የጉባኤያችሁን ሕዝባዊ ስብሰባ ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ደግፉ
1 ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ወጣት አካባቢው የሚገኝ አንድ ጉባኤ የሚያደርገውን ፕሮግራም የሚያስተዋውቅ የግብዣ ወረቀት አገኘ። እውነትን ይፈልግ ስለነበር ምንም ጊዜ ሳያጠፋ እሁድ ዕለት ወደ አዳራሹ ቀደም ብሎ በመምጣት እዚያ በሚደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኘ። አንድ አስፋፊ ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጠው በኋላ በንግግራቸው መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ጋበዘው፤ እርሱ ግን አልተቀበለውም። ይሁን እንጂ ጥሩ ዝግጅት ተደርጎበት በቀረበው የሕዝብ ንግግር በጣም ተነክቶ ስለነበር ሐሳቡን ቀየረና ስብሰባው እንዳበቃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ቀርቦለት የነበረውን ጥያቄ ተቀበለ። ይህ ወጣት ፈጣን እድገት አደረገና ከሦስትና ከአራት ወራት በኋላ ተጠመቀ። ከዚህ ተሞክሮ ቢያንስ ሦስት ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኛለን።
2 አንደኛ ሕዝባዊ ስብሰባው ቀደም ሲል ተዋውቆ ነበር። የጉባኤያችሁን የስብሰባ ፕሮግራም ለማስተዋወቅ የታተሙ ትንንሽ ወረቀቶችን ትጠቀማላችሁን? የስብሰባው ሊቀመንበር በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረገውን የሕዝብ ንግግር ርዕስ ሲያስተዋውቅ በወቅቱ ጽሑፎቻችንን እያነበቡም ይሁን አይሁን ርዕሱ ሊማርካቸው ስለሚችሉት በክልላችሁ ስለሚገኙት ሰዎች አስቡ። አንዳንድ ሰዎች ማንበብ አይወዱም ወይም ደግሞ የሚያነቡት በብዙ ችግር ይሆናል፤ ነገር ግን በቅዱስ ጽሑፉ ላይ ያተኮረ ርዕስ ያለው ንግግር ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
3 ሁለተኛ አዲስ የመጣው ሰው ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎለታል። ቀደም ብላችሁ በአዳራሹ ለመገኘት እቅድ ካወጣችሁ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩትንም ሰዎች ሰላም ልትሉ ትችላላችሁ። (ዕብ. 10:24) አንድ አዲስ ሰው በዚያ ሲገኝ የመጀመሪያ ጊዜው ከሆነ ምን ማድረግ እንዳለበት ላያውቅ ይችላል። ስብሰባችን በጸሎትና በመዝሙር እንደሚጀመር እንዲሁም ስብሰባው እንዴት እንደሚመራ አስረዱት። ከተቻለ መጽሐፍ ቅዱሳችሁንና የመዝሙር መጽሐፋቸሁን ለማየት እንዲችል ከጎናችሁ እንዲቀመጥ ልትጋብዙት ትችላላችሁ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ጥያቄ ካለው ከእናንተ ጋር እንዲወያይበት ጋብዙት።
4 ሦስተኛ ንግግሩ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ነበር። የሕዝብ ተናጋሪ በመሆን ጉባኤውን ወክለው ለመቅረብ መብት የሚያገኙ ወንድሞች ተሰብሳቢዎችን ለበለጠ ፍቅርና መልካም ሥራ ለማነቃቃት ንግግሩን በመዘጋጀትና እንደገና ደግመው ነጥቦቹን በመከለስ ብዙ ሰዓት ያጠፋሉ። ዛሬ ሁላችንም በውጥረት ውስጥ ስለሆንን ለመጽናት የሚያስቸለን ከአምላክ ቃል የሚገኘው የሚያነቃቃ እውነት ያስፈልገናል። የሕዝብ ንግግሩ ምንም ያህል ትምህርት አዘል ቢሆን የሚነገረውን ነገር ትኩረት ሰጥተን እስካላዳመጥን ድረስ በግላችን የሚሰጠን ጥቅም በጣም የተወሰነ ይሆናል። አልፎ አልፎ ንግግር እየተሰጠ ትኩረትህን ሰብሰብ አድርገህ ማዳመጥ አስቸጋሪ ይሆንብሃልን? ብዙውን ጊዜ በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ እንደምናደርገው አጠር ያለ ማስታወሻ መያዙ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲነበብና ሲብራራ መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ተከታተል
5 ማኅበሩ ዓይነታቸው የተለያዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሶች ያላቸውን የሕዝብ ንግግሮች አዘጋጅቷል። የሽማግሌዎች አካል በመሪ የበላይ ተመልካቹ ወይም እርሱ በሚወክለው አንድ ወንድም አማካኝነት የሕዝባዊ ስብሰባዎችን ፕሮግራም ያደራጃል። ለጉባኤው በወቅቱ የሚያስፈልጉትን ርዕሰ ጉዳዮች ማኅበሩ ካዘጋጃቸው የንግግር አስተዋጽዎች ይመርጣሉ። እነዚህ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶች አያምልጧችሁ። ጉባኤያችሁ በየሳምንቱ የሚያደርጋቸውን ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ ደግፉ።