አስደሳች የአገልግሎት መብት
1 ለስድስት ዓመታት ያህል በዩኒቨርሲቲ ሲማር ካገኘው ይልቅ የመጠበቂያ ግንብ ና የንቁ! መጽሔቶችን በማንበቡ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት እንዳገኘ አንድ አንባቢ ተናገረ። ቅን የሆኑ አንባቢዎች እነዚህን መጽሔቶች ለአጭር ጊዜ ብቻ ካነበቡ በኋላ እንኳን እንዲህ ያሉ ልብን በደስታ የሚያሞቁ የአድናቆት ቃላት ማሰማታቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። መጽሔቶቻችንን ከልባቸው ከፍተኛ ዋጋ ለሚሰጧቸው ሰዎች ዘወትር ለማካፈል በመቻላችን ምንኛ የታደልን ነን!
2 ብዙ ሰዎች ለእውነት መጠነኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው እስከመቀበል ድረስ አልገፉበትም። ነገር ግን አንድ ሰው አዲስ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ ና የንቁ! መጽሔቶች ይዞ እየሄደ አዘውትሮ ቢጠይቃቸው ፍላጎታቸው ሊዳብር ይችል ይሆናል። አዎን ለመጽሔት ደንበኞች መጽሔቶችን በትክክል ማዳረስ ሰዎች ውሎ አድሮ ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ለመስማማት እንዲገፋፉ ረድቷቸዋል።
3 ለመጽሔት ደንበኞቻችን መጽሔቶችን በማደል መጽሔቶቹን በቅድሚያ ካነበብናቸውና በያዝነው ዝርዝር ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተለይ ሊስበው ይችላል የምንላቸውን የተወሰኑ ነጥቦች በማስታወሻ ከወሰድን በግላችን እንጠቀማለን።
4 የሰውየውን ስም በመጽሔት ደንበኞቻችሁ ስም ዝርዝር ውስጥ ልታስገቡት እንደሚገባ የሚወስነው የቤቱ ባለቤት ያለው የፍላጎት መጠን እንደሆነ በአእምሮአችሁ ያዙ። ሰውየው መጽሔቶቹን ሲቀበል እውነተኛ ፍላጐት ካሳየ በመጽሔቶቻችን ውስጥ በየሁለት ሳምንቱ ተወዳዳሪ የሌላቸው ርዕሰ ትምህርቶች እንደሚወጡ ልትገልጹለትና ብትወስዱለትም ደስተኛ እንደምትሆኑ ልትነግሩት ትችላላችሁ። አጋጣሚዎቹን ከቤቱ ባለቤት ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶች ላይ ለመወያየት እየተጠቀማችሁባቸው አዘውትራችሁ መጎብኘታችሁን አረጋግጡ። በዚህ አስደሳች የአገልግሎት መብት እንደምትደሰቱ እናውቃለን።