ቀላልና ውጤታማ የሆነ መልዕክት ማቅረብ
1 ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ያወጀው ቀላልና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ነበር። በግ መሰል የሆኑ ሰዎች እውነትን ሲሰሙ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስዱ ያውቅ ነበር። ሰዎች በአስተሳሰባቸው፣ በፍላጎታቸውና በማመዛዘን ችሎታቸው እንደሚለያዩም ያውቅ ነበር። በዚህ መሠረት የሰሚዎቹን ትኩረት ለመሳብና ልባቸውን ለመንካት ሲል ያልተወሳሰቡ መግቢያዎችን፣ ጥያቄዎችንና ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። የሱን ምሳሌ ልንከተልና ቀላልና ውጤታማ የሆኑ መልእክቶችን ለማቅረብ እንችላለን።
2 ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ በሚገባ ተጠቀሙበት፦ ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 11 ላይ “ሥራ/ቤት ማግኘት” የሚለው ርዕስ ለጊዜው ተስማሚና ለአቀራረብም ቀላል የሆነ ነው።
እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ሁሉም ሰው ሥራና ቤት የማግኘት ዋስትና እንዲኖረው ምን ሊደረግ እንደሚችል ከጎረቤቶችዎ ጋር እየተነጋገርን ነበር። አንድ ቀን ይህ ችግር ይቃለል ይሆናል ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው ብለው ያምናሉ? . . . ነገር ግን እነዚህን ችግሮች እንዴት ማቃለል እንደሚቻል የሚያውቅ አለ። እሱም የሰው ዘሮች ፈጣሪ ነው።” ኢሳይያስ 65:21–23ን አንብብ። ከዚያም የቤቱን ባለቤት ስለተነበበው ነገር ምን እንደተሰማው ልትጠይቀው ትችላለህ።
3 “የፍትህ መዛባት/መከራ” በሚለው በገጽ 12 ላይ የሚገኘው ርዕስ ሥር ያለው መግቢያ በዛሬው ጊዜ ያሉ የብዙ ሰዎችን ስሜት የሚቀሰቅስ ነው።
እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ፦
◼ “ሰዎች ስለሚደርስባቸው የፍትህ መዛባትና መከራ አምላክ ግድ ይኖረው ይሆን? ብለው ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉን?” የቤቱ ባለቤት መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት፤ ከዚያም መክብብ 4:1ና መዝሙር 72:12–14ን አንብብ። ሁኔታው ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ለማስተዋወቅ ተስማሚ ከሆነ ገጽ 150–153 ላይ ያሉትን ሥዕሎች ግለጥና በዛሬው ጊዜ ያለው የዓለም ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን በአጭሩ አሳይ። ከዚያም ወደ ገጽ 161–162 ግለጥና አምላክ ለሰው ልጆች በረከት ለማምጣት ምን ተጨማሪ ትንቢቶችን እንደተናገረ አሳየው። ይበልጥ ስሜቱን የቀሰቀሰው የትኛው ሁኔታ እንደሆነ የቤቱን ባለቤት ጠይቀው።
4 ከቤቱ ባለቤት ጋር አጠር ያለ ውይይት ካደረጋችሁ በኋላ ለዘላለም መኖር ከተባለው መጽሐፍ ይልቅ ወደ አንድ መጽሔት፣ ብሮሹር ወይም ትራክት ትኩረቱን ማዞር ይበልጥ ተስማሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
ለምሳሌ በዚህ ርዕሰ ትምህርት አንቀጽ 2 ላይ የተሰጠውን መግቢያ ከተጠቀምክ በኋላ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለው ይህ ብሮሹር አምላክ በየዕለቱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት ምን ተስፋ እንደሰጠ በግልጽ ያብራራል፤ እንዲሁም ከዚህ እንዴት ልንጠቀም እንደምንችል ያሳያል።” ብሮሹሩን ገጽ 26ና 27 ላይ ግለጥና ትኩረቱን ወደ አንቀጽ 21 አዙረው።
5 ወይም በአንቀጽ 3 ላይ ያለውን መግቢያ ከተጠቀምክ በኋላ ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን? ወደምትለው ትራክት ትኩረቱን ልታዞረው ትችላለህ።
እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል፦
◼ “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ብዙ መከራና ችግር አለ። ይህ ትራክት ጦርነት፣ የምግብ እጥረትና የጤና ችግሮች ሁሉ እንደሚመጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተተንብዮ እንደነበር ያሳያል። አምላክ ግን ለሰው ልጆች አስደናቂ ለውጥ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።” በትራክቱ ውስጥ ገጽ 5 ላይ ያለውን የመጨረሻ አንቀጽ አንብበው።
6 ለሰዎች ያለን ቅን ስሜት ልብን የሚነኩ ቀላልና ውጤታማ መልእክቶች ከማቅረባችን ጋር ተዳምሮ በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን ስሜት እንደሚማርክ የተረጋገጠ ነው። — ዮሐንስ 10:16