በሽማግሌዎችና በዲያቆናት መካከል ያለውን ስምምነት መጠበቅ
ከ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ብዙም ሳይቆይ አዲስ በተመሠረተው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድ አጣዳፊ እርምጃ የሚያሻው ነገር ተከሰተ። የተቸገሩ መበለቶችን ለመንከባከብ የተደረገ አንድ ዝግጅት ነበር። ይሁንና ትንሽ ቆይቶ “የግሪክ ቋንቋ የሚናገሩ አይሁዳውያን፣ የይሁዳ አገር ተወላጆች በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ማጉረምረም ጀመሩ፤ ምክንያቱም በየቀኑ ይታደል በነበረው እርዳታ መበለቶቻቸው ችላ ይባሉባቸው ስለነበር ነው።”—ሥራ 6:1 የ1980 ትርጉም።
ይህ ቅሬታ ወደ ሐዋርያት ጆሮ ደረሰ። “ስለዚህ አሥራ ሁለቱ፣ አማኞችን ሁሉ ሰብስበው እንዲህ አሏቸው፣ ‘ምግብ ለማደል ብለን፣ የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማር ሥራችንን መተው አይገባንም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ፣ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ፣ ሰባት ሰዎችን ከመካከላችሁ ምረጡ፤ እነርሱን ለዚህ ኃላፊነት እንሾማቸዋለን።”—ሥራ 6:2, 3 የ1980 ትርጉም።
ይህ ነገር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚኖረው አስፈላጊ የሆነ የአደረጃጀት መሠረታዊ ሥርዓት ምሳሌ ይሆናል። አንዳንድ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች ተደጋጋሚ የሆኑ የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴዎች ሲያከናውኑ ሌሎች ደግሞ ከበድ ያሉ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ይከታተላሉ። ይህ በዚያን ጊዜ የተጀመረ አልነበረም። በጥንቷ እስራኤል አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው በማገልገል ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ተመርጠው ነበር። ይሁን እንጂ ሌዋውያን ‘የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ በመጠበቅ’ እነርሱን እንዲረዷቸው ይሖዋ ትዕዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘኁልቁ 3:5–10) በተመሳሳይም ዛሬ ዲያቆናት የበላይ ተመልካቾችን በሥራ ያግዟቸዋል።
የሽማግሌዎችና የዲያቆናት ሚና
ቅዱሳን ጽሑፎች ሽማግሌዎችም ሆኑ ዲያቆናት ሊያሟሏቸው የሚገቡትን ከፍተኛ የብቃት ደረጃዎች ይዘረዝራሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:6-9) ሽማግሌዎችና ዲያቆናት እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩ ሳይሆኑ ለአንድ ግብ ይኸውም ጉባኤውን ለማነጽ የተሰለፉ ናቸው። (ከኤፌሶን 4:11–13 ጋር አወዳድር) ሆኖም ግን በጉባኤ ውስጥ በሚያከናውኗቸው የሥራ ድርሻዎች ላይ አንዳንድ ልዩነቶች አሉ። በ1 ጴጥሮስ 5:2 ላይ የበላይ ተመልካቾች እንደሚከተለው ተብለዋል፦ “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔር መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጎብኙት።” የተሰጣቸውን ይህን ቅዱስ ኃላፊነት እንዴት እንደተወጡት ለአምላክ ስሌት ያቀርባሉ።—ዕብራውያን 13:17
ስለ ዲያቆናትስ ምን ማለት ይቻላል? ቅዱሳን ጽሑፎች ዲያቆናት የሽማግሌዎችን ያህል የማስተማር ብቃት እንዲኖራቸው አይጠይቁም። የሚያከናውኗቸው ተግባሮች ከሽማግሌዎች ተግባር የተለየ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መሠራት የሚገባቸው የቁሳዊነት ባሕርይ ያላቸው የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴዎች ወይም ከጥገና ጋር የተያያዙ ሥራዎች እንደነበሩ ምንም አያጠራጥርም። ይህ ምናልባትም የቅዱሳን ጽሑፎችን ቅጂ ለማባዛት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች መግዛትን አለበለዚያም ቅጂውን የመገልበጥንም ሥራ ሊጨምር ይችላል።
ዛሬም ዲያቆናት የጉባኤውን ሒሳብ መያዝን፣ የጉባኤውን የአገልግሎት ክልል ድልድል መቆጣጠርን፣ መጽሔቶችንና መጽሐፎችን ማከፋፈልን እንዲሁም የመንግሥት አዳራሹን መንከባከብን የመሳሰሉትን አስፈላጊ ሥራዎች በጉባኤ ውስጥ ያከናውናሉ። ችሎታው ያላቸው አንዳንድ ዲያቆናት በማስተማሩም ሥራ ሊያገለግሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ሊመሩ፣ በአገልግሎት ስብሰባዎች ላይ ክፍል ሊያቀርቡና የሕዝብ ንግግርም ሊሰጡ ይችላሉ።
ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ተስማምተው በአንድነት ሲሠሩ የጉባኤው ፍላጎቶች ይኸውም መንፈሳዊም ሆነ ድርጅታዊ ፍላጎቶቹ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ይጠበቃሉ። የጉባኤውም አባላት ደስተኞች፣ ብርቱዎች እና በመንፈሳዊ ፍሬያማ ይሆናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት ቅቡአን ምን ብሎ እንደጻፈላቸው አስታውሱ፦ “ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፣ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ [በስምምነት አዓት] እየተጋጠመና እየተያያዘ፣ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።”—ኤፌሶን 4:16
ሽማግሌዎችና ዲያቆናት እርስ በእርስ በመደጋገፍ የመሥራትን ልማድ ለማዳበር መጣር ይኖርባቸዋል። ይኸውም በስምምነት፣ በመግባባት፣ በትብብርና በአንድነት መሥራት ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ስምምነት ራሱ አውቆ የሚመጣ ነገር አይደለም። ሊኮተኮትና በጥንቃቄ ሊጠበቅ ይገባል።
ሽማግሌዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
አንዱ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ በሽማግሌዎችና በዲያቆናት መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የባሪያ ወይም የአሠሪና የሠራተኛ ዓይነት እንዳልሆነ መገንዘብ ነው። በመካከላቸው እውነተኛ ስምምነት ካለ ሽማግሌዎች ዲያቆናትን አብረዋቸው እንደሚያገለግሉ የአምላክ አገልጋዮች አድርገው ይመለከቷቸዋል። (ከ1 ቆሮንቶስ 3:6–9 ጋር አወዳድር) ሮሜ 12:10 (እንደ 1980 ትርጉም) “እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ” ይላል። እንግዲያውስ ሽማግሌዎች ዲያቆናትን የበታች እንደሆኑ በሚያስመስል ወይም ዝቅ በሚያደርግ መንገድ ከመያዝ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። የሚያቀርቧቸውን መልካም የሆኑ ሐሳቦች ከማንኳሰስ ይልቅ ሐሳብ እንዲያፈልቁ ያበረታቷቸዋል። ዲያቆናትን በአክብሮት መያዙ በውስጣቸው የታመቀውን ችሎታ ከቀድሞው በበለጠ መንገድ እንዲጠቀሙበትና በጉባኤ ውስጥ በሚሠሩትም ሥራ እንዲደሰቱ ይረዳቸዋል።
ከዚህም በላይ ሽማግሌዎች በእነርሱ ዘንድ ያለውን መንጋ በእረኝነት እንዲጠብቁ የተሰጣቸው ተልእኮ ዲያቆናት ሆነው የሚያገለግሉትን ወንድሞችም እንደሚጨምር መዘንጋት የለባቸውም። ዲያቆን ሆነው የማገልገል መብት የሚያገኙ ወንድሞች የበሰሉ ክርስቲያኖች መሆን እንዳለባቸው የታወቀ ነው። የሆኖ ሆኖ ግን እንደተቀረው የመንጋው ክፍል ሁሉ እነርሱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ትኩረት ያሻቸዋል። ሽማግሌዎች እነርሱ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ መሻሻል ከልብ መከታተል ይገባቸዋል።
ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገኘው ጢሞቴዎስ ለመሥራት ያለውን እምቅ ችሎታ ስለተረዳ “ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ።” (ሥራ 16:3) ጢሞቴዎስ የጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ ሆኖ አገልግሏል፤ ከዚህ የተነሣ በዋጋ ሊተመን የማይችል ሥልጠና አግኝቷል። እንዲያውም ጳውሎስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በቆሮንቶስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት ሊጽፍላቸው ችሎ ነበር፦ “ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፣ እኔም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 4:17
እናንተ ሽማግሌዎች፤ በጉባኤያችሁ ውስጥ ያሉት ዲያቆናት ባላቸው እምቅ ችሎታ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ጀምራችኋልን? በሕዝብ ፊት ንግግር መስጠትን እንዲሁም በልዩ ልዩ ጽሑፎች ላይ ምርምር ማድረግን ስለመሳሰሉት ነገሮች በግል ሥልጠና በመስጠት መሻሻል እንዲያደርጉ እየረዳችኋቸው ነውን? የእረኝነት ጥየቃ በምታድርጉበት ጊዜ ብቃት ያላቸውን አብረዋችሁ እንዲሄዱ ጋብዛችኋቸዋልን? አብራችኋቸው ወደ መስክ አገልግሎት ትሄዳላችሁን? ኢየሱስ ስለመክሊቶቹ በሰጠው ምሳሌ ላይ ጌታው ለታማኝ አገልጋዮቹ “መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ!” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 25:23) እናንተስ የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ በግሩም ሁኔታ ቦታቸውን ጠብቀው ለሚወጡ ዲያቆናት ምስጋናና ሙገሳ ትለግሳላችሁን? (ከምሳሌ 3:27 ጋር አወዳድር) እንዲህ የማታደርጉ ከሆነ ሥራቸው ምንም ተቀባይነት እንዳላገኘ አይሰማቸውምን?
በተመሳሳይም ስምምነት ለሰፈነበት የሥራ ግንኙነት የሐሳብ ልውውጥ የማድረጉ አስፈላጊነት አንገብጋቢ ነው። (ከምሳሌ 15:22 ጋር አወዳድር።) ለአንድ ዲያቆን ኃላፊነት የሚሰጠውም ሆነ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚነጠቀው እንዳሻው በሚደረግ ውሳኔ ወይም ሳይታሰብበት መሆን የለበትም። ሽማግሌዎች አንድ ወንድም ባለው ችሎታ ጉባኤውን በተሻለ ሁኔታ እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል በጸሎት ሊያስቡበት ይገባል። (ከማቴዎስ 25:15 ጋር አወዳድር) አንድ ወንድም ኃላፊነት ሲሰጠው ከእርሱ ምን እንደሚፈለግበት ጥሩ ማብራሪያ ሊሰጠው ይገባል። ምሳሌ 11:4 “መልካም ምክር [ጥበብ የተሞላበት መመሪያ አዓት] ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል” በማለት ያስጠነቅቃል።
አንድን ወንድም ከአሁን በኋላ የጉባኤውን የሒሳብ፣ የመጽሔት ወይም የሥነ ጽሑፍ ሥራ ተረክበህ የምትሠራው አንተ ነህ ብሎ መንገሩ ብቻ አይበቃም። አንዳንድ ጊዜ አንድ አዲስ አገልጋይ ብዙ የተሳሳቱ ወይም ገና ያልተሟሉ መዝገቦች ይረከባል። ይህ እንዴት ወኔን የሚያዳክም ነው! 1 ቆሮንቶስ 14:40 “ነገር ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” በማለት ይመክረናል። ሽማግሌዎች ወንድሞችን በማሠልጠን፣ ከጉባኤው የአሠራር ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግና ራሳቸውም እነዚህን የአሠራር ሥርዓቶች በመከተል ረገድ ምሳሌ በመሆን ቀዳሚዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ሽማግሌዎች የጉባኤው ሒሳብ በየሦስት ወሩ እንዲመረመር ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱን ጠቃሚ ዝግጅት ችላ ማለታቸው ግን ችግሮች እንዲፈጠሩ ሊያደርግና ዲያቆናትም ለድርጅታዊ መመሪያዎች ያላቸውን አክብሮት ሊያመናምንባቸው ይችላል።
ይሁንና አንድ ወንድም ለተሰጠው ኃላፊነት ቸልተኛ ሆኖ ቢገኝስ? የተሰጠውን ኃላፊነት ዝም ብሎ ከመንጠቅ ይልቅ ሽማግሌዎች ከእርሱ ጋር ስለ ጉዳዩ መወያየት ይኖርባቸዋል። ምናልባትም ችግሩ ከሥልጠና ማጣት የመጣ ሊሆን ይችላል። ይህ ወንድም ኃላፊነቱን ለመወጣት ያሉበትን ችግሮች ሳያሽሽል ከቀጠለ ምናልባት ሌላ የሥራ ድርሻ ቢሰጠው በተሻለ ሁኔታ ሊያከናውነው ይችል ይሆናል።
ሽማግሌዎች ትሕትና በማሳየትም ስምምነትን ለማስፈን ይችላሉ። ፊልጵስዩስ 2:3 ክርስቲያኖችን እንደሚከተለው ሲል ያበረታታቸዋል:– “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር።” እንግዲያው አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ በአስተናጋጅነት የሚያገለግል ወንድም መጥቶ የሚቀመጥበትን ቦታ ቢያሳየው ሽማግሌ ስለሆነ ብቻ ለእርሱ መታዘዝ እንደሌለበት አድርጎ ባለማሰብ ከእርሱ ጋር ለመተባበር መሞከር ይኖርበታል። ምናልባት አስተናጋጁ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ቦታ እየቀያየሩ ስለመቀመጥ የቀረበውን ሐሳብ ተከትሎ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ሁሉም ሰው እንደዚያ ማድረግ አለበት የሚል ደንብ እንደሌለ መርሳት አይኖርበትም።a አንድ ሽማግሌ ለአንድ ዲያቆን በተመደበ የሥራ ድርሻ ላይ የዲያቆኑን ሐሳብ ገሸሽ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን ከመስጠት መቆጠብ ይኖርበታል።
ስምምነት ለማስፈን የሚተጉ ዲያቆናት
“እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች [ቁም ነገረኞች] . . . ሊሆኑ ይገባቸዋል።” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ያሳስባል። (1 ጢሞቴዎስ 3:8) የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ የቅዱስ አገልግሎታቸው አንዱ ክፍል አድርገው በቁም ነገር መመልከታቸው የስሜት ውጥረት እንዳይፈጠር ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ዲያቆን ሆነህ የምታገለግል ከሆነ የተሰጠህን የሥራ ድርሻ ሞቅ ባለ ስሜት ታከናውናለሀን? (ሮሜ 12:7, 8) በተሰጠህ የሥራ ድርሻ ይበልጥ ብቃት ያለህ ሆነህ ለመገኘት እየተጣጣርክ ነውን? እምነት የሚጣልብህ ሰው ነህን? አንድ ሥራ እንድታከናውን ሲሰጥህ የፈቃደኝነት መንፈስ ታሳያለህን? በአንዲት አፍሪካዊት አገር የሚገኝ ዲያቆን በጉባኤው ውስጥ ሦስት የተለያዩ ዓይነት ሥራዎችን ደርቦ ይሠራል። ታዲያ ለሥራው ያለው ዝንባሌ ምንድን ነው? እንዲህ ይላል፦ “ይህ የሚጠይቀው የበለጠ ጠንክሮ መሥራትን ብቻ ነው። ጠንክሮ መሥራት ደግሞ ሰውን አይገድልም።” በእርግጥም ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለሥራው የሚያቀርቡ ሁሉ ይበልጥ ደስተኛ ይሆናሉ።—ሥራ 20:35
ከሽማግሌዎች ጋር ሙሉ በሙሉ ተባብረህ በመሥራትም ስምምነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ልታደርግ ትችላለህ። ዕብራውያን 13:17 እንዲህ ይላል፦ “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው ይህንኑ በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።” እውነት ነው፤ ሽማግሌዎች ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች እንደመሆናቸው በእነርሱ ላይ ጉድለት ማግኘቱ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ ሌሎችን የመንቀፍ ዝንባሌ እርስ በእርስ አለመተማመንን ይፈጥራል። ይህ ደስታህን ሊያጠፋብህ ከዚያም አልፎ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ሊነካ ይችላል። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ጎበዞች ሆይ፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ . . . እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ።”—1 ጴጥሮስ 5:5, 6
በተለይ አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ለማግኘት እንደተረሳህ ሆኖ ከተሰማህ እንዲህ ዓይነቱ ምክር ለአንተ ተስማሚ ነው። ምናልባትም ‘የበላይ ተመልካችነትን ሥራ እየተመኘህ’ ነገር ግን ምንም ዓይነት የኃላፊነት ሹመት አላገኘህ ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) ትሕትና “የመጠበቅ ዝንባሌ” በመያዝ እንድትጸና ይረዳሃል። (ሰቆቃው ኤርምያስ 3:24 አዓት) ከሽማግሌዎቹ ጋር ያለህን መልካም ግንኙነት የሚያሻክርብህን ቅሬታ በእነርሱ ላይ ከማሳደር ይልቅ ማሻሻል የሚገቡህ ነገሮች ምን እንደሆኑ ቀረብ ብለህ ጠይቃቸው። ምክር ለመቀበልና ያንንም በሥራ ላይ ለማዋል ያለህ ልባዊ ፈቃደኝነት የመንፈሳዊ እድገትህ ማረጋገጫ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።
አንድ ዲያቆን ሌሎች የሌላቸው ልዩ ችሎታ ቢኖረው ወይም በትምህርቱና በማኅበራዊ ኑሮው ከሌሎች የበለጠ ቢሆን አምላካዊ ትሕትና እንዲሁም አቅሙንና ቦታውን ማወቁ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲመላለስ ይረዳዋል። ከሽማግሌዎች ልቆ ለመታየት ወይም ችሎታውን ሰዎች እንዲያደንቁለት ለማድረግ በጣም ሊፈተን ይችላል! ምሳሌ 11:2 “በትሑታን [አቅማቸውንና ቦታቸውን ጠብቀው በሚመላለሱት አዓት] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ያሳስበናል። አቅሙንና ቦታውን የሚያውቅ ወንድም ድንበሩን ያውቃል። ብዙም ጎልቶ ሳይታይ በጸጥታ ለመሥራትና በችሎታዎቹ ሽማግሌዎችን ለመደገፍ ፈቃደኛ ነው። ምንም እንኳን በአለማዊ መንገድ ያካበተው ብዙ እውቀት ሊኖረው ቢችልም እንኳ ቦታውን ጠብቆ መመላለሱ ሽማግሌዎቹ እርሱን በሚበልጡበት በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል በኩል የሚጎድለው ነገር እንዳለ እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 1:26–2:13፤ ፊሊጵስዩስ 1:9
ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ግልጽ ነው። አንድ ላይ በመተባበር ሲሠሩ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሁሉ ለማነጽ ብዙ ነገር ማከናወን ይችላሉ። እንዲህ ለማድረግ ግን ‘በትሕትናና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳቸው በፍቅር በመታገሥ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ በመትጋት’ በአንድነት ተስማምተው መሥራት ይገባቸዋል።—ኤፌሶን 4:2,3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የነሐሴ 15, 1992, መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12ን ተመልከት።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ዲያቆናትን የሚመለከቷቸው የበታች ሠራተኞች እንደሆኑ አድርገው ሳይሆን አብረዋቸው እንደሚያገለግሉ የአምላክ አገልጋዮች አድርገው ነው