ፍላጎት ያሳዩትን በፍቅር እርዷቸው
1 የይሖዋ መልአክ ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስን ለአምላክ ቃል እውነት ልባዊ ፍላጎት ወዳሳየ ኢትዮጵያዊ ሲመራው ፊልጶስ ሰውዬው የሚያነበውን እንዲገባው ፍቅራዊ እርዳታ አድርጎለታል። (ሥራ 8:26–39) ፍላጎት ያሳዩትን ለመርዳት ተጨማሪ ጥረት እናደርጋለንን? መለኮታዊ ተልእኮአችን ደቀ መዛሙርት ማድረግንም የሚጨምር ስለሆነ ይህን ማድረግ አለብን። (ማቴ. 28:19, 20) እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
2 በየሳምንቱ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ጊዜ መድብ። ፍላጎት ያሳዩትን ለመጠየቅ ዝግጅት አድርግ፤ በመጀመሪያ ጉብኝትህ የተጀመረውን ውይይት ለመቀጠል ሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመጀመርን ግብ በአእምሮህ ያዝ። በቅርብ ጊዜ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! እትሞችን ለማበርከት ዘወትር ተመላልሰህ ሂድ። ሰውዬው ልባዊ ፍላጎት ካሳየ ኮንትራት እንዲገባ ልትጠይቀው ትችላለህ።
3 በመጀመሪያ ጉብኝትህ ወቅት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም አወያይተኸው ከነበረ “ማመራመር ” (ሪዝኒንግ) ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 66 ላይ ባለው ሐሳብ ተጠቅመህ ውይይትህን ልትቀጥልና እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለዘመናዊው ዓለም ተግባራዊ ጥቅም እንደሌለው ይሰማቸዋል። እርስዎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ እድል ስጠው።] ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን የሚያስችል ጥሩ ምክር የሚሰጥ መጽሐፍ ተግባራዊ ጥቅም አለው ቢባል አይስማሙምን? [አስተያየት እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የቤተሰብን ሕይወት የሚመለከቱ ንድፈ ሐሳቦችና ልማዶች ተለዋውጠዋል። እነሱ ያስከተሏቸው ዛሬ የምናያቸው ውጤቶች ጥሩ አይደሉም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የሚሠሩበት ቤተሰቦች ጽኑና ደስተኛ ቤተሰብ ናቸው።” ቆላስይስ 3:18–21ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው? የተባለውን ትራክት አበርክት፤ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንደምናስጠና ግለጽ።
4 ስለ ሙታን ሁኔታ በዚህ መልኩ ውይይት ልትጀምር ትችላለህ:-
◼ “ስለ ሙታን ሁኔታ ብዙ ይወራል። ስንሞት ምን እንሆናለን ብለው ያስባሉ? [መልስ አንዲሰጥ እድል ስጠው።] ብዙ ሃይማኖቶች ሕይወታችን በሆነ መንገድ ይቀጥላል በማለት ያስተምራሉ። ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረውን ሲያውቁ ተገርመዋል። [መክብብ 9:5ን አንብብ።] ሙታን አንዳች የማያውቁ ቢሆንም አልተረሱም። አምላክ በንጉሣዊ አገዛዙ ሥር እነሱን ወደ ሕይወት ለመመለስ ቃል ገብቷል።” የጥቅምት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ን ወይም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 162ን ግለጥና ጥቅሶቹንና ሥዕሎቹን አብራራ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርን ግብ በማድረግ ሌላ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ቀጠሮ ያዝ።
5 በዓለም ሁኔታዎች ላይ ወይም በሰዎች መካከል ስላለው አለመግባባት አስተያየት መስጠት ከፈለግህ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “አንዳንዶች አለመግባባትን መፍቻው መንገድ ውጊያ ብቻ ይመስላቸዋል። ስለዚህ ነገር ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎች በአንድነት ሆነው በሰላም አንዲኖሩ እንደሚፈልግ ያሳያል። [ሮሜ 12:17, 18ን አንብብ።] ይህ በአምላክ መንግሥት አማካይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውን ይሆናል።” አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? በተባለው ብሮሹር ገጽ 25, 26ን አሳየው። ኢየሱስ ‘የአምላክ ፍቃድ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን’ ብለን እንድንጸልይ ለምን እንዳስተማረን ለመግለጽ ተመልሰህ መምጣት አንደምትፈልግ ተናገር።— ማቴ. 6:10
6 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሚመራው ሳይኖር የሚያነበውን መረዳት እንደማይችል አምኗል። (ሥራ 8:31) ፊልጶስ የሚያስፈልገውን እርዳታ በፍቅር ሰጥቶታል። እኛም በተመሳሳይ መንገድ ሌሎችን በመርዳት ለእነሱ ያለንን እውነተኛ ፍቅር ልናሳይ እንችላለን።