የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 5/8 ገጽ 24-26
  • የተራራ ጎሪላዎችን መጎብኘት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የተራራ ጎሪላዎችን መጎብኘት
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በእጃችን ልንነካቸው እስከምንችል ድረስ ተጠጋናቸው!
  • የቆላ ጎሪላዎችን መጎብኘት
    ንቁ!—2012
  • ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ የሆነችው ጋቦን
    ንቁ!—2008
  • የሕፃኗ ጎሪላ ለቅሶ
    ንቁ!—2008
  • ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረበ እንስሳት
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 5/8 ገጽ 24-26

የተራራ ጎሪላዎችን መጎብኘት

በታንዛኒያ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በአሁኑ ጊዜ በሩዋንዳና በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ድንበር ላይ በሚገኘው የእሳተ ገሞራ አካባቢ 320 የሚያክሉ ብቻ ይኖራሉ። ሌሎች 300 የሚያክሉት ደግሞ በኡጋንዳ በሚገኘው ጥቅጥቅ ያለ ደን ይኖራሉ። እነዚህ እንስሳት የተራራ ጎሪላዎች ሲሆኑ በዓለማችን ፈጽሞ የመጥፋት አደጋ ከተደቀነባቸው አጥቢ እንስሳት መካከል የሚመደቡ ናቸው!

እነዚህ ፍጥረታት የሚገኙበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ከፍተኛ ሥራ የሠሩት አሜሪካዊቷ ሊቀ ስነ እንስሳ (zoologist) ዳያን ፎሲ ናቸው። ፎሲ ስለ ተራራ ጎሪላዎች ለማጥናት ወደ አፍሪካ የመጡት በ1960ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ነበር። በዚያ ጊዜ በአደን ምክንያት ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ ተመናምኖ ነበር። መንፈሰ ጠንካራ የሆኑት እኚህ ሳይንቲስት በቪሩንጋ ተራራዎች የመናኝ ዓይነት ኑሮ እየኖሩ ከጎሪላዎች ጋር ተወዳጁ። ፎሲ የጥናታቸውን ግኝቶች በመጽሔቶችና ጎሪላስ ኢን ዘ ሚስት በተባለው መጽሐፋቸው አወጡ። ከዓመታት በኋላ እነኚህን ፀጉራም ወዳጆቻቸውን ከእልቂት ለማዳን አዳኞችን አምርረው ለመዋጋት ቆርጠው ተነሱ። ይሁን እንጂ ራሳቸው በጀመሩት ዘመቻ ሳቢያ በ1985 ማንነቱ ባልታወቀ ሰው ተገደሉ።

እኔና ባለቤቴ እነዚህን ሰላማዊ ፍጥረታት በዓይናችን ለማየት ባደረብን ጉጉት በመነሳሳት በ1993 የጎሪላዎቹን መኖሪያ ለመጎብኘት ወሰንን። ያጋጠመንን ሁኔታ እንድንተርክ ይፈቀደልን።

ከአስጎብኚዎቻችን ጋር የ3,700 ሜትር ከፍታ ካለው የቪሶኬ እሳተ ገሞራ ግርጌ ተነስተን በሩዋንዳ እስከሚገኘው የእሳተ ገሞራዎች ብሔራዊ ፓርክ እስክንደርስ ድረስ ለአንድ ሰዓት ያህል ተራራውን ወጣን። በጣም ደክሞን ስለነበረ እረፍት በማድረግ ላይ እንዳለን ጎሪላዎቹ አካባቢ ስንደርስ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን አስጎብኚዎቻችን አስረዱን። እነዚህን እንስሳት በአንድ ቀን ውስጥ እንዲጎበኙ የሚፈቀድላቸው ስምንት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ተነገረን። ይህ የሆነው እንስሶቹ በሽታ እንዳይጋባባቸውና እንዳይረበሹ ሲባል ነው።

ከአስጎብኚዎቹ አንዱ “ጫካው ውስጥ ከገባን በኋላ ድምፃችንን በጣም ዝቅ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን በጫካው ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች አራዊትና አእዋፍ ለማየት ያስችለናል። በዚህ ጫካ ከተራራ ጎሪላዎች በተጨማሪ ወርቃማ ዝንጀሮዎች፣ ሚዳቋዎች፣ ድኩላዎች፣ ዝሆኖችና ጎሾች ይገኛሉ” ሲል አሳሰበን።

በተጨማሪም በፓርኩ ውስጥ ጉንዳንና ሳማ እንደሚኖር፣ እንዲሁም በመንገዳችን ላይ ካፊያና ጭቃ ሊያጋጥመን እንደሚችል ተነገረን። እኔና ባለቤቴ ተያየን። እንዲህ ላለው ሁኔታ ተዘጋጅተን አልመጣንም ነበር። ይሁን እንጂ ደጎቹ አስጎብኚዎች የዝናብ ልብስና የጭቃ ጫማ በማዋስ ረዱን።

ከዚያም አስጎብኚያችን ጎሪላዎቹ ከሰው የሚተላለፍ በሽታ በጣም እንደሚያጠቃቸውና እንስሳቱን ከበሽታ ለመጠበቅ የታመመ ወይም ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ያለበት ሰው ካለ ወደ ኋላ መመለስ እንደሚኖርበት ነገረን። “ጎሪላዎቹ አጠገብ በምትሆኑበት ጊዜ መሳል ወይም ማስነጠስ ካስፈለጋችሁ ከእንስሳቱ ዞር በሉ፣ አፍንጫችሁንና አፋችሁንም ለመሸፈን ሞክሩ” አለን ሌላው አስጎብኚ። “በጭጋጋማ መኖሪያቸው እንግዶች መሆናችንን አትዘንጉ!” አለን።

በእጃችን ልንነካቸው እስከምንችል ድረስ ተጠጋናቸው!

የምንወጣው አቀበት እየጨመረ መጣ። 3,000 ሜትር ከፍታ ላይ ደረስን። አየሩ እየሳሳ በመምጣቱ መተንፈስ ያስቸግረን ጀመር። መንገዱም እየቀጠነ መጣ። ቢሆንም በሰፊው የተንሰራፉትንና በሐረጎች፣ በቁጥቋጦዎችና በዛፍ ሽበት የተከበቡትን የኮሶ ዛፎች ማየታችን በጣም አስደሰተን። ለጫካው ገነታዊ ውበት ሰጥተውት ነበር።

ጎሪላዎች ምግብ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩና በአንድ ቦታ የማይረጉ ቢሆኑም አስጎብኚዎቹ በትናንትናው ቀን የነበሩበትን ቦታ መፈለግ ጀመሩ። ከመሃከላችን አንዱ “ያውላችሁ እዚያ!” አለ። የባለ ብርማ ጀርባው ጎሪላ መኝታ በለስላሳ ቁጥቋጦዎች ላይ ተነጥፏል።

“ኡሙጎሜ ይባላል” ሲል ነገረን አስጎብኚያችን። “አንድ ወንድ ጎሪላ 14 ዓመት ሲሞላው ጀርባው ነጭ ይሆንና ብርማ ቀለም ይይዛል። በዚህ ጊዜ የቡድኑ መሪ መሆኑ ይታወቃል። ሁሉንም ሴት ጎሪላዎች የሚያጠቃው ባለ ብርማ ጀርባው ጎሪላ ብቻ ነው። የእሱ ታናናሾች የሆኑት ለማጥቃት ቢሞክሩ ወዲያው ከቡድኑ ይወገዳሉ። ይሁን እንጂ ባለ ብርማ ጀርባውን ለመግደል የሚችል ተቀናቃኝ ከተነሳ ሁሉንም ልጆች ጭምር ይገድላል። ከዚያ በኋላ አዲሱ መሪ በቦታው ተተክቶ በቡድኑ ውስጥ ካሉት ሴቶች የራሱን ልጆች ይወልዳል።”

አስጎብኚዎቹን ተከትለን በጣም ወደሚያምር የቀርካሃ ጫካ በመግባት ላይ እንዳለን ከመካከላችን አንዱ “ጎሪላ ምን ያህል ዓመት ይኖራል?” ሲል ጠየቀ።

“እስከ 40 ዓመት” የሚል አጭር መልስ ተሰጠን።

ጎርነን ያለ የጉርምርምታ ድምፅ እንደሰማን ከመካከላችን አንዱ ቀስ ብሎ “እሽ . . .” አለ። “ምንድነው? ጎሪላ ነው?” አይደለም። አንደኛው አስጎብኚ ምላሽ ለማግኘት ሲል የጎሪላ ድምፅ ማሰማቱ ነበር። በጣም ሳንቀርብ አልቀረንም!

በእርግጥም ደርሰናል። ከእኛ 5 ሜትር ብቻ በሚያህል ርቀት 30 የሚያክሉ ጎሪላዎች አሉ! በጸጥታ በርከክ እንድንል ተነገረን። “አንድ ነገር የምትወረውሩባቸው ሊመስላቸው ስለሚችል ጣታችሁን ወደ እነርሱ አታመልክቱ። አትጩሁባቸው። ፎቶግራፍ በምታነሱበት ጊዜ በቀስታና በጥንቃቄ አንሱ። ፍላሽ አትጠቀሙ” ሲል አንደኛው አስጎብኚ ተማጸነን።

በእጃችን ልንነካቸው እስከምንችል ድረስ ተጠጋናቸው! ይሁን እንጂ ማናችንም እጃችንን ከመሰንዘራችን በፊት አስጎብኚያችን “አትንኳቸው!” በማለት በሹክሹክታ ነገረን። ይህ እንደተነገረን ወዲያው ሁለት ትናንሽ ጎሪላዎች ወደ እኛ መጡ። አስጎብኚያችን በትንሽ እንጨት ቀስ ብሎ መታ መታ ሲያደርጋቸው ግልገሎቹ ጎሪላዎች እንደ ሕፃናት እየተላፉ ቁልቁል ተንከባለሉ። ይህ ዓይነቱ ጨዋታ ገደቡን እንዳያልፍ እናትየዋ ትቆጣጠራለች።

ባለ ብርማ ጀርባው ጎሪላ ራቅ ብሎ ይመለከተናል። በድንገት ወደ እኛ መጣ አለና ከተቀመጥንበት ጥቂት ሜትሮች ብቻ ርቆ ተቀመጠ። በጣም ግዙፍ ሲሆን 200 ኪሎ ግራም ያህል ሳይመዝን አይቀርም! ዓይኑን ከእኛ ላይ ባይነቅልም ምግቡን እየበላ ስለነበረ ብዙም ትኩረት አልሰጠንም። የጎሪላ ዋነኛ ሥራ መብላት ነው። አንድ ባለ ብርማ ጀርባ ጎሪላ በቀን ውስጥ እስከ 30 ኪሎ ግራም የሚመዝን ምግብ ሊበላ ይችላል። የቡድኑ አባላት በሙሉ ከማለዳ እስከ ምሽት ያለውን ጊዜ የሚያሳልፉት ምግብ በመፈለግ ነው። አንዳንድ ጊዜ ባገኙት ጣፋጭ ምግብ ምክንያት ሲጣሉ ይታያሉ።

በጣም የሚወዱት ምግብ ሴኔሲዮ የተባለውን ግዙፍ ተክል ውስጠኛ አካል ነው። በተጨማሪም ሰለሪ የተባለውን ተክል፣ የአንዳንድ ተክሎችን ሥርና የቀርካሃ ቀንበጥ ይወዳሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የቀርካሃ ቀንበጥ ከእሾህ ቅጠል፣ ከሳማ፣ ከአሽክትና ከተለያዩ ሥራ ሥሮችና ሐረጎች ጋር ቀላቅለው “ሰላጣ” ይሠራሉ። ከመካከላችን አንዱ “ጎሪላዎች ሳማ ሲይዙና ሲጠራርጉ እጃቸው የማይቃጠለው ለምንድን ነው” ሲል ጠየቀ። “የእጃቸው መዳፍ በጣም ወፍራም ቆዳ ስላለው ነው” ሲል አንደኛው አስጎብኚ መለሰ።

ይህን ሰላማዊ ትዕይንት እያየን በመደሰት ላይ ሳለን ግዙፉ ወንድ ጎሪላ በሁለት እግሮቹ ቆመና ደረቱን በቡጢ ከመታ በኋላ በጣም የሚያስደነግጥ ጩኸት አሰማ! ወደ አንደኛው አስጎብኚ ከሮጠ በኋላ ሊደርስበት ትንሽ ሲቀረው ቀጥ ብሎ ቆመ። አስጎብኚውን በሚያስፈራ አስተያየት ተመለከተው! አስጎብኚያችን ግን ምንም አልደነገጠም። ይልቁንም ቁጭ ካለ በኋላ የማጉረምረም ድምፅ እያሰማ በቀስታ ወደኋላ ተንቀሳቀሰ። ባለ ብርማ ጀርባው ጎሪላ ጉልበቱን ሊያሳየን የፈለገ ይመስላል። በእርግጥም አሳይቶናል!

አሁን አስጎብኚዎቹ ለመልስ ጉዞ እንድንዘጋጅ ምልክት ሰጡን። “የጭጋጋማው አካባቢ” እንግዶች በመሆን ከእነዚህ አስደናቂና ሰላማዊ ፍጥረታት ጋር ከአንድ ሰዓት በላይ ቆየን። ጉብኝታችን በጣም አጭር ቢሆንም ምን ጊዜም የማይረሳ ነው። በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ አራዊትና የሰው ልጅ ተስማምተው ለዘላለም እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ ለማስታወስ ተገድደናል።—ኢሳይያስ 11:6-9

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የተራራ ጎሪላዎች መኖሪያ የሆነው የተራራ ሰንሰለት

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ

የኪቩ ሐይቅ

ኡጋንዳ

ሩዋንዳ

አፍሪካ

አካባቢው ጎላ ብሎ ሲታይ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ