ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22
በመከራ ውስጥ እያለንም እጅግ እንደሰት።—ሮም 5:3
ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አብረናችሁ በነበርንበት ጊዜ መከራ መቀበላችን እንደማይቀር አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ ደግሞም እንደምታውቁት ይኸው ነገር ደርሷል።” (1 ተሰ. 3:4) በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ደግሞ “ወንድሞች . . . ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን። . . . በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር” ብሏቸዋል። (2 ቆሮ. 1:8፤ 11:23-27) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም በሆነ መልኩ መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። (2 ጢሞ. 3:12) አንተም በኢየሱስ በማመንህና እሱን በመከተልህ የተነሳ ጓደኞችህና ዘመዶችህ ስደት አድርሰውብህ ሊሆን ይችላል። በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ያደረግከው ውሳኔ በሥራ ቦታህ ችግር አስከትሎብሃል? (ዕብ. 13:18) ተስፋህን ለሌሎች በማካፈልህ የተነሳ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተቃውመውሃል? ይሁንና የሚደርስብን መከራ ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ልንደሰት እንደሚገባ ገልጿል። w23.12 10-11 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23
ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከተታችሁኝ።—ዘፍ. 34:30
ያዕቆብ ብዙ መከራዎች አጋጥመውታል። ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ ቤተሰባቸውን ያሳፈሩ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ አምጥተዋል። በተጨማሪም ያዕቆብ የሚወዳት ሚስቱ ራሔል ሁለተኛ ልጇን ስትወልድ ሞተችበት። በኋላም ከባድ ረሃብ በመከሰቱ ያዕቆብ በስተ እርጅናው ወደ ግብፅ ለመሰደድ ተገደደ። (ዘፍ. 35:16-19፤ 37:28፤ 45:9-11, 28) ያዕቆብ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም በይሖዋና እሱ በገባው ቃል ላይ ያለውን እምነት አላጣም። ይሖዋም የእሱ ሞገስ እንዳልተለየው ለያዕቆብ አረጋግጦለታል። ለምሳሌ ይሖዋ ያዕቆብን በቁሳዊ አበልጽጎታል። በተጨማሪም ያዕቆብ፣ ‘ሞቷል’ ብሎ ከሚያስበው ልጁ ጋር ከረጅም ጊዜ በኋላ ሲገናኝ ይሖዋን ምን ያህል አመስግኖት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ያዕቆብ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው ያጋጠመውን መከራ በጽናት መወጣት ችሏል። (ዘፍ. 30:43፤ 32:9, 10፤ 46:28-30) እኛም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ካለን ያልተጠበቁ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት እንችላለን። w23.04 15 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24
ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ ነገር የለም።—መዝ. 23:1
በመዝሙር 23 ላይ ዳዊት በይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት ገልጿል። ዳዊት በእሱና በእረኛው በይሖዋ መካከል ስላለው የጠበቀ ዝምድና ተናግሯል። ዳዊት የይሖዋን አመራር በመከተሉ የደህንነት ስሜት ተሰምቶታል፤ እንዲሁም በእሱ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ዳዊት የይሖዋ ፍቅር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደሚከተለው ያውቅ ነበር። ይህን ያህል እንዲተማመን ያደረገው ምንድን ነው? ዳዊት የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ ይሖዋ ስላሟላለት በደንብ እንደተንከባከበው ተሰምቶታል። ዳዊት የይሖዋን ወዳጅነትና ሞገስ አግኝቷል። በመሆኑም ወደፊት ምንም ቢመጣ የይሖዋ እንክብካቤ እንደማይቋረጥበት እርግጠኛ ነበር። ዳዊት በይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ማንኛውንም ጭንቀት አሸንፎ ጥልቅ ደስታና እርካታ ማግኘት ችሏል።—መዝ. 16:11፤ w24.01 28-29 አን. 12-13