ፍላጎት ላላቸው ሁሉ ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 በዓለም ዙሪያ የሚደረገው የመንግሥቱ እወጃ በቅርቡ ከተጠናቀቀ በኋላ “እግዚአብሔርን የማያውቁት” ሁሉ ይጠፋሉ። (2 ተሰ. 1:7-9) ስለዚህ የይሖዋ ሕዝቦች ለሌሎች ሕይወት ያላቸው ልባዊ አሳቢነት አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን የመንግሥቱን መልእክት ለብዙ ሰዎች እንዲያዳርሱ ያንቀሳቅሳቸዋል።— ሶፎ. 2:3
2 በየወሩ ‘የመልካምን ወሬ ምስራች’ መስማት የሚፈልጉ ሰዎችን ፈልጎ ለማግኘት በሚልዮን የሚቆጠር ሰዓት ይጠፋል። (ኢሳ. 52:7) ከግንቦት እስከ ሐምሌ በቅናሽ ዋጋ የሚበረከተውን ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ብዙ ሰዎች እንደሚወስዱ ምንም ጥርጥር የለውም። ለእነዚህ ሰዎች ያለን ልባዊ አሳቢነት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሁሉ ተከታትለን እንድንረዳ ሊገፋፋን ይገባል።— ምሳሌ 3:27
3 በትክክል የምትመዘግቡበት ማስታወሻ ይኑራችሁ:- ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችንና የተበረከቱትን ጽሑፎች በተሟላና በትክክል ማስታወሻ ላይ ካሰፈራችሁ ውጤታማ የሆነ ነገር ማከናወን ይቻላል። የቤቱን ባለቤት ስምና አድራሻ፣ ያነጋገራችሁበትን ቀንና ሰዓት፣ ያበረከታችሁትን ጽሑፍና ውይይት ያደረጋችሁበትን ርዕስ የመሳሰሉ መረጃዎችን መያዝ ተመልሳችሁ በምትሄዱበት ጊዜ የበለጠ ውጤታማ እንድትሆኑ ይረዷችኋል። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ባደረጋችሁበት ወቅት የቤቱ ባለቤት የተናገራቸውን አንዳንድ አስተያየቶች የምትጽፉ ከሆነ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ውይይታችሁን በምትቀጥሉበት ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ያለፈውን ሐሳብ ለመጥቀስ ያስችላችኋል።
4 ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ፈጣኖች ሁኑ:- ባለፈው ወር ጽሑፍ ከተቀበሏችሁ ሰዎች መካከል ስንቶቹን እንደገና ለመጎብኘት ጥረት አድርጋችኋል? ተጨማሪ ጉብኝት ሳታደርጉ ብዙ ሳምንታት አልፈው ይሆን? ለዘለቄታዊ ደህንነታቸው ያላችሁ ልባዊ አሳቢነት በተቻለ ፍጥነት ተመልሳችሁ እንድትሄዱ ሊያንቀሳቅሳችሁ ይገባል። ያደረጋችሁት ውይይት ከአእምሯቸው ከመጥፋቱ በፊት በጥቂት ቀናት ውስጥ ተመልሳችሁ ብትሄዱ ይመረጣል። ፍላጎታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ወዲያውኑ ተመልሶ በመሄድ ሰይጣን “መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል” ከመውሰዱ በፊት ጥረቱን ለማክሸፍ ያስችላችኋል።— ማር. 4:15
5 ዝግጅት ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው:- ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ውጤታማነታችሁ የሚለካው ሰውዬውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማነጋገር ባደረጋችሁት ጥሩ ዝግጅት ላይ ነው። ከመሄዳችሁ በፊት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እቅድ አውጡ። የሚያዝያ 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን የመጨረሻ ገጽ መጽሔቶችን ወይም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር በተሳካ መንገድ ለማበርከት እንድትችሉ በርካታ መግቢያዎችን ያቀርባል። የሚቀጥለው ጉዳይ ተመልሳችሁ ስትሄዱ የምትናገሯቸውን አንዳንድ ሐሳቦች በአእምሮ መያዝ ነው። ፍላጎት ያሳዩትን ተከታትላችሁ በምትረዱበት ጊዜ ምን ልትናገሩ ትችላላችሁ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጀመር የሚቻለውስ እንዴት ነው?
6 ለመጀመሪያ ጊዜ በምታነጋግርበት ጊዜ በቅርቡ የሰማኸውን አሳዛኝ ዜና በአእምሮህ ይዘህ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ይህን [የተፈጸመውን ነገር ጠቅሰህ] ነገር ሳይሰሙ አይቀሩም። በአካባቢያችን የሚፈጸመው ወይም በእኛ ላይ የሚደርሰው ግፍና ሥቃይ በእርግጥ አምላክን ያሳስበው ይሆን ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ እንደሚወደንና ችግር በሚደርስብን ጊዜ የእርዳታ እጁን እንደሚዘረጋልን መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።” መዝሙር 72:12-17 ላይ ያሉትን አንዳንድ ክፍሎች አንብብ። ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 99 ላይ አውጣና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ብለው ለሚጠይቁት ጥያቄ ይህ መጽሐፍ መልሱን እንደሚሰጥ ጠቁም። “መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በጣም አጽናኝ ሆኖ ያገኙታል። ስለዚህ ጉዳይ ራስዎ ማንበብ እንዲችሉ ይህን መጽሐፍ ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል።”
7 አምላክ ክፋትን የፈቀደው ለምን እንደሆነ ውይይትህን ለመቀጠል ተመልሰህ የምትሄድ ከሆነ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ [የተፈጸመውን ጉዳይ አንስተህ] ተነጋግረን ነበር። አምላክ ይህን ያህል ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ታዲያ እርስዎ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ እንዲህ ለመሰሉ አሳዛኝ ችግሮች ተጠያቂ አለመሆኑን ማወቃችን የሚያበረታታ ነው።” ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 99 እና 100ን አውጣና አንቀጾቹ ውስጥ ሰፍረው በሚገኙት ጥቅሶች ላይ ውይይት አድርግ። አምላክ እንዲኖር የፈቀደው ክፋት በቅርቡ እንደሚያከትም እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ ለማብራራት ተመልሰህ እንደምትመጣ ግለጽ።
8 አንድ ወላጅ ካጋጠመህ በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ትችላለህ:-
◼ “ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮን ሊያናጉ የሚችሉ ብዙ ችግሮች እንዳሉ አብዛኞቹ ወላጆቸ ይስማማሉ። ችግሩ እንዲፈጠር ያደረገው ምንድን ነው ይላሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አብዛኞቻችን የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። ሆኖም የተሻለ ውጤት ላይ ለመድረስ ረዳት ብናገኝ ደስ ይለናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የላቀ ምክር ይሰጣል። [ቆላስይስ 3:12, 18-21 ላይ ያሉትን አንዳንድ ክፍሎች አንብብ።] በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምዕራፍ 29 ላይ ‘የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ’ በሚለው ርዕስ ሥር እንደተዘረዘረው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚናገረው ብዙ ነገር አለው። መጽሐፉ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠረውን ውጥረት እንዴት ማርገብ እንደሚቻልና በልጆቻችን ላይ የሚደርሱትን ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደምንችል በማብራራት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ምክሮች ይከልሳል። ይህን መጽሐፍ በማንበብ እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ነኝ።”
9 የቤተሰብ ደስታን አስመልክቶ ያደረጋችሁትን ውይይት ለመቀጠል ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ የሚከተለውን በመናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “በመጀመሪያ ተገናኝተን በነበረ ጊዜ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ምክሮች በሥራ ላይ ማዋል መሆኑን አብራርቼልዎት ነበር። ዘመናዊው ቤተሰብ የሚያስፈልገውን ምክር በመስጠት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ እንዳለፈበት ሆኖ ይሰማዎታልን?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 29ን አውጣና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያደርጉ ጋብዛቸው።
10 አጠር ያለ ሐሳብ መናገር የምትመርጥ ከሆነ ይህን ልትሞክር ትችላለህ:-
◼ “የምናረጀውና የምንሞተው ለምን እንደሆነ አስበው ያውቃሉ? ይህ መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ገጽ 74 ላይ ሞት የጀመረው እንዴት እንደሆነና አምላክ እንዴት እንደሚያስወግደው ይናገራል። አምላክ ለሚወዱት ሁሉ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ቃል መግባቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። [ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።] ስለዚህ ጉዳይ ማንበብ የሚፈልጉ ከሆነ መጽሐፉ እውቀት ሰጪ ሆኖ ያገኙታል።”
11 በትክክል የምትመዘግብበት ማስታወሻ በመያዝ፣ በቅድሚያ በመዘጋጀትና ያሳዩትን ፍላጎት የበለጠ ለማሳደግ በፍጥነት በመሄድ ደህንነት ወደሚገኝበት ጎዳና እንዲሳቡ የሚያደርገውን የጎረቤት ፍቅር ልናሳይ እንችላለን።— ማቴ. 22:39፤ ገላ. 6:10