አእምሮህን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል አሸናፊ መሆን
ጥቃት እየተሰነዘረብህ ነው! ዋነኛው ጠላትህ የሆነው ሰይጣን አንተን ለማጥቃት የሚጠቀምበት መሣሪያ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው። ይህ መሣሪያ ምንድን ነው? ፕሮፓጋንዳ ነው! ፕሮፓጋንዳ፣ አካልህን ሳይሆን አእምሮህን ለማጥቃት ታስቦ የተዘጋጀ መሣሪያ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰይጣን የሚያስፋፋው ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ የዚህን መሣሪያ አደገኛነት የተገነዘቡት ግን ሁሉም ክርስቲያኖች አልነበሩም። ለምሳሌ፣ በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከልክ በላይ በራስ የመተማመን ስሜት የነበራቸው ይመስላል፤ በእውነት ውስጥ ጠንካራ አቋም ስላላቸው ጨርሶ ሊወድቁ እንደማይችሉ አስበው ነበር። (1 ቆሮ. 10:12) ጳውሎስ የሚከተለውን ማሳሰቢያ የሰጠው ለዚህ ነው፦ “እባቡ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳታለላት ሁሉ እናንተም አስተሳሰባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ልታሳዩ የሚገባውን ቅንነትና ንጽሕና በሆነ መንገድ እንዳታጡ እፈራለሁ።”—2 ቆሮ. 11:3
ጉዳዩ ጳውሎስን ይህን ያህል ያሳሰበው መሆኑ፣ ፈጽሞ መዘናጋት እንደሌለብን ያሳያል። አእምሮህን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል አሸናፊ ለመሆን ከፈለግክ፣ ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ መገንዘብና ራስህን ከዚህ አደጋ መጠበቅ ይኖርብሃል።
ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ ነው?
ፕሮፓጋንዳ ምንድን ነው? ይህ ቃል በዚህ ርዕስ ውስጥ የተሠራበት፣ ሚዛናዊ ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ በሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረግ ጥረትን ለማመልከት ነው። አንዳንዶች ፕሮፓጋንዳ ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው “መዋሸት፣ እውነትን አዛብቶ ማቅረብ፣ ማታለል፣ ተጽዕኖ ማሳደር፣ የሌሎችን አእምሮ ለመቆጣጠር መሞከርና ሥነ ልቦናዊ ጦርነት” ነው፤ በመሆኑም ፕሮፓጋንዳ “ተገቢ ያልሆነ፣ ጎጂ እንዲሁም መሠሪ የሆነ ዘዴ” እንደሆነ ይናገራሉ።—ፕሮፓጋንዳ ኤንድ ፐርስዌዥን
ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ ነው? ቀለምና ሽታ እንደሌለው መርዛማ ጋዝ ሁሉ፣ ፕሮፓጋንዳም ሳይታወቀን አስተሳሰባችንን ሊመርዘው ይችላል። ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ላናስተውል እንችላለን፤ በመሆኑም የባሕርይ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ቫንስ ፓካርድ እንደተናገሩት “ብዙዎቻችን፣ በአስተሳሰባችን ላይ ከምንገምተው በላይ ተጽዕኖ እየደረሰብን ነው።” አንድ ምሁር እንደገለጹት ደግሞ በርካታ ሰዎች በፕሮፓጋንዳ ተመርተው “ለማመን የሚከብድ አደገኛ ነገር ፈጽመዋል።” ‘የዘር ማጥፋት ዘመቻን፣ ጦርነትን፣ ዘረኝነትን፣ ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትን እና ሌሎች ምክንያታዊነት የጎደላቸው ነገሮችን’ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።—ኢዝሊ ሌድ—ኤ ሂስትሪ ኦቭ ፕሮፓጋንዳ
እንደ እኛው ያሉ ሰዎች እንኳ በፕሮፓጋንዳ ተጠቅመው ይህን ያህል ሊያታልሉን ከቻሉ፣ ሰይጣንማ ከዚህ የበለጠ እንደሚያደርግ ጥያቄ የለውም! ሰይጣን፣ የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ባሕርያቸውን ሲያጠና ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት “መላው ዓለም” በእሱ ቁጥጥር ሥር ነው። በመሆኑም የውሸት ሐሳቦቹን ለማሰራጨት፣ በቁጥጥሩ ሥር ያለውን ዓለም የትኛውንም ክፍል ሊጠቀም ይችላል። (1 ዮሐ. 5:19፤ ዮሐ. 8:44) ሰይጣን ‘የሰዎችን አእምሮ በማሳወር’ ረገድ በጣም ስኬታማ ከመሆኑ የተነሳ በአሁኑ ወቅት “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። (2 ቆሮ. 4:4፤ ራእይ 12:9) ታዲያ እሱ የሚያስፋፋው ፕሮፓጋንዳ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
መከላከያህን አጠናክር
ኢየሱስ “[እውነትን] ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” በማለት ፕሮፓጋንዳን መዋጋት የሚቻልበትን ቀላል ዘዴ ገልጿል። (ዮሐ. 8:31, 32) ይሁን እንጂ በጦርነት ወቅት ጠላት የሚጠቀምበት የመጀመሪያው መሣሪያ እውነትን መሰወር ነው፤ በመሆኑም በተጧጧፈ ጦርነት ላይ ያለ ማንኛውም ወታደር፣ ጠላቱ እንዳያታልለው አስተማማኝና እምነት የሚጣልበት መረጃ ማግኘት ይኖርበታል። አእምሮህን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ አስተማማኝና እምነት የሚጣልበት መረጃ ከየት ማግኘት ትችላለህ? ይሖዋ፣ ሰይጣን የሚሰነዝረውን ፕሮፓጋንዳ ለመዋጋት የሚያስፈልገንን መረጃ በሙሉ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሰጥቶናል።—2 ጢሞ. 3:16, 17
እርግጥ ነው፣ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ረገድ የተዋጣለት ሰይጣንም ይህን ያውቃል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳናነብና እንዳናጠና እንቅፋት ለመፍጠር በእሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ይጠቀማል። ሰይጣን በሚጠቀምባቸው መሠሪ ዘዴዎች አትታለል። (ኤፌ. 6:11) መሠረታዊ ነገሮችን በማወቅ ብቻ ሳትወሰን እውነትን ‘በሚገባ ለመረዳት’ ጥረት አድርግ። (ኤፌ. 3:18) ይህን ማድረግ ትልቅ ጥረት እንደሚጠይቅብህ የታወቀ ነው። ሆኖም ኖአም ቾምስኪ የተባሉት ደራሲ የተናገሩትን የሚከተለውን መሠረታዊ እውነታ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፦ “ማንም ሰው፣ እውነት ወደ አእምሮህ ዘልቆ እንዲገባ ሊያደርግ አይችልም። አንተ ራስህ እውነትን ፈልገህ ማግኘት አለብህ።” እንግዲያው “በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር” “አንተ ራስህ እውነትን ፈልገህ” አግኝ።—ሥራ 17:11
አእምሮህን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል አሸናፊ ለመሆን ከፈለግክ፣ ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ መገንዘብና ራስህን ከዚህ አደጋ መጠበቅ ይኖርብሃል
ሰይጣን በትክክል እንድታስብ ወይም ነገሮችን እንድታመዛዝን እንደማይፈልግ አትዘንጋ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ ምንጭ እንደገለጸው፣ ፕሮፓጋንዳ “ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው ሰዎች . . . ነገሮችን በሚገባ እንዳያመዛዝኑ የሚያደርግ ሁኔታ ሲኖር ነው።” (ሜዲያ ኤንድ ሶሳይቲ ኢን ዘ ትዌንቲዝ ሴንቸሪ) ስለዚህ የምትሰማውን ነገር ሁሉ ሳታጣራ አትቀበል። (ምሳሌ 14:15) ከዚህ ይልቅ አምላክ የሰጠህን የማመዛዘንና የማሰብ ችሎታ በመጠቀም እውነትን የራስህ አድርግ።—ምሳሌ 2:10-15፤ ሮም 12:1, 2
አንድነትን ለማናጋት በሚደረጉ ጥረቶች አትሸነፍ
የውትድርና ስልት የሚነድፉ ሰዎች፣ የጠላቶቻቸውን ወኔ ለመስበር ብሎም የውጊያ መንፈሳቸውን ለማዳከም ፕሮፓጋንዳን ይጠቀማሉ። የጠላት ወታደሮች እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ ያደርጉ ይሆናል፤ አሊያም ወታደሮቹ ከዋናው ሠራዊት ራሳቸውን እንዲያገልሉ የሚያደርጉ ማታለያዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። አንድ የጀርመን ጄኔራል፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ሠራዊት እንዲሸነፍ ያደረገው አንዱ ምክንያት “እባብ ጥንቸልን እንደሚያፈዝዛት ሁሉ [ሕዝቡም] በጠላት ፕሮፓጋንዳ መፍዘዙ” እንደሆነ ገልጿል። ሰይጣንም በአምላክ ሕዝቦች መካከል መከፋፈል በመፍጠር እነሱን ድል ለመንሳት ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማል፤ ለምሳሌ በወንድሞችና እህቶች መካከል ግጭት ለመፍጠር አሊያም የፍትሕ መጓደል እንደደረሰባቸው ወይም በደል እንደተፈጸመባቸው አስበው ከይሖዋ ድርጅት እንዲርቁ ለማነሳሳት ይሞክራል።
አንተም በሰይጣን ዘዴ አትታለል! ከዚህ ይልቅ የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር በመከተል ከወንድሞችህ ጋር ያለህን አንድነት ጠብቅ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በነፃ ይቅር መባባላችንን እንድንቀጥል’ እንዲሁም አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ቶሎ እንድንፈታቸው ያበረታታናል። (ቆላ. 3:13, 14፤ ማቴ. 5:23, 24) በተጨማሪም ራሳችንን ከጉባኤ እንዳናገልል አጥብቆ ያሳስበናል። (ምሳሌ 18:1) የሰይጣንን ፕሮፓጋንዳ ለመቋቋም ዝግጁ መሆንህን ለማወቅ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከዚህ ቀደም ወንድሞቼ ቅር ባሰኙኝ ወቅት ምን እርምጃ ወሰድኩ? ያደረግኩት ነገር በአምላክ መንፈስ እንደምመራ የሚያሳይ ነው ወይስ በዓለም መንፈስ?’—ገላ. 5:16-26፤ ኤፌ. 2:2, 3
አመራር በሚሰጡት ላይ እምነት እንዳታጣ ተጠንቀቅ
አንድ ወታደር ለመሪው ያለው ታማኝነት ከተሸረሸረ በሚገባ አይዋጋም። በመሆኑም ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ሰዎች፣ በወታደሮችና በመሪያቸው መካከል ያለው መተማመን እንዲጠፋ ለማድረግ ይጥራሉ። “መሪዎቻችሁን ልትተማመኑባቸው አትችሉም!” እንዲሁም “እነሱን ተከትላችሁ አደጋ ውስጥ አትግቡ!” እንደሚሉት ያሉ ፕሮፓጋንዳዎችን ይነዙ ይሆናል። ሐሳባቸው ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሲሉ ደግሞ እነዚህ መሪዎች የሠሯቸውን ስህተቶች ይጠቅሳሉ። ሰይጣንም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል። አመራር እንዲሰጡ ይሖዋ በሾማቸው ላይ ያለህን እምነት እንድታጣ ጥረት ማድረጉን አያቋርጥም።
ታዲያ ይህን ጥቃት መከላከል የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ አመራር እንዲሰጡ የሾማቸው ሰዎች ፍጹማን ባለመሆናቸው ስህተቶች ሲፈጽሙ ብታይም እንኳ፣ ምንጊዜም ከድርጅቱ ጎን ለመቆምና የሚሰጡትን አመራር በታማኝነት ለመደገፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። (1 ተሰ. 5:12, 13) ከሃዲዎችም ሆኑ ሌሎች አታላይ ሰዎች የሚሰነዝሩት ክስ ምንም ያህል እውነተኛ ቢመስል ‘የማመዛዘን ችሎታህ በቀላሉ አይናወጥ።’ (2 ተሰ. 2:2፤ ቲቶ 1:10) ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተከተል፦ “በተማርካቸው . . . ነገሮች ጸንተህ ኑር” እንዲሁም “እነዚህን ነገሮች እነማን እንዳስተማሩህ” አትዘንጋ። (2 ጢሞ. 3:14, 15) በእርግጥም፣ ይሖዋ እኛን በእውነት መንገድ ለመምራት ወደ መቶ ለሚጠጉ ዓመታት በተጠቀመበት በዚህ መሥመር ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አለህ።—ማቴ. 24:45-47፤ ዕብ. 13:7, 17
ለማስፈራሪያዎች አትበገር
ሰይጣን የሚጠቀምበት ፕሮፓጋንዳ ሁልጊዜ ስውር ነው ማለት አይደለም። “በጣም ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩት የፕሮፓጋንዳ ዓይነቶች አንዱ” የሆነውን ሽብር የመንዛት ዘዴ የሚጠቀምበት ጊዜም አለ። (ኢዝሊ ሌድ—ኤ ሂስትሪ ኦቭ ፕሮፓጋንዳ) ብሪታንያዊው ፕሮፌሰር ፊሊፕ ቴይለር እንደጻፉት አሦራውያን፣ ጠላቶቻቸውን በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል “ፕሮፓጋንዳን ከማስፈራሪያ ጋር አቀናጅተው” ይጠቀሙ ነበር። ሰይጣንም ሰውን፣ ስደትን፣ ሞትን እና ሌሎች ነገሮችን በመፍራት በእሱ ቁጥጥር ሥር እንድትሆንና ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ ይጥራል።—ኢሳ. 8:12፤ ኤር. 42:11፤ ዕብ. 2:15
ሰይጣን በፍርሃት ተጠቅሞ ወኔህን እንዲያዳክመው ወይም ንጹሕ አቋምህን እንድታላላ እንዲያደርግህ አትፍቀድ። ኢየሱስ “ሥጋን የሚገድሉትን ከዚያ በላይ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ” ብሏል። (ሉቃስ 12:4) ይሖዋ፣ ጥበቃ እንደሚያደርግልህና “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” እንደሚሰጥህ እንዲሁም ፈርተህ እጅ እንድትሰጥ ለማድረግ የሚሰነዘሩ ሙከራዎችን በሙሉ እንድትቋቋም እንደሚረዳህ በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት ይኑርህ።—2 ቆሮ. 4:7-9፤ 1 ጴጥ. 3:14
እርግጥ ነው፣ በፍርሃት እንድትርድና ወኔ እንዲከዳህ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። ያም ቢሆን ይሖዋ ለኢያሱ የሰጠውን የሚከተለውን የሚያበረታታ ሐሳብ አስታውስ፦ “ደፋርና ብርቱ ሁን . . . አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።” (ኢያሱ 1:9) አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ፣ የሚያሳስብህን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ለይሖዋ በጸሎት ንገረው። የሰይጣንን ፕሮፓጋንዳዎች በሙሉ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም እንዲኖርህ ‘የአምላክ ሰላም ልብህንና አእምሮህን እንደሚጠብቅ’ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ፊልጵ. 4:6, 7, 13
የአሦር ንጉሥ የላከው ራብሻቅ የአምላክን ሕዝቦች ለማስፈራራት የተጠቀመበትን ፕሮፓጋንዳ ታስታውሳለህ? የተናገረውን ሐሳብ ጠቅለል ብናደርገው ‘ማንም ከአሦር ሊያስጥላችሁ አይችልም። አምላካችሁ ይሖዋ እንኳ ምንም ሊረዳችሁ አይችልም’ ያለ ያህል ነው። ‘ይህን ምድር እንድናጠፋ የላከን ይሖዋ ራሱ ነው’ በማለት በድፍረት ተናግሯል። ታዲያ ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? “የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች እኔን በመሳደብ የተናገሩትን ቃል በመስማትህ አትፍራ” የሚል መልእክት ላከ። (2 ነገ. 18:22-25፤ 19:6) ከዚያም መልአኩን በመላክ በአንድ ሌሊት 185,000 አሦራውያንን እንዲገድል አደረገ።—2 ነገ. 19:35
ጥበበኛ በመሆን ምንጊዜም ይሖዋን ስማ
አንድ ፊልም እያየህ እንደሆነ አድርገን እናስብ፤ እንደ ተመልካች ሆነህ ስታየው፣ በፊልሙ ላይ ያለው ገጸ ባሕርይ እየተታለለ እንዳለ ቁልጭ ብሎ ይታይህ ይሆናል። በመሆኑም ለግለሰቡ ‘አትመናቸው! ውሸታቸውን ነው!’ ብለህ ለመናገር ዳድቶህ ይሆናል። በተመሳሳይም መላእክት “በሰይጣን ውሸቶች አትታለል!” ብለው ሲነግሩህ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ።
እንግዲያው ለሰይጣን ፕሮፓጋንዳ ጆሮ አትስጥ። (ምሳሌ 26:24, 25) ይሖዋ የሚልህን አድምጥ እንዲሁም በመንገድህ ሁሉ በእሱ ታመን። (ምሳሌ 3:5-7) “ልጄ ሆይ፣ . . . ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው” በማለት ላቀረበልህ ፍቅራዊ ግብዣ ምላሽ ስጥ። (ምሳሌ 27:11) እንዲህ ካደረግክ አእምሮህን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል አሸናፊ መሆን ትችላለህ!