ በመሆኑም ሁኔታውን ለመከር ከደረሰ አዝመራ ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐ. 4:35) ከአንድ ዓመት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “አዝመራው ብዙ ነው” ብሏቸዋል። (ማቴ. 9:37, 38) በኋላ ላይ ደግሞ “አዝመራው ብዙ ነው፤ . . . የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት ይህንኑ አስረግጦ ተናግሯል። (ሉቃስ 10:2) ኢየሱስ ሰዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ምንጊዜም ተስፋ ያደርግ ነበር፤ ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ተደስቷል።—ሉቃስ 10:21

16. ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች ለአገልግሎት አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዱን እንዴት ነው? (ሉቃስ 13:18-21) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚሰብኩት መልእክት ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯል፤ ይህም ቅንዓታቸውን እንዳያጡ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ የተናገራቸውን ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት። (ሉቃስ 13:18-21⁠ን አንብብ።) ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት በሰናፍጭ ዘር መስሎታል፤ ይህም የመንግሥቱ መልእክት በአስደናቂ ሁኔታ እንደሚስፋፋና እድገቱን የሚገታው ነገር እንደሌለ ያስገነዝበናል። እርሾን እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም ደግሞ የመንግሥቱ መልእክት በስፋት እንደሚሰራጭ አስተምሯል፤ እንዲሁም ወዲያውኑ ባይታየንም እንኳ መልእክቱ ለውጥ እንደሚያመጣ ከእርሾው ምሳሌ እንረዳለን። ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች የተናገረው ደቀ መዛሙርቱ የሚሰብኩት መልእክት በእርግጥ ውጤት እንደሚያስገኝ ሊያስገነዝባቸው ፈልጎ ነው።

ሰው በሚበዛበት የእግረኞች መንገድ ላይ ሁለት እህቶች በጋሪ ምሥክርነት ሲካፈሉ። ብዙ ሰዎች በዚያ የሚተላለፉ ቢሆንም አንዳቸውም ቆም አላሉም።

ልክ እንደ ኢየሱስ፣ ለስብከቱ ሥራችን ጆሮ የሚሰጡ ሰዎች እንደሚኖሩ ምንጊዜም ተስፋ እናደርጋለን (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)


17. በአገልግሎታችን ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?

17 ዛሬ በስብከቱ ሥራ በዓለም ዙሪያ ማከናወን የተቻለውን ነገር ስንመለከት በቅንዓት መስበካችንን ለመቀጠል እንነሳሳለን። በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ እንዲሁም ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። መቶ ሺዎች ደግሞ ተጠምቀው በስብከቱ ሥራ ከጎናችን ይሰለፋሉ። ለስብከቱ ሥራችን አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ምን ያህል ሰዎች እንደቀሩ አናውቅም። ሆኖም ይሖዋ መጪውን ታላቅ መከራ በሕይወት የሚሻገር እጅግ ብዙ ሕዝብ እየሰበሰበ እንደሆነ እናውቃለን። (ራእይ 7:9, 14) የመከሩ ጌታ አሁንም መሰብሰብ ያለበት አዝመራ እንዳለ ይታየዋል፤ በመሆኑም መስበካችንን የምንቀጥልበት አጥጋቢ ምክንያት አለን።

18. ሰዎች ስለ እኛ ምን እንዲያስተውሉ እንፈልጋለን?

18 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከጥንትም ጀምሮ በቅንዓት በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ተለይተው ይታወቃሉ። ሐዋርያቱ በድፍረት ሲሰብኩ የተመለከቱ ሰዎች “ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩ” ተገንዝበዋል። (ሥራ 4:13) ዛሬም አገልግሎታችንን ስናከናውን የሚመለከቱ ሰዎች የኢየሱስ ቅንዓት ወደ እኛም እንደተጋባ ይመሠክሩ ዘንድ ምኞታችን ነው።

በሚከተሉት አቅጣጫዎች ኢየሱስን በመምሰል ቅንዓታችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

  • ለአገልግሎቱ የሰጠው ቦታ

  • በይሖዋ ድጋፍ መተማመኑ

  • ምንጊዜም አዎንታዊ መሆኑ

መዝሙር 58 ሰላም ወዳዶችን መፈለግ

a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህ ርዕስ ላይ “ቅንዓት” ስንል ክርስቲያኖች ይሖዋን የሚያመልኩበትን የማይበርድ ስሜትና ጉጉት ማመልከታችን ነው።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ ነዳጅ ማደያ ውስጥ አንድ ወንድም በጥንቃቄ ምሥክርነት እየሰጠ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ