ታስታውሳለህን?
በቅርብ ጊዜያት የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በጥሞና አሰላስለህባቸዋልን? እንግዲያው ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች ብታስታውስ ደስ ይልህ ይሆናል፦
▫ በሰውና በእንስሳት መካከል ያለው ዋናው ልዩነት ምንድን ነው?
ዋናው ልዩነታቸው በሰው አንጎል አሠራር፣ ችሎታና ተግባራት ላይ የሚያተኩር ነው። እንስሳት አንጎላቸው የሚሠራው አስቀድሞ በተወሰነለት ፕሮግራም ወይም አስቀድሞ በተቀረጸ ጥበብ ወይም በደመ ነፍስ ነው። የሰው ልጆች ሁኔታ ግን እንዲህ አይደለም። አምላክ ለሰው ልጆች የነፃ ምርጫ ስጦታ ሰጥቷቸዋል። (ምሳሌ 30:24–28)—4/15፣ ገጽ 5
▫ እሥራኤላውያን በቤተ መቅደስ ውስጥ ያካሄዱት ለነበረው አምልኮ መዝሙር ምን ሚና ነበረው?
ለሙዚቃ፣ በተለይም ለመዘምራን በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶ ነበር። ይህም የተደረገበት ምክንያት የሕጉን ከበድ ያሉ ጉዳዮች ለማስገንዘብ ብቻ ሳይሆን የአምልኮቱን ሥርዓት በትክክለኛ መንፈስ እንዲካሄድ ለማድረግም ጭምር ታስቦ ነው። መዝሙር እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያቀርቡትን የአምልኮ ሥርዓት በጋለ መንፈስ እንዲፈጽሙ ረድቷቸዋል። (1 ዜና መዋዕል 23:4, 5፤ 25:7)—5/1፣ ገጽ 10, 11
▫ ልጆች ከሕፃንነታቸው አንሥቶ ምን ዓይነት ትኩረት ያሻቸዋል?
ወላጆች አዲስ ለተወለደ ልጃቸው የማያቋርጥ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። ጳውሎስ “ከሕፃንነትህም ጀምረህ . . . መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል” ብሎ ጽፎ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ስለዚህ ወላጆቹ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ለጢሞቴዎስ በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድም ትኩረት ይሰጡት ነበር።—5/15፣ ገጽ 11
▫ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች ሁሉ ለማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት የያዘ መሆኑን የሚያረጋግጡ አራት ማስረጃዎች ምን ምን ናቸው?
(1) በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ። 98 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን አግኝቶ ሊያነበው ይችላል። (2) ታሪካዊነቱ። መጽሐፍ ቅዱስ በማስረጃ ሊረጋገጡ የማይችሉ አፈ ታሪኮች ጥርቅም ሳይሆን እውነተኛ ታሪኮችን የያዘ መጽሐፍ ነው። (3) ተግባራዊነቱ። ትዕዛዞቹና መሠረታዊ ሥርዓቶቹ አጥብቀው ለሚከተሏቸው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ጥቅም ያመጡላቸዋል። (4) ትንቢታዊነቱ። ወደፊት የሚሆነውን ነገር አንድ በአንድ በመዘርዘር የሚናገር መጽሐፍ ነው።—6/1፣ ገጽ 8, 9
▫ እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ ምን ኃላፊነት ያስከትላል?
ትክክለኛውን ሃይማኖት ካገኘን በኋላ አኗኗራችንን በእርሱ መሠረት መቅረጽ አለብን። እውነተኛው ሃይማኖት የሕይወት መንገድ ነው። (መዝሙር 119:105፤ ኢሳይያስ 2:3)—6/1፣ ገጽ 13
▫ መጽሐፍ ቅዱስን በግል ማጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የቃሉን እውነት አዳዲስ ወይም ጥልቀት ያላቸውን ገጽታዎች በማስተዋል ደስታቸውና ኃይላቸውን ዕለት ተዕለት ማደስ ይኖርባቸዋል። እንዲህ በማድረግ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው ለመቀጠል ይችላሉ።—6/15፣ ገጽ 8
▫ “ኃጢአት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ትርጉሙ ምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአት” የሚለውን ቃል ለማመልከት የገቡት የዕብራይስጥም ሆነ የግሪክኛ ግሦች “መሳት” የሚል ፍቺ ያላቸው ሲሆን ይህ ቃል አንድን ግብ ወይም አንድን ዒላማ ወይም ያነጣጠሩበትን ነገር አለመምታት የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አምላክ ክብር የጎደላቸው ሆኑ፤ በአምላክ መልክ የተፈጠሩበትንም ዓላማ ሳቱ። በሌላ አነጋገር ኃጢአት ሠሩ። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6)—6/15፣ ገጽ 12
▫ ከሐዲዎች የሚያዘጋጁአቸውን ጽሑፎች ማንበብ ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
አንዳንድ የከሐዲያን ጽሑፎች የሐሰት ትምህርቶችን “በመልካም . . . ንግግር” እና “አስመሳይ በሆኑ ቃላት” አሳምረው ያቀርባሉ። (ሮሜ 16:17, 18፤ 2 ጴጥሮስ 2:3 አዓት) የከሐዲያን ጽሑፎች በሙሉ እንዲሁ በትችትና በአፍራሽ አስተሳሰብ የተሞሉ ናቸው! ምንም የሚያንጽ ነገር የለባቸውም።—7/1፣ ገጽ 12
▫ ግሪክ የዲሞክራሲ ጀማሪ ነበረችን?
በጥንቷ ግሪክ ዲሞክራሲ ይሠራበት የነበረው የራሳቸው መንግሥት በነበራቸው በጥቂት ከተሞች ውስጥ ብቻ ነበር። በእዚህም ከተሞች ቢሆን በምርጫ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡት ወንዶች ብቻ ነበሩ። ይህም ማለት አራት አምስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ከሂደቱ ውጭ ነበር ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሕዝቦች ሉዓላዊነት ወይም ዲሞክራሲ ነበር ለማለት አያስደፍርም!—7/1፣ ገጽ 16
▫ አንድን ክርስቲያናዊ ጋብቻ የተሳካ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?
ባልም ሆነ ሚስት አምላክ ስለ ጋብቻ ያለውን አመለካከት የሚያከብሩ ከሆኑና በቃሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመሩ ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ነው። (ኤፌሶን 5:21–33)—7/15፣ ገጽ 10
▫ የቤተሰብ ጥናታችሁ አስደሳች ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ልጆቹ ሁሉ በጥናቱ እንዲሳተፉ አድርጉ። አዎንታዊ መንፈስ ያላችሁና የምታንጹ ሁኑ፤ ልጆቻችሁ ለሚያደርጉት ተሳትፎም ሞቅ ባለ ስሜት አመስግኗቸው። አንድን ጽሑፍ አጥንታችሁ ለመሸፈን ሳይሆን የልጆቻችሁን ልብ ለመንካት ጣሩ።—7/15፣ ገጽ 18
▫ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ” የሚለው አነጋገር ምን ያመለክታል? (1 ተሰሎንቄ 5:3)
መጽሐፍ ቅዱስ በየአገሩ “ሰላምና ደኅንነት” ይሰፍናል እንዳላለ ልብ በሉ። ይሁን እንጂ እስካሁን አድርገውት በማያውቁት የተለየ መንገድ ስለ “ሰላምና ደኅንነት” ያወራሉ። ከዚህ በፊት ያልታየ አዎንታዊ ስሜትና እምነት ያድርባቸዋል፤ ይህንኑም ይናገራሉ። ሰላምና ደኅንነት ከመቼውም የተሻለ ዕድል ያላቸው መስለው ይታያሉ።—8/1፣ ገጽ 6
▫ ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች ግለጽ።
ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። (መዝሙር 86:5 አዓት) አዲስ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ቀደም ሲል ሊወስደው አስቦት የነበረውን እርምጃ ለመለወጥ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮናስ ምዕራፍ 3ን ተመልከት።) በተጨማሪም ይሖዋ በሥልጣን አጠቃቀሙ ረገድ ምክንያታዊነቱን አሳይቷል። (1 ነገሥት 22:19–22)—8/1፣ ገጽ 12–14