ሥራው እየተስፋፋ ስለሄደ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች አስፈልገዋል
1 ከብዙ ዓመታት በፊት “በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል” በማለት የይሖዋ ነቢይ ተናግሮ ነበር። (ሐጌ 2:7) መለኮታዊ ትምህርት ብዙዎች እውነትን እንዲያውቁና የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ እንዴት እያስቻላቸው እንዳለ እያየን ነው። በ1993 የአገልግሎት ዓመት በምሥራቅ አፍሪካ 2,735 ሰዎች የተጠመቁ መሆናቸውን ስናውቅ ምን ያህል እንገረም ይሆን! እነዚህን አዲስ ሰዎች ለመርዳት ‘ልባችንን በመንገዳችን ላይ አድርገን’ የአምላክን ሥራ እስከሚቻለው ደረጃ ድረስ በሙሉ ልባችን መደገፍ ያስፈልገናል። (ከሐጌ 1:5 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ለአምላክ ሥራ ድጋፋችንን መስጠታችንን ከምንቀጥልበት ዋነኛው መንገድ ይሖዋን ለማወደስ ለሚጎርፉት አዲሶች ተስማሚ የሆነ የአምልኮ ቤት ለመሥራት ይቻል ዘንድ ያለማቋረጥ የምንሰጠው እርዳታ ነው።
2 ማኅበሩ ጉባኤዎች አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ገንዘብ ማበደሩን ቀጥሏል። በ1993 የአገልግሎት ዓመት በ4 አገሮች የሚገኙ 14 ጉባኤዎች የመንግሥት አዳራሾቻቸውን ለመሥራት የሚያስችል ብድር አግኝተዋል። በሁሉም አገሮች ያሉ ወንድሞች ቦታ ለማግኘትና የመንግሥት አዳራሾቹን ለመሥራት ያሳዩት ቅንዓትና ቆራጥነት የሚያስመሰግን ነው። በመዋጮ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከዓመት ወደ ዓመት ለሚሠሩት አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ሥራ መዋሉ ይቀጥል ዘንድ ለጉባኤዎች በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከነወለዱ በመመለስ ላይ ነው።
3 የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች የሚሰጡት እርዳታ፦ በክልላችን የመጀመሪያው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ በናይሮቢ መቋቋሙን ስናስታውቃችሁ ደስ ይለናል። የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎችን በሞምባሳ፣ በምዕራባዊ ኬንያ፣ በአዲስ አበባና በኪጋሊ ለማቋቋም ታስቧል። የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን በመሥራትና ያረጁትን ከማደስ ጋር በተያያዙት የግንባታ ሥራዎች ላይ የተሠማሩትን ሽማግሌዎች ይረዳሉ። አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ወይም የነበረውን አፍርሶ በአዲስ ፕላን ለመሥራት የሚያስችል እርዳታ ይሰጣሉ። እንዲሁም የመንግሥት አዳራሹ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በማቅረብ በኩል ይረዳሉ። ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች ከእነዚህ ኮሚቴዎች ወደ አንዱ ይመደባሉ።
4 በሌሎች አገሮች በራሳቸው ፈቃድ የተነሣሱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ በሚያወጣው ፕሮግራም ለመካፈል ፈቃደኞች ሆነዋል። ብዙ ባለሙያዎችንና የንግድ ሰዎችን ያጠቃልላል። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች አንዳንድ ቁሳቁሶችን በመግዛት፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ፋይሎችን በመያዝ፣ የሕንጻውን ፕላን በማውጣትና መገዛት ያለባቸውን ቁሳቁሶች ዝርዝር በማዘጋጀት ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን በነፃ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት፣ ተጀምሮ የነበረው ሥራ እንዲጠናቀቅ በማድረግና የሕንፃ ሥራውን በበላይነት በመቆጣጠር ብዙ ይረዳሉ። በእኛም አካባቢ ያለንን ሀብት ተመሳሰይ በሆነ የልግስና መንፈስ የመንግሥቱን ጉዳዮች በማስቀደሙ ተግባር ላይ እንደምናውለው ተስፋ እናደርጋለን። ይህ በጣም የሚያስመሰግንና ከይሖዋ ብዙ በረከትን የሚያስገኝ ሥራ ነው።—ምሳሌ 11:25
5 ሽማግሌዎች ጉባኤው አሁን ያለውን አዳራሽ ማደስ ወይም አዲስ አዳራሽ መሥራት የሚያስፈልገው ሆኖ ሲያገኙት መጀመሪያ ከአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ ጋር መነጋገር ይኖርባቸዋል። ለምን? የአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች ጉባኤዎች ሥራ ለመጀመር ሲያስቡ ሊረዷቸው የሚችሉ መመሪያዎች ይኖሯቸዋል። አዳራሹ የሚሠራበትን ቦታ መምረጥ ወይም መፈለግ ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላል። ከሕንፃው ግንባታ ሌላ ግቢውን ማዘጋጀቱ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑ፣ አደገኛ ወይም መርዝነት ያላቸው ነገሮችን ማስወግዱ ወይም ውስብስብ የሆኑ አንዳንድ ሕግ ነክ ጉዳዮችን ማከናወኑ ከሚገዙት ቁሳቁሶችና ከሕንጻው የሚበልጥ ወጭ ይጠይቃሉ። አንድ ጉባኤ ገንዘብ ነክ የሆኑ እርዳታዎችን ከማኅበሩ ማግኘት የሚያስፈልገው ከሆነ የአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች ጉባኤው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመገመት እንዲችልና ከማኅበሩ የግንባታ ብድር ለመጠየቅ የጉባኤው ሽማግሌዎች ማመልከቻ እንዲያስገቡ ሊረዷቸው ይችላሉ።
6 የአካባቢ የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች የመንግሥት አዳራሽ ሕንፃዎችን ለመሥራት የሚያገለግሉ ፕላኖች አሏቸው። የጉባኤ ሽማግሌዎች የሕንፃውን ንድፍ ከመምረጣቸው በፊት ከአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ ጋር ተገናኝተው በማኅበሩ የቀረቡትን ፕላኖች እንደመመሪያ በመጠቀም ስለ ሕንፃው በአጠቃላይ መወያየት ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረጉ ለሥራው የሚያስፈልጉትን ወጭዎች ከመቀነሱም በላይ ጉባኤው ልከኛና ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጥ እንዲሁም በአጭር ጊዜ የሚሠራ የሕንፃ ፕላን ለመምረጥ ያስችላቸዋል።
7 ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች በትክክልና በዝርዝር ተመዝግበው መያዝ አለባቸው። ጉባኤው አስፈላጊውን የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት እንዲከተልና ሥራው እስኪያልቅ ድረስ ያንኑ ሥርዓት ጠብቆ እንዲቆይ የታወቁ ወንድሞች ከአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴዎች ጋር ሆነው ሊሠሩ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ የጉባኤው ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉትን የመንግሥት አዳራሽ ገንዘብ ነክ መዝገቦች በቋሚነት ስለማይዙ ይህን ማድረጋቸው ትልቅ እርዳታ ነው። ሥራው ሲጠናቀቅ የአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ የግንባታውን ሙሉ የሒሳብ መግለጫ አንድ ቅጂ ማግኘት ይኖርበታል።
8 ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ፦ የአካባቢው የግንባታ ኮሚቴዎች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ወይም የነበረውን ለማደስ በሚያስፈልጋቸው ጉባኤዎች ውስጥ በሚገኙ ችሎታ ባላቸው ሰዎች ለመጠቀም ይፈልጋሉ። በተጨማሪም ለሌሎች የጉባኤው ወንድሞች በተለይም ለሽማግሌዎችና ለዲያቆናት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል ስልጠና ይሰጣሉ። የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት አስፈላጊውን ችሎታ ካገኙ በኋላ እነዚህ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንድሞች በአካባቢው ሊሠሩ በታቀዱ ሌሎች የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሊረዱ ይችላሉ። ስለዚህ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክትን በተመለከተ ከጉባኤዎች ጋር የፈቃደኝነትና የመተባበር መንፈስ ማሳየት አለባቸው እንጂ የአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴና ከኮሚቴው ጋር የሚሠሩት ወንድሞች የመንግሥት አዳራሻቸውን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ሥራ ሁሉ እነርሱ እንዲሠሩላቸው መጠበቅ የለባቸውም። (ነህ. 4:6) ወንድሞች ስልጠናውን ካገኙ በኋላ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ በአስቸኳይ መሥራት ወይም የነበራቸውን ማደስ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ጉባኤዎች ለመርዳት በፍቅር የሚገፋፉ መሆን ይኖርባቸዋል።—ነህ. 5:19፤ ፊል. 2:3, 4
9 ተገቢው ችሎታ ያላቸውና በጉባኤው ውስጥ ጥሩ አቋም ያላቸው የተጠመቁ አስፋፊዎች በጣም ሰፊ በሆነው በዚህ ሥራ በፈቃደኝነት እንዲያግዙ ይበረታታሉ። የግንባታም ሆነ ግንባታ ነክ ያልሆኑ ችሎታዎች ለሥራው ያስፈልጋሉ። በፈቃደኝነት ለመሥራት የሚፈልጉ ይህንኑ ፍላጎታቸውን ለመሪ የበላይ ተመልካቹ ወይም ለጸሐፊው ሊያስታውቁና እነርሱም የሽማግሌዎች አካል ያስተላለፈውን ውሳኔ ለአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ ሊልኩ ይችላሉ። የፈቃደኛ ሠራተኞች እንደ የእጅ ሥራ ሙያ ወይም እንደ ምግብ አቅርቦት፣ አደጋን በመከላከል፣ የዕቃዎች አያያዝ፣ የሒሳብ አያያዝ እና ሕግ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን ማስፈጸም የመሳሰሉ ልምድ ካላቸው ይህንኑ ለይተው ማስታወቅ አለባቸው። በዚህ መንገድ ምላሽ በመስጠት በጣም ቅርብ ለሆኑት ጎረቤቶቻችን ማለትም ለክርስቲያን ወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር እናሳያለን።—ማቴ. 7:12፤ 22:39፤ ዮሐ. 13:35
10 ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚሰጡት እርዳታ የሚደነቅ ነው፦ በሕንፃ ሥራ ፕሮጀክት ከመካፈላቸው በፊት ይህን ሥራ ማጠናቀቁ ምን ያህል ትልቅ እንደነበረ የተገነዘቡት ብዙዎች አልነበሩም። አንድ የመንግሥት አዳራሽ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ሽማግሌዎቹ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከአካባቢው የሕንፃ ሥራ ኮሚቴ በትዕግሥት ይሰጠን የነበረው መመሪያ ትልቅ በረከት ሆኖልን ነበር። ያደረጉልን ድጋፍና ችሎታ ያላቸውን ሠራተኞች ቅንጅት ስንመለከት ‘በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ የራስን ጥቅም በመፈለግ ሳይሆን የአምላክ ውርሻ በሆኑት እንደጌታ ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ’ በማለት ስለ እረኝነት የሚናገሩት የ1 ጴጥሮስ 5:2, 3ን ቃላት አስታወሱን። እነዚህ ወንድሞች በከፍተኛ የሥራ ፍቅር ለይሖዋ አገልግሎት በማቅረብ በኩል በጣም ጥሩ ምሳሌ ናቸው። አዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ሥራ ተጀምሮ እስካለቀበት ጊዜ ድረስ እኛን በሚያስፈልገው ሁሉ ለመርዳት ከሩቅ ቦታዎች ተጉዘው የመጡት ወንድሞች በሥራው ላይ ብዙ ሰዓታት በማሳለፍ፣ መሣሪያዎቻቸውን በመለገስና በቁሳዊ ነገሮችም እንኳ ሳይቀር መዋጮ በማድረግ ለቁጥር የሚያታክቱ ብዙ እርዳታ አድርገውልናል። የእነዚህ ወንድሞች ልግስና ‘ለመላው የወንድማማች ማኅበር’ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው። በመሆኑም በጣም አበረታቶናል።—1 ጴጥሮስ 2:17”
11 የመንግሥት አዳራሾችን ለመሥራት የሚደረጉት መዋጮዎች ቀጥለዋል፦ ባለፉት ጊዜያት በልግስና የተደረጉት መዋጮዎችና በታማኝነት የተመለሱት የሕንፃ ሥራ ብድሮች ጉባኤዎች የመንግሥት አዳራሽ መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ ረድተዋል። ለወደፊቱም ይህ እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን። በልግስና በመስጠት በኩል ቀዳሚ የሆነው ይሖዋ አይደለምን? (ያዕ. 1:17) ችሎታዎቻችንና ለመለገስ ያሉን አጋጣሚዎች የተለያዩ መሆናቸው እውነት ቢሆንም ለሕንፃ ሥራው ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት እንችል ዘንድ የግል ወጭዎቻችንን ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ እናገኘው ይሆናል። እንዲህ ያለው ለጋስነት የይሖዋን ልብ እንደሚያስደስትና ለወንድሞቻችን ትልቅ የመበረታቻ ምንጭ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው።
12 ዛሬ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ‘የተመረጡት ዕቃዎች’ ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በመጉረፍ ላይ ናቸው፤ ይሖዋም ‘ቤቱን በክብር እየሞላው ነው።’ (ራእይ 7:9፤ ሐጌ 2:7) በአስቸኳይ የሚያስፈልጉትን ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎች ሙሉ በሙሉ በመደገፍ በሐጌ ዘመን እንደነበሩት ታማኝ አይሁዶች ልባችንን በአምላክ ሥራ ላይ እናድርግ። ምንም እንኳ በቅርብ ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች የተሠሩ ቢሆንም እድገቱ በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩን ቀጥሏል። ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች የምንሰጠውን ድጋፍ መቀጠላችን በአምላክ ሥራ የምንካፈልበት እጅግ በጣም ጥሩ መንገድ ነው።