የተጣራ ምሥክርነት በመስጠት ተደሰቱ
1 ሁላችንም በደንብ የምንችላቸውን ነገሮች መሥራት ያስደስተናል። ማርቆስ 7:37 [የ1980 ትርጉም] እንደሚናገረው ብዙ ሰዎች “ሁሉን ነገር በመልካም አደረገ” በማለት ስለ ኢየሱስ ገልጸዋል። ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ማግኘቱ አያስገርምም! (ከመዝሙር 40:8 ጋር አወዳድር።) ቀጥሎ ለቀረቡት ሐሳቦች ትኩረት በመስጠት ኢየሱስ “ለሕዝብም እንድንሰብክና . . . እንመሰክር ዘንድ [“የተጣራ ምስክርነት እንድንሰጥ፣” NW]” የሰጠውን ትእዛዝ ስንፈጽም እኛም በተመሳሳይ ደስታ እናገኛለን። (ሥራ 10:42) በጥርና በየካቲት ወራት ወጣትነትህን እና/ወይም የቤተሰብ ኑሮ የተባሉትን መጻሕፍት እናበረክታለን። እነዚህን መጻሕፍት ለማበርከት የሚረዱ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
2 ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የጤና ጉዳይ ስለሚያሳስባቸው እንዲህ ለማለት ትችል ይሆናል:-
◼ “በሕክምናው መስክ ድንቅ ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም በሕመም ምክንያት ብዙ ሰዎች ይሰቃያሉ። እርስዎ ይህ የሆነው ለምንድን ነው ይላሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ኢየሱስ ክርስቶስ ቸነፈር የመጨረሻዎቹ ቀናት ምልክት እንደሚሆን ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በሽታ የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣም ይገልጻል። [ኢሳይያስ 33:24ን አንብብ።] ይህ መጽሐፍ በዚህ መሠረታዊ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ ተስፋ እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ልብ ይበሉ።” በምታበረክተው መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ተስማሚ ሐሳቦችን ጎላ አድርገህ ከገለጽህ በኋላ መጽሐፉን አበርክት።
3 በገበያ አካባቢዎች መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በምትሰጥበት ጊዜ ሰላምታ ከሰጠህ በኋላ እንዲህ በማለት መጠየቅ ትችላለህ:-
◼ “በዛሬው ጊዜ ኑሮ በጣም ከመወደዱ የተነሳ ገንዘቡን ከወር ወር ማብቃቃት አስቸጋሪ እንደሆነ ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ የሌለበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ከምታበረክተው መጽሐፍ ላይ ከጉዳዩ ጋር የሚዛመድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አሳየው። እንዲህ በማለት ቀጥል:- “ይህ መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ሕይወት አዳጋች እንዲሆን ያደረጉትን ችግሮች አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት እንዴት እልባት እንደሚያመጣላቸው ያሳያል።” መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው። ምን ያህል በውይይቱ እንደተደሰትክ ከተናገርህ በኋላ “በሌላ ጊዜ ይህንን ውይይት ልንቀጥል የምንችልበት መንገድ ይኖራል?” በማለት ጠይቅ። በዚህ መንገድ የሰውዬውን ስልክ ቁጥር ወይም የቤቱን አድራሻ ልታገኝ ትችል ይሆናል።
4 ወጣትነትህ የተባለውን መጽሐፍ የቤተሰባቸው አባሎች ለሆኑ ወጣት ልጆች መመሪያ ለመስጠት ለሚፈልጉ ትልልቅ ሰዎች (ለወላጆች፣ ለአጎትና ለአክስት) ወይም ለወጣቶች (በቤታቸው፣ በትምህርት ቤት፣ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ወይም ሲመለሱ፣ በገበያ ቦታ፣ ወዘተ) በሦስት ብር ልታበረክት ትችላለህ።
◼ “ብዙ ወላጆችን ለሚያሳስቧቸው ነገሮች መፍትሄ የያዘ ጠቃሚ ሐሳብ ባካፍልዎት ደስ ይለኛል። ይህ ሐሳብ ወጣቶች ከትክክለኛው መንገድ እንዳይወጡ እንዴት መርዳት እንደሚቻል የሚጠቁም ነው። በትምህርት ቤትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ብዙ ፈተናዎች የሚገጥሟቸው ልጆች (ወይም የልጅ ልጆች፣ የወንድምና የእህት ልጆች) ይኖርዎት ይሆናል። እነርሱን ለመርዳት እነዚህን ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሊጠቀሙ ይችላሉ። [መክ. 11:9 እና 12:1ን አውጥተህ አንብብ።] በእነዚህ ሐሳቦች በመጠቀም ሊረዷቸው ይችላሉ።” [መጽሐፉን ገጽ 191 ላይ ገልጠህ አንቀጽ 15 የመጀመሪያ ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን አንብብ። ከዚያም የርዕስ ማውጫውን አሳይተህ መጽሐፉን አበርክት።]
◼ አንድን ወጣት በምታነጋግርበት ጊዜ ደግሞ ቀጥሎ ባለው አቀራረብ መጠቀም ትችላለህ:-
“ለአንተ በጣም የሚጠቅም አንድ ነገር ለጥቂት ደቂቃ ባካፍልህ ደስ ይለኛል። ብዙ ወጣቶች እውነተኛ ጓደኛ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ለማወቅ ይፈልጋሉ። በዚህ መጽሐፍ ላይ አንዳንድ ጥሩ ምክሮች ቀርበዋል።” [1 ቆሮ. 15:33ን ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከመጽሐፉ ከገጽ 64 ላይ አንብብ። ከዚያም ከምዕራፍ 8 ላይ አንዳንድ ጎላ ያሉ ነጥቦችን ካካፈልከው በኋላ መጽሐፉን አበርክት።]
◼ ወይም ደግሞ ይህንንም መግቢያ ለመጠቀም ትመርጥ ይሆናል:-
“ወጣቶች ከሕይወት ማግኘት ስለሚፈልጉት ነገር የተለያየ አመለካከት አላቸው። ሆኖም ልንዘነጋው የማይገባን አንድ ነጥብ አለ።” [መክ. 11:9 እና 12:1ን አውጥተህ በማንበብ ሐሳብ ከሰጠህ በኋላ ከመጽሐፉ ውስጥ ምዕራፍ 23ን አሳየውና አበርክትለት።]
5 የቤተሰብ ኑሮ የተባለውንም መጽሐፍ በሦስት ብር ማበርከት እንችላለን። ወጣቶችን በምናነጋግርበት ጊዜ ምዕራፍ 2ን በተለይ ደግሞ ንዑስ ርዕሱን ጨምሮ አንቀጽ 13ን እና 15ን መጥቀስ እንችላለን ወይም በምዕራፍ 12 በአንቀጽ 3 እና 4 ላይ ትኩረት ማድረግ እንችላለን። ለትልልቅ ሰዎች ሁለቱን መጽሐፍ በአንድ ላይ በስድስት ብር ማበርከት እንችላለን። ከቤተሰብ ኑሮ መጽሐፍ ምዕራፍ 8ንና ንዑስ ርዕሶቹን ጎላ አድርገህ መግለጽ ትችላለህ። በተጨማሪም በገጽ 107 ላይ የአንቀጽ 20ን የመጀመሪያ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ማንበብና ከዚያም የርዕስ ማውጫውን በማሳየት መጽሐፉን ማበርከት ትችላለህ።
6 ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ለመጠየቅ ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ ይህንን አቀራረብ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ጥረት ማድረግ ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ስንወያይ አንድ ጥሩ አስተያየት ሰጥተው ነበር። [ሰውዬው የተናገረውን አንድ ሐሳብ ጥቀስ።] ስለ ጉዳዩ ሳስብ ነበር። በርዕሱ ላይ ተጨማሪ ነጥቦች ለማግኘት ሳነብብ ያገኘኋቸውን አንዳንድ ሐሳቦች ላካፍልዎት እወዳለሁ። [ከጉዳዩ ጋር የሚስማማ አንድ ጥቅስ አንብብ።] በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች እንዲረዱ ያስቻላቸውን ነፃ ጥናት ከእርስዎም ጋር ብናደርግ ደስ ይለናል። እንዲህ ዓይነቱ ምርምር አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች በእርግጠኝነት እንደሚፈጸሙ ያለዎትን ትምክህት ሊገነባልዎት ይችላል።” በጥናቱ መልስ የሚያገኙ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጎላ አድርገህ ጥቀስ። ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ካልተቀበለ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያልቅ ለየት ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መኖሩን ግለጽለት። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር አሳየውና ትምህርት 1ን ገልጠህ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ በመጀመሪያው ትምህርት አማካኝነት ለማየት ፈቃደኛ እንደሆነ ጠይቀው።
7 የስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶችን መጠቀም አትዘንጉ፦ የስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶች ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸውን ፍላጎት ለመቀስቀስ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመግቢያህ ላይ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ፤ ወይም ጽሑፍ መውሰድ ላልፈለገ ሰው መስጠትም ይቻላል። ሰውዬው ፍላጎት ካሳየ ከመጋበዣው ወረቀት ጀርባ ያለውን ሐሳብ በመጠቀም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምርና ስብሰባ እንዲመጣ አበረታታው።
8 በሥራህ ጥሩ ችሎታ ያለህ ሁን፤ ደስታ ታገኝበታለህ። የተጣራ ምሥክርነት ለመስጠቱ ጉዳይ ትኩረት ስጠው፤ በተጨማሪም በሁሉም የአገልግሎቱ ገጽታዎች ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ ተደሰት።—1 ጢሞ. 4:16