የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 7/8 ገጽ 9-11
  • ኤድስ ማቆሚያው ምን ይሆን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኤድስ ማቆሚያው ምን ይሆን?
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመወሰድ ላይ ያለው እርምጃ
  • የኤድስ ማቆሚያ
  • አፍሪካ ክፉኛ የተጠቃችው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1995
  • ኤድስ የያዛቸውን ሰዎች መርዳት
    ንቁ!—1995
  • ስለ ኤድስ የቀረበ አስደንጋጭ አኃዛዊ መረጃ!
    ንቁ!—2001
  • ከኤድስ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1993
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 7/8 ገጽ 9-11

ኤድስ ማቆሚያው ምን ይሆን?

“በዚህ አሥርተ ዓመት ውስጥ ለኤድስ ክትባት እንደምናገኝለት ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ።”— ፊላደልፊያ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሚገኘው ዊት አይርስት የምርምር ማዕከል የክትባት ምርምር ኃላፊ የሆኑት ጆርግ ኢችበርግ

እስቲ ያስቡት፣ ለኤድስ መድኃኒት አልፎ ተርፎም መከላከያ ክትባት ቢገኝለት ምንኛ ደስ ይለን ነበር! በ1991 በኢጣሊያ ፍሎረንስ ከተማ ውስጥ “ሳይንስን የሚፈታተን ኤድስ” በሚል ጭብጥ ላይ ለመነጋገር ተሰብስበው የነበሩት 9,000 የኤድስ ስፔሻሊስቶች ዋነኛ ዓላማቸው እንዲህ ያለ ፈውስ ማግኘት እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።

በበሽታው ከሚለከፉት አዳዲስ ሰዎች መካከል ከአሥሩ ዘጠኙ በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ውጤታማ የሆነ መፍትሔ እንዲገኝ የሚደረገው ግፊት እያየለ መጥቷል። ሆኖም ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንደሚለው ከሆነ በፍሎረንሱ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት አብዛኛዎቹ “የጉዳዩን አጣዳፊነት የዘነጉት” ይመስላል። “ምናልባት” ይላል መጽሔቱ፣ አውዳሚው መቅሰፍት ከቁጥጥር ውጪ ስለሆነባቸው ብዙዎች “ከችግሩ ጋር መታገሉን ትተውት ይሆናል።”

ጎምዛዛው እውነታ ሳይንቲስቶች እያገኙ ያሉት መፍትሔዎችን ሳይሆን ተጨማሪ ጥያቄዎችን መሆኑ ነው። “ወረርሽኙ ከተከሰተ 10 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ቫይሮሎጂስቶችና የሰውነትን የተፈጥሮ መከላከያ የሚያጠኑ ባለሙያዎች የተጋረጠባቸው ችግር ትንሽም እንኳ ፈቀቅ አላለም” በማለት ኒው ሳይንቲስት ገልጿል። በኤድስ ምርመራ ልዩ ባለሙያ የሆኑት ብሪታኒያዊው ኢያን ዌለር “እጅግ የተራቀቀና ዘመናዊ የፀረ–ቫይረስ ሕክምና የመስጠቱ ጉዳይ ገና ምኑም ያልተጨበጠ ነገር ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ይሁን እንጂ ፀረ–ኤድስ ክትባት ቢገኝስ ሰዉ ምን ያህል ሊያገኘው ይችላል? በአፍሪካ ውስጥ በመሥራት ላይ የሚገኙትና ያሉትን እውነታዎች በዓይናቸው መመልከት የቻሉት ዶክተር ዴኒስ ሲፍሪስ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ለሳንባ ነቀርሳ እጅግ ውጤታማ የሆነ ክትባት አለን፤ ስለዚህ የሳንባ ነቀርሳ እስካሁን መጥፋት ነበረበት። ኩፍኝና ሄፐታይተስ ቢ የተባለው የጉበት በሽታም [ልክ እንደዚሁ] መጥፋት ነበረባቸው። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ በዋነኛነት የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ካሉት በሽታዎች መካከል . . . እነዚህ ሦስት በሽታዎች ይገኛሉ። ስለዚህ ክትባት ቢፈጠርም እንኳ ዋናው ችግር ሰዎች ሁሉ ክትባቱን ማግኘት አለመቻላቸው ነው።”

መድኃኒት የማግኘቱ ተስፋ በጣም የመነመነ በመሆኑ አፍሪካ ያላት ብቸኛ አማራጭ ሰዎች የጾታ ምግባራቸውን እንዲለውጡ ማድረግ ነው። ጥያቄው ግን ‘እንዴት?’ የሚለው ነው።

በመወሰድ ላይ ያለው እርምጃ

በአፍሪካ ውስጥ ኤድስን ለመግታት በመወሰድ ላይ ያለው እርምጃ ኮንዶሞችን ለሰዎች በገፍ ማቅረብ ነው። የከባድ መኪና ሹፌሮች በየኬላው ኮንዶሞችን በነጻ ያገኛሉ። ጋዜጦችን እያተሙ የሚያወጡ ድርጅቶች በፖስታዎች እያሸጉ ይልኳቸዋል። ክሊኒኮችና የጤና ባለሙያዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ኮንዶሞችን ያስመጣሉ።

እንዲህ ዓይነቶቹ እርምጃዎች የኤድስን ስርጭት ለመግታት በተወሰነ ደረጃ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ሊኖር ቢችልም በተለይ በአፍሪካ ውስጥ ከእነዚህ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ። አንጎላ ውስጥ በሚገኘው ሜዲሳን ሳን ፍሮንትየ በጤና ባለሙያነት የሚሠሩት ስቴፋን ቫን ደር ቦርት ሦስት ሚልዮን ኮንዶሞች ቢታደሉ ነገሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት አንድ ሚልዮን ተኩል ወንዶች ኮንዶሞቹ ከማለቃቸው በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም የሚችሉት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው በማለት ገልጸዋል።

በአቅርቦት አኳያ ካለው ችግር ሌላ ኮንዶም ለማንም የሚታደል መሆኑ በአፍሪካ ውስጥ ለኤድስ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት በሆነው ልቅ የጾታ ብልግና ላይ ምን ውጤት ይኖረው ይሆን? ማስረጃዎቹ በሚጠቁሙት መሠረት እነዚህ እርምጃዎች የጾታ ብልግናን ከማዳከም ይልቅ የሚቀሰቅሱ ናቸው። ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ባለሥልጣኖች እንኳ ይህን ሐቅ እየተገነዘቡ ነው። የኮንዶም ማስታወቂያዎች ልቅ የጾታ ብልግናን የሚያበረታቱ በመሆናቸው የመንግሥት የዜና ማሰራጫዎች እነዚህን ማስታወቂያዎች ማስተላለፋቸውን እንዲያቆሙ አንድ የአፍሪካ አገር መመሪያ አስተላልፏል። ኪት ኤድስተን የተባሉ ደራሲ ኤድስ— ካውንትዳውን ቱ ዱምስዴይ (መዓቱን የሚያወርድበትን ቀን እያስቆጠረ ያለው ኤድስ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከዚህ የተሻለ ሐሳብ አቅርበዋል:- “ኮንዶሞችን መጠቀም . . . ከሚያስከትላቸው አደጋዎች አንጻር ሲታይ ሙሉ በሙሉ ከአደጋው ለመጠበቅ በጋብቻ አንድ ለአንድ ተወስኖ መኖር አማራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው።”

ይሁን እንጂ በጋብቻ ሥርዓት ውስጥ እንደ ቀድሞው አንድ ለአንድ ተወስኖ የመኖርን የሥነ ምግባር ደንብ መልሶ ማምጣት ሊጨበጥ የሚችል አማራጭ ነውን?

የኤድስ ማቆሚያ

በአፍሪካ ውስጥ የኤድስ ኤክስፐርት የሆኑት ፕሮፌሰር ሩበን ሼር “ሰዎች ከሴሰኝነት ቢታቀቡ ቫይረሱ ውሎ አድሮ ይጠፋል። በበሽታው የተለከፉት ሰዎች ይሞቱና ቫይረሱ ያከትምለታል” ሲሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይም በደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ ከተማ እየታተመ የሚወጣው ዘ ስታር የተባለው ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ “ከሴሰኝነት ምግባር የራቀ ወይም ሌላው ሰው በተወጋበት መርፌ ያልተወጋ አሊያም ደም ያልወሰደ ሰው [ኤች አይ ቪ] በቀላሉ ሊይዘው አይችልም።”

በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ከ450,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን ከእነዚህ ነገሮች ይጠብቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ሥነ ምግባር መጠበቃቸው ጠቃሚ እንደሆነ አጥብቀው ያምናሉ። ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት የሚከተለው ነው:- ሰዎችን የሠራው ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ስለሆነ ለሰዎች የአኗኗር መንገድ ያወጣው የሥነ ምግባር ደንብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው። በዕብራውያን 13:4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ለዚህ አንዱ ጥሩ ምሳሌ ነው። እንዲህ የመሰሉትን ጥቅሶች በሥራ ላይ የሚያውሉት ሰዎች ደስታ እንዳጡ ሆኖ አይሰማቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አካልንና ስሜትን ከሚጎዱ ከብዙ መጥፎ ነገሮች ራሳቸውን መጠበቅ ችለዋል።— ከሥራ 15:29፤ ከ2 ቆሮንቶስ 7:1ና ከኤፌሶን 5:3–5 ጋር አወዳድር።

የዜና ማሰራጫዎች በአፍሪካ ስለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ሥነ ምግባር ብዙ ጊዜ በጎ አስተያየት ሰንዝረዋል:- “[የይሖዋ ምሥክሮች] ጭምቶችና ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎችን የሚጠብቁ ሥርዓታማ ዜጎች መሆናቸውን . . . በተግባር አሳይተዋል” በማለት በለንደን ከተማ፣ እንግሊዝ ውስጥ የሚታተመው ዴይሊ ቴሌግራፍ ገልጿል። አክሎም “የአፍሪካ ሕብረተሰብ ጠባይ የሆነው ልቅ የጾታ ሥነ ምግባርና ከአንድ ሚስት በላይ የማግባት ልማድ በምሥክሮቹ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው” ብሏል። ኮንቴምፖራሪ ትራንስፎርሜሽንስ ኦቭ ሪሊጅን የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ብራያን ዊልሰን “በአፍሪካ ሕብረተሰብ ውስጥ ምሥክሮቹ . . . ፈጽሞ የተለዩ ሰዎች ናቸው፤” እንዲሁም “የሥነ ምግባር ሥርዓታቸው . . . ያስገኘው ውጤት በእነርሱ ላይ በግልጽ ይታያል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህ ማለት ግን የይሖዋ ምሥክሮች ኤድስ እንዳይነካቸው ሙሉ በሙሉ ተጋርደዋል ማለት አይደለም። አንዳንዶች እነርሱ የሚከተሉትን ዓይነት የክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓቶችን በማይከተሉ የትዳር ጓደኞቻቸው አማካኝነት በበሽታው ተለክፈዋል፤ ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ከመሆናቸው በፊት በሽታው ይዟቸዋል። በተጨማሪም ጥቂቶች በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ ወዳለው ልቅ ሥነ ምግባር ተመልሰዋል። ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት የተከተሉት ጎዳና ለኤድስ ዳርጓቸዋል። (ገላትያ 6:7) ይሁን እንጂ በራሳቸው ፍላጎት ብልሹ የሥነ ምግባር አኗኗር የተከተሉ ሰዎች የክርስቲያን ጉባኤ አባል የመሆንን መብት አጥተዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:13፤ 6:9, 10) ሆኖም ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ፈጣሪ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠበቃቸው የተነሳ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ደህንነት አግኝተዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኤድስ ለመሳሰሉ መቅሰፍቶች ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚገኝበት ጊዜ መቅረቡን የሚጠቁም መሆኑ ያስደስታል። (ራእይ 21:1–4) ይሖዋ አምላክ የመጥፎ ሥነ ምግባር ውጤቶች የሆኑት እንደ ኤድስ ያሉ በሽታዎች ሙሉ በሙሉ የሚወገዱበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። ሁሉም ሰው እውነተኛ ደስታን የሚያስገኝ ትክክለኛና ጤናማ አኗኗር ስለሚከተል ሌላው ሰው ባመጣው መዘዝ ለመከራ የሚዳረግ ሰው ፈጽሞ አይኖርም።— ኢሳይያስ 11:9፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በምርምርና ለእድገት በሚደረግ ጥረት በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማጥፋት አይገባንም . . . እንደገና ለንጹሕ ሥነ ምግባር መገዛት ያስፈልገናል።”

ስለ ሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ የሚያጠኑት ደቡብ አፍሪካዊው ዶክተር ማርክ ሄንድሪክስ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኤድስ መቅሰፍት ራስን ለመጠበቅ የሚረዳው ትልቁ መንገድ በጋብቻ አንድ ለአንድ ተወስኖ መኖር ነው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ እንደ ኤድስ የመሳሰሉ በሽታዎች ፈጽሞ የማይኖሩበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ