ዓለም በፍርሃት ተውጧል
የካቲት 26, 1993 አንድ በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ያስከተለው ከፍተኛ ፍንዳታ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን 110 ፎቅ ያለውን የዓለም የንግድ ማዕከል አናወጠው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች በድንገት ቀጥ ባሉ አሳንሱሮች ውስጥ ተቀርቅረው ቀሩ፤ ወይም ደግሞ በጭስ በተሞሉት ደረጃዎች ላይ ወደ ታች በመሮጥ ማምለጥ ነበረባቸው። በጭካኔ ድርጊቶች በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ በእጅጉ የተዛመተው ፍርሃት እነርሱንም አርበድብዷቸው ነበር።
በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በቦምብ ፍንዳታዎች ተሸብረዋል። እነዚህ ፍንዳታዎች እንደ አየርላንድና ሊባኖስ ባሉ አገሮች ውስጥ የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። እንዲያውም በህንድ ቦምቤ ከተማ ውስጥ መጋቢት 12, 1993 በአንድ ቀን 13 የቦምብ ፍንዳታዎች ደርሰው ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል! አንድ ታዛቢ “በመላዋ ቦምቤ ውስጥ ከፍተኛ ሽብር አለ” ብለዋል። ኒውስዊክ የተባለው መጽሔት እንዳለው በመኪና ላይ ቦምብ ማጥመድ “የተለመደ ክስተት መሆኑ ከበፊቱ የባሰ ፍርሃት አሳድሯል።”
የኑክሌር ስጋት አሁንም እንዳለ ነው
የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የቦምብ ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። በአንድ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ስኬታማ የሆነ ጥቃት ቢፈጸም የሚያስከትለው ውድመትና መከራ ሊሰላ የሚችል አይደለም። አንድ ሰው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስሪ ማይል አይላንድ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ በሚገኘው አንድ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መግቢያ ላይ ካለው ጥበቃ የሚካሄድበት በር ጋር መኪናውን በማጋጨት አደጋ ለመፍጠር መሞከሩ ስጋቱን አጠናክሮታል።
ሽብር ፈጣሪዎችና የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ መሪዎች የኑክሌር መሣሪያዎችን በእጃቸው ያስገባሉ ብለው ብዙዎች ይሰጋሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ የሶቭየት ሥራ አጥ የኑክሌር ሳይንቲስቶች ሙያቸውን ለመሸጥ ይሞክራሉ የሚል ስጋት በአንዳንዶች ዘንድ አለ። በሌላ በኩል ግን በመጀመሪያዎቹ የኑክሌር አምራች አገሮች የተፈረመው ስታርት የተባለው ውል ስትራቴጂካዊ የኑክሌር መሣሪያዎች በሙሉ እንዲወድሙ ያዛል። ይህ ውጥን እስከ 1999 መገባደጃ ድረስም ሆነ ከዚያም በኋላ የሚሳካ አይደለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ጊዜ የዚህ መሣሪያ ባለቤት የሆኑ አንዳንድ ግትር አቋም ያላቸው አገሮች መሣሪያውን ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ በሰው ዘር ላይ አስፈሪ ጥቁር ደመና ማንዣበቡ አይቀርም።
ዓመፅ ፍርሃትን ያስፋፋል
የዓመፅ ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እየጨመረ መምጣቱ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እያሉም ሆነ በጎዳናዎች ላይ ሲጓዙ ፍርሃት ፍርሃት እንዲላቸው አድርጓል። በ1990 23,200 አሜሪካውያን በዓመፅ እንደተገደሉ ተገምቷል። ለምሳሌ ያህል በቺካጎ ከተማ ውስጥ በኮኬይን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ በአንድ ዓመት ውስጥ ለተፈጸሙት ወደ 700 የሚጠጉ የግፍ ግድያዎች የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ቦታዎች ልጆችን ጨምሮ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች በተኩስ ልውውጥ የሚገደሉባቸው የውጊያ አውድማዎች ሆነዋል። አንድ መጽሔት እንዲህ ይላል፦ “መጠነኛ ስፋት ባላቸው ከተሞች ውስጥ ዓመፅ በፍጥነት እየጨመረ ነው። . . . በ[ዩናይትድ ስቴትስ] የሚገኙ ማኅበረሰቦች በዕፆችና በወጣት ወሮበሎች በመጥለቅለቃቸው ከዚህ ማምለጥ የሚችል አንድም ሰው የለም። በየዓመቱ ከ4 የአሜሪካ ቤተሰቦች መካከል አንዱ ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ወይም ሌብነት ይፈጸምበታል።”—ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት፣ ጥቅምት 7, 1991
አስገድዶ የመድፈር ድርጊት የፈጠረው ስጋት ሴቶችን ፍርሃት ለቆባቸዋል። በፈረንሳይ ከ1985 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ውስጥ ሪፖርት የተደረገው ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር ድርጊት ቁጥር 62 በመቶ አድጓል። በካናዳ የጾታ ብልግና ወንጀሎች በስድስት ዓመት ውስጥ በእጥፍ በመጨመር 27,000 ደርሰዋል። በጀርመን ውስጥ በየሰባት ደቂቃ በሴት ላይ አንድ የጾታ ብልግና ወንጀል እንደሚፈጸም ሪፖርት ተደርጓል።
ልጆችም ስለራሳቸው ደህንነት ይሰጋሉ። ኒውስዊክ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “በአራተኛና በአምስተኛ ክፍል ደረጃ የሚገኙ ልጆች እንኳ መሣሪያ እየታጠቁ ነው፤ አስተማሪዎችና የትምህርት ቤት ባለ ሥልጣኖችም በፍርሃት እየተዋጡ ነው” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ሁኔታው እጅግ አስጊ በመሆኑ በከተሞች ውስጥ ከሚገኙት ትላልቅ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሩብ የሚሆኑት ብረት ነክ የሆነ ነገር ሲነካው ድምጽ የሚሰጥ መሣሪያ መጠቀም ጀምረዋል። ይሁን እንጂ የወጠኑትን ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ ወጣቶች እነዚህ መሣሪያዎች ቢኖሩም ሽጉጡን በመስኮት በኩል ለሌሎች በማቀበል ወደ ግቢው ማስገባት የሚችሉበት መንገድ ቀይሰዋል።
ኤድስ የፈጠረው ፍርሃት
ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች ኤድስ ይይዘናል የሚል ፍርሃት አድሮባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ230,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በኤድስ ቫይረስ ተለክፈዋል። ከ15 ዓመት እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት የመሪነት ደረጃ የያዙ ነገሮች መካከል ኤድስ የስድስተኛነትን ደረጃ ይዟል። ኒውስዊክ “የወደፊቱ ጊዜ በሽታ እጅግ በላቀ መልኩ ይስፋፋል የሚል አስፈሪ ገጽታ ይዟል” ይላል።
በዳንስ፣ በቲያትር፣ በፊልሞች፣ በሙዚቃ፣ በፋሽን፣ በቴሌቪዥን፣ በኪነ ጥበብና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች በተሰማሩ ሰዎች መካከል በኤድስ ሳቢያ የሚከሰተው ሞት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ የተለመደ ነገር ሆኗል። በጋዜጠኝነትና በኪነ ጥበብ መስኮች ከተሰማሩት እንዲሁም የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ከሚያዘጋጁት ከ25 እስከ 44 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት በፓሪስ የሚኖሩ ወንዶች መካከል 60 በመቶዎቹ የሚሞቱት በኤድስ ምክንያት ነው። የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም ዙሪያ ከስምንት ሚልዮን እስከ አሥር ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች በኤች አይ ቪ እንደተለከፉ ሪፖርት አድርጓል። የዓለም የጤና ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ሚካኤል መርሰን “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በተለይም በመልማት ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል” ብለዋል።
እርግጥ ነው፤ የአካባቢ መበከልና ሌሎች ነገሮች የፈጠሩት ስጋትም አለ። ሆኖም ከላይ የቀረቡት ሪፖርቶች ብቻ እንኳ ዓለም በፍርሃት እንደተዋጠ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነውን? ከፍርሃት ተላቀን በደስታ መኖር የምንችልበትን ጊዜ መጠባበቅ እንችል ይሆን?
[ምንጭ]
Cover photos: Left: Tom Haley/Sipa Press; Bottom: Malanca/Sipa Press
[ምንጭ]
Bob Strong/Sipa Press