የይሖዋን ውለታ እንዴት ልንመልስ እንችላለን?
ይሖዋ አምላክ በመስጠት ረገድ ከሁሉ የበለጠ ምሳሌአችን ነው። ለሰው ልጆች ሁሉ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣል።” (ሥራ 17:25) አምላክ ጸሐዩን በክፉዎችና በጻድቃን መካከል ልዩነት ሳያደርግ ለሁሉም ይሰጣል። (ማቴዎስ 5:45) በእርግጥም ይሖዋ “ልባችንን በመብልና በደስታ ለመሙላት ከሰማይ ዝናብን፣ ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሰጥቶናል።” (ሥራ 14:15-17) እንዴታ! “በጎ ሥጦታ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው። መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።”—ያዕቆብ 1:17
ይሖዋ ቁሳዊ ስጦታዎችን ከመስጠቱም በተጨማሪ መንፈሳዊ ብርሃንና እውነትን ይልክልናል። (መዝሙር 43:3) የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች “በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት” በተገቢው ጊዜ በሚቀርብላቸው መንፈሳዊ ምግብ እጅግ ተባርከዋል። (ማቴዎስ 24:45-47) ከአምላክ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ልንጠቀም እንችላለን። ምክንያቱም እሱ ኃጢአተኛና ሟች ሰዎችን ከእሱ ጋር እንዲታረቁ አስችሏቸዋል። እንዴት? ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ በሰጠው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ሮሜ 5:8-12) ይህ ከአፍቃሪው አምላክ ከይሖዋ የተገኘ እንዴት ዓይነት ከፍተኛ ስጦታ ነው!—ዮሐንስ 3:16
ውለታ መክፈል ይቻላልን?
ቤዛው ከመቅረቡ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በመንፈስ የተገፋፋ አንድ መዝሙራዊ “ስላደረገልኝ ሁሉ ለይሖዋ ምንን እመልሳለሁ? የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ። የይሖዋንም ስም እጠራለሁ። በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ” ብሎ ለመናገር እስከመድረስ ከአምላክ የተሰጠውን ምሕረት ማዳንና እርዳት በጥልቅ አድንቆ ነበር።—መዝሙር 116:12-14
ራሳችንን በሙሉ ልባችን ለይሖዋ ከወሰንን ስሙን በእምነት እንጠራለን፤ ለእሱ የተሳልነውን ስዕለታችንንም እንከፍላለን። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ስለ አምላክ በማንኛውም ጊዜ ጥሩ በመናገርና የመንግሥቱን መልእክትም በማወጅ ልንባርከው እንችላለን። (መዝሙር 145:1, 2, 10-13፤ ማቴዎስ 24:14) ይሁን እንጂ የማንኛውም ነገር ባለቤት የሆነውን ይሖዋን እኛ ሰጥተን ልናበለጽገው ወይም ደግሞ ላደረገልን ሁሉ ውለታውን መመለስ አንችልም።—1 ዜና መዋዕል 29:14-17
ለመንግሥቱ ፍላጎቶች መስፋፋት የገንዘብ መዋጮ ማድረግ የይሖዋን ውለታ የመመለሻ ወይም ደግሞ እሱን የማበልጸጊያ መንገድ አይደለም። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ መስጠት ለአምላክ ያለንን ፍቅር እንድንገልጽ አጋጣሚ ይሰጠናል። መዋጮ ከራስ ወዳድነት የመነጨ ወይም ለታይታና ለከንቱ ውዳሴ ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን በለጋስነት መንፈስና እውነተኛ አምልኮን ለማስፋፋት ተብሎ የተሰጠ ከሆነ ለሰጭው ደስታና የይሖዋን በረከት ያመጣለታል። (ማቴዎስ 6:1-4፤ ሥራ 20:35) አንድ ሰው ከቁሳዊ ሀብቱ እውነተኛ አምልኮን ለመደገፍና የሚገባቸውን ለመርዳት ብሎ አዘውትሮ የተወሰነ መጠን የሚመድብ ከሆነ በዚህ ዓይነቱ መስጠትና ከመስጠት ከሚገኘው ደስታ ተካፋይ እንደሚሆን እርግጠኛ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 16:1, 2) ታዲያ ይህ መደረግ ያለበት አሥራት በመስጠት ነው?
አሥራት መስጠት አለብህን?
ይሖዋ በነቢዩ በሚልክያስ በኩል እንዲህ ብሏል፦ “በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራዬ አግቡ። የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ” (ሚልክያስ 3:10) በሌላ ትርጉም “አንድ አሥረኛውን ወደ ጎተራ አግቡ” በማለት ይነበባል።
አሥራት የአንድ ነገር አንድ አሥረኛ ወይም ከአሥር እጅ አንዱ እጅ ማለት ነው። በስጦታ ወይም ግብር እንዲሆን የሚከፈል አሥር በመቶ ነው። አሥራት የሚደረገው በተለይ ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ወይም ዓላማ ነው። አንድ ሰው አምልኮን ለማስፋፋት ብሎ ከገቢው አንድ አሥረኛውን ይሰጣል ማለት ነው።
የቀድሞ አባት የነበረው አብርሃም የሳሌም ንጉሥና ካህን ለነበረው ለመልከጼዴቅ ኮሎዶጎምርንና የሱን ተባባሪዎች ድል አድርጎ ሲመለስ ከምርኮው አንድ አሥረኛውን ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 14:18-20፤ ዕብራውያን 7:4-10) በኋላም ያዕቆብ ከሀብቱ ሁሉ ለአምላክ አሥራት እንደሚሰጥ ተስሏል። (ዘፍጥረት 28:20-22) በሁለቱም ረገድ አንድ አሥረኛውን የሰጡት በፈቃደኛነት ነበር። ምክንያቱም እነዚያ የቀድሞ ዕብራውያን አሥራት እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው ሕግ አልነበረም።
አሥራት በሕጉ ሥር
እሥራኤላውያን የይሖዋ ሕዝብ እንደ መሆናቸው የአሥራት ሕጎችን ተቀብለዋል። በግልጽ እንደሚታየው እነዚህ ሕጎች የዓመታዊውን ገቢ ሁለት አሥረኛ ወይም ሁለት አሥራቶችን የያዙ ነበሩ። አንዳንድ ምሁራን ግን አንድ ዓመታዊ አሥራት ብቻ ነበር ብለው ያስባሉ። በሰንበት ዓመት ማለትም በሰባተኛው ዓመት ብቻ ምንም የሚገኝ ገቢ ስላልነበረ አሥራት አይከፈልም ነበር። (ዘሌዋውያን 25:1-12) አሥራቶች ለአምላክ ከሚቀርቡት የበኩራት ፍሬ ሌላ በተጨማሪ የሚሰጡ ነበሩ።— ዘጸአት 23:19
የምድሪቱና የፍሬ ዛፍ ውጤቶች፣ በእርባታ የተገኙት ከብቶችና መንጎች አንድ አሥረኛ ወደ ቤተ መቅደስ ተወስዶ በምድሪቱ ውርሻ ላልተቀበሉት ለሌዋውያን ይሰጥ ነበር። ሌዋውያንም እንደገና ካገኙት ውስጥ አንድ አሥረኛውን ለአሮናዊው ክህነት ይሰጡ ነበር። በግልጽ እንደሚታየው አሥራቱ ከመሰጠቱ በፊት እህሉ መወቃት፣ ወይኑና ወይራውም ወደ ወይን ጠጅነትና ወደ ዘይት መለወጥ ነበረበት። አንድ እሥራኤላዊ ከምርቱ ይልቅ ገንዘብ መስጠት ከፈለገ የዋጋውን አንድ አምስተኛ ከጨመረ ገንዘብ ሊሰጥ ይችል ነበር። —ዘሌዋውያን 27:30-33፤ ዘኁልቁ 18:21-30
ሌላ ዓይነት አሥራትም ይመደብ የነበረ ይመስላል። ይህ አሥራት እንደተለመደው ሕዝቡ ለዓመታዊ በዓላቱ በሚሰበሰብበት ጊዜ ቤተሰቡ የሚጠቀምበት አሥራት ነበር። ነገር ግን ኢየሩሳሌም በጣም ሩቅ ቢሆንና ይህን አሥራት ለማጓጓዝ አመቺ ባይሆንስ? እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ እህሉ፣ አዲሱ ወይን፣ ዘይትና እንስሳት በቀላሉ መያዝ ወደሚቻለው ገንዘብ ይለውጡ ነበር። (ዘዳግም 12:4-18፤ 14:22-27) በየሰባቱ የሰንበት ዓመት ኡደት ውስጥ በሦስተኛውና በስድስተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ አሥራቱ ለሌዋውያን፣ ለመጻተኞች ለመበለቶችና አባት ለሞተባቸው ልጆች ይከፋፈል ነበር።—ዘዳግም 14:28, 29፤ 26:12
በሕጉ ሥር አሥራት ሳይሰጥ ለሚቀር ሰው የተወሰነ ቅጣት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ሕዝቡን አሥራት ለመስጠት የሚገፋፋ ጠንካራ የስነ ምግባር ግዴታ ጥሎባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ አሥራቱን ሙሉ በሙሉ የተከፈለ መሆኑን በይሖዋ ፊት መናገር ነበረባቸው። (ዘዳግም 26:13-15) በንፉግነት ሳይሰጥ የቀረ ማንኛውም ነገር ከአምላክ እንደተሰረቀ ያህል ይቆጠር ነበር። ሚልክያስ 3:7-9
የአሥራት ዝግጅት ከባድ ሸክም አይሆንባቸውም ነበር። እንዲያውም እሥራኤላውያን እንዲህ ዓይነቶቹን ሕጎች ሲጠብቁ ይበልጥ ይበለጽጉ ነበር። አሥራት እውነተኛ አምልኮን ለማስፋፋት የሚረዳ ነበር። ይሁን እንጂ የተንዛዛ ቁሳዊ ዝግጅት ለማድረግ ተብሎ አላስፈላጊ ጭነት የሚፈጥር አልነበረም። ስለዚህ የአሥራት ዝግጅት ለእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ጠቃሚ ነበር። ይሁንና ክርስቲያኖች አሥራት መስጠት ይገባቸዋልን?
ክርስቲያኖች አሥራት መስጠት አለባቸውን?
ለተወሰነ ጊዜ አሥራት ማውጣት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተለመደ ነገር ሆኖ ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና እንዲህ በማለት አትቷል፦ “አሥራት . . . እስከ 6ኛው መቶ ዘመን ድረስ ቀስ በቀስ የተለመደ ሆኖ ነበር። በ567 የተደረገው የቱረስ ጉባኤና በ585 የተደረገው የማኮን ጉባኤ አሥራትን ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ ወስኗል። በተለይ አሥራት የመሰብሰቡ ሥልጣን ለተራ ሰዎች ሲሰጥ ወይም ሲሸጥ በአሥራቱ ያለ አግባብ መጠቀም የተለ ሆኖ ነበር። ከጳጳስ ግሪጎሪ ሰባተኛ ጀምሮ ይህ ልማድ ሕገወጥ መሆኑ ተነገረ። በዚያን ጊዜ ብዙ ተራ ሰዎች አሥራት የመቀበል መብታቸውን ለገዳማትና ለካቴድራል ቅርንጫፎች አስረከቡ። የተሐድሶ ዘመንም ቢሆን አሥራትን አላስቀረም። ስለዚህ ልማዱ በሮማ ካቶሊክና በፕሮቴስታንት አገሮችም ቀጥሎ ነበር።” አሥራት በልዩ ልዩ አገሮች ቀስ በቀስ ቀርቷል። በዛሬ ጊዜ የሚሠሩበት ጥቂት ሃይማኖቶች ብቻ ናቸው።
ታዲያ ክርስቲያኖች አሥራት መክፈል አለባቸውን? አሌክሳንደር ክሩደን በመጽሐፍ ቅዱስ የቃላት ዝርዝራቸው ውስጥ “አዳኛችንም ሆነ የሱ ሐዋርያት በዚህ የአሥራት ጉዳይ ላይ ምንም ትዕዛዝ አልሰጡም” በማለት ተናግረዋል። በእርግጥም ክርስቲያኖች አሥራት እንዲከፍሉ አልታዘዙም። አምላክ ራሱ የሙሴን ሕግ ከአሥራት ዝግጅት ጋር በኢየሱስ የመከራ እንጨት ላይ ጠርቆ አስወግዶታል። (ሮሜ 6:14፤ ቆላስይስ 2:13, 14) ክርስቲያኖች የጉባኤ ወጪዎችን ለመሸፈን የተወሰነ መጠን እንዲሰጡ ከመጠየቅ ፋንታ የፈቃደኛነት መዋጮ ያደርጋሉ።
ይሖዋን በሀብትህ አክብር
በእርግጥ አንድ ክርስቲያን እውነተኛ አምልኮን ለማራመድ ከገቢው አንድ አሥረኛውን በፈቃደኝነት ለመስጠት ከመረጠ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ላለመቀበል ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የለም። በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚኖር አንድ የ15 ዓመት ልጅ ከላከው የእርዳታ ገንዘብ ጋር አባሪ አድርጎ በላከው ደብዳቤ ላይ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ትንሽ ልጅ እያለሁ አባቴ ‘ሥራ ስትጀምር የሥራህን የበኩራት ፍሬ ለይሖዋ መስጠት አለብህ’ ይለኝ ነበር። ይሖዋን ለማክበር የፍሬያችንን ሁሉ በኩራት ለይሖዋ መስጠት እንዳለብን የሚናገሩትን በምሳሌ 3:1, 9 ላይ ያሉትን ቃላት አስታውሳለሁ። ስለዚህ ይህን ለማድረግ ቃል ስለገባሁ እነሆ አሁን ቃሌን መፈጸም አለብኝ። ይህን ገንዘብ የመንግሥቱን ሥራ ለማገዝ ስልክ ደስ እያለኝ ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲህ ዓይነት ቃል እንዲገቡ ጥሪ አያቀርብም። ይሁን እንጂ የለጋስነት ስጦታ እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ ያለንን ልባዊ ፍላጎት ከምናሳይበት መልካም መንገድ አንዱ ነው።
አንድ ክርስቲያን የይሖዋ አምላክን አምልኮ ለማራመድ ብሎ ለሚሰጠው የገንዘብ እርዳታ የተወሰነ ገደብ ለማድረግ አይመርጥ ይሆናል። ለማስረዳት ያህል በይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ እያሉ ሁለት በዕድሜ የገፉ እህቶች ለመንግሥቱ ሥራ ሊያደርጉት ስለሚችሉት እርዳታ ይወያዩ ነበር። የ87 ዓመት አሮጊት የሆነችው እህት በስብሰባው ቦታ የሚቀርበው ምግብ የሚያወጣውን ዋጋ ያህል በዕርዳታ ለመላክ ፈለገችና የምግቡ ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ጠየቀች። የ90 ዓመት አሮጊት የሆነችው ሌላዋ እህት “ምግቡ ያወጣል ብለሽ ከምታስቢው ገንዘብ ላይ ትንሽ ጨመር አድርገሽ ስጭ” አለቻት። ይህች አረጋዊት እህት ያሳየችው እንዴት ዓይነት ግሩም መንፈስ ነበር!
የይሖዋ ሕዝቦች ሁለመናቸውን ለሱ ስለወሰኑ እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ የገንዘብ እርዳታና ሌላ መዋጮዎችንም የሚያደርጉት በደስታ ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:12 ጋር አወዳድር) እንዲያውም ክርስቲያናዊው አሰጣጥ ለይሖዋ አምልኮ ያለንን ጥልቅ አድናቆት ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጣል። እንዲህ ዓይነቱ መስጠት በአንድ አሥረኛ ወይም አሥራት ብቻ የተወሰነ አይደለም። አንድ ግለሰብ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማራመድ የበለጠ ለመስጠት የሚገፋፋባቸው ሁኔታዎች አሉ።-ማቴዎስ 6:33
ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ። በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ብሎአል። (2 ቆሮንቶስ 9:7)እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ በደስታና በልግስና ከሰጠህ የምትሠራው ሁሉ ያሳካልሃል። የጥበበኛው ምሳሌ “ይሖዋን ከሀብትህ አክብር ከፍሬህም ሁሉ በኩራት። ጎተራህም እህልን ይሞላል። መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች” ይላል።—ምሳሌ 3:9, 10
ልዑሉን አምላክ እና ልናበለጽገው አንችልም። ወርቁና ብሩ በሺ ተራራዎች ያሉ እንስሳትና ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ክቡር ነገሮች ሁሉ የሱ የራሱ ናቸው። (መዝሙር 50:10-12) አምላክ ላደረገልን ሁሉ ውለታውን ልንከፍል አንችልም። ነገር ግን ለሱና እሱን የሚያስመሰግን ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ ለተሰጠን መብት ያለንን ጥልቅ አድናቆት ልናሳይ እንችላለን። እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድና አፍቃሪና ለጋስ የሆነው ይሖዋ አምላክን ለማስከበር ሲሉ በልግስና ለሚሰጡ ሁሉ ብዙ በረከቶች እንደሚፈሱላቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 9:11
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለመንግሥቱ ሥራ እንዴት እንዳዋጡ
◻ ለዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ፦- ብዙ ወንድሞችና እህቶች “ለማህበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” የሚል ጽሑፍ በተለጠፈበት ሳጥን ውስጥ የተወሰነ መጠን መድበው ያስቀምጣሉ። ጉባኤዎችም እነዚህን መዋጮዎች በየወሩ በብሩክሊን ኒውዮርክ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።
◻ ስጦታዎች፦ በፈቃደኝነት የተሰጠ የገንዘብ ዕርዳታ ለፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና የትናንሽ ጽሑፎች ማህበር በሚከተለው አድራሻ መላክ ይቻላል። To the watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201 ወይም በአካባቢው ላለ የማህበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ሊላክ ይችላል። ጌጣጌጥና ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ዕቃ ሲላክም ስጦታ መሆኑን ከሚገልጽ ደብዳቤ ጋር መሸኘት አለበት።
◻ በውለታ የሚሰጥ ዕርዳታ ዝግጅት፦ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ገንዘብ በአደራ እንዲያስቀምጥ ሊሰጥ ይችላል። ይህም ገንዘብ የሚቀመጠው ሰጪው እስኪሞት ሲሆን ሰጪው ለራሱ ከፈለገው ደግሞ ሊወስደው ይችላል።
◻ኢንሹራንስ፦ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር የሕይወት ኢንሹራንስ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን መናዘዝ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ሲደረግ ማህበሩን ማሳወቅ ያስፈልጋል።
◻ የባንክ ሂሳብ፦ የባንክ ደብተር ወይም የጡረታ ሂሳብ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እጅ እንዲቀመጥና ባለመብቱ በሚሞትበት ጊዜ ለማህበሩ እንዲከፈል ማድረግ ይቻላል። ይህ ዓይነቱ ዝግጅት ከአገሩ የባንክ አሠራር ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሲኖር ለማህበሩ ማሳወቅ ያስፈልጋል።
◻ አክሲዮንና የግምጃ ቤት ሰነድ፦ አክሲዮኖችንና የግምጃ ቤት ሰነዶችን ሙሉ በሙሉ ለማኅበሩ መስጠት ወይም ከአክሲዮኑ የሚገኘው ጥቅም ለባለንብረቱ ተከፋይ ሆኖ ንብረትነቱን ግን ለማህበሩ ማስተላለፍ ይቻላል።
◻ መሬትና ሕንፃ፦ ሊሸጡ የሚችሉት መሬቶችና ቤቶችን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በቀጥታ መስጠት ወይም ባለንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ኖሮበት ሲሞት ግን የማኅበሩ ንብረት እንዲሆን መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም ንብረት ለማህበሩ ከማስተላለፉ በፊት ከማህበሩ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።
◻ ኑዛዜ ወይም ባለአደራነት፦ ማንኛውም ንብረት ወይም ገንዘብ ለመጠበቂያ ግንብ ማህበር ሕጋዊ በሆነ የኑዛዜ ቃል አማካኝነት ሊተላለፍ ይችላል። ማህበሩ የባለአደራነት ተጠቃሚ እንዲሆንም ውል መግባት ይቻላል። አንድን ሃይማኖታዊ ድርጅት የሚጠቅም የባለአደራነት ውል የግብር ቅናሽ የሚያስገኝበት ጊዜ አለ። የኑዛዜ ወይም የባለአደራነቱ ውል ቅጂ ለማህበሩ መላክ ይኖርበታል።
ስለእነዚህ ጉዳዮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት The Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201 ወይም በአካባቢው ላለ የማህበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፍ ትችላላችሁ።