የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 10/8 ገጽ 18-20
  • ለኤድስ ተጋልጫለሁን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለኤድስ ተጋልጫለሁን?
  • ንቁ!—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሳይታወቅ ውስጥ ውስጡን የሚበላ በሽታ
  • ወጣቶች ለበሽታው የተጋለጡ ናቸውን?
  • ሊይዝህ ይችላል!
  • ከኤድስ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1993
  • ኤድስ የያዛቸውን ሰዎች መርዳት
    ንቁ!—1995
  • ኤድስን እንዴት መከላከል ይቻላል?
    ንቁ!—1999
  • ኤድስ በአፍሪካ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
    ንቁ!—1995
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1994
g94 10/8 ገጽ 18-20

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ለኤድስ ተጋልጫለሁን?

የኒውስዊክ መጽሔት ዜናው ‘ዓለምን አስደንግጧል’ ሲል ዘግቧል። ኅዳር 7, 1991 ታዋቂው አሜሪካዊ ሯጭ ኧርቪን “ማጂክ” (“ተአምረኛው”) ጆንሰን የኤድስ ቫይረስ እንዳለበት ለመጽሔቱ አስታወቀ። ነገሩን ማመኑ ከተሰማ በኋላ ስለ ኤድስ ገለጻ የሚሰጡ ጣቢያዎችን የስልክ ጥሪዎች አጣደፏቸው። አንዳንድ ሆስፒታሎች ኤድስ ያለባቸው መሆን አለመሆናቸውን ሊመረመሩ በመጡ ሰዎች ተጥለቀለቁ። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ለትንሽ ጊዜም ቢሆን የልክስክስነት ባሕርያቸውን ቀነሱ።

ምናልባትም ይህ ማስታወቂያ ኃይለኛ ተጽዕኖ ያሳደረው በወጣቶች ላይ ሳይሆን አይቀርም። የአንድ ዩኒቨርሲቲ የጤና አገልግሎት ዲሬክተር እንዲህ ብለዋል:- “ተማሪዎች ‘እሱ ላይ የደረሰው እኔም ላይ ሊደርስ ይችላል’ የሚለውን ነገር ለአጭር ጊዜም ቢሆን አስበውበት ነበር። . . . አብዛኞቹ ተማሪዎች ግን ማጂክ ጆንሰን ላይ የደረሰው ነገር ባሕርያቸውን እንዲለውጡ አላደረጋቸውም። አሁንም ‘ላመልጥ እችላለሁ’ ብለው ያስባሉ።”

“ቸነፈር” ማለትም በፍጥነት የሚዛመት ተላላፊ በሽታ የጊዜያችን ዋና መለያ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮ ነበር። (ሉቃስ 21:​11) ኤድስ በርግጥም ቸነፈር ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ኤድስ ተሠራጭቶ 100,000 ሰዎች በኤድስ መያዛቸው እስኪታወቅ ድረስ ስምንት ዓመታት (ከ1981 እስከ 1989) ፈጅቶ ነበር። ሌሎች 100, 000 ተጨማሪ ሰዎች መያዛቸው የታወቀው ግን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነበር!

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳለው ይህ አስጨናቂ አኀዛዊ ዘገባ “[የኤድስ] ወረርሽኝ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በምን ያህል ከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ እንዳለ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል።” ይሁን እንጂ ኤድስ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ ብዙ ሕዝብ በሞትና በሥቃይ እያጨደ ያለ በዓለም ዙሪያ የተሠራጨ ወረርሺኝ ነው። በሎስ አንጀለስ የሕፃናት ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶክተር ማርቪን ቤልዘር ኤድስን “በ1990ዎቹ በወጣቶች ፊት የተደቀነ ከሁሉ ይበልጥ አስፈሪ የሆነ ችግር” ሲሉ መጥራታቸው የጎላ ትርጉም ያለው ነው።

ሳይታወቅ ውስጥ ውስጡን የሚበላ በሽታ

ለመሆኑ ይህ ግራ የሚያጋባ በሽታ ምንድን ነው? ይህን ያህል ቀሳፊ የሆነውስ ለምንድን ነው? ዶክተሮች እንደሚያምኑት ኤድስ የሚጀምረው ረቂቅ የሆነው ኤች አይ ቪ (ሂውማን ኢሚውኖዴፊሸንሲ ቫይረስ) ደም ውስጥ ሲገባ ነው። ቫይረሱ ከገባ በኋላ በሰውነት ውስጥ የሚገኙትን ቲ ሴል የሚባሉ አጋዥ ነጭ የደም ሴሎች እያሳደደ የማጥፋት ዘመቻ ይጀምራል። እነዚህ ሴሎች ሰውነት በሽታን እንዲከላከል በማገዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው። የኤድስ ቫይረስ ግን የነሱን ሥራ በማስተጓጎል የሰውነትን የበሽታ መከላከያ ሥርዓት ያንኮታኩተዋል።

በቫይረሱ የተለከፈው ሰው ሕመም ሳይሰማው ረጅም ጊዜ ሊያልፍ ይችላል። አንዳንዶች በቫይረሱ ከተለከፉ በኋላ ለአሥር ዓመታት ያህል ምንም ዓይነት የበሽታው ምልክት ላይታይባቸው ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን አንድ ሰው ጉንፋን ሲይዘው የሚሰማውን ዓይነት ምልክቶች ማለትም የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ትኩሳትና ተቅማጥ የመሳሰሉ የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ። የበሽታ መከላከያው ሥርዓት በአደገኛ ሁኔታ እየተዳከመ ሲሄድ በሽተኛው የሳምባ ምች (ኒሞኒያ)፣ ማጅራት ገትር (ሜነንጃይተስ)፣ የሳምባ ነቀርሳ (ቱበርክሎሲስ)፣ ወይም አንድ ዓይነት ካንሰር፣ ባጠቃላይ ብዙ ዓይነት በሽታዎች ይይዙታል። እነዚህ በሽታዎች አጋጣሚ ጠባቂዎች ይባላሉ፤ ምክንያቱም በሽተኛው በሽታን ለመከላከል ያለው ኃይል ሲቀንስ ጠብቀው የሚይዙ ናቸው።

“በማያቋርጥ ሥቃይ ላይ ነኝ” ይላል ኤድስ የያዘው አንድ የ20 ዓመት ወጣት። በሽታው በትልቁ አንጀቱና ሬክተም በሚባለው የሰውነቱ ክፍል ላይ የማይድን ቁስል (አልሰር) አስከትሎበታል። ኤድስ ግን ቀላል የጤንነት መቃወስና ሥቃይ ማስከተል ብቻ ሳይሆን በበሽታው የተያዙትን በሙሉ የሚገድል ነው። በሽታው ከ1981 ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንኳን በሚልዮን ወደሚቆጠሩ ሰዎች ተሰራጭቷል። እስካሁን ከ160,000 በላይ የሚሆኑት ሞተዋል። በ1995 የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር የዚህ እጥፍ እንደሚሆን ጠበብት ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ኤድስን እንደሚያድን የሚታወቅ ምንም መድኃኒት የለም።

ወጣቶች ለበሽታው የተጋለጡ ናቸውን?

እስካሁን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኤድስ መያዛቸው ከታወቀው መካከል በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ከ1 በመቶ ያነሱ ናቸው። ስለሆነም አንተም በግልህ የምታውቀው በዚህ በሽታ የሞተ ወጣት አይኖር ይሆናል። ይህ ማለት ግን ወጣቶች ለበሽታው አልተጋለጡም ማለት አይደለም! በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኤድስ ከተለከፉት መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። የበሽታው ምልክት ሳይታይ ለብዙ ዓመታት ሊቆይ ስለሚችል ከነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ በቫይረሱ የተለከፉት በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ እያሉ መሆን አለበት። ሁኔታው በዚህ ዓይነት ከቀጠለ በሺህ የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወጣቶች የኤድስ በሽተኞች ይሆናሉ።

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳለው ይህ ቀሳፊ ቫይረስ በሽታው ባለባቸው ሰዎች “ደም እንዲሁም ከወንድና ከሴት የጾታ ብልት በሚወጡ ፈሳሾች” ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ “በበሽታው ከተለከፈ ሰው ጋር በጾታ ብልት፣ በአፍም ሆነ በፊንጢጣ በኩል በሚደረግ የጾታ ግንኙነት” አማካኝነት ኤች አይ ቪ ይተላለፋል። አብዛኞቹ ሰዎች በበሽታው የተለከፉት በዚህ መንገድ ነው። “በሽታው ያለበት ሰው በተጠቀመበት መርፌ ወይም ስሪንጋ በመጠቀም ወይም በመወጋትም” ኤድስ ሊተላለፍ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ “አንዳንድ ሰዎች” በኤች አይ ቪ የተበከለ “ደም በመውሰድ በሽታው ተላልፎባቸዋል።” — ቮልዩንታሪ ኤች አይ ቪ ካውንስሊንግ ኤንድ ቴስቲንግ:– ፋክትስ፣ ኢሹስ ኤንድ አንሰርስ (ስለ ኤች አይ ቪ የሚሰጥ ምክርና ምርመራ:– እውነታዎቹ፣ አከራካሪዎቹ ጉዳዮችና መልሶቻቸው )

እንግዲያው ብዙ ወጣቶች ለበሽታው ተጋልጠዋል። የሚያስደነግጥ ብዛት ያላቸው ወጣቶች (አንዳንዶች እንደሚሉት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉት ወጣቶች 60 በመቶ የሚሆኑት) የተከለከሉ አደንዛዥ መድኃኒቶችን ወስደዋል። ከነዚህ መድኃኒቶች አንዳንዶቹ በመርፌ የሚወሰዱ በመሆናቸው በቫይረሱ በተበከለ መርፌ አማካኝነት በበሽታው ለመያዝ ያላቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት 82 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የአልኮል መጠጦች እንደወሰዱ፣ 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ እስካሁን እየወሰዱ እንዳሉ ታውቋል። አንድ ጠርሙስ ቢራ ስለጠጣህ ኤድስ አይዝህም፤ ይሁን እንጂ መጠጥ ከወሰድክ በኋላ አስተሳሰብህ ሊዛባና በልክስክስነት ወንድ ከወንድ ጋር የሚደረግ ወይም ከሴት ጋር የሚደረግ በጣም አደገኛ የሆነ የጾታ ግንኙነት ልትፈጽም ትችላለህ።

በ1970 በ15 ዓመታቸው የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ልጃገረዶች ብዛት ከ5 በመቶ ያንስ ነበር። በ1988 ቁጥሩ ወደ 25 በመቶ ከፍ አለ። የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 20 ዓመት ከሆናቸው ወጣቶች ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና 86 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች የጾታ ግንኙነት ማድረግ የጀመሩ ናቸው። ሌላው የሚያስፈራ ዘገባ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ ከሚገኙ 5 ወጣቶች 1ዱ ከአራት ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት ያደርጋል። አዎን፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ብዙ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ያደርጋሉ፤ የጾታ ግንኙነት ማድረግ የሚጀምሩትም ገና በትንሽነታቸው ነው።

በሌሎች አገሮችም ያለው ሁኔታ ከዚህ ያነሰ አይደለም። በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ ካሉት ወጣቶች ወደ ሰባ አምስት በመቶ የሚጠጉት ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። በአፍሪካ ባሉ አገሮች ውስጥ ብዙ ወንዶች በኤድስ ቫይረስ ላለመለከፍ ሲሉ በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ ከሚገኙ ወጣት ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለማድረግ መርጠዋል። ውጤቱ ምን ሆነ? በኤድስ የተያዙት በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።

የኤድስ መስፋፋት ይህን ጎጂ ባሕርይ ምንም ያህል የቀነሰው አይመስልም። አንዱን የላቲን አሜሪካ አገር እንውሰድ። “የጾታ ግንኙነት ማድረግ ከጀመሩ ያላገቡ ወጣቶች” ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት “በኤድስ ቫይረስ ለመለከፍ ያላቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።” ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ ለበሽታው የተጋለጡ መሆናቸው የሚሰማቸው 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ‘እኔን አይዘኝም’ ይላሉ። ሆኖም “ይህ አገር በአሜሪካ አኅጉሮች ውስጥ በኤች አይ ቪ የተለከፉ በጣም ብዙ ሰዎች ካሉባቸው አገሮች አንዱ ነው።” — የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል

ሊይዝህ ይችላል!

የኤድስ ወረርሽኝ፣ የጾታ ብልግና ‘ፍጻሜ’ “እንደ እሬት የመረረ ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ እውነተኝነት ያረጋግጣል። (ምሳሌ 5:​3–5፤ 7:​21–23) እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የሚጠቅሰው ይህ ዓይነቱ ድርጊት የሚያስከትለውን መንፈሳዊና ስሜታዊ ጉዳት ነው። ሆኖም የጾታ ብልግና ብዙ አካላዊ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም።

እንግዲያው ወጣቶች በኤድስም ሆነ በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች ለመለከፍ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ከእውነታው ባልራቀ መንገድ መመልከታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ኤድስ ‘እኔን አይዘኝም’ የሚለው አመለካከት ሞት ሊያስከትል የሚችል ነው። ዴቪድ የተባለ አንድ ወጣት “በአሥራ አምስት ወይም በአሥራ ስድስት ወይም በአሥራ ሰባት፣ በአሥራ ስምንት፣ በአሥራ ዘጠኝ ወይም በሃያ ዓመትህ በበሽታው ልያዝ አልችልም ብለህ ታስብ ይሆናል” ብሏል። ሐቁ ግን የተገላቢጦሽ ነው። ዴቪድ በ15 ዓመቱ ኤድስ ያዘው።

እንግዲያው በግልጽ ለመናገር፣ ያልተፈቀዱ አደንዛዥ መድኃኒቶች እየወሰድክ ወይም ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት እየፈጸምክ ከሆነ ለኤድስ ተጋልጠሃል!

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች

በርዕሰ አንቀጹ ላይ የሚወጣው ስለ ኤድስ ነው። ይሁን እንጂ ዘ ሜዲካል ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- ‘ካናዳ በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች ወረርሽኝ ተጥለቅልቃለች።’ ካናዳ ብቻ አይደለችም። “በየዓመቱ 2.5 ሚልዮን የሚሆኑ በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ የሚገኙ አሜሪካዊያን በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች ይለከፋሉ” ይላል የዩናይትድ ስቴትስ የሥነ ሕዝብ አማራጮች ማዕከል የተባለው ድርጅት። “ይህ አኀዝ የጾታ ግንኙነት ማድረግ ከጀመሩ በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ የሚገኙ ስድስት ወጣቶች አንዱንና በአገሪቱ ውስጥ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ከተለከፉት አንድ አምስተኛውን የሚወክል ነው።”

ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ቂጥኝ በመጥፋት ላይ ያለ በሽታ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እንደገና አገርሽቷል። በበሽታው መለከፋቸው በአኀዝ ከሚገለጸው ውስጥ ደግሞ ምን ጊዜም ወጣቶች አይጠፉም። ጨብጥና ቻላሜድያ (በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በብዛት ተስፋፍተው የሚገኙ የአባለዘር በሽታዎች ናቸው) እነሱን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በአስደናቂ ሁኔታ ተቋቁመውታል። ብዙ ወጣቶች በነዚህ በሽታዎች ተይዘዋል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔትም በተመሳሳይ በጾታ ብልት ላይ በሚወጣ ኪንታሮት የሚሠቃዩ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር “ከፍተኛ ጭማሪ” ማሳየቱን ዘግቧል። በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች የኸርፕስ ቫይረስ አለባቸው። ሳይንስ ኒውስ በተባለው መጽሔት መሠረት “በጾታ ብልታቸው ላይ ኸርፕስ የወጣባቸው ሰዎች ኤድስን በሚያመጣው ቫይረስ [ኤች አይ ቪ] ለመለከፍ ያላቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።”

የሥነ ሕዝብ አማራጮች ማዕከል እንዳለው “በሌላ የዕድሜ ቡድን ውስጥ ካሉት ይበልጥ በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች በብዛት የሚጠቁት ወጣቶች ቢሆኑም እነሱ ትንሽ እንኳን ጥንቃቄ አያደርጉም። በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሳይታወቁ ከቀሩ እንዲሁም ሕክምና ካልተደረገላቸው በዳሌ አካባቢ ያሉ ብልቶች በከፍተኛ ሁኔታ የመቆጣት በሽታ፣ መካንነት፣ ከማኅፀን ውጭ ማርገዝ እንዲሁም የማኅፀን አፍ ካንሰር ሊያስይዙ ይችላሉ።”

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የተከለከሉ መድኃኒቶች በመርፌ የሚወስድ ወይም ልቅ የጾታ ግንኙነት የሚፈጽም ማንኛውም ሰው በኤድስ ለመያዝ ራሱን በከፍተኛ ሁኔታ ያጋልጣል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ