የገና በዓል በጃፓን አገር በጣም ተወዳጅ የሆነው ለምንድን ነው?
የቡዲስትና የሺንቶ አገር በሆነችው በጃፓን በገና አባት ማመን በልጆች ልብ ውስጥ ጠልቆ ገብቷል። በ1989 ጃፓናውያን ልጆች በስዊድን ላለችው ቅድስት ዓለም 160,000 ደብዳቤዎችን ጽፈዋል። ከዚህ የሚበልጥ ብዙ ደብዳቤ የላከ ሌላ አገር የለም። ልጆቹ ለማግኘት የፈለጉት 18,000 የን (የጃፓን ገንዘብ) ወይም $136 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የግራፊክ ኮምፒዩተር 12,500 የን ($95 የአሜሪካ ዶላር) የሚያወጣ የእጅ ቪዲዮ መጫወቻ የልባቸውን ምኞት ለማርካት በማሰብ ደብዳቤ ጽፈዋል።
ለወጣት ጃፓናውያን ልጃገረዶች በገና ዋዜማ ዕለት ከወንዶች ልጆች ጋር መቀጣጠር ልዩ ትርጉም አለው። “በወጣት ሴቶች ላይ በተደረገው ጥናት መሠረት” ይላል ሜይኒቺ ዴይሊ ኒውስ “38 በመቶዎቹ ገና ከአንድ ወር ቀደም ብለው ለገና ዋዜማ ዝግጅት አድርገው እንደነበረ ተናግረዋል።” ወጣት ወንዶች በገና ዋዜማ ዕለት ከሴት ጓደኞቻቸው ጋር መሆን የሚፈልጉበት ስውር ምክንያት አላቸው። አንድ መጽሔት ለወጣት ወንዶች “ከሴት ጓደኞቻቸው ጋር በጸጥታ መጸለይ ጥሩ ሐሳብ ነው” በማለት ይመክራል። “ውብ በሆነ ስፍራ አብራችሁ በጸጥታ ጸልዩ። በጣም የተቀራረበ ዝምድና ይኖራችኋል።”
ጃፓናውያን ባሎችም ከሥራ ወደ ቤት ሲመለሱ “ያጌጠ ኬክ” በመግዛት በገና ባሕላቸው አማካኝነት አንድ ዓይነት አስማታዊ ኃይል ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። የሳንታ ክላውስን ሚና መጫወት በቀሪው ዓመት ሙሉ በቤተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ችላ ማለት ያካክሳል ተብሎ ይታሰባል።
በእርግጥም የገና በዓል ክርስቲያን ባልሆኑት ጃፓናውያን ዘንድ ስር ሰድዷል። አንድ ትልቅ የገበያ አዳራሾች ዝግጅት ጥናት ካደረገባቸው ሰዎች 78 በመቶ የሚያክሉት በገና ዕለት የተለየ ነገር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል አንድ በመቶ ብቻ የሚሆነው ክርስቲያን እንደሆነ በሚነገርበት አገር ይህን ያህል ብዛት ያለው ሕዝብ ለገና ከፍተኛ ስሜት ማሳደሩ የሚገርም ነው። ቡዲስቶች ወይም ሺንቶይስቶች እንደሆኑ ቢናገሩም ‘ክርስቲያናዊ’ በሆነው በዓል መደሰት አይከብዳቸውም። የሺንቶ አይሲ ቅዱስ ስፍራ በዕለታዊ ሁኔታ መመዝገቢያ መጽሐፍ ላይ ታህሣሥ 25ን “የክርስቶስ ልደት” በማለት ከሌሎች የጃፓን በዓሎች ጋር መዝግቦታል። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች በገና በዓል ጊዜ በተለያዩ ፈንጠዝያዎች መዋጣቸው የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሣል።
ገና የማን በዓል ነው?
የዌብስተር ናይንዝ ኒው ኮልጂያት ዲክሽነሪ ገናን “የክርስቶስ ልደት የሚከበርበት . . . ታህሣሥ 25 ላይ የሚውል የክርስቲያን በዓል” በማለት ይተረጉመዋል። “ክርስቲያኖች በክርስቶስ የልደት ቀን በደስታ ስሜት አንድ የሚሆኑበት” ጊዜ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።
ገናን በሃይማኖታዊ በዓልነቱ ብቻ የሚያከብሩ ሰዎች ዕለቱን በፈንጠዝያና ስጦታ በመለዋወጥ ዓለማዊ መልክ በሚያሰጡት ሰዎች በጣም ይናደዳሉ። የክርስቶስን ስም እንደማጉደፍም ይቆጥሩታል። አንድ በጃፓን የሚኖር አሜሪካዊ ሲጽፍ “በጃፓን አገር የሚፈጸመው በጣም ከፍተኛ የሆነ የንግድ ብልግና ነው። ክርስቶስ ፈጽሞ የለበትም” ብሏል። ሌላው ጸሐፊ ደግሞ ስለ ጃፓናውያን ገና “አንድ ምዕራባዊ ተመልካች ሊያገኝ የማይችለው (በጃፓን ገበያ በብዛት ሊገኝ የማይችለውን) የቱርክ ዶሮ ሳይሆን ዋናው አስፈላጊ ነገር የሆነውን መንፈሱን ነው” ብሏል።
ታዲያ የገና መንፈስ ምንድን ነው? ብዙ ሰዎችን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሄዱ የሚያደርጓቸው የልደት መዝሙሮች፣ ለገና ማስጌጫ የሚያገለግለው እሾህማ ዛፍና ሻማዎች ያሉበት ሁኔታ ነውን? ወይስ ደግሞ ብዙዎችን ለጋሶች እንዲሆኑ የሚገፋፋቸው ፍቅር፣ እልልታ፣ ጭብጨባና የስጦታ መለዋወጥ ነውን? ወታደሮች ለጥቂት ቀናት “ሰላም በምድር ይሁን” በማለት ውጊያ በሚያቆሙባቸው ጥቂት ቀናት በጦር ሜዳዎች የሚሰፍነው መረጋጋት ነውን?
የሚገርመው ነገር የገና መንፈስ በቤት ውስጥ እንኳ ሰላም ሳያመጣ የሚቀርበት ጊዜ መኖሩ ነው። በ1987 በእንግሊዝ አገር በተደረገው ጥናት መሠረት 70 በመቶ በሚያክሉ የእንግሊዛውያን ቤቶች ውስጥ በገና ወቅት ‘የእርስ በርስ’ ጦርነት እንደሚነሣ ተገምቷል። ዋናው የጠብ ምክንያት የገንዘብ ጭቅጭቅ ነው። ያለልክ መጠጣትና የቤተሰብ ግዴታን ያለመፈጸምም ብዙውን ጊዜ ወደመጣላት ይመራሉ።
አንድ በጃፓን የሚኖሩና በቅርቡ በገና ወራት ወደ ቤታቸው ለጥየቃ መጥተው የነበሩ ምዕራባዊ “ስለ ገና እውነተኛ ትርጉም አንድ ነገር ስተን ሳይህን አይቀርም ብዬ አስባለሁ። በየታህሣሥ 25ቱ ያን የድሮ የገና አከባበር ማለትም የክረምቱን ማለፍ ዛፎችን በማምለክና የፈንጠዝያ ፓርቲ በማድረግ ያከብሩት በነበረው ዓይነት የአረማዊ ሥርዓት ማክበርን በጣም እናፍቃለሁ። እስካሁንም አረማዊ አጋጌጦች አሉን። አረማውያን ያጌጡባቸው የነበሩትን የጥድ፣ የእሾህ፣ የተቀጽላና ወዘተ ቅጠሎች አሁንም እንጠቀምባቸዋለን። ይሁን እንጂ ገና በክርስቲያኖች ተቀምቶ ሃይማኖታዊ በዓል ከሆነ ወዲህ ብዙ ዓይነት ለውጥ ታይቶበታል” በማለት ጽፈዋል።
ገና የአረማውያን በዓል መሆኑ የማይካድ ነገር ነው። የቀድሞ ክርስቲያኖች ገናን አያከብሩም ነበር። “ምክንያቱም የማንኛውንም ሰው የልደት በዓል ማክበርን አረማዊ ልማድ አድርገው ይመለከቱት ስለነበረ ነው” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ ይናገራል። ፈንጠዝያውና የስጦታ መለዋወጡ ልማድ የመጣው ከአረማዊው የሳተርንና የአዲስ ዓመት በዓል አከባበር ነው።
ታዲያ ገና በመሠረቱ አረማዊ በዓል ከሆነ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄ ክርስቲያኖች ገናን ሊያከብሩት ይገባልን? የሚለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስን ልደት ስለማክበር የሚናገረውን እንመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የገና በዓል አመጣጥ
ምንም እንኳ ዝርዝር መረጃዎች በዘመናት ጭጋግ ውስጥ ቢሰወሩም በ336 እዘአ አንድ ዓይነት የገና በዓል አከባበር በሮማ ቤተ ክርስቲያን ተጀምሮ እንደነበረ የሚያመለክት ፍንጭ አለ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ሲያብራራ “የገና ዕለት ታህሣሥ 25 እንዲሆን የተወሰነው ሆን ተብሎ ታላቁን የፀሐይን በዓል ወደጐን ገሸሽ ለማድረግ ነው” ይላል። ይህ በዓል ይከበር የነበረው አረማውያን በሮማውያን የሳተርን በዓልና በሴልቲክና በጀርመን የክረምት በዓል ድግስ ላይ ልቅ የሆነ ፈንጠዝያ ይፈጽሙበት በነበረው ጊዜ ነበር። ዘ ኒው ካክስተን ኢንሳይክሎፒድያ “ቤተ ክርስቲያን አጋጣሚውን እነዚህን በዓሎች ክርስቲያናዊ በዓሎች ለማድረግ ተጠቀመችበት” ይላል።