የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt 1 ተሰሎንቄ 1:1-5:28
  • 1 ተሰሎንቄ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 1 ተሰሎንቄ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
1 ተሰሎንቄ

ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ

1 ከጳውሎስ፣ ከስልዋኖስና*+ ከጢሞቴዎስ፤+ አባት ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነት ላለው የተሰሎንቄ ሰዎች ጉባኤ፦

የአምላክ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

2 ሁላችሁንም በጸሎታችን+ በጠቀስን ቁጥር ሁልጊዜ አምላክን እናመሰግናለን፤ 3 የእምነት ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨ ድካማችሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተስፋ በማድረጋችሁ+ የተነሳ የምታሳዩትን ጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን። 4 አምላክ የሚወዳችሁ ወንድሞች፣ እሱ እንደመረጣችሁ እናውቃለን፤ 5 ምክንያቱም የሰበክንላችሁ ምሥራች ወደ እናንተ የመጣው በቃል ብቻ ሳይሆን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም በጠንካራ እምነት ነው። ደግሞም ለእናንተ ስንል በመካከላችሁ ምን ዓይነት ሰዎች ሆነን እንደኖርን ታውቃላችሁ። 6 ብዙ መከራ ቢደርስባችሁም+ ቃሉን ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ደስታ ስለተቀበላችሁ የእኛንም+ ሆነ የጌታን+ አርዓያ ተከትላችኋል፤ 7 በመሆኑም በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙ አማኞች ሁሉ ምሳሌ ሆናችኋል።

8 የይሖዋ* ቃል ከእናንተ ወጥቶ የተሰማው በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ ላይ ያላችሁ እምነት በሌሎች ቦታዎችም ሁሉ ተሰራጭቷል፤+ ስለዚህ እኛ ምንም መናገር አያስፈልገንም። 9 ምክንያቱም መጀመሪያ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደተገናኘን እንዲሁም ሕያው የሆነውንና እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ጣዖቶቻችሁን በመተው+ እንዴት ወደ አምላክ እንደተመለሳችሁ እነሱ ራሳቸው ሁልጊዜ ይናገራሉ፤ 10 በተጨማሪም ወደ አምላክ የተመለሳችሁት ከሞት ያስነሳውንና ከሚመጣው ቁጣ+ የሚታደገንን የልጁን ይኸውም የኢየሱስን ከሰማይ መምጣት ለመጠባበቅ ነው።+

2 ወንድሞች፣ የእኛ ወደ እናንተ መምጣት ፍሬ ቢስ ሆኖ እንዳልቀረ እናንተ ራሳችሁ እንደምትገነዘቡ ምንም ጥርጥር የለውም።+ 2 እንደምታውቁት በመጀመሪያ በፊልጵስዩስ+ መከራና እንግልት ደርሶብን ነበር፤ ይሁንና ከባድ ተቃውሞ እያለም* የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ለመንገር+ በአምላካችን እርዳታ እንደ ምንም ብለን ድፍረት አገኘን። 3 የምንሰጠው ምክር ከተሳሳተ ሐሳብ ወይም ከመጥፎ ዓላማ የመነጨ ወይም ደግሞ ማታለያ ያዘለ አይደለም፤ 4 ሆኖም ምሥራቹን በአደራ ለመቀበል በአምላክ ዘንድ ብቁ ሆነን የተቆጠርን እንደመሆናችን መጠን የምንናገረው ሰዎችን ለማስደሰት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን+ አምላክ ለማስደሰት ብለን ነው።

5 እንዲያውም የሽንገላ ቃል የተናገርንበት ወይም ስግብግብነት የሚንጸባረቅበትን ፍላጎታችንን ለመሸፈን ብለን በማስመሰል የቀረብንበት ጊዜ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤+ ለዚህም አምላክ ምሥክር ነው! 6 በተጨማሪም የክርስቶስ ሐዋርያት እንደመሆናችን መጠን እናንተን ብዙ ወጪ በማስወጣት ሸክም ልንሆንባችሁ እንችል የነበረ ቢሆንም እንኳ ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ክብር ለማግኘት አልሞከርንም።+ 7 ከዚህ ይልቅ የምታጠባ እናት ልጆቿን በፍቅር እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በነበርንበት ጊዜ በገርነት ተንከባከብናችሁ። 8 በመሆኑም ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን የአምላክን ምሥራች ለማካፈል ብቻ ሳይሆን ራሳችንን* ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር፤+ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።+

9 ወንድሞች፣ ድካማችንንና ልፋታችንን እንደምታስታውሱ ጥርጥር የለውም። የአምላክን ምሥራች በሰበክንላችሁ ጊዜ፣ ማናችሁንም ብዙ ወጪ በማስወጣት ሸክም እንዳንሆንባችሁ+ በማሰብ ሌት ተቀን እንሠራ ነበር። 10 አማኞች ከሆናችሁት ከእናንተ ጋር በነበረን ግንኙነት ታማኞች፣ ጻድቃንና ነቀፋ የሌለብን ሆነን እንደተመላለስን ምሥክሮች ናችሁ፤ አምላክም ምሥክር ነው። 11 አባት+ ለልጆቹ እንደሚያደርገው ሁሉ እያንዳንዳችሁን እንዴት እንመክራችሁ፣ እናጽናናችሁና አጥብቀን እናሳስባችሁ+ እንደነበረ በሚገባ ታውቃላችሁ፤ 12 ይህን ያደረግነው ወደ መንግሥቱና+ ወደ ክብሩ+ በጠራችሁ አምላክ ፊት በአግባቡ መመላለሳችሁን እንድትቀጥሉ ነው።+

13 በእርግጥም አምላክን ያለማቋረጥ የምናመሰግነው ለዚህ ነው፤+ ምክንያቱም የአምላክን ቃል ከእኛ በሰማችሁ ጊዜ እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው፤ አማኞች በሆናችሁት በእናንተም ላይ በእርግጥ እየሠራ ነው። 14 ወንድሞች፣ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ያላቸውን በይሁዳ የሚገኙትን የአምላክ ጉባኤዎች ምሳሌ ተከትላችኋል፤ ምክንያቱም እነሱ በአይሁዳውያን እጅ መከራ እየተቀበሉ እንዳሉ ሁሉ እናንተም በገዛ አገራችሁ ሰዎች እጅ ተመሳሳይ መከራ ተቀብላችኋል፤+ 15 አይሁዳውያን ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን ሳይቀር የገደሉ+ ከመሆኑም በላይ በእኛ ላይ ስደት አድርሰዋል።+ ከዚህም በተጨማሪ አምላክን እያስደሰቱ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሰውን ሁሉ ጥቅም የሚጻረሩ ናቸው፤ 16 አሕዛብ ይድኑ ዘንድ ለእነሱ እንዳንሰብክ ሊከለክሉን ይሞክራሉ።+ በዚህ መንገድ ሁልጊዜ ብዙ ኃጢአት ይፈጽማሉ። ይሁንና ቁጣው የሚገለጽበት ጊዜ ደርሷል።+

17 እኛ ግን ወንድሞች፣ (በልብ ሳይሆን በአካል) ለአጭር ጊዜ ከእናንተ ለመለየት በተገደድንበት ወቅት እጅግ ስለናፈቅናችሁ ከእናንተ ጋር በአካል ለመገናኘት* ብርቱ ጥረት አደረግን። 18 በመሆኑም ወደ እናንተ መምጣት ፈልገን ነበር፤ አዎ፣ እኔ ጳውሎስ ከአንዴም ሁለቴ ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ሰይጣን መንገድ ዘጋብን። 19 ጌታችን ኢየሱስ በሚገኝበት ጊዜ በእሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም የሐሴታችን አክሊል ምንድን ነው? እናንተ አይደላችሁም?+ 20 በእርግጥም እናንተ ክብራችንና ደስታችን ናችሁ።

3 ስለዚህ ከዚህ በላይ መታገሥ ስላልቻልን* በአቴንስ+ ብቻችንን መቅረት እንደሚሻል ተሰማን፤ 2 በመሆኑም እምነታችሁ ይጠነክር ዘንድ እንዲያጸናችሁ እንዲሁም እንዲያበረታታችሁ ጢሞቴዎስን+ ላክንላችሁ፤ እሱ ወንድማችንና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች የሚያውጅ የአምላክ አገልጋይ* ነው፤ 3 የላክነውም ማንም በእነዚህ መከራዎች እንዳይናወጥ* ነው። እንዲህ ካሉ መከራዎች ማምለጥ እንደማንችል እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።+ 4 አብረናችሁ በነበርንበት ጊዜ መከራ መቀበላችን እንደማይቀር አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ ደግሞም እንደምታውቁት ይኸው ነገር ደርሷል።+ 5 ስለዚህ ከዚህ በላይ መታገሥ ባልቻልኩ ጊዜ ስለ ታማኝነታችሁ ለመስማት እሱን ላክሁት፤+ ይህን ያደረግኩት ምናልባት ፈታኙ+ በሆነ መንገድ ፈትኗችሁ ድካማችን ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ስለሰጋሁ ነው።

6 ይሁንና ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ አሁን ወደ እኛ መጥቶ+ ስለ ታማኝነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ ምሥራች አብስሮናል፤ ደግሞም እኛን ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስታውሱንና እኛ እናንተን ለማየት እንደምንናፍቅ ሁሉ እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁ ነግሮናል። 7 ወንድሞች፣ በችግራችንና በመከራችን ሁሉ በእናንተና ባሳያችሁት ታማኝነት የተነሳ የተጽናናነው ለዚህ ነው።+ 8 ምክንያቱም ከጌታ ጋር ባላችሁ ዝምድና ጸንታችሁ የምትቆሙ ከሆነ ሕይወታችን ይታደሳል።* 9 በእናንተ የተነሳ በአምላካችን ፊት ለተሰማን ታላቅ ደስታ በአጸፋው ስለ እናንተ ምስጋናችንን ለአምላክ ለመግለጽ ምን ማድረግ እንችላለን? 10 ፊታችሁን ማየትና ከእምነታችሁ የጎደለውን ነገር ማሟላት እንችል ዘንድ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ሌት ተቀን ምልጃ እናቀርባለን።+

11 አሁንም አምላካችንና አባታችን እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ወደ እናንተ እንድንመጣ መንገዳችንን ያቅኑልን። 12 በተጨማሪም እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስም ሆነ ለሰዎች ሁሉ የምታሳዩትን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ ብሎም ያትረፍርፍላችሁ፤+ 13 ይህም ጌታችን ኢየሱስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በሚገኝበት ጊዜ+ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ልባችሁን እንዲያጸናና ያላንዳች እንከን ቅዱስ እንዲያደርግ ነው።+

4 በመጨረሻም ወንድሞች፣ አምላክን ማስደሰት እንድትችሉ እንዴት መመላለስ እንዳለባችሁ አስተምረናችኋል፤+ ደግሞም በዚሁ መንገድ እየተመላለሳችሁ ነው፤ በመሆኑም ይህንኑ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ በጌታ ኢየሱስ ስም እንጠይቃችኋለን እንዲሁም እንለምናችኋለን። 2 በጌታ ኢየሱስ ስም የሰጠናችሁን መመሪያዎች ታውቃላችሁና።

3 የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱና+ ከፆታ ብልግና* እንድትርቁ ነው።+ 4 ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል* በመቆጣጠር+ እንዴት በቅድስናና+ በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። 5 ይህም አምላክን እንደማያውቁት አሕዛብ+ ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።+ 6 ማንም ሰው በዚህ ጉዳይ ከገደቡ ማለፍና ወንድሙን መጠቀሚያ ማድረግ አይኖርበትም፤ ምክንያቱም አስቀድመን እንደነገርናችሁና በጥብቅ እንዳስጠነቀቅናችሁ ይሖዋ* በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የተነሳ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል። 7 አምላክ የጠራን ለቅድስና ነው እንጂ ለርኩሰት አይደለም።+ 8 እንግዲህ ለዚህ ንቀት የሚያሳይ ሰው የሚንቀው ሰውን ሳይሆን ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን+ አምላክ ነው።+

9 ይሁን እንጂ እናንተ ራሳችሁ እርስ በርስ እንድትዋደዱ ከአምላክ ስለተማራችሁ+ የወንድማማች ፍቅርን በተመለከተ+ እንድንጽፍላችሁ አያስፈልግም። 10 ደግሞም በመላው መቄዶንያ ለሚገኙ ወንድሞች ሁሉ ይህን እያደረጋችሁ ነው። ሆኖም ወንድሞች፣ ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ እናሳስባችኋለን። 11 ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁ በሰላም ለመኖር፣+ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባትና+ በገዛ እጃችሁ ለመሥራት ተጣጣሩ፤+ 12 ይህም በውጭ ባሉት* ሰዎች ፊት ሥርዓት ባለው መንገድ እንድትመላለሱና+ ምንም ነገር የሚጎድላችሁ እንዳትሆኑ ነው።

13 በተጨማሪም ወንድሞች፣ ተስፋ እንደሌላቸው+ እንደ ሌሎቹ ሰዎች እንዳታዝኑ በሞት አንቀላፍተው ስላሉት+ ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም። 14 ኢየሱስ እንደሞተና ከሞት እንደተነሳ የምናምን ከሆነ+ ከኢየሱስ ጋር አንድነት ኖሯቸው በሞት ያንቀላፉትንም አምላክ ሕይወት ሰጥቶ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ያደርጋል።+ 15 የይሖዋን* ቃል መሠረት አድርገን የምንነግራችሁ ይህ ነውና፤ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በሕይወት የምንኖር በሞት አንቀላፍተው ያሉትን በምንም መንገድ አንቀድምም፤ 16 ምክንያቱም ጌታ ራሱ በትእዛዝ ድምፅ፣ በመላእክት አለቃ+ ድምፅና በአምላክ መለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳል፤ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው የሞቱትም ቀድመው ይነሳሉ።+ 17 ከዚያም በሕይወት ቆይተን የምንተርፈው እኛ በአየር ላይ ከጌታ ጋር ለመገናኘት+ ከእነሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤+ በዚህም መንገድ ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።+ 18 ስለሆነም በእነዚህ ቃላት ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።

5 እንግዲህ ወንድሞች፣ ጊዜያትንና ወቅቶችን በተመለከተ ምንም ነገር እንዲጻፍላችሁ አያስፈልግም። 2 የይሖዋ* ቀን+ የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ+ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁና። 3 “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ሲሉ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤+ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም። 4 እናንተ ግን ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤ 5 እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁና።+ እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ልጆች አይደለንም።+

6 ስለዚህ ነቅተን እንኑር+ እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ+ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ።+ 7 የሚያንቀላፉ ሰዎች፣ የሚያንቀላፉት በሌሊት ነው፤ የሚሰክሩም ቢሆኑ የሚሰክሩት በሌሊት ነው።+ 8 የቀን ልጆች የሆንነው እኛ ግን የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ፤ ደግሞም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ፤+ 9 ምክንያቱም አምላክ የመረጠን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን እንድናገኝ+ ነው እንጂ ለቁጣ አይደለም። 10 እሱ በሕይወት ብንኖርም ሆነ ብናንቀላፋ* አብረነው እንድንኖር+ ለእኛ ሞቶልናል።+ 11 ስለዚህ አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ* እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።+

12 እንግዲህ ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ 13 በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን።+ እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ።+ 14 በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን፦ በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤*+ የተጨነቁትን* አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።+ 15 ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።+

16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ።+ 17 ዘወትር ጸልዩ።+ 18 ለሁሉም ነገር አመስግኑ።+ አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ያለው ፈቃድ ይህ ነው። 19 የመንፈስን እሳት አታጥፉ።+ 20 ትንቢቶችን አትናቁ።+ 21 ሁሉንም ነገር መርምሩ፤+ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። 22 ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ራቁ።+

23 የሰላም አምላክ ራሱ ሙሉ በሙሉ ይቀድሳችሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና* አካላችሁ በማንኛውም ረገድ ጤናማ ይሁን፤ ደግሞም ነቀፋ አይገኝበት።+ 24 የጠራችሁ ታማኝ ነው፤ ይህን በእርግጥ ያደርገዋል።

25 ወንድሞች፣ ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ።+

26 ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው።

27 ይህ ደብዳቤ ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አደራ እላችኋለሁ።+

28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

ሲላስ ተብሎም ይጠራል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ይሁንና በከፍተኛ ተጋድሎ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳችንን።”

ቃል በቃል “ፊታችሁን ለማየት።”

ወይም “ስላልቻልኩ።” እዚህ ላይ ጳውሎስ በብዙ ቁጥር የተጠቀመው ራሱን ለማመልከት ሊሆን ይችላል።

“ከአምላክ ጋር አብሮ የሚሠራ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እንዳይዋልል።”

ቃል በቃል “በሕይወት እንኖራለን።”

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ዕቃ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ባልሆኑት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በሞት ብናንቀላፋ።”

ወይም “ተጽናኑ።”

ወይም “ምከሯቸው።”

ወይም “ተስፋ የቆረጡትን።” ቃል በቃል “ትንሽ ነፍስ ያላቸውን።”

ወይም “ሕይወታችሁና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ