ማደግህ በግልጥ ይታይ
1 ሕጋዊ እውቅና ካገኘንና በነፃነት መሰብሰብ ከጀመርን ሦስት ዓመት ያህል ሆኖናል። ከዚያ ወዲህ የተከሰቱት ነገሮች 1 ቆሮንቶስ 16:9 ላይ ያሉትን የሚከተሉተን የጳውሎስ ቃላት ያስታውሱናል:- “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።” በእርግጥም የይሖዋ ሥራ እየተፋጠነ ነው፤ የማንም ተቃውሞም ሊያግደው አይችልም። (2 ተሰ. 3:1) የተትረፈረፈ ተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ አግኝተናል፣ ሥራው እስከ መስኩ ዳርቻ ተዳርሷል፣ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ተጨማሪ ሥልጠና አግኝተዋል፣ እንዲሁም ብዙ አዳዲሶችና ቀዝቅዘው የነበሩ አሁን ግን የተነቃቁ አስፋፊዎች በእውነት ውስጥ ይሖዋን ለማምለክ ከእኛ ጋር ተሰልፈዋል። በተገኙት በእነዚህ ክስተቶች በጣም እንደተደሰትን አያጠራጥርም፤ ስለዚህ አመስጋኝነታችንን ማሳየታችንን መቀጠል እንፈልጋለን።— ቆላ. 3:15
2 እነዚህ ያለፉ ዓመታት ከተሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እና ከዓለም አቀፍ ወንድማማቾች ማኅበር ጋር ይበልጥ ተቀራርበን አንድ ሆነን እንድንሠራ የሚያስችል አጋጣሚ ፈጥረውልናል። (ማቴ. 24:45–47፤ 1 ጴጥ. 2:17፤ 1 ቆሮ. 1:10) በቅንጅት እንደተገጣጠመ አካል በመሆን ‘ራስ ወደሚሆነው ክርስቶስ እንድናድግ’ እና መሻሻላችንን እንድናሳይ በር ተከፍቶልናል። (ኤፌ. 4:15, 16፤ 1 ጢሞ. 4:15, 16) በመካከላችን ያሉ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ታማኝነታቸውን ያሳዩ ብዙ ታማኞች ለውጥ የማድረግ ፈተናዎችን ተቀብለው አዳዲስ ነገሮችን በመማር ተጨማሪ እድገት አሳይተዋል። አዳዲሶችም የጉልምስናን አስፈላጊነት ተገንዝበዋል፤ (ዕብ. 6:1) እድገታቸው በግልጥ እንዲታይም አድርገዋል።
3 አንተስ በግለሰብ ደረጃ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ በኩል እንዴት ነህ? በገላትያ 6:4 ላይ ‘የገዛ ራስህን ሥራ ፈትን’ የሚለውን መንፈስ በመያዝ እድገት ለማድረግ የሚያስችሉ ጥቂት ነጥቦችን ብንመረምርስ? ለመጀመር ያህል መጽሐፍ ጥናትን ጨምሮ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች የመገኘት ጥሩ ልማድ አለህን? በዚህ መንገድ እንዴት ያለ ጥሩ የአመስጋኝነትና ለማደግ የመፈለግ መንፈስ ሊታይ ይችላል! ይህ ከግል ጥናትና ከመዘጋጀት ጋር የተያያዘ ነው። መጽሔቶቻችንን ከዳር እስከ ዳር ታነባለህን? ጥልቅ የሆኑ ወይም ለአንተ አዲስ የሆኑ ነገሮችን ለማሰላሰልና እንዴት ልትሠራባቸው እንደምትችል ለማጤን ቆም ትላለህን? ለስብሰባዎቻችን ትዘጋጃለህን? ጽሑፎችህን ታሰምርባቸዋለህን? እነዚህ ሁሉ የእድገት ምልክቶች ናቸው።
4 ሌላው የእድገት መስክ ከክርስቲያናዊ ባሕርይ ጋር የተያያዘ ነው። በመጋቢት 1994 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ እንደወጣው ባሉ ጽሑፎች ቤታችንን፣ ልብሳችንና ገላችንን በንጽሕና ስለመያዝ በየጊዜው ማሳሰቢያዎችና ሐሳቦች ቀርበውልናል። ቅዱሱን ሰማያዊ አባታችንን ስለምንወክል ከሌሎች ሰዎች ላቅ ያሉ የአቋም ደረጃዎች እንዲኖሩን ይፈለግብናል፤ ስለዚህ ዘወትር የመታጠብ፣ ልብስን ለማጠብ ፕሮግራም የማውጣት፣ ምግብን በንጽሕና የማዘጋጀትና ቤትን በሚገባ የማጽዳት አስፈላጊነት አጽንኦት ተሰጥቶታል። (1 ጴጥ. 1:16) ከዚያ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ለውጦችን አድርገሃልን? አስፈላጊ ሲሆን የራስህን የንጽሕና ደረጃ ከፍ አድርገሃልን? ሌላው ጥረት የሚጠይቀው የአዲሱ ባሕርይ ገጽታ ትሕትና ነው። (ፊልጵ. 2:3) በዓለም ያሉ ሰዎች ስሕተታቸውን ማመን ወይም ይቅርታ መጠየቅ የሚያስቸግራቸውና ብዙውን ጊዜ ባላቸው ነገር፣ በችሎታቸው ወይም በዘራቸው በመታወር ቢኮሩም ይሖዋ በትሑታን ይደሰታል። (መዝ. 138:6) ለትሕትና ትኩረት ትሰጣለህን? በዚህ ረገድም ሆነ በንጽሕና በኩል የምናሳየው እድገት በብዙ መንገዶች ይጠቅመናል።
5 እድገትህ በመስክ አገልግሎት ላይ የተገለጠው እንዴት ነው? መጽሔቶችንና በወሩ የሚበረከቱትን ጽሑፎች መያዝ የሚችል ቦርሳ ይዘህ ወደ አገልግሎት ትሄዳለህን? በየወሩ ጽሑፎችን ለማበርከት ትኩረት ትሰጣለህን? መጽሔት የምታበረክትባቸውን ቀኖች መድበሃልን? በዓመት አራት ጊዜ ባለቀለም ሆኖ በሚወጣው ንቁ! ረገድስ በደንብ የታጠቅህ ለመሆንና መጽሔቶችን በጥንድ ለማበርከት እንድትችል በቂ መጠን ያላቸውን መጽሔቶች አዝዘሃልን? የመጽሔቶቻችንና የጽሑፍ ስርጭታችን በእርግጥ ሊሻሻል ይችላል! ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽን በመጠቀም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ስም በጥሩ ማስታወሻ ትይዛለህን? በየወሩ በቋሚነት ከቤት ወደ ቤት በመመሥከሩ ሥራ ትሳተፋለህን? እንዲያውም አንዳንዶች ከሱቅ ወደ ሱቅና ከቢሮ ወደ ቢሮ በመሄድ ተሳክቶላቸዋል! በተጨማሪም በመንገድ ላይ ስትመሠክር ብዙ ሰዓት ሳትጠብቅ ወይም ጊዜ ባለማባከን ሰዎችን በመቅረብ ጊዜህን ትዋጃለህን? እነዚህ ነጥቦች ሁሉ ለውጥ ማድረግን ጠይቀውብህ ይሆናል፤ ሆኖም ማደግህን ያሳያሉ።
6 ተመላልሶ መጠየቆች በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት በኩልም እድገት ሊደረግ ይችላል። ራስህ ብዙ በመናገር ፈንታ ተማሪህን እንዲመራመር የሚያደርጉትን ጥያቄዎች በማቅረብ በጥሩ የማስተማር ዘዴ ትጠቀማለህን? በተመላልሶ መጠየቅ ጊዜ ጥያቄዎችን ለመመለስ በትራክቶች፣ በብሮሹሮች ወይም በአንድ መጽሐፍ ተጠቅመህ ጉብኝቱን ወደ ጥናት ትለውጣለህን? በትራክቶች በመጠቀም ወይም የቤቱን ባለቤት ለዘላለም መኖር ከተባለው መጽሐፍ አርዕስት በማስመረጥ ጥናቶች ለማስጀመር ሞክረሃልን? እንዲሁም ጥናቱ በደንብ ከተደላደለ በኋላ በየጥናቱ መጨረሻ ላይ ጥቂት ደቂቃዎችን በማጥፋት ስለ ይሖዋ ድርጅት በሚናገረው ብሮሹር ተጠቅመህ ታስረዳዋለህን? ብዙ ጥናቶችን መምራት እንችላለን፤ ብዙዎች በዚህ መስክ እድገት እንደሚያደርጉ ተስፋ እናደርጋለን።
7 እርግጥ አንዳችንም ፍጹም አይደለንም፤ ሆኖም ከመካከላችን ማንም ቢሆን ባለበት በመቆም መርካት የለበትም። በጸሎት እየታገዝን እድገታችን ግልጥ እንዲሆንና ለመሻሻል እንጣር። ይህ ደስታችንን ከመጨመሩም በላይ ብዙ በግ መሰል ሰዎች ላሳየን ፍቅራዊ ደግነት ሁሉ ሊመሰገን የሚገባውን ይሖዋ አምላክን እንዲያከብሩት ያስችላቸዋል።