ሐምሌ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1
መልካም ነገር እያደረገና . . . እየፈወሰ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ።—ሥራ 10:38
ኢየሱስ፣ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የአባቱን አስተሳሰብና ስሜት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ ይህም የፈጸማቸውን ተአምራት ይጨምራል። (ዮሐ. 14:9) ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስና አባቱ በጣም ይወዱናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ተአምር የመፈጸም ችሎታውን ተጠቅሞ ሥቃያቸውን በማቅለል ለሰዎች ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል። በአንድ ወቅት ሁለት ዓይነ ስውሮች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲረዳቸው ለመኑት። (ማቴ. 20:30-34) በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “በጣም አዘነላቸውና” ፈወሳቸው። እዚህ ጥቅስ ላይ “በጣም አዘነላቸው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ከአንጀት የመነጨ ጥልቅ የአዘኔታ ስሜትን ያመለክታል። ኢየሱስ የተራቡትን እንዲመግብና አንድን የሥጋ ደዌ በሽተኛ እንዲፈውስ ያነሳሳውም እንዲህ ያለው ከፍቅር የሚመነጭ ጥልቅ ርኅራኄ ነው። (ማቴ. 15:32፤ ማር. 1:41) ‘ከአንጀት የሚራራ’ አምላክ የሆነው ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ በጣም እንደሚወዱንና መከራ ሲደርስብን እጅግ እንደሚያዝኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሉቃስ 1:78፤ 1 ጴጥ. 5:7) በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ወዮታ በሙሉ ለማስወገድ ከልባቸው ይጓጓሉ! w23.04 3 አን. 4-5
ረቡዕ፣ ሐምሌ 2
እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ። እሱ የታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት ይጠብቃል፤ ከክፉዎች እጅ ይታደጋቸዋል።—መዝ. 97:10
የሰይጣን ሥርዓት ለሚያስፋፋቸው የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ያለንን ተጋላጭነት ለመቀነስ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት አእምሯችንን በጤናማ ሐሳቦች መሙላት እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ መገኘታችንና በአገልግሎት መካፈላችንም አስተሳሰባችንን ለመጠበቅ ይረዳናል። ይሖዋም ልንሸከም ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ ቃል ገብቶልናል። (1 ቆሮ. 10:12, 13) በእነዚህ ተፈታታኝ የመጨረሻ ቀናት ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ለመጠበቅ ሁላችንም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በትጋት መጸለይ ይኖርብናል። ይሖዋ ወደ እሱ በመጸለይ ‘ልባችንን በፊቱ እንድናፈስስ’ ይፈልጋል። (መዝ. 62:8) ይሖዋን አወድሰው፤ እንዲሁም ላደረገልህ ነገር ሁሉ አመስግነው። በአገልግሎት ደፋር ለመሆን እንዲረዳህ ጠይቀው። የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለመወጣትና ማንኛውንም ፈተና ለማሸነፍ እንዲረዳህ ለምነው። ማንም ሰው ወይም ማንኛውም ነገር ወደ ይሖዋ አዘውትረህ ከመጸለይ እንዲያግድህ አትፍቀድ። w23.05 7 አን. 17-18
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3
አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ . . . እርስ በርስ እንበረታታ።—ዕብ. 10:24, 25
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው? በዋነኝነት ይሖዋን ለማወደስ ነው። (መዝ. 26:12፤ 111:1) በስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ሌላው ምክንያት ደግሞ በዚህ አስቸጋሪ ዘመን እርስ በርስ እንድንበረታታ ነው። (1 ተሰ. 5:11) እጃችንን አውጥተን ሐሳብ ስንሰጥ ሁለቱንም ዓላማዎች እናሳካለን። ይሁንና ሐሳብ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሐሳብ መስጠት ሊያስፈራን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ተሳትፎ ለማድረግ ብንጓጓም የምንፈልገውን ያህል ዕድል ላይሰጠን ይችላል። እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እርስ በርስ በመበረታታት’ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ገልጿል። አጭር መልስ እንኳ በመመለስ እምነታችንን ስንገልጽ ሌሎቹ ተሰብሳቢዎች እንደሚበረታቱ ከተገነዘብን መልስ ለመመለስ የሚሰማን ፍርሃት ይቀንሳል። የምንፈልገውን ያህል ብዙ ዕድል የማይሰጠን ከሆነ ደግሞ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶችም ሐሳብ የሚሰጡበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ደስተኞች መሆን እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:8፤ w23.04 20 አን. 1-3
ዓርብ፣ ሐምሌ 4
ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ . . . የይሖዋን ቤትም መልሶ ይገንባ።—ዕዝራ 1:3
አዋጁ ወጥቷል! ለ70 ዓመት ገደማ በባቢሎን ግዞተኞች ሆነው የኖሩት አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ወደ እስራኤል እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸዋል። (ዕዝራ 1:2-4) ይህ ሊሆን የቻለው ይሖዋ ስለረዳቸው ብቻ ነው። ባቢሎናውያን ግዞተኞቻቸውን የመልቀቅ ልማድ አልነበራቸውም። (ኢሳ. 14:4, 17) አሁን ግን ባቢሎን ወድቃለች። አዲሱ ገዢም አይሁዳውያን ባቢሎንን ለቀው መውጣት እንደሚችሉ ነገራቸው። በመሆኑም በእያንዳንዱ አይሁዳዊ በተለይም በቤተሰብ ራሶች ፊት አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ተደቅኗል፤ ባቢሎንን ለቀው ለመውጣት ወይም እዚያው ለመቅረት መወሰን ነበረባቸው። ይሁንና እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ ስለነበሩ ያንን አስቸጋሪ ጉዞ ማድረግ ይከብዳቸዋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ አይሁዳውያን የተወለዱት በባቢሎን ስለነበር ‘ቤቴ’ የሚሉት ባቢሎንን ነው። በእነሱ ዓይን እስራኤል የአያቶቻቸው እንጂ የእነሱ አገር አይደለም። አንዳንድ አይሁዳውያን በባቢሎን የተደላደለ ሕይወት መሥርተው የነበረ ይመስላል። በመሆኑም የሞቀ ቤታቸውንና ንግዳቸውን ትተው ወደማያውቁት አገር መሄድ ከብዷቸው ሊሆን ይችላል። w23.05 14 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 5
ዝግጁ ሁኑ።—ማቴ. 24:44
የአምላክ ቃል ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ማዳበራችንን እንድንቀጥል ያበረታታናል። ሉቃስ 21:19 “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” ይላል። ቆላስይስ 3:12 “ርኅራኄን . . . ልበሱ” ይላል። አንደኛ ተሰሎንቄ 4:9, 10 ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርስ እንድትዋደዱ ከአምላክ [ተምራችኋል]። . . . ሆኖም ወንድሞች፣ ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ እናሳስባችኋለን።” እነዚህ ሦስቱም ምክሮች የተሰጡት ቀድሞውንም ቢሆን ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ያሳዩ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት ነው። ሆኖም እነዚህን ባሕርያት ማዳበራቸውን መቀጠል ያስፈልጋቸው ነበር፤ እኛም እንደዛው። ለዚህ እንዲያግዛችሁ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እያንዳንዱን ባሕርይ እንዴት እንዳሳዩ ለማሰብ ሞክሩ። ከዚያም የእነሱን ምሳሌ መከተል የምትችሉት እንዴት እንደሆነ አስተውሉ፤ ይህም ለታላቁ መከራ ያዘጋጃችኋል። ታላቁ መከራ ሲጀምር ደግሞ አስቀድማችሁ ጽናትን ስለተማራችሁ ፈተናውን ለማለፍ ቁርጠኝነት ይኖራችኋል። w23.07 2 አን. 4፤ 3 አን. 8
እሁድ፣ ሐምሌ 6
በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፤ ደግሞም “የቅድስና ጎዳና” ተብሎ ይጠራል።—ኢሳ. 35:8
ቅቡዓንም ሆንን “ሌሎች በጎች” በቅድስና ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠል ይኖርብናል። ምክንያቱም ይህ መንገድ በመንፈሳዊው ገነት በኩል አድርጎ ወደፊት መንግሥቱ ወደሚያመጣቸው በረከቶች ይወስደናል። (ዮሐ. 10:16) ከ1919 ዓ.ም. አንስቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ከታላቂቱ ባቢሎን ማለትም ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተው በዚህ ምሳሌያዊ መንገድ ላይ መጓዝ ጀምረዋል። አይሁዳውያኑ ከባቢሎን ሲወጡ ይሖዋ እንቅፋቶችን ሁሉ አስወግዶላቸው ነበር። (ኢሳ. 57:14) በዘመናችን ካለው “የቅድስና ጎዳና” ጋር በተያያዘስ ምን ማለት ይቻላል? ከ1919 በፊት በነበሩት በርካታ መቶ ዓመታት፣ ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን የሚያስወጣውን መንገድ እንዲጠርጉ አድርጎ ነበር። (ከኢሳይያስ 40:3 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ሰዎች፣ ከጊዜ በኋላ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥተው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ወደተቋቋመበት መንፈሳዊ ገነት መግባት እንዲችሉ አስፈላጊውን መንፈሳዊ የመንገድ ሥራ አከናውነዋል። w23.05 16 አን. 8-9
ሰኞ፣ ሐምሌ 7
ይሖዋን በደስታ አገልግሉት። በእልልታ ወደ ፊቱ ቅረቡ።—መዝ. 100:2
ይሖዋ በደስታና በፈቃደኝነት እንድናገለግለው ይፈልጋል። (2 ቆሮ. 9:7) ታዲያ አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ ለመድረስ ተነሳሽነቱ ከሌለን ጥረት ማድረጋችንን መቀጠላችን ተገቢ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ “ሰውነቴን አጥብቄ እየገሠጽኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” ብሏል። (1 ቆሮ. 9:25-27 ግርጌ) ጳውሎስ ይሖዋ የሚጠብቅበትን ነገር ለማድረግ ተነሳሽነት ባይኖረውም እንኳ ራሱን አስገድዶ ትክክለኛውን ነገር አድርጓል። ታዲያ ይሖዋ ጳውሎስ ባደረገው ነገር ተደስቷል? በሚገባ! በተጨማሪም ላደረገው ጥረት ይሖዋ ባርኮታል። (2 ጢሞ. 4:7, 8) እኛም ተነሳሽነት ባይኖረንም እንኳ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ስናደርግ ይሖዋ ይደሰታል። አንድ ግብ ላይ ለመድረስ የምንጣጣረው ለዚያ ነገር ባለን ፍቅር ተነሳስተን ባይሆንም እንኳ ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን እንደሆነ ስለሚያውቅ ይደሰትብናል። ይሖዋ ጳውሎስን እንደባረከው ሁሉ እኛም ጥረት በማድረጋችን ይባርከናል። (መዝ. 126:5) የይሖዋን በረከት ስናጣጥም ደግሞ ተነሳሽነታችን እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። w23.05 29 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8
የይሖዋ ቀን [ይመጣል]።—1 ተሰ. 5:2
ሐዋርያው ጳውሎስ ከይሖዋ ቀን የማይተርፉ ሰዎችን ከሚያንቀላፉ ሰዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። በዙሪያቸው እየተከናወነ ያለውን ነገርም ሆነ የጊዜውን መሄድ አያስተውሉም። በመሆኑም ወሳኝ ክንውኖች ሲፈጸሙ ልብ ማለትም ሆነ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አይችሉም። በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በመንፈሳዊ አንቀላፍተዋል። (ሮም 11:8) የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ እንደሆነና ታላቁ መከራ በቅርቡ እንደሚመጣ የሚያሳየውን ማስረጃ ችላ ይላሉ። (2 ጴጥ. 3:3, 4) እኛ ግን፣ ንቁ እንድንሆን የተሰጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ቀን አልፎ ቀን ሲተካ አጣዳፊነቱ እየጨመረ እንደሚሄድ እንገነዘባለን። (1 ተሰ. 5:6) በመሆኑም መረጋጋትና ማመዛዘን ያስፈልገናል። ለምን? በዓለም ላይ ባሉት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዳንጠላለፍ ነው። የይሖዋ ቀን እየተቃረበ ሲመጣ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ አንዱን ወገን እንድንይዝ የሚደርስብን ጫና ይጨምራል። ሆኖም ‘እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ምላሽ እንሰጥ ይሆን’ የሚለውን በማሰብ መጨነቅ አይኖርብንም። የአምላክ መንፈስ መረጋጋትና ማመዛዘን እንድንችል እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ይረዳናል።—ሉቃስ 12:11, 12፤ w23.06 9-10 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ሐምሌ 9
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ አስበኝ፤ . . . ብርታት ስጠኝ።—መሳ. 16:28
ሳምሶን የሚለውን ስም ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አስደናቂ ጥንካሬ የነበረው ሰው መሆኑን ታስታውስ ይሆናል። ደግሞም እውነት ነው። ይሁንና ሳምሶን አስከፊ መዘዝ ያስከተለ መጥፎ ውሳኔም አድርጓል። ያም ቢሆን ይሖዋ ያተኮረው ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ባሳየው ታማኝነት ላይ ነው። ይህ ታሪክ ለእኛ ጥቅም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተትልን አድርጓል። ይሖዋ የተመረጡ ሕዝቦቹ የሆኑትን እስራኤላውያንን ለመርዳት ሲል አስደናቂ ነገሮችን እንዲፈጽም ሳምሶንን ተጠቅሞበታል። ሳምሶን ከሞተ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ሐዋርያው ጳውሎስን በመንፈሱ በመምራት የሳምሶንን ስም አስደናቂ እምነት ባሳዩ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲያካትት አድርጓል። (ዕብ. 11:32-34) የሳምሶን ምሳሌ ሊያበረታታን ይችላል። አስቸጋሪ ነገሮች ሲያጋጥሙትም ጭምር በይሖዋ ታምኗል። ከሳምሶን ታሪክ ማበረታቻና ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። w23.09 2 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ሐምሌ 10
ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።—ፊልጵ. 4:6
ወደ ይሖዋ አዘውትረን በመጸለይና የልባችንን ጭንቀት በማፍሰስ ጽናት ማዳበር እንችላለን። (1 ተሰ. 5:17) እርግጥ በአሁኑ ወቅት ከባድ መከራ አልደረሰብህ ይሆናል። ያም ቢሆን ስትበሳጭ፣ ግራ ስትጋባ ወይም ነገሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሲሰማህ የይሖዋን መመሪያ የመፈለግ ልማድ አለህ? ዛሬ በዕለት ተዕለት የሕይወት ውጣ ውረድ የይሖዋን እርዳታ አዘውትረህ የምትጠይቅ ከሆነ ወደፊት ከበድ ያለ ነገር ሲያጋጥምህ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትልም። ይሖዋ እሱ የተሻለ ነው ብሎ በሚያስበው ጊዜና መንገድ እንደሚረዳህ ያለህ እምነትም ጠንካራ ይሆናል። (መዝ. 27:1, 3) በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ መጪውን ታላቅ መከራ በጽናት የማለፍ አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል። (ሮም 5:3) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ብዙ ወንድሞቻችን ከራሳቸው ተሞክሮ እንደተረዱት በጽናት የተወጡት እያንዳንዱ ፈተና ለቀጣዩ መከራ አዘጋጅቷቸዋል። በፈተና መጽናት ማንነታቸውን እንደሚያጠራው አስተውለዋል። ይሖዋ እነሱን ለመርዳት ፍላጎቱ እንዳለውና በችግራቸው ፈጥኖ እንደሚደርስላቸው ያላቸው እምነት ተጠናክሯል። ይህ እምነታቸው ደግሞ ቀጣዩን ፈተና በጽናት ለመወጣት ረድቷቸዋል።—ያዕ. 1:2-4፤ w23.07 3 አን. 7-8
ዓርብ፣ ሐምሌ 11
አሳቢነት አሳይሃለሁ።—ዘፍ. 19:21
ይሖዋ ምክንያታዊ እንዲሆን የሚያነሳሳው ትሕትናውና ርኅራኄው ነው። ለምሳሌ፣ ክፉ የሆኑትን የሰዶም ነዋሪዎች ለማጥፋት በወሰነበት ወቅት ትሕትናው በግልጽ ታይቷል። ይሖዋ መላእክቱን ልኮ፣ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ለጻድቁ ሎጥ መመሪያ ሰጠው። ሎጥ ግን እዚያ መሄድ ፈራ። በመሆኑም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዞአር ለመሸሽ እንዲፈቀድለት ለመነ፤ ዞአር ይሖዋ ለጥፋት ካሰባቸው ከተሞች አንዷ ነበረች። ይሖዋ ሎጥን ‘አንዴ ብያለሁ፣ የተባልከውን አድርግ’ ማለት ይችል ነበር። ሆኖም ልመናውን ሰማው፤ ቀድሞ ያሰበው ባይሆንም ዞአርን ላለማጥፋት ወሰነ። (ዘፍ. 19:18-22) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች ርኅራኄ አሳይቷል። በከተማዋና ክፉ በሆኑት ነዋሪዎቿ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዲያውጅ ነቢዩ ዮናስን ላከው። ነዋሪዎቿ ንስሐ ሲገቡ ግን ይሖዋ አዘነላቸው፤ ከተማዋንም ሳያጠፋት ቀረ።—ዮናስ 3:1, 10፤ 4:10, 11፤ w23.07 21 አን. 5
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 12
[ኢዮዓስን] ገደሉት። . . . በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ግን አልቀበሩትም።—2 ዜና 24:25
ከኢዮዓስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢዮዓስ በእንጨት ተደግፎ እንደቆመና ሥር እንዳልሰደደ ዛፍ ነበር። እንደ እንጨት ደግፎ ያቆመው ዮዳሄ ከሞተና የክህደት ነፋስ መንፈስ ከጀመረ በኋላ ኢዮዓስ ተገንድሶ ወደቀ። ይህ ታሪክ እንደሚያሳየው ለአምላክ ያለን ፍርሃት የእምነት አጋሮቻችን ወይም ቤተሰቦቻችን በሚያሳድሩብን በጎ ተጽዕኖ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም። በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን መኖር ከፈለግን አዘውትረን በማጥናት፣ በማሰላሰልና በመጸለይ ለአምላክ ያለንን ፍቅርና ፍርሃት ልናጠናክረው ይገባል። (ኤር. 17:7, 8፤ ቆላ. 2:6, 7) ይሖዋ የሚጠብቅብን ነገር ከአቅማችን በላይ አይደለም። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር በመክብብ 12:13 ላይ ጠቅለል ተደርጎ ተቀምጧል፦ “እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው አጠቃላይ ግዴታ ነውና።” አምላክን የምንፈራ ከሆነ ወደፊት ምንም ይምጣ ምን ጸንተን መቆም እንችላለን። ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ምንም ነገር አያበላሽብንም። w23.06 18-19 አን. 17-19
እሁድ፣ ሐምሌ 13
እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ።—ራእይ 21:5
ቁጥር 5 ሲጀምር፣ ይህን ሐሳብ የተናገረው ‘በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው’ እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 21:5ሀ) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ ራሱ በቀጥታ የተናገረባቸው ጊዜያት ሦስት ብቻ ናቸው፤ ከእነዚህ አንዱ ይሄኛው ነው። ስለዚህ ይህን ዋስትና የሰጠው ኃያል የሆነ መልአክ፣ ሌላው ቀርቶ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ እንኳ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ራሱ ነው። ይህም ቀጣዩ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ያሳያል። ምክንያቱም ይሖዋ ‘ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) ስለዚህ በራእይ 21:5, 6 ላይ በሚገኙት ቃላት ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን። “እነሆ” የሚለውን ቃል እንመልከት። “እነሆ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። እዚህ ጥቅስ ላይ “እነሆ” ካለ በኋላ ምን ይላል? አምላክ “ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ አገላለጽ በመከናወን ላይ ያለን ነገር ያመለክታል። ይሖዋ እዚህ ጥቅስ ላይ እየተናገረ ያለው ወደፊት ስለሚከናወኑ ነገሮች ቢሆንም ቃሉ መፈጸሙ የተረጋገጠ ከመሆኑ የተነሳ እየተፈጸመ እንዳለ አድርጎ ገልጾታል።—ኢሳ. 46:10፤ w23.11 3-4 አን. 7-8
ሰኞ፣ ሐምሌ 14
ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።—ማቴ. 26:75
ሐዋርያው ጴጥሮስ ከድክመቱ ጋር መታገል አስፈልጎታል። ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት እንደሚሠቃይና እንደሚሞት ሲናገር ጴጥሮስ ገሠጸው። (ማር. 8:31-33) ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ከሁሉም የሚበልጠው ማን እንደሆነ በተደጋጋሚ ይከራከሩ ነበር። (ማር. 9:33, 34) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ጴጥሮስ የአንድን ሰው ጆሮ ቆርጧል። (ዮሐ. 18:10) በዚያው ምሽት ጴጥሮስ በፍርሃት ተሸንፎ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ክዶታል። (ማር. 14:66-72) በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ ምርር ብሎ አልቅሷል። ኢየሱስ ቅስሙ በተሰበረው ሐዋርያው ላይ ተስፋ አልቆረጠበትም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ፍቅር እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጠው። ኢየሱስ የበጎቹ እረኛ ሆኖ በትሕትና እንዲያገለግል ጴጥሮስን ጋበዘው። (ዮሐ. 21:15-17) ጴጥሮስም ግብዣውን ተቀብሏል። ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በመገኘት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መካከል ለመሆን በቅቷል። w23.09 22 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15
ግልገሎቼን ጠብቅ።—ዮሐ. 21:16
ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች “የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥ. 5:1-4) ሽማግሌ ከሆንክ፣ ወንድሞችህንና እህቶችህን እንደምትወዳቸው እንዲሁም እነሱን መንከባከብ እንደምትፈልግ እርግጠኞች ነን። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ በሥራ ከመወጠርህ ወይም ከመድከምህ የተነሳ ይህን ኃላፊነትህን መወጣት እንደማትችል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? ስሜትህን አውጥተህ ለይሖዋ ንገረው። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሚያገለግል ማንም ቢኖር አምላክ በሚሰጠው ኃይል ተማምኖ ያገልግል።” (1 ጴጥ. 4:11) ወንድሞችህንና እህቶችህን የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ችግሮች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሊፈቱ አይችሉ ይሆናል። ይሁንና “የእረኞች አለቃ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንተ ይበልጥ ሊረዳቸው እንደሚችል አትዘንጋ፤ በአሁኑ ጊዜም ሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሊረዳቸው ይችላል። አምላክ ከሽማግሌዎች የሚጠብቅባቸው ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ፣ እንደ እረኛ እንዲንከባከቧቸው እንዲሁም ‘ለመንጋው ምሳሌ እንዲሆኑ’ ብቻ ነው። w23.09 29-30 አን. 13-14
ረቡዕ፣ ሐምሌ 16
ይሖዋ የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል።—1 ቆሮ. 3:20
ከሰብዓዊ አስተሳሰብ መራቅ ይኖርብናል። ነገሮችን በሰብዓዊ ዓይን መመልከት ከጀመርን ይሖዋንና መሥፈርቶቹን ችላ ልንል እንችላለን። (1 ቆሮ. 3:19) “የዚህ ዓለም ጥበብ” በአብዛኛው ለኃጢአተኛው ሥጋችን የሚማርክ ነው። አንዳንድ የጴርጋሞንና የትያጥሮን ክርስቲያኖች በከተሞቹ በተስፋፋው ጣዖት አምልኮና የብልግና አኗኗር ተስበው ነበር። የፆታ ብልግናን በቸልታ በማለፋቸው ኢየሱስ ለሁለቱም ጉባኤዎች ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 2:14, 20) በዛሬው ጊዜም የዓለምን የተሳሳተ አመለካከት እንድንቀበል ጫና ይደረግብናል። የቤተሰባችን አባላትና የምናውቃቸው ሰዎች ሊያባብሉንና አቋማችንን እንድናላላ ሊያሳምኑን ይሞክሩ ይሆናል። ለምሳሌ፣ ለምኞታችን እጅ መስጠት ምንም ችግር እንደሌለው ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ይናገሩ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የይሖዋ መመሪያዎች በበቂ መጠን ግልጽ እንዳልሆኑ እናስብ ይሆናል። ይባስ ብሎም ‘ከተጻፈው ለማለፍ’ ልንፈተን እንችላለን።—1 ቆሮ. 4:6፤ w23.07 16 አን. 10-11
ሐሙስ፣ ሐምሌ 17
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17
የኢየሱስ እናት ማርያም ጥንካሬ አስፈልጓት ነበር። ማርያም አላገባችም፤ ሆኖም እንደምትፀንስ ተነገራት። የራሷን ልጆች አሳድጋ አታውቅም፤ ሆኖም መሲሑን ማሳደግ ሊኖርባት ነው። ደግሞም ከወንድ ጋር ግንኙነት ሳትፈጽም ስላረገዘች ሁኔታውን ለእጮኛዋ ለዮሴፍ እንዴት ልታብራራለት ትችላለች? (ሉቃስ 1:26-33) ማርያም ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት ነው? የሌሎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጋለች። ለምሳሌ የተሰጣትን ኃላፊነት አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጣት ገብርኤልን ጠይቃዋለች። (ሉቃስ 1:34) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ረጅም መንገድ ተጉዛ “በተራራማው አገር” ወደምትገኝ አንዲት የይሁዳ ከተማ ሄዳለች። ኤልሳቤጥ ማርያምን አመሰገነቻት፤ እንዲሁም በይሖዋ መንፈስ ተመርታ በማርያም ማኅፀን ውስጥ ያለውን ልጅ በተመለከተ የሚያበረታታ ትንቢት ተናገረች። (ሉቃስ 1:39-45) ማርያም፣ ይሖዋ ‘በክንዱ ታላላቅ ሥራዎች እንዳከናወነ’ ገልጻለች። (ሉቃስ 1:46-51) ይሖዋ በገብርኤልና በኤልሳቤጥ አማካኝነት ማርያምን አጠንክሯታል። w23.10 14-15 አን. 10-12
ዓርብ፣ ሐምሌ 18
ነገሥታት እንዲሁም ለአምላኩና ለአባቱ ካህናት [አደረገን]።—ራእይ 1:6
የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል፤ እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና አላቸው። እነዚህ 144,000 ሰዎች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 14:1) ቅድስት የተባለው የማደሪያ ድንኳኑ ክፍል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና ምድር ላይ ሳሉ ያሉበትን ሁኔታ ማለትም በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች መሆናቸውን ያመለክታል። (ሮም 8:15-17) ቅድስተ ቅዱሳን የተባለው የማደሪያ ድንኳኑ ክፍል ደግሞ ይሖዋ የሚኖርበትን ሰማይን ያመለክታል። ቅድስቱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን የሚለየው “መጋረጃ” ኢየሱስ የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ታላቅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ወደ ሰማይ እንዳይገባ ያገደውን ሥጋዊ አካሉን ያመለክታል። ኢየሱስ ሰብዓዊ አካሉን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል። እነሱም ቢሆኑ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለመቀበል ሥጋዊ አካላቸውን መተው ይጠበቅባቸዋል።—ዕብ. 10:19, 20፤ 1 ቆሮ. 15:50፤ w23.10 28 አን. 13
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 19
ስለ ጌድዮን . . . እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል።—ዕብ. 11:32
ጌድዮን ኤፍሬማውያን ትችት በሰነዘሩበት ወቅት በገርነት ምላሽ ሰጥቷል። (መሳ. 8:1-3) መልስ የሰጠው በቁጣ አልነበረም። ስሜታቸውን ሲገልጹ በማዳመጥ ትሕትና አሳይቷል፤ እንዲሁም ውጥረት የሰፈነበትን ሁኔታ በዘዴ አርግቧል። ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎችም ትችት ሲሰነዘርባቸው በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም በገርነት ምላሽ በመስጠት የጌድዮንን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ያዕ. 3:13) በዚህ መንገድ ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ጌድዮን ምድያማውያንን ድል በማድረጉ የተነሳ ክብር ሲሰጠው የሰዎቹ ትኩረት ወደ ይሖዋ እንዲዞር አድርጓል። (መሳ. 8:22, 23) ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የጌድዮንን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ላከናወኑት ሥራ ይሖዋ እንዲመሰገን ማድረግ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 4:6, 7) ለምሳሌ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የማስተማር ችሎታውን በተመለከተ ቢመሰገን የሰዎቹን ትኩረት የትምህርቱ ምንጭ ወደሆነው ወደ አምላክ ቃል ወይም ከይሖዋ ድርጅት ወደምናገኘው ሥልጠና ማዞር ይችላል። ሽማግሌዎች ‘ወደ ራሴ አላስፈላጊ ትኩረት እየሳብኩ ነው?’ ብለው አልፎ አልፎ ራሳቸውን መመርመራቸው ጠቃሚ ነው። w23.06 4 አን. 7-8
እሁድ፣ ሐምሌ 20
ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ . . . አይደለም።—ኢሳ. 55:8
በጸሎት የጠየቅነውን ነገር ካላገኘን ‘ጥያቄዬ ተገቢ ነው?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። ብዙውን ጊዜ፣ የሚበጀንን ነገር እንደምናውቅ ይሰማናል። ሆኖም የጠየቅናቸው ነገሮች ላይጠቅሙን ይችላሉ። የምንጸልየው ስለ አንድ ችግር ከሆነ ለዚያ ችግር እኛ ከጠየቅነው የተሻለ መፍትሔ ሊኖር ይችላል። የምንጠይቃቸው አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ላይስማሙ ይችላሉ። (1 ዮሐ. 5:14) ልጃቸው እውነት ውስጥ እንዲቆይ ይሖዋን በጸሎት የጠየቁ ወላጆችን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጥያቄያቸው ተገቢ ይመስላል። ይሁንና ይሖዋ ማናችንንም እንድናገለግለው አያስገድደንም። ልጆቻችንን ጨምሮ ሁላችንም እሱን ለማገልገል እንድንመርጥ ይፈልጋል። (ዘዳ. 10:12, 13፤ 30:19, 20) በመሆኑም እነዚህ ወላጆች የልጃቸውን ልብ ለመንካት እንዲረዳቸው ይሖዋን ቢጠይቁ የተሻለ ነው፤ ይህም ልጃቸው ይሖዋን እንዲወደውና የእሱ ወዳጅ እንዲሆን ሊያነሳሳው ይችላል።—ምሳሌ 22:6፤ ኤፌ. 6:4፤ w23.11 21 አን. 5፤ 23 አን. 12
ሰኞ፣ ሐምሌ 21
ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።—1 ተሰ. 4:18
ሌሎችን ማጽናናት አስፈላጊ የፍቅር መግለጫ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ እንደገለጸው፣ ጳውሎስ የተጠቀመበት “ማጽናናት” የሚለው ቃል “አንድ ሰው ከባድ ፈተና ሲያጋጥመው ከጎኑ ቆሞ እሱን ማበረታታት” የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም ማጽናኛ በመስጠት በጭንቀት የተዋጠ የእምነት አጋራችን ተነስቶ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዙን እንዲቀጥል እንረዳዋለን። አንድ ወንድማችንን ወይም እህታችንን ባጽናናን ቁጥር ለእነሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። (2 ቆሮ. 7:6, 7, 13) ርኅራኄ እና ማጽናኛ በጥብቅ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። በምን መንገድ? ሩኅሩኅ ሰው ሌሎችን ለማጽናናትና መከራቸውን ለማቅለል ይነሳሳል። ስለዚህ ርኅራኄ ካለን ሌሎችን ለማጽናናት እንነሳሳለን። ጳውሎስ የይሖዋን ርኅራኄ ከሚሰጠው ማጽናኛ ጋር ያያያዘው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” እንደሆነ ገልጿል።—2 ቆሮ. 1:3፤ w23.11 9-10 አን. 8-10
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22
በመከራ ውስጥ እያለንም እጅግ እንደሰት።—ሮም 5:3
ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አብረናችሁ በነበርንበት ጊዜ መከራ መቀበላችን እንደማይቀር አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ ደግሞም እንደምታውቁት ይኸው ነገር ደርሷል።” (1 ተሰ. 3:4) በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ደግሞ “ወንድሞች . . . ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን። . . . በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር” ብሏቸዋል። (2 ቆሮ. 1:8፤ 11:23-27) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም በሆነ መልኩ መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። (2 ጢሞ. 3:12) አንተም በኢየሱስ በማመንህና እሱን በመከተልህ የተነሳ ጓደኞችህና ዘመዶችህ ስደት አድርሰውብህ ሊሆን ይችላል። በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ያደረግከው ውሳኔ በሥራ ቦታህ ችግር አስከትሎብሃል? (ዕብ. 13:18) ተስፋህን ለሌሎች በማካፈልህ የተነሳ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተቃውመውሃል? ይሁንና የሚደርስብን መከራ ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ልንደሰት እንደሚገባ ገልጿል። w23.12 10-11 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23
ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከተታችሁኝ።—ዘፍ. 34:30
ያዕቆብ ብዙ መከራዎች አጋጥመውታል። ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ ቤተሰባቸውን ያሳፈሩ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ አምጥተዋል። በተጨማሪም ያዕቆብ የሚወዳት ሚስቱ ራሔል ሁለተኛ ልጇን ስትወልድ ሞተችበት። በኋላም ከባድ ረሃብ በመከሰቱ ያዕቆብ በስተ እርጅናው ወደ ግብፅ ለመሰደድ ተገደደ። (ዘፍ. 35:16-19፤ 37:28፤ 45:9-11, 28) ያዕቆብ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም በይሖዋና እሱ በገባው ቃል ላይ ያለውን እምነት አላጣም። ይሖዋም የእሱ ሞገስ እንዳልተለየው ለያዕቆብ አረጋግጦለታል። ለምሳሌ ይሖዋ ያዕቆብን በቁሳዊ አበልጽጎታል። በተጨማሪም ያዕቆብ፣ ‘ሞቷል’ ብሎ ከሚያስበው ልጁ ጋር ከረጅም ጊዜ በኋላ ሲገናኝ ይሖዋን ምን ያህል አመስግኖት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ያዕቆብ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረው ያጋጠመውን መከራ በጽናት መወጣት ችሏል። (ዘፍ. 30:43፤ 32:9, 10፤ 46:28-30) እኛም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ካለን ያልተጠበቁ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት እንችላለን። w23.04 15 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24
ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ ነገር የለም።—መዝ. 23:1
በመዝሙር 23 ላይ ዳዊት በይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት ገልጿል። ዳዊት በእሱና በእረኛው በይሖዋ መካከል ስላለው የጠበቀ ዝምድና ተናግሯል። ዳዊት የይሖዋን አመራር በመከተሉ የደህንነት ስሜት ተሰምቶታል፤ እንዲሁም በእሱ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ዳዊት የይሖዋ ፍቅር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደሚከተለው ያውቅ ነበር። ይህን ያህል እንዲተማመን ያደረገው ምንድን ነው? ዳዊት የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ ይሖዋ ስላሟላለት በደንብ እንደተንከባከበው ተሰምቶታል። ዳዊት የይሖዋን ወዳጅነትና ሞገስ አግኝቷል። በመሆኑም ወደፊት ምንም ቢመጣ የይሖዋ እንክብካቤ እንደማይቋረጥበት እርግጠኛ ነበር። ዳዊት በይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ማንኛውንም ጭንቀት አሸንፎ ጥልቅ ደስታና እርካታ ማግኘት ችሏል።—መዝ. 16:11፤ w24.01 28-29 አን. 12-13
ዓርብ፣ ሐምሌ 25
እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።—ማቴ. 28:20
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በበርካታ አገሮች ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች የስብከቱን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል መጠነኛ ሰላምና ነፃነት አግኝተዋል። እንዲያውም ሥራው በእጅጉ ተስፋፍቷል። በዛሬው ጊዜ የበላይ አካል አባላት የክርስቶስን አመራር ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ለወንድሞች የሚሰጡት መመሪያ የይሖዋንና የኢየሱስን አመለካከት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ይፈልጋሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሽማግሌዎች ደግሞ ለጉባኤዎች መመሪያ ይሰጣሉ። ቅቡዓን ሽማግሌዎች በክርስቶስ ‘ቀኝ እጅ’ ውስጥ ናቸው። (ራእይ 2:1) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሽማግሌዎች ፍጹማን ስላልሆኑ ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። ሙሴና ኢያሱ ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሐዋርያትም እንደዚያው። (ዘኁ. 20:12፤ ኢያሱ 9:14, 15፤ ሮም 3:23) ያም ቢሆን፣ ክርስቶስ ታማኙን ባሪያና የተሾሙ ሽማግሌዎችን በጥንቃቄ እየመራቸው ነው። ደግሞም እንዲህ ማድረጉን ይቀጥላል። በመሆኑም ኃላፊነት ባላቸው ወንድሞች አማካኝነት በሚሰጠን አመራር ላይ ለመተማመን የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን። w24.02 23 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26
የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1
በዛሬው ጊዜ ቅንዓት፣ አመስጋኝነትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለ ይሖዋ በመናገር እሱን ማስደሰት እንችላለን። አገልግሎት ስንወጣ ዋነኛው ዓላማችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ እንዲሁም ለሰማዩ አባታችን የእኛ ዓይነት አመለካከት እንዲያዳብሩ መርዳት እንደሆነ አንዘነጋም። (ያዕ. 4:8) ለሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚል ማለትም እንደ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ያሉትን ባሕርያቱን እንዴት አድርጎ እንደሚገልጽ ስናሳያቸው ደስ ይለናል። በተጨማሪም ይሖዋን ለመምሰል የቻልነውን ሁሉ በማድረግ እሱን ማወደስና ማስደሰት እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች የተለየን እንደሆንን ይታያል። (ማቴ. 5:14-16) ሰዎች የተለየን መሆናችንን ሲያስተውሉ ምክንያቱን ማወቅ ይፈልጉ ይሆናል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከሰዎች ጋር ስንገናኝ የተለየን የሆንበትን ምክንያት ልናብራራላቸው እንችላለን። በዚህም የተነሳ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ አምላካችን ለመቅረብ ይነሳሳሉ። በእነዚህ መንገዶች ይሖዋን ስናወድስ ልቡን እናስደስታለን።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w24.02 10 አን. 7
እሁድ፣ ሐምሌ 27
ማበረታታትም ሆነ . . . መውቀስ [የሚችል] ሊሆን ይገባል።—ቲቶ 1:9
ጎልማሳ ክርስቲያን መሆን ከፈለጋችሁ ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር ይኖርባችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበል፣ ራሳችሁን ወይም ቤተሰባችሁን ለማስተዳደር የሚያስችል ሥራ ለመያዝ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ይረዳችኋል። ለምሳሌ ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ አዳብሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛና ስኬታማ የሆነ ሰው በየዕለቱ የአምላክን ቃል እንደሚያነብና እንደሚያሰላስልበት ይናገራል። (መዝ. 1:1-3) አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቡ የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ያስችለዋል፤ ይህ ደግሞ አጥርቶ ለማሰብና በሚገባ ለማመዛዘን ይረዳዋል። (ምሳሌ 1:3, 4) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያና ምክር ለማግኘት ብቃት ያላቸው ወንድሞች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ጥሩ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ ካላችሁ ግንዛቤ የሚያሰፉና እምነት የሚያጠናክሩ ንግግሮችንና ሐሳቦችን መዘጋጀት ትችላላችሁ። በተጨማሪም ጥሩ ማስታወሻ በመያዝ እምነታችሁን ማጠናከር እንዲሁም ሌሎችን ማበረታታት ትችላላችሁ። w23.12 26-27 አን. 9-11
ሰኞ፣ ሐምሌ 28
ከእናንተ ጎን ያለው፣ ከዓለም ጎን ካለው ይበልጣል።—1 ዮሐ. 4:4
ፍርሃት በሚሰማህ ጊዜ ይሖዋ ወደፊት ሰይጣን ሲጠፋ በሚያደርገው ነገር ላይ አሰላስል። በ2014 የክልል ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ሠርቶ ማሳያ አንድ አባት 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ምን ይል እንደነበር ከልጆቹ ጋር ሲወያይ አሳይቶን ነበር፦ “በአዲሱ ዓለም እጅግ አስደሳች የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ሌሎችን የሚወዱ፣ መንፈሳዊ ሀብት የሚወዱ፣ ልካቸውን የሚያውቁ፣ ትሑቶች፣ አምላክን የሚያወድሱ፣ ለወላጆች የሚታዘዙ፣ የሚያመሰግኑ፣ ታማኝ የሆኑ፣ ለቤተሰባቸው ጥልቅ ፍቅር ያላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች የሆኑ፣ ሁልጊዜ ስለ ሌሎች መልካም ነገር የሚያወሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ገሮች፣ ጥሩ ነገር የሚወዱ፣ ታማኞች፣ እሺ ባዮች፣ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ፣ ሥጋዊ ደስታን ከመውደድ ይልቅ አምላክን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ከልብ ለአምላክ ያደሩ ናቸው፤ ከእነዚህ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኑርህ።” በአዲሱ ዓለም ስለሚኖረው ሕይወት ከቤተሰቦችህ ወይም ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር የመወያየት ልማድ አለህ? w24.01 6 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29
በአንተ ደስ ይለኛል።—ሉቃስ 3:22
መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ በሕዝቡ ደስ ይሰኛል” ይላል። (መዝ. 149:4) በእርግጥም ይሖዋ በቡድን ደረጃ በሕዝቡ እንደሚደሰት ማወቅ በጣም የሚያጽናና ነው! ይሁንና አንዳንዶች ተስፋ ሲቆርጡ ‘ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በእኔ ይደሰት ይሆን?’ የሚል ጥርጣሬ ይፈጠርባቸዋል። በጥንት ዘመን የኖሩ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር የታገሉበት ወቅት ነበር። (1 ሳሙ. 1:6-10፤ ኢዮብ 29:2, 4፤ መዝ. 51:11) መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ይችላሉ። ታዲያ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እንዲሁም መጠመቅ ይኖርብናል። (ዮሐ. 3:16) ይህን ስናደርግ ከኃጢአታችን ንስሐ እንደገባንና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ለእሱ ቃል እንደገባን በሕዝብ ፊት እናሳያለን። (ሥራ 2:38፤ 3:19) ይሖዋ የእሱ ወዳጆች ለመሆን ስንል እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳችን ያስደስተዋል። ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንችለውን ሁሉ እስካደረግን ድረስ ይሖዋ ይደሰትብናል፤ እንደ ቅርብ ወዳጆቹ አድርጎም ይመለከተናል።—መዝ. 25:14፤ w24.03 26 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30
ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።—ሥራ 4:20
የመንግሥት ባለሥልጣናት መስበካችንን እንድናቆም ቢያዝዙንም መስበካችንን በመቀጠል የደቀ መዛሙርቱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይሖዋ አገልግሎታችንን ለመፈጸም እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን። ስለዚህ ይሖዋ ድፍረትና ጥበብ እንዲሰጠን እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም እንዲረዳን እንጠይቀው። ብዙዎቻችን አካላዊ ሕመም፣ ስሜታዊ ቀውስ፣ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት፣ የቤተሰብ ችግር፣ ስደት ወይም ሌላ ዓይነት ፈተና ያጋጥመናል። እንደ ጦርነትና ወረርሽኝ ያሉት ነገሮች ደግሞ የሚያጋጥመንን ችግር መቋቋም ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋሉ። እንግዲያው በይሖዋ ፊት ልብህን አፍስስ። ለአንድ የቅርብ ጓደኛህ እንደምታደርገው፣ የሚሰማህን ነገር ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። ይሖዋ “ለአንተ ሲል እርምጃ” እንደሚወስድ እርግጠኛ ሁን። (መዝ. 37:3, 5) ሳንታክት መጸለያችን ‘መከራን በጽናት ለመቋቋም’ ይረዳናል። (ሮም 12:12) ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን መከራ ያውቃል፤ “እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል።”—መዝ. 145:18, 19፤ w23.05 5-6 አን. 12-15
ሐሙስ፣ ሐምሌ 31
በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።—ኤፌ. 5:10
ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ስናደርግ “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ማስተዋልና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:17) ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ስንፈልግ አምላክ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት እያደረግን ነው። ከዚያም የእሱን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን። “ክፉው” የተባለው ጠላታችን ሰይጣን በዚህ ዓለም ጉዳዮች ከመጠመዳችን የተነሳ ለአምላክ አገልግሎት ጊዜ እንድናጣ ማድረግ ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 5:19) አንድ ክርስቲያን ካልተጠነቀቀ አምላክን ለማገልገል ከሚያስችሉት አጋጣሚዎች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች፣ ለትምህርት ወይም ለሙያው ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮበታል ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት እንዳልሆኑ አይካድም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ ሊይዙ አይገባም። w24.03 24 አን. 16-17